ዳግም ከበደ
ድምፃውያን ከጥበብ አድባርና ኪናዊ ሙያቸው ባሻገር በህዝብ ዘንድ ሰፊ ዝናን ከሚያተርፉና ተፅእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ዘንድ ይመደባሉ። ዝና ደግሞ ከህዝብ የሚገኝ ልብን የሚያሞቅ ጭብጨባ ብቻ ሳይሆን ተሰሚነትንም ይጨምራል። ታዲያ ተቀባይነት ያላቸው እነዚህ የሙዚቃው ዓለም ሰዎች በስራዎቻቸው አድማጭ ተመልካቾቻውን ማዝናናት ብቻ ሳይሆን ቁምነገር አዘል መልዕክትም በማቀበል የአመለካከትና የመልካም ምግባር አርአያ ይሆናሉ።
ሙዚቀኞች በዘፈኖቻቸው፣ በስነ ምግባር፣ባህልና ወግ አጠባበቅ፣ አለባበስና ፋሽን ሳይቀር በዘመናቸው በሚወዷቸው ተከታዮቻቸው ላይ ተፅእኖ የመፍጠር አቅም አላቸው። ዛሬ በዝነኞች እረፍት ውሎ ከነዚህ ውስጥ አንዱ የሆነውን ወጣትና ከፍተኛ ተስፋ የተጣለበትን አርቲስት ይዘንላችሁ እንቀርባለን። ይህ ወጣት በመድረክ ስሙ ድምፃዊ ማፊ ልኡል (ማእላፍ አወቀ) ይባላል። የዛሬው የዝነኞች የእረፍት ውሎ አምድ እንግዳችን ነው።
ማፊ- ከየት ወዴት
ድምፃዊና ዳንሰኛ ነው። ተወልዶ ያደገው ደግሞ ኮልፌ በተለምዶው 18 የሚባለው አካባቢ ነው። የሙዚቃ ህይወቱ የሚጀምረው ከትምህርት ቤት ከልጅነቱ አንስቶ ነው። በሚማርበት ትምህርት ቤትና በሰፈር አካባቢ የሙዚቃ ፍላጎቱን የሚያሳድግለትን ልምምድ ያደርግ ነበር።
ከዚህ የተነሳው ጥረቱና ፍላጎቱ እያደገ ሄዶ በህፃናትና ወጣቶች ቲያትር ቤት እንዲሁም በሜሪጆይ የልማት ተራድኦ ድርጅት ውስጥ ከስምንትና ዘጠኝ ዓመት በላይ በበጎ ፈቃደኝነት በድምፃዊነትና በባህላዊ ውዝዋዜ (ዳንስ) ስራ ላይ ሲሰራ ቆይቷል። በተለይ በኤች አይቪ ኤድስ ለተጎዱ ህፃናት ወጣቶች እንዲሁም ጧሪ ቀባሪ ላጡ እናቶች የማነቃቂያና አእምሮን ዘና የሚያደርጉ ስራዎችን በማቅረብ የበኩሉን ድርሻ ሲወጣ ሙያውንም እግረ መንገዱን ሲያዳብር ቆይቷል።
የሙዚቃ ሙያ ጉዞው እዚህ ላይ ሳያበቃ በምሽት ክለቦች በተለይ ታዋቂና ዝነኛ ሙዚቀኞች ጭምር በሚሳተፉበት በፒያኖ ባር፣ መሳፍንት፣ ትእግስት፣ አይቤክስ፣በሁለት ሺ አበሻ፣ ዮድ አቢሲኒያ፣ ማጀና ሌሎች በርካታ ቤቶች ውስጥ የራሱን ጨምሮ ተወዳጅ የሆኑ ሙዚቀኞችን ስራዎች በማዜም ተወዳጅነትንና አድናቆትን እያገኘ መጥቷል።
ሃይለየሱስ ግርማ፣ አስቴር ግርማ፣ ገረመው አሰፋ፣ አስናቀ ገብረየስ በኮልፌ የአንድ አካባቢ ሰው የሆኑ በእርሱ ሙዚቃ ህይወት ላይ አሻራቸውን ያሳረፉ ታዋቂ ድምፃዊያን ናቸው። በዋናነት ግን በልጅነቱ ወንድሙ ጎበዝ ሙዚቀኛ ስለነበር ወደ ጫካ ይዞት በመሄድ የድምፅ ልምምድ እንዲያደርግ ፍላጎቱንና ምኞቱን እውን እንዲያደርግ እገዛ አድርጎለታል።
በዘፈን ምርጫውም ቢሆን የታላላቅ ድምፃዊያን እንደእነ ጥላሁን ገሰሰ፣ ነዋይ ደበበ ቴዎድሮስ ታደሰ ያሉትን ድምጻውያን ስራዎች መጫወትና ማዳመጥ ምርጫው ነበር። ይሄም የሙዚቃ አረዳዱንና የሙያውን ምንነት ግንዛቤ እንዲያገኝና ክህሎቱን እንዲያሻሽል እንደረዳው ይናገራል።
ድምፃዊ ማፊ ከሙዚቃው ባሻገር ከስድስት ዓመት በፊት በባህላዊ ውዝዋዜ ከብሄራዊ ቲያትር ምሩቅ ነው። በዚህም በስራዎቹና በተለያዩ ኮንሰርቶች ላይ ተወዳጅ ስራዎቹን ከዳንስ ቡድን ጋር በጋራ በመሆን በተጨማሪ ተወዳጅ ውዝዋዜ ያቀርባል። ይሄም ገና ከጅምሩ ተቀባይነት እንዲያገኝ እርሱም በሚወደው መክሊት እንዲቆይ አግዞታል።
ሌዊዮ- የበኩር ስራ
የድምፃዊ ማፊ የበኩር ስራ “ሌዊዮ” የሚል ርእስ ያለው የጉራግኛ ሙዚቃ ነው። በመጀመሪያ ስራውም ከፍተኛ ተቀባይነትና ተወዳጅነት አግኝቶበታል። ይህ ስራው እስካሁንም ድረስ ተደማጭነት ያለው ሲሆን በዩቱዩብ ላይም ከ3ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ተመልካችን ማግኘት የቻለ ነው። ዜማውን የሰራው እሱባለው ይታየው የሺ፣ ሙላለም ታከለ (ራህዋ)፣ አድል ረዲ የተሰራ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ሙዚቃውን ሲሰራው እና አሁን ላገኘው ተወዳጅነት አብረውት የሰሩት የቡድኑ አጋራች በሙሉ ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን አይዘነጋውም።
ድምፃዊ ማፊ ልኡል ይሄ የመጀመሪያው ስራው ይሁን እንጂ ከዚያ ቀጥሎ የተጫወታቸውም ሙዚቃዎች አሉ። ሁለተኛው ስራው የኦሮምኛ ስራው “ሽር በይና” የሚል ርእስ ያለው ሲሆን ፣ከእርሱ ቀጥሎ “ልክ እንደ እኔ” የሚል ሙዚቃን ለወዳጅ አድናቂዎቹ አድርሷል።
በዚህ ሳይገደብ ከወር በፊት “ሸዊት መዓረይ” የሚል ተወዳጅ ሙዚቃን ለአድማጮች እነሆ ብሏል። ይሀ የመጨረሻ ስራው በአሁኑ ሰዓት በዩቱይብ ላይ ከፍተኛ ተቀባይነትና ተመልካች ካገኙ ሌሎች ሙዚቃዎች ተርታ የሚመደብ ነው። ማፊ ልኡል በተለይ በወጣቶች ተወዳጅ ነው። በጥቂት ጊዜ ውስጥ በሰራቸው ውስን ስራዎች ተቀባይነትን አትርፏል። በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሙሉ አልበም በመስራት የበሰለ ስራ ለአድናቂዎቹ እንደሚያቀርብ ቃል ገብቷል።
የቀደሙት ከአሁኑ
ድምፃዊ ማፊ የቀደሙት የሙያ አጋሮቹና ታላላቅ አርቲስቶች ሙዚቃን የእውነት ወደውት ነው የሚሰሩት ይላል። አሁን ላይ በተለያዩ ምክንያቶች ካለፈው ባነሰ ጥራትና የተወዳጅነት መጠን ስራዎች እንደሚወጡ፤ የግብር ይውጣ ስራም መብዛቱንም ይጠቁማል። ለዚህ የተለያዩ ምክንያቶች ቢያስቀምጥም እንደ እርሱ ግን በተለይ አሁን ላይ እየሰራ ባለው አልበም ያለፉትን የሙያ አጋሮቹን ፈለግ ለመከተልና በተቻለው አቅም የተሻሉ ስራዎችን ይዞ ለመቅረብና አድማጩን ለማክበር ጥረት እንደሚያደርግ ይገልፃል።
የእረፍትና የመዝናኛ ጊዜ
ወጣት አርቲስት ማፊ ልኡል ሙያውን የሚወድና የሚያከብር ድምፃዊ ነው። ረጅሙን ጊዜውንም በኪን ስራው ላይ ያሳልፋል። ከዚህ ባለፈ መፅሃፍትን ማንበብ፣ ከጓደኞቹና ቤተሰቦቹ ጋር በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ዙሪያ በመጨዋወት ማሳለፍ ይመርጣል። በዋናነት ግን ስሜት የሚሰጥ ውሎ ማሳለፉ የሚታወቀው ግጥምና ዜማ በመስራት፣ ስቱዲዮ በመቆየት ነው። ይሄም በቀጣይ ይዞት ለመምጣት ላሰበው ሙሉ አልበም እንደሚረዳው ነው የሚናገረው።
ማፊ ዘናጭ ነው። ፋሽን ተከታይ ነው። ወጣት በመሆኑ ለስሜቱና ለፍላጎቱ የሚመጥኑ አለባበሶችን ምርጫው ያደርጋል። ከዚያ ባለፈ ግን በእረፍት ጊዜው ቀለል ያሉ ልብሶችን እንደ ቱታና ቲሸርቶችን ያዘወትራል። ይህን ሲያደርግ መንፈሱ ይታደሳል። በዚህ ምክንያት አሁን ስሙን በዚህ ላይ የማንጠቅሰው ብራንድ የአልባሳት ካምፓኒ አምባሳደር ሆኖ ይሰራል። ይሄም ለፋሽን ካለው ልዩ ፍላጎት የመነጨ መሆኑን ነው የሚገልፀው።
ከወጣቱ ምን ይጠበቃል
ድምፃዊው ወጣቶች በዚህ እድሜ ላይ ሰርተው የሚለወጡበት ወቅት እንደሆነ ይናገራል። አራዳ ማለትም ሰርቶ የሚለወጥና ሃላፊነት የሚሰማው መሆኑን ይገልፃል። በመሆኑም ሃላፊነት ከጎደለው ውሎና መዝናናት ርቀው በእድሜያቸው ቁምነገር ላይ እንዲደርሱ መሰረት የሚጥሉበት በመሆኑ ልብ ሊሉ ይገባል የሚል መልክት ያስተላልፋል። ስለዚህ “መዝናናትና እረፍት መጥፎ ባይሆንም የወጣትነት እድሜን ራስን ለቁምነገር የምናበቃበት ይሁን። ይዞ መገኘት መልካም ነገር ነው” የሚል መልክት አድርሶን ከድምፃዊው ጋር የነበረን ቆይታ አጠናቀቅን። ሰላም!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 24/2013