ዛሬ የትንሳኤ በአል ነው። ለመላ የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለበአሉ በሰላም አደረሳችሁ! የእምነቱ ተከታዮች ሁለት ወራት ለሚጠጋ ጊዜ ሲያካሂዱ የቆዩትን ጾም ዛሬ ይፈታሉ። ለዚህ በአል ዶሮ እና በግ ይታረዳል። በሬ ታርዶ ቅርጫ ይደረጋል፤ በኪሎ መግዛት የፈለገው ደግሞ ከየስጋ ቤቱ እየገዛ በአሉን ያከብራል። ዳቦው፣ ጠላው፣ ጠጁ፣ ቡናው፣ ፈንዲሻው ወዘተ ሌሎች በበአሉ የማይጎሉት ዝግጅቶች ናቸው። ይህ ታላቅ ቀን ቅቤውም ስጋውም አንደ አቅም እንደ አቅም እየተደረገ ይከበራል። ኢትዮጵያውያን በመረዳዳት ስለሚታወቁ የተቸገሩትን ጾም ለማስፈታት ድጋፍ ያደርጋሉ።
ቄጠማ ግን ከሁሉም ቤት አይቀርም፤ ቄጠማ መጎዝጎዝ ሃይማኖታዊ አስተምህሮ ሳይሆን በልምድና በባህል የሚደረግ ነው። ለጉዝጓነት ከሚያገለግሉ መካከል ቄጠማው ዋና ይሁን እንጂ ሌሎች የሳር አይነቶችም ለእዚሁ አገልግሎት ይውላሉ፤ ዋናው እርጥብና ለምለም መሆናቸው ላይ ነው። እንደ ጠጅ ሣር፣ አጡንባርና አሪቲ ያሉትም ጥሩ መዓዛ ስላላቸው ከተገኙ በጉዝጓዙ ላይ ጣል ጣል ይደረጋሉ።
በበአላት ወቅት ገበያውን ከሚያጨናንቁት አንዱ የቄጠማ ግብይት ነው። ከፍተኛ መጠን ያለው የቄጠማ ሳር ወደ አዲስ አበባ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ይገባል። ከፍተኛ የሆነ የቄጠማ ንግድ በአዲስ አበባ እንዳለም የሰማሁ መሰለኝ።
ስለቄጠማ ገጠር ያደገ ብዙ ያውቃል። የሚገኘው ጨፌ ወይም ውሃ በብዛት በሚገኝበት አካባቢ ነው። ጨፌ ስፍራ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ውሃው እየተጠነፈፈ ለእርሻ ካልዋለ በቀር ለቄጠማ ነው የሚመቸው። ቄጠማ ውሃ በተኘበት ቦታ ሁሉ ይበቅላል።
ከዚህ በመለስ ሰዎች በየአትክልት ስፍራቸው ሊተክሉትም ይችላሉ። ይህ ግን እንዲያው ለግቢ ውበት እንጂ ለጉዝጓዝ ብዙም የሚበቃ አይሆንም። ሰፋ አድርገው ካለሙት ግን ሊሆን ይችላል። ዋናው ነገር ውሃ ይፈልጋል።
በሀገራችን ውሃ ጉድጓድ ለመቆፈር ሲፈለግ በቅድሚያ የሚታየው ቄጠማ ያለበት ስፍራ ነው ሲባል ሰምቻለሁ። አካባቢው ላይ ቄጠማ ካለ እዚያ ላይ ጉድጓድ ቢቆፈር ውሃ ሊወጣ ይችላል ይባላል።
ቄጠማ በዚህ የትንሳኤ ወቅት በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ሌላ የተለየ ትርጉምም አለው። በፋሲካ ዋዜማ ቅዳሜ (ቀዳም ስዑር) ቀሳውስት ቄጠማ ለአማኞቻቸው ያድላሉ፤ አማኒያኑም ቄጠማውን ሰንጥቀው ራሳቸው ላይ ያስራሉ። አንዳንድ ሰዎች ደጃቸው ያለሙትን ቄጠማ በዚህ ወቅት ለቤተክርስቲያን ሲሰጡም አይቻለሁ።
ቄጠማ የበዓልን ድባብ ማለትም ፈረንጆች አትሞስፌር የሚሉትን አይነት በመቀየር መልካም ሚና አለው። የቱንም አይነት ነገር ጉዝጓዝ ቢደረግ ማን እንደ ቄጠማ፤ ቤት ሲያደምቅ በልዩ ነው። ህዝቡ እርጥብ እና የለመለመ ነገር ይወደዳል፤ ቄጠማ ለበዓል የሚጎዘጎዝበት አንድምታው ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የመልካም ምኞት የደስታ አንዱ መገለጫ ነው። በዓልን ያደምቃል፤ ከሚል ዕሳቤ ነው እንጂ ራሱን ችሎ የእምነት አካል አይደለም። ቄጠማ ከደስታ ጋር ተቆራኝቷል።
አሁን…አሁን ደግሞ በየቤቱ ቡና በተፈላ ቁጥር ቄጠማ ይጎዘጎዛል። የጀበና ቡና በደራበት የአዲስ አበባ ከተማ ቄጠማ ማግኘት ቢከበድም መጎዝጎዙ
ሊሳሳ ይችላል እንጂ ጨርሶ አይተውም። ደንበኞች ብቻ ሳይሆኑ አላፊ አግዳሚዎችም ጉዝጓዝ ሲመለከቱ ይደሰታሉ። ቄጠማ እየተወደደ የመጣው ለዚህ ይሆን? ይህን ችግር ለመፍታት ይመስለኛል በፕላስቲክ የሚሰራ አረንጓዴ ምንጣፍ ተፈጥሯል። ግን ማን እንደ ቄጠማ ።
መጠጥ ቤቶች፣ ምግብ ቤቶችም በበአላት ወቅት ቄጠማ መጎዝጎዝ ለምደዋል፤ አሁን…አሁን ደግሞ ግዙፍ የገበያ ማእከላትና የመስሪያ ቤት ህንጻዎች መግቢያ በአመት በአል ዋዜማ ላይ ጉዝጉዝ ሲደረግ ይታያል። የሆነ የደስ ደስ ያመጣል። ከማንም ቢሆን ጉዝጓዝ በዚህ መልኩ ሲመለከት በአል ወይም አንድ ዝግጅት መኖሩን ያስባል። ጉዝጓዙ ስለልጅነት ጊዜው ስለቤተሰቡ ወዘተ… ሁሉ መለስ ብሎ እንዲያስብ ያረገዋል። ቄጠማ ከቤት ወደ አደባባዮች፣ ጎዳናዎችም እየወጣ ነው። ይህን ለጥምቀት እና ከተራ በአል ሳትመለከቱ አትቀሩም።
መቼም አዲስ አበባ ቄጠማ የማምረት ብቃትም ንቃትም የላትም፤ በሌላት መሬትና ውሃ ቄጠማ ማለት እንዴት ይቻላታል፤ ልምላሜን የሚያሳየውን ቄጠማ በሰማይ ታምርተው ካላልን በስተቀር፣ ቄጠማው የሚመጣልን ከአዲስ አበባ ዙሪያ አርሶ አደሮች ነው። ለነገሩ እድሜ ለመኪና ከዚያም ራቅ ካለ ቦታ ሊመጣ ይችላል። ኧረ እድሜ ለነጋዴ ዋጋው ይወደዳል እንጂ ከየትም…ከየትም ብሎ ያመጣዋል።
በሀገሪቱ ብሄረሶበች ዘንድ ተወራራሽ ባህል ስላለ በአብዛኛዎቹ ብሄረሰቦች የለመለመ ሣር መያዝና መጎዝጎዝ የበጎነት ምሳሌ ነው። ከሚጎዞጎዙት ዓይነቶች ደግሞ ቄጠማና አሸንዳ ይጠቀሳሉ። እነ ጠጅ ሣር እና አሪቲም አይብዛ እንጂ ቤት ላይ ጣል ጣል ይደረጋሉ፤ እነዚህ ደግሞ ለጉዝጓዙ ጥሩ መአዛ ይሰጡታል። ሰው ሲረግጣቸው መአዛቸው ይወጣል። እንደ ቄጠማ እንደ አሪቲ የሚለው የአረጋኸኝ ወራሽ ዘፈን ትዝ አለኝ።
ለቡና ምንም ስሜት እንደሌላቸው ከሚናገሩ አንዳንድ ሰዎች እንደሰማሁት፤ ቡናውን ባይጠጡም በጀበና ሲፈላ ፈንዲሻውና የሚጎዘጎውን ቄጠማ ሲያዩ የደስታ ስሜት ይጭርባቸዋል። ጥሩ ስሜት ይሰማቸዋል።
ከደስታ መግለጫ አንዱ ነው ማለት ይቻላል። ቄጠማ ለቅሶ ቤት አይጎዘግዝም። ለቅሶ ቤት ያለው ድባብ ሌላ ነው። የፈለገውን ያህል ይህን ድባብ ለመቀየር ቢሞከር ቄጠማ አይጎዘጎዝም። ምክንያቱም ህብረተሰቡ የደስታና የሐዘን ብሎ የለያቸው ነገሮች አሉና።
ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት በብዛት በኢትዮጵያ ብሔሮች ዘንድ በዓልን ቡና አፍልቶ ቄጠማ ጎዝጉዞ ማከባበር ባህላዊ ስርአት ነው፤ በኦሮሞ ብሄር ኢሬቻ ለማክበር ሲወጣ ሰዎች በእጃቸው ለምለም ቄጠማ ይይዛሉ፤ ይህን የሚያደርጉት ክረምቱን አሻግሮ ለአዲሱ ዓመት ላቀረበ ፈጣሪ ምስጋና ለማቅረብ ነው። ቄጠማው የልምላሜ የብሩ ተስፋ ምልክት ነው።
ቄጠማን አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የሚጋሩት ባህል ስለሆነ ልንከባከበው ይገባል። ለአርሶ አደሩም እኮ የገቢ ምንጭ ነው።
እንደልብ ማግኘት ግን እየተቻለ አይደለም። ለቄጠማ የሚሆኑ ውሃ ገብ ወይም ጨፌ ስፍራዎች ወደ እርሻ እየተቀየሩ ነው፤ በዚህ ላይ የአየር ንብረት ለውጡ አለ፤ ቄጠማ ካለው ባህላዊ ፋይዳ አኳያ እንዲለማ ቢደረግ ለአርሶ አደሩ ጥሩ ገቢ ማስገኛ ሊሆን ይችላል። ከዚህም ባለፈ አካባቢን አረንጓዴ በማልበስ ለአካባቢ ጥበቃም ይጠቅማል። መልካም አመት በአል።
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 24/2013