በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በጎንደር ዙሪያ ወረዳ እየተገነበ ያለው የመገጭ ግድብ ግንባታ የተጀመረው በ2005 ዓ.ም ነበር። የግድቡ ውሃ ለመስኖና ለንጹህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት ለማዋል ነው ግንባታው የተጀመረው። ግድቡ 185 ሚሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃ እንደሚይዝ የሚጠበቅ ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ 116 ሜትር ኪዩብ የሚሆነው በጎንደር ዙሪያና ደምቢያ ወረዳዎች ላሉ አርሶ አደሮች ለመስኖ ልማት የሚውል ነው። ይህም 17 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ የማልማት አቅም ያለው ሲሆን፤ በዚህም 34 ሺህ አርሶ አደሮችን የመስኖ ተጠቃሚ የማድረግ አቅም ያለው ነው።
ቀሪው ውሃ ደግሞ ለጎንደር ከተማና አካባቢው የንጹህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት እንዲውል የታቀደ ነበር። ግድቡ በከተማዋ አካባቢ ሰው ሰራሽ ሀይቅ የሚፈጥር በመሆኑ ለመዝናኛ እና ለዓሳ እርባታ ትልቅ ጠቃሜታ ይኖረዋል። ለፕሮጀክቱ ግንባታ 5 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በጀት ተይዞለታል።
የዛሬ 13 ዓመት ገደማ የግድቡ ግንባታ ሲጀመር በአምስት ዓመት ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞለት የነበረው ይኼ ፕሮጀክት፤ በአሁኑ ወቅት 70 ነጥብ 22 በመቶ መጠናቀቁን ከመስኖ ልማት ኮርፖሬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል። ፕሮጀክቱ እንዲጓተት ያደረጉ የተለያዩ ምክንያቶች መኖራቸውን የመስኖ ልማት ኮሚሽን የውጭ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ብዙነህ ቶልቻ ይናገራሉ።
አቶ ብዙነህ እንደሚሉት፤ የግድቡ ግንባታ የመጀመሪያው አምስት አመታት ውስጥ የተሰራው ስራ እጅግ ውስን ነበር። በመጀመሪያዎቹ አምስት ዓመታት የግድቡ ግንባታ ስራ ተሰርቷል ብሎ ለመናገር የሚያዳግት ነው። አምስት ዓመታት የተለያዩ ችግሮች ሲያጋጥሙ ስለነበር በአግባቡ ወደ ስራ መግባት አልተቻለም ነበር። በተለይም የፋይናንስ ችግር ዋነኛው ችግር ነበር። ከአምስት ዓመት በኋላ የገንዘብ ምንጭ ሲገኝ ነው በሙሉ አቅም ወደ ስራ የተገባው።
በሙሉ አቅም ወደ ስራ ከተገባ በኋላም የወሰን ማስከበር ችግርን ጨምሮ የተለያዩ ችግሮች ሲያጋጥሙ እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ ብዙነህ፤ የግድቡን ግንባታ ለማፋጠንና የተጓተተውን ጊዜ ለማካካስ የተለያዩ የመፍትሄ ርምጃዎች መወሰዳቸውን ጠቁመዋል።
ከተወሰዱት የመፍትሄ ርምጃዎች መካከልም የተለያዩ ኩባንያዎች በንዑስ ተቋራጭነት እንዲገቡ በመደረግ በፕሮጀክቱ ግንባታ ላይ ይስተዋል የነበረውን የአቅም ውስንነት ችግር መቀነስ መቻሉን ነው ያብራሩት።
የተለያዩ ችግሮችን በመቋቋምና በመቅረፍ በአሁኑ ወቅት ግድቡን 70 ነጥብ 22 በመቶ ማድረስ ተችሏል። በተያዘው በጀት ዓመት ግድቡን ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞ እየተሰራ እንደነበርም አንስተዋል።
ሆኖም ግድቡን በዚህ ዓመት ለማጠናቀቅ የተያዘው እቅድ ለማሳካት አዳጋች መሆኑን የሚያብራሩት አቶ ብዙነህ፤ የሲሚንቶ እጥረት እና ብዙ ቢሮኪራሲ የሚፈልጉ ከውጭ የሚገቡ የግድቡ ማጠናቀቂያ እቃዎች በጊዜው ወደ ሀገር ውስጥ አለመግባት የግድቡ ግንባታ በሚፈለገው ልክ እንዳይፋጠን አድርጓል። አሁን ባለው ወቅታዊ አፈጻጸም ግድቡን በዚህ ዓመት ለማጠናቀቅ የሚያስችል እንዳልሆነ ከተቋራጩ እና ከአማካሪው ጋር እየተደረጉ ባሉ ውይይቶች ማወቅ መቻሉን ጠቁመዋል።
እንደ አቶ ብዙነህ ማብራሪያ የግድቡ ቀሪ ስራዎች ሲሚንቶን በከፍተኛ ደረጃ የሚፈልጉ ናቸው። ሲሚንቶ በከፍተኛ ደረጃ የሚፈልግ መሆኑን በመገንዘብ መንግስት የሲሚንቶ እጥረት ችግር ለመቅረፍ ጥረት እያደረገ ነው። ሆኖም የሲሚንቶ እጥረት ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር ለመቅረፍ አልተቻለም። ይህም ግድቡን በዚህ ዓመት ለማጠናቀቅ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ተግዳሮት ሆኗል።
ከውጭ ሀገራት በውጭ ምንዛሬ የሚገቡ የግድቡን ደህንነት ማስጠበቂያ መሳሪያዎች እስካሁን ከውጭ አለመግባቱን የጠቆሙት አቶ ብዙነህ፤ እቃዎቹን ከውጭ ሀገር የማስመጣት ተግባር ብዙ ሂደት የሚጠይቅ መሆኑን አንስተዋል። በአጠቃላይ አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ እንደሚያመልክተው ግን ግድቡን በዚህ አመት ለማጠናቀቅ በሚያስችል ደረጃ ላይ አለመድረሱን ነው የጠቆሙት።
የግድቡ ግንባታ እና የክፍያ ስራ ጎን ለጎን እየሄደ እንደነበር ያብራሩት አቶ ብዙነህ እስካሁን ድረስ ለግድቡ ግንባታ ከተያዘው 5 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ውስጥ 70 በመቶ ገደማ ክፍያ መፈጸሙንም ጠቁመዋል።
የግድቡ ግንባታ መጓተት በሀገሪቱ ላይ ያስከተለው ኢኮኖሚያዊ ጫና ዙሪያ እስካሁን ድረስ የተሰሩ ጥናቶች ባይኖሩም ብዙ ቢሊየን ብሮች ወጪ የተደረጉበት ፕሮጀክት በተያዘለት ጊዜ አለመጠናቀቅ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ያደረሰው ጫና ቀላል እንደማይሆን ግልጽ ነው። ፕሮጀክቱ ከዚህ በላይ በመጓተት ሀገሪቱን ተጨማሪ ዋጋ ሊያስከፍላት አይገባም። በመሆኑም የፌዴራልና የክልል መንግስታት፣ ኮንትራክተርና ኮንሰልታት እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅ የሚያደርጉትን ጥረት በማጠናከር ግድቡ ከዚህ በላይ በመጓተት አላስፈላጊ ዋጋ እንዳያስከፍል ማድረግ አለባቸው።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23/2013