ፍሬህይወት አወቀ
በአገሪቱ እየተስፋፉና ተፈላጊነታቸው እየጨመረ ከመጡ ከተሞች መካከል ሀዋሳ ከተማ አንዷ ናት። ሀዋሳ የቱሪስት መስዕብ እንደመሆኗ በርካቶች ለመዝናናት ይመርጧታል። ከመዝናናት ባለፈ ብዙዎች ለመኖሪያነት ምቹ ከተማ ስለመሆኗም ይመሰክራሉ።
በአካባቢዋ ያሉ ነዋሪዎቿን ጨምሮ ምቾቷን ፈልገው በየጊዜው ወደ ከተማዋ የሚገቡ ነዋሪዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞም እንደ ማንኛውም በማደግ ላይ ያሉ ከተሞች የተለያዩ የመሠረተ ልማት እጥረቶች ሀዋሳ ከተማን ገጥመዋታል። ከእነዚህም መካከል በከተማዋ ያለው የመኖሪያ ቤት አቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም አንዱ ማሳያ ነው።
የመኖሪያ ቤት እጥረቱን ለማቃለልም ከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ ሥራዎች እየሰራ ይገኛል። ከእነዚህም መካከል ከተማ አስተዳደሩ በራሱ ወጪ የመኖሪያ ቤት ገንብቶ ለተጠቃሚዎች የሚያቀርብበትን ፕሮግራም አንድ አማራጭ አድርጎ እየሰራ ሲሆን፣ በቅርቡም ያስገነባቸውን 152 ቤቶች ለተጠቃሚዎች አስተላልፏል።
ዕጣ ወጥቶላቸው የቤት ባለቤት ከሆኑት ዕድለኞች መካከልም መምህርት ተረፈች ታደሰ አንዷ ናቸው። በዕለቱ መምህርቷ ዕደለኛ የሚያደርጋቸውን ዕጣ በማውጣት የቤት ባለቤትነታቸውን ለማረጋገጥ ችለዋል። መምህርቷ ደስታቸውን የገለጹበት ሁኔታ የመኖሪያ ቤት አንገብጋቢነት ጥግን ያሳየ ነው።
የመኖሪያ ቤት ችግሩ መምህርቷን ምን ያህል እንደፈተናቸው መገመት ባያዳግትም ከአንደበታቸው ለመስማት ባገኘናቸው ወቅት ደግሞ ለደረሳቸው ባለ አንድ መኝታ ቤት ውል ፈጽመው ደስታቸው እጥፍ ድርብ ሆኖ ነበር። መምህርት ተረፈች ታደሰ፤ ነዋሪነታቸው በሀዋሳ ከተማ ታቦር ክፍለ ከተማ ቂልጤ ቀበሌ ልዩ ስሙ መገናኛ አካባቢ ነው።
‹‹በወቅቱ ደስታዬን የገለጽኩበት መንገድ ለአምላኬ ምስጋናን ለማቅረብ ጭምር ነው። ዕጣው ከወጣልኝና ቤት ካገኘሁ አምላኬን በአደባባይ አመሰግናለሁ›› ብለው በገቡት ቃል መሠረት ደስታቸውን መሬት ላይ ወድቀው በመንከባለል እንደገለጹ ተናግረዋል።
‹‹ሀዋሳ ከተማ ውስጥ ለ35 ዓመታት ስኖር የመኖሪያ ቤት ችግር እንዴት አድርጎ እንደፈተነኝ እኔና እግዚአብሔር ነን የምናውቀው›› ያሉት መምህርት ተረፈች፤ እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት ሀዋሳ ከተማ ላይ የኑሮ ውድነቱ ከአዲስ አበባ ቢበልጥ እንጂ አያንስም። የመንግሥት ሠራተኛ የወር ደመወዙን በሙሉ ለቤት ኪራይ እያዋለ ነው ቢባል ማጋነን አይደለም።
አዲስ አበባ ከተማ ላይ መልካም ተሞክሮዎች አሉ። ለመምህራን የመኖሪያ ቤትና ተጨማሪ ገንዘብ ድጎማ ይደረጋል። ሀዋሳ ከተማ ላይ ግን ለመምህራን እንዲህ ያለድጋፍ የለም። በአዲስ አበባ ከተማ ያለው ተሞክሮ በአካባቢያቸውም ቢተገበር ተመኝተዋል።
ሀዋሳ ከተማ ላይ የቤት ኪራይ ውድ ከመሆኑም በላይ ልጆች ይዞ ከአንዱ ቦታ ወደሌላ መዘዋወር አስቸጋሪ ነው። ቤት አከራዮችም ልጆች ያላቸውን ቤተሰቦች ለማከራየት ፈቃደኛ አይደሉም። በዚህ ምክንያትም መምህርት ተረፈች ልጆቻቸውን ገጠር ውስጥ ቤተሰቦቻቸው ጋር ለማስቀመጥ ተገደዋል። እንደ ዕድር ያሉ ማህበራዊ ኃላፊነቶችን ለመካፈልም ተቸግረው ቆይተዋል።
በቤት ኪራይ ከ30 ዓመታት በላይ ተቸግረውና ተማርረው የቆዩት መምህር ተረፈች እንዳጫወቱኝ፤ ከተማ አስተዳደሩ በገነባው ወጪ ቆጣቢ ቤቶች ዕድለኛ በመሆናቸው የተሰማቸው ደስታ እጅግ ጥልቅ ነው። የከተማ አስተዳደሩ የጀመረውን የቤት ግንባታ አጠናክሮ ቢቀጥል እንደርሳቸው የተቸገሩ የከተማዋ ነዋሪዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ።
መንግሥት በተለያዩ ዘርፎች ጥሩ ሥራ እየሰራ ይገኛል። በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎችን የቤት ባለቤት የማድረግ ተሞክሮን በሀዋሳ ከተማ የማስፋት ሥራ እየሰራ በመሆኑ መልካም ሥራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ነው የመምህርቷ ፍላጎት።
ሌላኛው የቤት ዕድለኛ በሲዳማ ክልል ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ባለሙያ የሆኑት አቶ ስጦታ ከተማ ናቸው። አቶ ስጦታ ነዋሪነታቸው በሀዋሳ ከተማ ሲሆን፣ የቤት ኪራይ እጅግ አማሯቸው እንደነበርና አሁን ዕድለኛ በመሆናቸው እጅግ ተደስተዋል። በከተማ አስተዳደሩ በ2008 ዓ.ም ላይ ተመዝግበው ሲጠባበቁ እንደቆዩና በትክክለኛና ፍትሀዊ በሆነ መንገድ የቤት ባለቤት መሆን እንደቻሉ ተናግረዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ለተጠቃሚዎች ያቀረባቸው ቤቶች ለተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች በመሆኑ እርሳቸውም በአካል ጉዳተኞች ኮታ ውስጥ ተመዝግበው ማግኘታቸውን አጫውተውናል። አቶ ስጦታው እግራቸው ላይ በደረሰባቸው አደጋ አካል ጉዳተኛ ሲሆኑ እርሳቸውን ጨምሮ 10 አካል ጉዳተኞች ቤት ፈላጊ ሆነው ቀርበው ሁለት ሰዎች ብቻ ዕድለኛ መሆን ችለዋል። ያለባቸውን የአካል ጉዳት ከግምት ውስጥ በማስገባትም ከተማ አስተዳደሩ ምድር ወይም የታችኛው ወለል ላይ የሚገኙ ቤቶችን አስተላልፎላቸዋል።
በወር እስከ 3000 ብር ድረስ የግለሰብ ቤት ተከራይተው የሚኖሩት አቶ ስጦታ በአሁኑ ወቅት ያለው የኑሮ ውድነት በቤት ኪራይ ላለ ሰው ይቅርና ቤት ላለውም የሚፈትን እንደሆነ ይናገራሉ። ከተማ አስተዳደሩ አሁን የጀመረውን የቤት ልማት አጠናክሮ በመቀጠል በርካታ በቤት ችግር ውስጥ ለሚገኙ ነዋሪዎች በተለያዩ አማራጮች ቤቶችን ተደራሽ ያድርግ ሲሉ አሳስበዋል።
አያይዘውም ከተማ አስተዳደሩ አሁን ላይ አበረታች ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይም ዕጣ የሚያወጣባቸው ቤቶች መኖራቸውን አመልክቷል። ስለዚህ ቤቶቹን በፍጥነት አጠናቅቆ ለነዋሪዎች ቢያስተላልፉ መልካም ነው የሚል መልዕክታቸውን በማስተላለፍ እርሳቸው ያገኙትን ደስታ ለሌሎችም እንዲደርስ ልባዊ ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።
አጠቃላይ በሀዋሳ ከተማ ያለው የመኖሪያ ቤት አቅርቦትና ፍላጎት ምን ይመስላል፤ ያለውን ክፍተት ለመሙላትስ ከተማ አስተዳደሩ ምን እየሰራ ነው ስንል ላነሳነው ጥያቄም የሀዋሳ ከተማ ምክትል ከንቲባና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ሚልኪያስ ብትሬ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተዋል።
ሀዋሳ ከተማ ፍጹም ሰላማዊና ለነዋሪዎቿ ምቹ የሆነች ከተማ ናት። ነዋሪዎች የሚጎበኟትና የሚዝናኑባት ከተማ በመሆኗም በርካቶች ወደ ሀዋሳ ይሳባሉ። ከዚሁ ጋር ተያይዞም በከተማዋ የመኖሪያ ቤት ፍላጎት በጣም ከፍተኛና ከአቅርቦቱ ጋር ሊጣጣም ያልቻለ ነው። ይሁንና ከተማ አስተዳደሩ ችግሩ ከአቅም በላይ ነው ብሎ እጁን አጣጥፎ አልተቀመጠም። ይልቁንም የተለያዩ የቤት ልማት ፕሮግራሞችን ተግባራዊ በማድረግ የመኖሪያ ቤት ፍላጎቱን ለማርካት እየሰራ ይገኛል።
ከእነዚህም መካከል ከተማ አስተዳደሩ ለነዋሪዎች ሙሉ ወጪውን ሸፍኖ በራሱ አቅም የሚሰራቸው ወጪ ቆጣቢ ቤቶች ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው። ወጪ ቆጣቢ የሚባሉትን ቤቶች አስገንበቶ ለነዋሪዎች ተደራሽ እያደረገ ያለበት ፕሮግራም በ2008 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን፣ በዚህ ፕሮግራም ከተማ አስተዳደሩ ሊገነባቸው የያዛቸው መኖሪያ ቤቶች 352 ሲሆኑ፤ በአሁኑ ወቅት 152 ቤቶች ግንባታቸው ተጠናቅቆ ለነዋሪዎች በዕጣ ተላልፈዋል። በቅርቡም ቀሪዎቹ 200 ቤቶች ተጠናቅቀው ለተጠቃሚዎች የሚተላለፉ ይተላለፋሉ። ለመተላለፍ ዝግጁ የሆኑት ቤቶች ግንባታ 84 በመቶ የግንባታ አፈጻጸም ላይ እንደሆነ ተናግረዋል።
እንደ ኃላፊው ማብራሪያ ለቤቶቹ ግንባታም ከተማ አስተዳደሩ አጠቃላይ 262 ሚሊዮን ብር ወጪ አድርጓል። ቤቶቹ ወጪ ቆጣቢ እንደመሆናቸው ከተማ አስተዳደሩ በመጠነኛ ወጪ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ነዋሪዎች የቤት ባለቤት ለማድረግ አስቦ እየሰራ ሲሆን፣ በቀጣይም መሰል ፕሮግራሞችን ተግባራዊ በማድር የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ለማርካት ይሰራል።
ከተማ አስተዳደሩ በራሱ ወጪ እያስገነባቸው ካሉ ወጪ ቆጣቢ ቤቶች በተጨማሪም ሌሎች የመኖሪያ ቤት አማራጮች ከተማ ውስጥ ተግባራዊ እየሆኑ ነው። አጠቃላይ በከተማ ውስጥ 4200 የቀበሌ የሆኑ መንግሥት የሚያስተዳድራቸው ቤቶች ይገኛሉ። በቤቶቹ የሚጠቀመው ማህበረሰብ ትክክለኛ ስለመሆኑም የማጣራት ሥራ በመሥራት ለተገቢው ሰው እንዲውል ይደረጋል። ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል።
ሌሎች የቤት ልማት ፕሮግራሞችንም ከተለያዩ ባለድርሻ አካላትና ድጋፍ ሰጪ ከሆኑ ድርጅቶች ጋር በጋራ እየሰሩ ስለመሆኑ የጠቀሱት ምክትል ከንቲባ አቶ ሚልኪያስ፤ ዩኤን ሀቢታት የተሰኘ ድርጅት ከኢንዱስትሪ ፓርክ ኮርፖሬሽን ጋር በጋራ በመሆን የሚገነባቸው ቤቶች ይኖራሉ። ከተማ አስተዳደሩም እንዲሁ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በጋራ በመሆን የቤት ግንባታ ለማከናወን የጀመረው ሥራ አለ።
በእነዚህ ሁለት ፕሮግራሞች በተለየ ሁኔታ ተጠቃሚ መሆን የሚችሉት ከኢንዱስትሪ ፓርክ ጋር ተያይዞ በኢንዱስትሪ ውስጥ የሚሰሩ ሠራተኞች ናቸው። በኢንዱስትሪ ፓርክ ዙሪያ ያሉ የማህበረሰብ ክፍሎች ሰፋፊ ግቢ የያዙና ባለይዞታ የሆኑ ግለሰቦችን ተሳታፊ ያደርጋል። እነዚህ ግለሰቦች ቤት ገንብተው ለማከራየት አቅም የሌላቸው ይሆናል። ስለዚህ ብድር ወስደው ቤት ገንብተው ለቤት ፈላጊዎች የሚያከራዩበትን ዕድል ያመቻቻል።
በአሁኑ ወቅትም ሥራው የተጀመረ ሲሆን በፕሮግራሙ ተሳታፊ ለመሆን ፈቃደኛ የሆኑ 800 አባወራዎች ተገኝተዋል። በእያንዳንዱ አባወራ የመኖሪያ ግቢ ውስጥም ለአራት ሰዎች ቤት ተገንብተው ማከራየት እንዲችሉ ይደረጋል።
ሌላው ከተማ አስተዳደሩ መሬት በማዘጋጀት በማህበር ተደራጅተው የማህበር ቤቶችን ለመገንባት አቅምና ፍላጎት ያላቸውን በማሰባሰብ መገንባት እንዲችሉ ያደረጋል። ቤት አልሚዎች(ሪልስቴት) እንዲሁ አሳታፊ በማድረግ የማህበረሰቡን የኑሮ ደረጃ ታሳቢ በማድረግ እንዲሁም ከተማዋን የሚመጥን ግንባታ መገንባት እንዲቻል የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ይገኛል። ይሁንና በከተማ ውስጥ ያለውን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት እና አቅርቦት ማጣጣም አልተቻለም። ስለዚህ ከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ አማራጮችን በማፈላለግ ላይ ይገኛል።
ይህም ሆኖ በቅርቡ ለተጠቃሚዎች የተላለፉት ወጪ ቆጣቢ የሆኑ መኖሪያ ቤቶች ላይ ዕጣ የደረሳቸው ተጠቃሚዎች የነበራቸው ስሜት መኖሪያ ቤት ለነዋሪዎች ምን ያህል አንገብጋቢ ጥያቄ እንደሆነና አስተዳደሩንም ስሜት ውስጥ የከተተ ስለመሆኑ ምክትል ከንቲባው አቶ ሚልኪያስ አንስተዋል። ስለሆነም በቀጣይ ለቤት ልማት ፕሮግራሙ ትልቅ ትኩረት በመስጠት ከተማ አስተዳደሩ በሰፊው የሚሰራበት ይሆናል።
በቅርቡ ለነዋሪዎች የተላለፉት 152 ቤቶች በምን መስፈርት እንደተላለፉና ምን ያህል ግልጽነት ነበረው ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄም ምክትል ከንቲባ አቶ ሚልኪያስ፤ በቅርቡ በመንግሥት አቅም ተገንብተው የተላለፉት ወጪ ቆጣቢ ቤቶች ከሁሉም ማህበራዊ ዘርፎች ለተውጣጡ የማህበረሰብ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ ጥረት መደረጉን ተናግረው በዚህም አብዛኛው ነዋሪ ደስተኛ እንደነበር አስታውሰዋል። ተሳታፊ ከሆኑት የማህበረሰብ ክፍሎች መካከልም የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ 12 ማህበራዊ ዘርፎችን ያሳተፈ ሲሆን ለአብነትም የመንግሥት ሠራተኛ፣ አካል ጉዳተኛና የልማት ተነሺዎች ይጠቀሳሉ።
የዕጣ አወጣጥ ሥነሥርዓቱም ዕጣው ላይ ቤት የሚል እና ዜሮ የሚል ተጽፎ በጥንቃቄ ተጠቅልሏል። በመሆኑም ከየዘርፉ ተሳታፊ የሆኑት ሰዎችም ዕጣቸውን እንዲያነሱ ተደርጓል። በዚህም 152 ሰዎች የቤት ባለቤት የሆኑበትን ዕጣ አንስተው የቤት ባለቤት መሆን ችለዋል። በሥነሥርዓቱ ላይም የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የተለያዩ ባለሥልጣናትና የከተማው ነዋሪዎች በታዛቢነት ተገኝተዋል።
እንደ ሀዋሳ ከተማ በየጊዜው ቤት ፈላጊ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ወደ ከተማ አስተዳደሩ የሚመጡ መሆኑን የተናገሩት ምክትል ከንቲባ አቶ ሚልኪያስ፤ ቤት ፈላጊዎችን በየዘርፉ ተመዝግበው በመረጃ ቋት የሚያደራጁ መሆኑን ነግረውናል። በመሆኑም በብዛት የመኖሪያ ቤት ጥያቄ ይዘው ወደ ከተማ አስተዳደሩ የሚቀርቡት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች መሆናቸውን ተናግረው ችግሩን በየደረጃው ማቃለል እንዲቻልም እየተሰራ እንደሆነም አስረድተዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23/2013