በኢትዮጵያ የሕብረት ሥራ ማህበር ከሌላው ዓለም ዘግየት ብሎ የተጀመረ ሲሆን፣የ60 ዓመት ዕድሜ አለው ። ማህበራቱ የሚመሩበት ዓለም አቀፍ የተለያዩ ድንጋጌዎች ወጥተዋል ። በዚህ መሠረት በገጠርና በከተማ የገንዘብ፣ብድርና ቁጠባ ሕብረት ሥራ ማህበራት ሥራ በመጀመር እስካሁን መዝለቅ ችለዋል ።
በፌዴራል ሕብረት ሥራ ማህበር የፋይናንስ ሕብረት ሥራ ልማት ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ዱፌራ እንደሚሉት በኢትዮጵያ ባለፉት ረጅም ዓመታት የተሰራው ሥራ ከአፍሪካም ሆነ ከዓለም የህብረት ሥራ እንቅስቃሴ ጋር በንጽጽር ሲታይ በሚፈለገው ደረጃ ላይ ደርሷል ለማለት አያስደፍርም ። ማህበራት በዘርፈ ብዙ ውጣ ውረዶች ውስጥ አልፈው ነው አሁን ደረጃ ላይ የደረሱት።
የሕብረት ሥራ ማህበራቱ ከፖለቲካ፣ከሃይማኖት ከየትኛውም ተጽዕኖ ነፃ ሆነው እራሳቸውን በራሳቸው በማስተዳደር የአባሎቻቸውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በማስጠበቅ መሰረታዊ ችግሮቻቸውን ለመፍታት እንዲችሉ ተደርገው ቢቋቋሙም ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን ማህበራቱ ከመንግሥት ጋር ጥገኛ ሆነው ነው የሚንቀሳቀሱት። ይህ ደግሞ ነፃነታቸውን አላስጠበቀላቸውም። በመሆኑም የዕድገት እንቅስቃሴያቸው እንዲገታ አድርጎታል። ማህበራቱ በሚፈለገው ደረጃ አቅም ባለመፍጠራቸው ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆን አልቻሉም ። የአባላቶቻቸውንም የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት አላሳደጉም።
አዋጅ 147/91 ከወጣ ወዲህ ዓለም አቀፍ የሕብረት ሥራ ማህበራትን መርህ በተከተለ የማደራጀት ሥራ በመከናወኑ በተወሰነ መልኩ ከመንግሥት የፖለቲካ መዋቅር ጋር ተሳስረው እንዲንቀሳቀሱ ይደረግ የነበረው አሰራር እየቀነሰ መጥቷል ። ይህ ደግሞ እንቅስቃሴያቸው በተሻለ ደረጃ ላይ እንዲገኝ አስችሏል። እንቅስቃሴያቸው በገንዘብ ቁጠባ፣ በሸማቾች፣ በአገልግሎት አሰጣጥ ቅልጥፍና ይገለጻል ። የተሻለ እንቅስቃሴ እየታየ ቢሆንም ህብረተሰቡን ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ ብዙ ሥራ ይጠበቅባቸዋል።
እንዲህ ያሉ ችግሮችን በመፍታትና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በመጠቆም የፌዴራል የሕብረት ሥራ ማህበር ኤጀንሲ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ እየሰራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ብርሃኑ በዘርፉ የሕዝብ ተጠቃሚነት እስከምን ደረጃ መድረስ አለበት የሚለውን ለማሳካት የአጭር፣የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ዕቅድ ነድፎ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል ። በ2028ዓ.ም በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የሕብረት ሥራ ማህበር እንዲመሰረት፣በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥም የጎላ ሚና ሊወጡ የሚችሉ ጠንካራ የሕብረት ሥራ ማህበር ተፈጥሮ ማየት የሚለውን አገራዊ ግብ ለማሳካት ኤጀንሲው የማህበራቱ የአካባቢውን ሀብት መሠረት አድርገው የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመፍታት እንዲችሉ አቅማቸውን በመገንባት፣ የግብይት ድርሻቸውን በማሳደግ ፣ ደህንነታቸውም የተጠበቀ እንዲሆን፣ አገልግሎታቸው እንዲዘመን ፣በትኩረት ይሰራል።
በአሁኑ ጊዜ የሕብረት ሥራ ማህበራት በቁጥር አድገዋል ። አገልግሎታቸውም እንዲሁ ሰፍቷል። የተወሰኑት በከፍተኛና በመካከለኛ የአገልግሎት ደረጃ ላይ ቢሆኑም አብዛኞቹ ግን ገና ይቀራቸዋል። በመሆኑም አገልግሎታቸው እንዲዘመን የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ለተሻለ ነገር ማብቃት ከኤጀንሲው ተልዕኮዎች አንዱ ነው ያሉት አቶ ብርሃኑ ማህበራቱ ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ የግብርና ግብአቶችን በማቅረብ እንደሚንቀሳቀሱና መልሰውም ከአርሶአደሩ ምርት ሰብስበው ወደ ሸማቹ የሚያቀርቡ በመሆናቸው በግብይቱ አቅማቸውን በማጎልበት በተለይም በግብርናው ዘርፍ ላይ የተሰማሩ የሕብረት ሥራ ማህበራት እሴት ጨምረው ለሸማቹ እንዲያቀርቡ ለማስቻልም እንዲሁ በኤጀንሲው አስፈላጊው እገዛና ክትትል ይደረጋል ብለዋል። ውጤታማ እየሆኑ ሲሄዱ አቅርቦታቸው ከሀገር ውጭም አድጎ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን በማሳደግ አገርን የሚጠቅም ሥራ ሊሰሩ እንደሚችል አስረድተዋል ።
ቁጠባና ኢንቨስትመንት ማሳደግ በሚለው ርዕሰ ጉዳይ ላይም አቶ ብርሃኑ በሰጡት ማብራሪያ ማህበራት ከአባሎቻቸው ቁጠባን በስፋት ማሰባሰብ ይኖርባቸዋል። ቁጠባው መልሶ ለአባሎቻቸው የብድር አገልግሎት ውሎ ወደ ኢንቨስትመንት እንዲለወጥ ማድረግ ትልቁ ተግባራቸው ነው ። የገንዘብ፣ብድርና ቁጠባ ማህበራት ተደራጅተው አገልግሎት እንዲሰጡ ከተፈለገ በሕግና ደንብ እንዲመሩ ማድረግ ይጠበቃል ። እስካሁን በአጠቃላይ የተሰበሰበው የቁጠባ መጠን ወደ 20 ቢሊዮን ብር ደርሷል። እዚህ ደረጃ ለመድረስ ወደ 30 ዓመት ጊዜ ወስዷል። ኤጀንሲው ማህበራቱን በማገዝ የተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስ እየተከተለ ያለው አቅጣጫ በትክክል ከተተገበረ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በሶስት እጥፍ ወደ 60 ቢሊዮን ብር ከፍ ለማድረግ አቅዷል።
ባንኮች የሚሰበስቡት፣የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ከሚሰበስቡት የቁጠባ መጠን የገንዘብ፣ብድርና ቁጠባ ድርሻ ወደ አምስት በመቶ ደርሷል ። አጠቃላይ የቁጠባውን ድርሻ ወደ 20 በመቶ ከፍ የማድረግ ሥራ ይከናወናል ። ዕቅዱ የተለጠጠ ቢመስልም ባለፉት አራትና አምስት ዓመታት ብቻ ከተሰሩት ሥራዎች በመነሳት ማከናወን እንደሚቻል ማረጋገጥ ተችሏል ። ማህበራቱ ለአባላቶቻቸው የሚሰጡትንም ብድር በአምስት ዓመታት ወደ 63 ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ማድረስ ነው። ማህበራቱ ከባንክና ከማይክሮ ፋይናንስ በተሻለ ጤና የብድር አመላለስ ሥርዓት እንዳላቸው፣ በየዓመቱ የብድር አመላለሳቸውም ከ98 በመቶ በላይ እንደሆነና የማይመለሰው ብድርም አነስተኛ መሆኑን አመልክተዋል። በአሁኑ ጊዜ ከ92ሺ በላይ መሠረታዊ የህብረት ሥራ ማህበራት ሲኖሩ አንድ መሠረታዊ ማህበርም እስከ 50ሺ አባላት ይኖሩታል። ከዚህ ውስጥ የገንዘብ፣ብድርና ቁጠባ ማህበር ድርሻ 24 በመቶ፣ግብርና 25 በመቶ፣ሌሎች 14 በመቶ፣የቤቶች 32 በመቶ፣ ሸማች አምስት በመቶ ነው።
የገንዘብ፣ብድርና ቁጠባ ማህበራት ከሌሎች የፋይናንስ ዘርፎች በተሻለ አገልግሎት መስጠት በመቻላቸው፣ በአካባቢ ተደራሽ በመሆናቸው፣ከአርሶአደርና አነስተኛ ገቢ ካላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ገቢ በመሰብሰብ ኢንቨስትመንት ስለሚያበረታቱ፣ በፋይናንስ ተደራሽነታቸው፣ የሥራ ዕድል በመፍጠርም ባላቸው ሚና ተፈላጊነታቸው እየጨመረ መጥቷል።
ስለወለድ አልባ አገልግሎትም አቶ ብርሃኑ እንደገለጹት በሌሎች ሀገሮች የተለመደ ሲሆን ፍትሐዊ አሰራርን ያሰፍናል ። በአሰራሩ ኪሳራ በሚያጋጥም በሸሪአ ሕግ መሠረት መፍትሄ ያገኛል ። በኢትዮጵያ ገና ጅምር በመሆኑ በስልጠና የማስፋፋትና የማጠናከር ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 22/2013