አገር ሊመሰረት የሚችለው ሰዎች ተስማምተው በአንድ ሕግ ስር ለመተዳደር ሲወስኑ ነው ። በአለም ላይ የሚገኙ ሁሉም አገራት በሰዎች ስምምነት የተመሰረተ ቢሆንም የሀሳብ ብልጫ ለማግኘት ግን ጦርነትም አድርገዋል ። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ልትሆን የምትችለው ኢትዮጵያ ናት ። ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት ያስተዳደሯት መንግሥታት ሀሳባቸውን ለማስፋት ጦርነት አድርገዋል ። ስለዚህ ኢትዮጵያን ለመመስረት ከሀሳብ ስምምነት ውጪ ጦርነት መካሄዱ መዘንጋት የለበትም።
በሌላ በኩል አገርን ለመመስረት ለመኖሪያነት ምቹ የሆነ በመልክዓ ምድር መምረጥና በዛም መስፈር የግድ ብሏል ። ሁሉም አገራት አንድ ወጥ የሆነ አሰፋፈር ቢኖራቸውም ለኑሮ ምቹ የሆነ መልክዓ ምድር ለማግኘት ከጎረቤት አገራት ጋር ረጅም ጊዜ የፈጀ ጦርነት ያደርጋሉ ። በዚህም ግዛታቸውን ማስፋፋት ችለዋል ። በተጨማሪም ጉልበታቸውን አጠናክረው ቅኝ የሚገዙትን አገር ፍለጋ የተለያዩ አህጉራትንም ይዞራሉ ።
አፍሪካ በቅኝ ግዛት ለረጅም ዓመታት የተገዛች ስትሆን ከኢትዮጵያና ከላይቤሪያ በስተቀር ሌሎች አገራት በውጭ ወራሪዎች እጅ ወድቀው ነበር ። በዚህም ባህላቸውና የአኗኗር ዘይቤያቸው እንዲለውጡ ተገደዋል። ኢትዮጵያን በቅኝ ገዥዎች እጅ እንዳትወድቅ ያደረጋት በአንድ አገር መንፈስ የተዋደቁ ጀግና ልጆች ስለነበሯት ነው ። በአድዋም ሆነ በሌሎች አውድማ ከጠላት ጦር ጋር የተዋደቁ ጀግና አባቶች ተገቢው ክብር ሲሰጣቸው ብዙም አይስተዋልም ። በተለይ ለአገር ብዙ ውለታ የሰሩ አባቶች በየመንገዱ ወድቀው የሚገኙ ሲሆን ከተወሰኑት በስተቀር አብዛኛዎቹ አሁንም በጎዳና ላይ ይገኛሉ ።
አረጋውያን አመቺ የሆነ የማህበራዊ፣ የኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ ከተፈጠረላቸው በልዩ ልዩ የእውቀት ዘርፍ ያካበቱትን ልምድና ተሞክሮ ተተኪ ለሆነው ለአዲሱ ትውልድ ታሪኩን፣ ባህሉን፣ ወጉን እና አጠቃላይ ማንነቱን ጠብቆ እንዲያስቀጥል በማስቻል በራሱ የሚተማመን ትውልድ በማፍራት አገሪቱን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ማሸጋገራቸው አያጠያይቅም ። ከዚህ በተጨማሪ አረጋውያን በህይወት ዘመናቸው ባጋጠማቸው ውጣ ውረድ ያካበቱትን ዕውቀትና ልምድ በመጠቀም ማህበረሰቡ ለሚገጥመው ችግሮች መፍትሄ በማፈላለግ፣ የሚነሱ ግጭቶችን በመዳኘትና በማስማማት፣ በአጠቃላይ የአካባቢን ሰላምና ደህንነት በማስጠበቅ ረገድ ጉልህ ሚና አላቸው ።
በአገሪቱ ከመንግሥት ፈቃድ አግኝተው ከሚንቀሳቀሱ በጎ አድራጎት ማህበራት ውስጥ በብዛት በአረጋውያን ዙሪያ ሰፊ እንቅስቃሴ ያደርጋሉ ። ነገር ግን በአቅም ውስንነት የተፈለገውን ያክል እየሰሩ አይደለም ። መንገድ ላይ ወድቀው ከሚገኙ አረጋውያን በተጨማሪ በየቤታቸው ሆነው ጧሪ ቀባሪ የሌላቸውን አረጋውያን መንከባከብ የእነዚህ በጎ አድራጊ ማህበራት ኃላፊነት ነው ። የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በበዓላት ወቅትና በሌሎች ኩነቶች ብቻ ለአረጋውያን ድጋፍ የሚያደርጉ በመሆናቸው የተፈለገውን ያክል ለውጥ እንዲመጣ አላስቻለም ።
ለዛሬ የመረጥነው በጎንደር ከተማ የሚገኘውን ካለን ብናካፍል የህፃናት፣ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከልን ነው ። ማዕከሉ አረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማንን በዋነኝነት ድጋፍ እና እንክብካቤ የሚደርግላቸው ሲሆን ለተማሪዎችና ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶችና ህፃናትም በተወሰነ መልኩ ድጋፍ ይሰጣል ። ማዕከሉ እየሰራቸው ስላሉ ስራዎች፣ ስላጋጠሙ ተግዳሮቶችና ስለቀጣይ እቅዳቸው ከማዕከሉ መስራችና ስራ አስኪያጅ አቶ ዳዊት አየነው ጋር ቆይታ አድርገናል። እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
የማዕከሉ አመሰራረት
ማዕከሉ ሀምሌ 24 ቀን 2010 ዓ.ም ላይ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ውስጥ ነበር የተመሰረተው ። ቀደም ብሎ በሳይኮሎጂ ካውንስሊንግ ላይ በመቄዶንያ አረጋውያንና አዕምሮ መርጃ ማዕከል ውስጥ በአማኑኤል የአዕምሮ ሕክምና ስፔሻላይዜሽን ሆስፒታል ውስጥ በበጎ ፈቃደኝነት አቶ ዳዊት አገልግሏል ። ከዚህ በኋላ ወደ ጎንደር በማምራት ጎንደር ዩኒቨርስቲ ሆስፒታል ውስጥም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ይሰጥ ነበር ። በበጎ ፈቃደኝነት በሚያገለግልበት ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ውስጥ ህመምተኛ ሰዎች አስታማሚ ሳይኖራቸው በሆስፒታል ውስጥ ተኝተው ይመለከት ነበር ። በሌላ በኩልም በጎንደር ከተማ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ሰዎች ወድቀውም ይመለከትም ነበር። በሆስፒታል ውስጥና በመንገድ ላይ አብዛኛው ሰው ገንዘብና ምግብ ይዞ መንገድ ላይ ወድቆና ያለአስታማሚ ይገኛል ። እነዚህ ሰዎች ለመርዳትና ያለን ነገር ማካፈል ቢቻል በሚል ሆስፒታል ውስጥ ከሚገኙና በጎ ፈቃደኞችን በማሰባሰብ ማዕከሉ እንዲመሰረት ተደረገ ። ሲመሰረትም ቤተሰብና ደጋፊ የሌላቸውን ሰዎች በየተኙበት ክፍል እንዲሁም በየቤታቸው በመሄድ ድጋፍ በማድረግ ስራዎች ተጀመሩ።
ማዕከሉ ያከናወናቸው ተግባራት
ማዕከሉ ከተመሰረተ በኋላ ያከናወናቸው ተግባራት ብዙ ናቸው ። የመጀመሪያው አስታማሚ የሌላቸውን ሰዎች ማስታመም፣ ድጋፍ ማድረግ፣ በአቅራቢያው የማይገኙ መድኃኒቶችም አፈላልጎ ማምጣት፣ ቤት ለቤት በመንቀሳቀስ ደጋፊ የሌላቸውን ሰዎች ባሉበት መጦር፣ በሳምንት አንድ ጊዜ እሁድ ሰውነታቸውን ማጠብ እንዲሁም የልብስ ማጠብ ሥነሥርዓት ይካሄዳል ። ከዚህ ባሻገር በዓመት መጀመሪያ ላይ የመማሪያ ቁሳቁስ በመሰብሰብ ወላጆቻቸውን በተለያየ ምክንያት ላጡና አነስተኛ ገቢ ካለው ቤተሰብ ለመጡ ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል።
የተለያዩ የሕይወት ክህሎት ስልጠናዎችን በየትምህርት ቤቱ የመስጠት ስራዎች የተከናወኑ ሲሆን የጎንደር ከተማ በሚያዘጋጃቸው ፕሮግራሞች ላይ በመገኘት ደም በመለገስና በእምቦጭ ነቀላ ላይ በግንባር ቀደምትነት በመሳተፋቸው የጎንደር አስተዳደር ከንቲባ የማዕከሉን እንቅስቃሴ በማየት ቦታ ተሰጣቸው ። በተሰጣቸውም ቦታ ላይ ማዕከሉ ተመሰረተ ። የሰው ድጋፍ የሚፈልጉና ጠያቂ የሌላቸው እንዲሁም እራሳቸውን ችለው መንቀሳቀስና መመገብ የማይችሉ አረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን እንዲሁም ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶችና ሕፃናትን ጨምሮ ማዕከል ውስጥ የመጠለያ፣ የሕክምና የምግብ፣ የአልባሳትና የቤት ውስጥ እንክብካቤ እየተደረገላቸው ይገኛል።
አቅም የሌላቸውን አረጋውያን በከተማ ውስጥና ከከተማው ውጪ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የማንሳት ስራ ይከናወናል ። ለምሳሌ በደቡብ ጎንደር ደብረታቦር፣ በማዕከላዊ ጎንደር እንዲሁም በሌሎች ከተሞች በመሄድ ጧሪና ደጋፊ የሌላቸውን በመምረጥ እንዲደገፉ ይደረጋል ። ቤተሰቦቻቸውን በሞትና በችግር ምክንያት ያጡ ለረጅም ዓመታት በቤተክርስትያን አካባቢ ወይም ከተሞች ላይ ተቀምጠው የነበሩ ሰዎች ወደ ማዕከሉ እንዲገቡ ይደረጋል። አብዛኛዎቹ በከባድ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ወድቀው የሚገኙ በመሆናቸው በአፋጣኝ ህክምናና እንክብካቤ ይደረግላቸዋል ። በተለያየ መንገድ ሕይወታቸውን ሲመሩ የነበሩ ሰዎች በጉዳትና በጤና ማጣት ምክንያት መንገድ ላይ የወደቁ አረጋውያንን በቅርብ ከሚገኝ ሰው አድራሻ በመጠቆም ወይም የማህበሩ አባላት በመንቀሳቀስ በየአካባቢው በመጠየቅ ይገኛሉ ። አንዳንዴ ደግሞ የሰራተኛና ማህበራዊ ቢሮ በሚያደርሰው ጥቆማ መሰረት መስፈርቱን የሚያሟሉ ወደ ማዕከሉ እንዲገቡ ይደረጋል።
ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶችና ህፃናት የሚገኙት በጥቆማ ሲሆን ከሆስፒታልና ከሴቶችና ሕፃናት ቢሮዎች በሚገኙ መረጃዎች ወደ ማዕከሉ እንዲገቡ ይደረጋል ። በተጨማሪም አባላቱ በሚያደርጉት አካባቢያዊ ቅኝት ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶችና ህፃናት የማግኘት እድሎች ይኖራሉ ። ማዕከሉ ድጋፍ እየሰበሰበ ያለው ማዕከሉ ድረስ መጥተው በመጎብኘት ድጋፍ ከሚያደርጉት ሲሆን ለምሳሌ በቁሳቁስ ድጋፍ ሊያደርጉ ይችላሉ ። የተወሰኑት ለምግብነት የሚውሉ መኮሮኒ፣ ፓስታ እንዲሁም ሌሎች ነገሮችን ያመጣሉ። የተወሰኑ ሰዎች ደግሞ የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋሉ ። በሌላ በኩል ማዕከሉ በከፈታቸው የባንክ አካውንቶች ውስጥ ገንዘብ የሚያስገቡ አሉ ። እነዚህ ድጋፎች ውስን ሲሆኑ በቋሚነት የሚያዝ አይደለም።
የህብረተሰቡ አቀባበል
የማዕከሉን መከፈት ማህበረሰቡ አስፈላጊ የሆኑ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል ። የተለያዩ ፕሮግራሞች ለምሳሌ ለልደት፣ ለሰርግ እንዲሁም ሌሎች ድግሶችን በማዕከሉ ውስጥ ያከብራሉ ። ባለው መረጃ መሰረት ማዕከሉን በየጊዜው እየመጡ ይጎበኛሉ ። የጎንደር ዩኒቨርስቲ ከማዕከሉ ጎን በመሆን በተለያዩ ጊዜያት ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል ። የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ማዕከሉን ከመጎብኘት ባለፈ በግላቸው ድጋፍ ያደርጋሉ። እስካሁን ባለው ሁኔታ የአካባቢው ሰውም ሆነ ዩኒቨርሲቲው ከማዕከሉ ጎን ነው ።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ቋሚ ባይሆንም በተለያዩ ጊዜያት የምግብ ግብዓቶችን ድጋፍ አድርጓል ። ከዚህም ባሻገር የሎጂስቲክስ ማለትም በአካባቢው የውሃ ችግር ስላለ ይህን ለመፍታት በቦቴ ውሃ የማቅረብ ስራ ያከናውናሉ። የጎንደር ከተማ አስተዳደር ደግሞ አሁን ማዕከሉ የሚገኝበትን ቦታ ሰጥቷል ። ከዚህ ባሻገር የሞራል ድጋፎችን ያደርጋል ።
ማዕከሉን ያጋጠሙት ችግሮች
ማዕከሉ ሥራውን ከጀመረ ወቅት አንስቶ ቋሚ የሆነ የገቢ ማስገኛ ነገር የለውም ። ቋሚ የሆነ ገቢ አለመኖሩ ድጋፍ የሚደረግላቸው ሰዎች ቁጥር ከፍ ያለ በመሆኑና በየሰዓቱ ከመንገድ እንዲነሱ በጥቆማ መልክ የሚመጡት በመብዛታቸው ያሉትን ለማስተዳደር ፈተና አጋጥሟል ። ስራዎችን ለማከናወን የገንዘብ አቅም የግድ ስለሚያስፈልግ ቋሚ ገቢዎች ያስፈልጋሉ ። በሌላ በኩል ማዕከሉ የሚሰራበት ተጨማሪ ቦታዎች የሚያስፈልጉት ሲሆን አረጋውያኑንና የአዕምሮ ህሙማኑን ከነበሩት ለማንሳት የመኪና እጥረት መኖር ሌላኛው ችግር ነው። አብዛኛዎቹ አረጋውያን በጣም የተጎዱ በመሆናቸው በቀላሉ በኮንትራት መኪና ማመላለስ አይቻልም ።
አሁን ማዕከሉ የሚገኝበት ቦታና በውስጡ የሚገኙት የሰዎች ብዛት ተመጣጣኝ አይደለም ። በዚህም ችግሩን ለመፍታት ከከተማው አስተዳደር ጋር ውይይት እየተደረገበት ነው ። ሌላው የቁሳቁስ ችግሮች ሲሆኑ አልጋ፣ ፍራሽ፣ የውሃ ታንከር፣ የምግብ ግብዓት እንዲሁም የንፅህና መጠበቂያዎችና ሌሎች እቃዎች እጥረት አለ ። ማዕከሉ ከተመሰረተ አጭር ጊዜው ሲሆን ምንም አይነት የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ እርዳታ የሚያገኝ አይደለም።
ቀጣይ እቅዶች
በቀጣይ ማዕከሉ ያሉትን የቦታ ውስንነቶች ተመልክቶ የማስፋፊያ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ እንቅስቃሴ ጀምሯል። ማዕከሉ በፕሮጀክቱ የራሱ የሆነ ገቢ የሚፈጥርበት በቀጣይ ደግሞ ሴቶችና ህፃናት እራሳቸውን ችለው የሚተዳደሩበት እንዲሁም አረጋውያንና አዕምሮ ህሙማን የራሳቸው መኖሪያ ተዘጋጅቶላቸው የሚስተናገዱበት እራሱን የቻለ ሁሉን አቀፍ አገልግሎት የሚሰጥበት ስራዎች ታስበዋል። በማዕከል ውስጥ የጤና መሻሻል ያመጡ ሰዎች ወደ ስራ የሚገቡበት ጭምር እቅዶች ተዘጋጅተው ስራዎች ተጀምሯል ። በቀጣይ እራሱን የቻለ ሁሉን አቀፍ እንዲሆን ለማስቻል የረጅም ጊዜ እቅድ አለ።
በመጪው በዓል ደግሞ ፈቃደኛ ከሆኑ ማህበረሰብ ክፍሎች ጋር በዓሉን ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነው ። ማዕከሉ ባለው አቅም ለማክበር የተዘጋጀ ሲሆን በዓሉን ከማዕከሉ ጋር ለማክበር የሚፈልጉ ሰዎች መምጣት ይችላሉ። ካላቸው ላይ አካፍለው ከአረጋውያንና ከአዕምሮ ህሙማኑ ጋር ለማሳለፍ ፈቃደኛ የሆነ ሰው መሳተፍ ይችላል።
መርድ ክፍሉ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 22/2013