ዛሬ ስለ ማይሞቱ ህያው ነፍሶች እናወራለን። ከሰው ወገን ተፈጥረው ለዘላለም ስለሚኖሩ የማይሞቱ ህያው ነፍሶች እነግራችኋለሁ። ይሄ ዓለም ከጥንት እስከዛሬ በነጻ ፍቃዳቸው ለሚኖሩ በርካታ ሰዎች የጋራ መኖሪያ ነው። ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ በምድር ላይ መቶ ቢሊዮን የሰው ልጅ ተፈጥሯል ተብሎ ይታመናል።
በአሁኑ ጊዜም ዓለም ላይ ስምንት ቢሊዮን የተጠጋ የሰው ልጅ ይኖራል። ወደፊትም ይሄ ተፈጥሯዊ ሂደት የሚቀጥል ይሆናል። ጉዳዩ ዓለም ላይ ምን ያክል የሰው ልጅ ተፈጥሯል ሳይሆን በዚህ ሁሉ ተፈጥሯዊ ሂደት ውስጥ ለሰው ልጅ ሁሉ የሚበጁ የማይሞቱ ህያው ነፍሶች ስለመኖራቸው ላወጋችሁ ነው። እንዴት አትሉኝም? በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ እስካሁን ድረስ ብዙ አይነት ሰዎች ተፈጥረዋል። በበጎ ስራቸው ታሪክ የማይረሳቸው በዛው ልክ ደግሞ በመኖራቸው ለሌሎች ስቃይና መከራ በመሆን ያለፉ ብዙ ሰዎች አሉ።
የማይሞቱ ነፍሶች ስል ለዛሬ የማወጋቸው ለሰው ልጅ ሁሉ መልካም ስለሆኑ ደጋግ ነፍሶች ነው። እንደ ሻማ ቀልጠው ለሌላው ብርን መሆን ስለቻሉ ደጋግ ነፍሶች ነው። እርግጠኛ ነኝ አሁን በደንብ ገብቷችኋል…የማይሞቱ ህያው ነፍሶች ያልኳችሁ እነሱን ነው። ወደዚህ ዓለም ስንመጣ በምክንያት ነው። ድንገት የመጣ የለም። በስህተት ሰው የሆነ ማንም የለም ። መፈጠራችን በምክንያት ነው። በዙሪያችን ደስታን የሰጡን፣ ለስኬታችን ብርታት የሆኑን ብዙ ሰዎች ይኖራሉ ። በመኖራቸው ያኖሩን፣ በኃይል በተስፋ ያቆሙን..እንዳንጠፋ እንዳንደበዝዝ እየቀለሙ ያደመቁን ነፍሶች ይኖራሉ። በዛው ልክ ከፍቅር ከእውነት ጎለው ከሙላታችን ያጎደሉንም፣ በመኖራቸው መኖራችንን የቀሙን እኩይ ልቦችም አሉ ብዬ አስባለሁ።
ዓለም የነዚህ ሁለት አይነት ሰዋዊ መልኮች ቅይጥ ናት። በአንዱ እየሳቅን በአንዱ እያዘንን እንድንኖር ተፈጥሮ የማይታበል ዘላለማዊ ሀቋን አውርሳናለች። ለዓለም የበሩ…በብርሃናቸው ብርሃን የሆኑ ለእኔና ለእናንተ ለተቀረውም ዓለም የመኖር ምክንያት የነበሩ ብዙ መልካም ሰዎች ተፈጥረዋል ። የማይሞቱ ህያው ነፍሶች ያልኳችሁ እነሱን ነው ። ለዘላለም ባልጸና በሚያልፍ ዓለም ውስጥ የማይሞቱ ነፍስና ስጋ ይዘው ከአዲሱ ትውልድ ጋር አዲስ ሆነው የሚኖሩ ንጹሐን እዚም እዛም አሉ።
በነፍሳቸው ተወራርደው ኢትዮጵያን ያቆሙልን አባቶቻችን በእኔና በእናንተ ልብ ውስጥ ሳይሞቱ የሚኖሩ ህያው ነፍሶች ናቸው ። ለዛሬ ታላቅ ክብር ያበቁን ቤተሰቦቻችን በእኔና በእናንተ ልብ ውስጥ ሳይዳምኑ ይኖራሉ ። የአሁኗን አለም ውብ የሆነችው በጥቂት መልካም አስተሳሰብ ባላቸው ግለሰቦች ነው ። ማዘር ተሬዛ የድሆች እናት ነበሩ ። አለም በአንድ ቋንቋ ያወራላቸው ፍጹም አዛኝ እናት ነበሩ ። በእሳቸው ሕይወት ውስጥ እውነት የማይመስሉ ግን ደግሞ እውነት የሆኑ የደግነት ጥጎች አሉ ። ከባለጸጋ እየለመኑ ድሀ ይረዱ ነበር ። ካላቸው ላይ ከሌላቸው ላይም ይሰጡ ነበር።
አንድ ቀን ከባለጸጋ የሰበሰቡትን ሩዝ ተሸክመው ወደ ድሆች መንደር ያቀናሉ…ሩዝ ያለበትን ቅርጫት በወገባቸው አዝለው በድሆቹ መንደር ይሄዳሉ..ማን ምን ያክል እንዳነሳ ላለማየት ፊታቸውን ወደ ኋላ ሳያዞሩ የያዙት ቅርጫት ባዶ እስኪቀር ድረስ በዛ መንደር ይመላለሳሉ። ሩዙ አልቆ ቅርጫቱ ባዶ ሲቀር ወደ ቤታቸው ሄደው ሌላ በሩዝ የተሞላ ቅርጫት ተሸክመው ወደ ድሆቹ መንደር ይመለሳሉ።
ድሆቹ በነጻነት የፈለጉትን እንዲወስዱ በመፍቀድ ፊታቸውን ወደ ኋላ ሳያዞሩ በድሆቹ መንደር ድሆቹን ሲያገለግሉ ይውሉ ነበር ። አንድ ቀን በጠና ታመው ህይወታቸው ሊያልፍ በተቃረበበት የመጨረሻዋ ሰዓት ላይ አንድ ጋዜጠኛ ወደ ቤታቸው ይሄዳል ። ያየው ነገር ግን በጣም የሚያሳዝን ነበር..ቤታቸው ውስጥ ከአንዲት የሳር ፍራሽ በቀር የውሀ መጠጫ እንኳን አልነበረም…ጋዜጠኛው በሀዘን ስሜት ተውጦ “በዚህ ሁሉ ድህነት ውስጥ እንዳሉ አናውቅም ነበር..በጣም አዝናለሁ ‹ “ሲላቸው።
ቀበል አድርገው ‹ቤቴን እንጂ ልቤን አላየኸውም..ልቤን ብታየው የዚህ ዓለም ባለጸጋዋ ሴት እኔ እንደሆንኩ ትረዳ ነበር አሉት። አሁን ለዘላለም በደስታ ወደ ሚያኖረኝ አምላኬ እየሄድኩ ነው። ለኔ ሰው መሆን በምድር ከስሮ በሰማይ ማትረፍ ነው ሲሉ መለሱለት።
የሀገራችንም ሌላዋ የድሆች እናት አበበች ጎበና…በእያንዳንዳችን ነፍስ ውስጥ ላትረሳ አለች። የአበበች ጎበናን ታሪክ ሁላችሁም የምታውቁት ነው። ለሰብዓዊነት የኖረች፣ በደግነት በሰውነት ከትላንት እስከዛሬ ለብዙዎች ጥላ ከለላ የሆነች አምላካዊት ሴት ናት። በእሷ ነፍስ የብዙዎች ነፍስ ስቃለች። በእሷ ቀና ልብ የብዙዎች ቁስል፣ የብዙዎች ህመም ሽሯል። በእሷ ህያውነት የብዙ ኢትዮጵያዊ ህጻናት ተስፋ ለምልሟል። በርካታ የማይነጉ ሌሊቶች ፤የማይመሹ ቀናት መሽተው ነግተዋል። የማይሞቱ ህያው ነፍሶች ያልኳችሁ እኚህን ነው።
እነ ማህተመ ጋንዲ፣ እነቼኮቬራ ለብዙዎች ኖረው ያለፉ ባለ ህያው ነፍሶች ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ በክፋታቸው ዓለም የማትረሳቸው ብዙ ሰዎችም ኖረው አልፈዋል። ለምሳሌ ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት በበላይነት ሲመራ የነበረው ለስድስት ሚሊዮን ንጹሀን ዜጎች ሞት ተጠያቂ የሆነው የናዚው ሂትለር አንዱ ነው። ሂትለር በክፉ ስራው በሰው ልብ ውስጥ በመጥፎነቱ ሁሌም ሲታወስ የሚኖር ሰው ነው። በክፋታቸው የአለምን ጸዓዳ መልክ አጠይመው ያለፉ በርካታ ክፉ ነፍሶች በተለያየ ጊዜ ተፈጥረዋል። እነኚህ ነፍሶች በትውልድ ውስጥ በኩራት የሚያኖራቸው ምንም መልካም ስራ የላቸውም። ሲኖሩም ሞተው ነበር አልፈውም ሲኮነኑ ይኖራሉ።
ፊታችሁን በመኖራቸው ብርሀን ወዳለበሱን ደጋግ ነፍሶች መልሱ። በሚመጣው ትውልድ ልብ ውስጥ በመልካም እንድትታወሱ የሚያደርጋችሁን በጎ ነገር እያደረጋችሁ አይቀሬውን ሞታችሁን ጠብቁ ። ሞት መጥፎ የሚሆነው በክፉ ስራችን ስንታወስ ነው። በጎ ስራ ለሰራ ልብ ሞት ትንሳኤ ነው። ሞታችሁን በፍቅር ግደሉት ። ሞታችሁን በመልካምነት ግደሉት ። ነገ ላይ ሳትኖሩ በትውልዱ ልብ ውስጥ ስትታወሱ እንድትኖሩ የሚያኮራ፣ የሚያስመሰግን ስራን ሰርታችሁ እለፉ።
አሁን ላይ ብዙዎቻችን ለበጎ ነገር ከመልፋት ይልቅ ለመጥፎ ነገር መልፋትን እንደ ጥሩ ነገር ይዘነው እንገኛለን። ወላጅ ከሆናችሁ በልጆቻችሁ ልብ ውስጥ ታላቅ ማንነትን ትከሉ ። የሀገር ፍቅርን፣ ሰብዓዊነትን ፍጠሩ ። መምህር ከሆናችሁ ለተማሪዎቻችሁ እውነትን፣ ይቅርታን አስተምሯቸው ። ጥሩ አርዓያ በመሆን ነጋቸውን ስሩላቸው። ከክፉ ስራ ወጥተን በሚጠቅመንና በምንባረክበት ቅዱስ ስፍራ ላይ እንቁም ።
አባቶቻችን በቀና ልብ፣ በጽኑ አገር ወዳድነት በፍቅር ብርሃን እንዳጠመቁን እኛም ለሌሎች የሚሆን ብዙ ፍቅርን ብዙ ይቅርታን መሰብሰብ አለብን። ያኔ ከማይሞቱት ህያው ነፍሶች እንደ አንዱ እንቆጠራለን። ይቅርታ ፍቅር ባለበት የሚኖር አምላካዊ ባህሪ ነው። በፈጣሪና በሰው ልጆች መካከል የተሰመረ ደማቅ መለኮታዊ መስመር ። ፍቅር የማይሞቱ ነፍሶች ህግ ነው…የቅን ነፍሶች ማደሪያም ነው ። በነፍሳችሁ ላይ ይቅርታን አክሉ ። እየማራችሁ ይቅርም እያላችሁ እንድትኖሩ እንጂ የበደላችሁን እየበደላችሁ ድንጋይ በወረወረባችሁ ላይ ድንጋይ እየወረወራችሁ እንድትኖሩ ሰው አልሆናችሁም።
ይቅርታ ፍቅርን የሚያውቁ ሁሉ የሚናገሩት የነፍሶች ቋንቋ ነው። የይቅርታ ልብ ሁሌ ያማረ፣ ሁሌ የፈካ የጸሀይ መውጫ አናት ነው…በብርሀን የተሞላ። ይቅርታ ሳትሞቱ ህያው ሆናችሁ በትውልድ ልብ ውስጥ የምትኖሩበት ጥበባችሁ ነው። ይቅርታ ክፉዎችን ማሸነፊያችሁ፣ እብሪተኞችን መርቻችሁ በትረ ሙሴአችሁ ነው። በዓለም ላይ በበጎ ስራቸው በትውልድ ልብ ውስጥ ደምቀው የተጻፉ ነፍሶች ይቅርታ አድራጊዎች ነበሩ።
በአሁኑ ሰዓትም በዓለም ላይ ደስተኛና ስኬታማ ሆነው የምናያቸው ሰዎች ከሁሉ ነገራቸው በላይ ፍቅርና ይቅርታን ያስቀደሙ ናቸው ። እግዚአብሔርን የሚፈራ ልብ ሁል ጊዜ ይቅርታ ያደርጋል ። የፈረሱ ትዳሮች፣ የፈረሱ ጓደኝነቶች፣ ጸጸት የዋጣቸው ትላንቶች ባጠቃላይ ያልተሳኩ ሰዋዊ ትልሞች ሁሉ ይቅርታ የሌለባቸው ናቸው። ፍቅርና ይቅርታን ሳታውቁ የምትኖሩት ሕይወት ዋጋ የለውም። ፍቅርና ይቅርታን ማወቅ ሳይሞቱ ህያው ሆኖ ለዘላለም የመኖር ምስጢር ነው ። ህልሞቻችን የሚሳኩት ስለቀደምን፣ ከሌሎች የተሻልን ስለሆንን ወይም ደግሞ በእውቀታችን ድንቆች ስለሆንን ሳይሆን በልባችን ውስጥ ለሰው ልጅ ሁሉ የሚበቃ በቅቶም የሚተርፍ የይቅርታ እውነት ሲኖረን ነው ።
ብዙዎቻችን ተምረን አውቀው ብዙ ዲግሪዎችን ይዘን ያልተሳካልን ሞልተናል ። ቢሳካልንም እርካታ የሌለን ብዙዎች ነን ። የእርካታ ሚስጢሩ ከእውቀትና ከገንዘብ በላይ የፍቅር ሰው መሆን ላይ ነው ። የደስታ ጥጉ ይቅርታን ማወቅ ላይ ነን ። ዓለም ሰፊ ናት ። ከብዙ አይነት ሰዎች ጋር ተቻችለን እንድንኖር ነው ሰው የሆነው ። ሆደ ሰፊነት ዋጋ አለው ። አንዳንድ ሰዎች ባልተገባ እኩይ ባህሪያቸው ስራቸውን ትዳራቸውን ያጣሉ። ሕይወት የገባቸው አንዳንዶች ደግሞ በትዕግስት በይቅርታ ግዛታቸውን ሲያሰፉ እንመለከታለን ። መኖር ጥበብ ይጠይቃል ። ፍቅርና ይቅርታ በማንም ልብ ውስጥ አሉ ። በፈጣሪ ጸጋ ተሞልተን ነው ወደ ምድር የመጣንው ። ልባችንን ለመጥፎ ነገር እያስገዛን ፍቅርና ይቅርታችንን አጠፋን እንጂ ሰውነታችን አምላካዊ ነበር ።
አሁንም የእውነት ሰው ሁኑና የማይሞት ዘለዓለማዊ ነፍስን በላያችሁ ላይ ትከሉ እላችኋለሁ ። ፍቅርና ይቅርታ በጠቢባን ልብ ውስጥ ያሉ እንቁዎች ናቸው ። የአንድ ሰው የእውቀቱ ጥግ፣ የስልጣኔው አጽናፍ የሚለካው በልቡ ውስጥ ባለው የፍቅርና የመልካምነት ብዛት ነው ። ከጥላቻ ውጡ ። ሰዎች እንደሚሳሳቱና ፍጹም እንዳይደሉ ከተረዳን ይቅርታ ማድረግ አይቸግረንም ። ዓለም በሚሳሳቱና ልክ ባልሆኑ ሰዎች እንደተሞላች መረዳት ጥሩ ነው ። በመንገዳችን ብዙ አይነት ሰዎች ይመላለሳሉ..ፍቅርን እውነትን ይዘው የሚመጡ አሉ ። በጥሩነት ሊባርኩን የሚመጡ እንዳሉ ሁሉ በደልን ክህደትን ይዘው ሊያቆሽሹን የሚመጡም ይኖራሉ ። ከእኛ የሚጠበቀው በታጋሽ ልብ ሁሉንም እንዳመጣጡ በመሸኘት ወደ ፊት መሄድ ብቻ ነው ።
በህይወታችሁ፣ በትዳራችሁ፣ በመውጣት በመግባታችሁ ውስጥ ለሌሎች የሚሆን በጎ ነገር ይኑራችሁ። መልካምን የማታውቅ ነፍስ ከአምላክ ዘንድ አይደለችም ። እዚህ ምድር ላይ በመልካም ስራችሁ ለሌሎች ክብርና ሞገስ ከመሆን ውጪ መጠሪያ የላችሁም። በምድር ቆይታችሁ በስራችሁ ከመደሰትና ሌሎችን ከማስደሰት ባለፈ ታላቅ ጀብድ የላችሁም። ስራችሁ ነው የሚቀረው ። ስማችሁ..ተግባራችሁ ነው በትውልድ ልብ ውስጥ የሚቀረው..
ስለዚህም እንዳልኳችሁ በመልካም ሥራችሁ የማይሞት ህያው ነፍስን የእናንተ አድርጉ። ሁሉም ነገር በጊዜ የተገደበ ነው…ይሄ ዓለም ትላንት የሌሎች ነበር ። ዛሬ ደግሞ የእናንተ ሆኗል ። ነገ የሌሎች ከመሆኑ በፊት በጊዜአችሁ ላይ ስማችሁን የሚያስጠራ ታሪካችሁን የሚመልስ ትርፋማ ስራ ሰርታችሁ እለፉ ። ኖራችሁ ለመሞት ሳይሆን ሞታችሁ ለመኖር ሆናችሁ ኑሩ ። ስማችሁ በጎ ካደረጉ ሰዎች መካከል እንዳይጠፋ ራሳችሁን በወርቅ ቀለም ከትቡ። በዘመን ውስጥ እንድትኖሩ፣ በትውልድ ውስጥ ዳግም እንድትፈጠሩ የማይሞት ህያው ነፍስን ተላበሱ። በሌሎች መልካምነት እንደተፈጠራችሁ ሁሉ በእናንተ መልካምነትም የሚፈጠሩ ስላሉ ልቦቻችሁን ለበጎ ስራ አዘጋጁ እያልኩ ላብቃ። ቸር ሰንብቱ ።
ዘለዓለም የሳጥን ወርቅ (የእፀ ሳቤቅ አባት)
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 22/2013