
አዲስ አበባ፦ ብልህና አስተዋይ ሆነን ነገን በማሰብ ዛሬ ላይ ሰከን ማለት ካልቻልን እንደ አገርና ሕዝብ መቀጠላችን አጠያያቂ እንደሚሆን የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት ፕሬዚዳንትና የአገር ሽማግሌ ፓስተር ጻድቁ አብዶ ገለጹ።
ፓስተር ጻድቁ በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፣ አሁን በአገሪቱ እየታየ ያለው አዝማሚያ በጣም አደገኛና ወዳልሆነ መንገድ እያመራ ያለ ነው።
አገር እንደ አገር እንድትቀጥል ሕዝብም እንዳይጠፋ ብልህና አስተዋይ ሆነን ነገን በማሰብ ዛሬ ላይ ሰከን ማለት ያስፈልጋል።
እነ የመን ሶሪያና ሌሎችም አገሮች ወዳልሆነ ጥፋት የገቡት ሲጀመር እንደዚህ አደርጓቸው ነው ያሉት ፓስተር ጻድቁ፣ «ውሃ ሲወስድ እያሳሳቀ» እንዳይሆንብን ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
«እኛ ኢትዮጵያውያን በውስጣችን ብዙ ብሔር ብሔረሰብ ያለን ብዙ ሕዝቦች ነን፤ ስለዚህ ይህንን የመጣብንን ቁጣ ለማብረድ በመጀመሪያ ወደ ፈጣሪ መመለስ፤ ሁለተኛ አንዳችን ለሌላችን ስጋትም ጥፋትም ህመም ከመሆን መቆጠብ ይኖርብናል። ከዚያ ይልቅ አንዳችን ለሌላችን መድኃኒት ሆነን መገኘት እንዳለብን አመልክተዋል።
የአገር ሽማግሌዎችን። የሃይማኖት አባቶችን፣ የኡስታዞችን፣ የአባገዳዎችን፣ የሱልጣኖችን ምክር መስማት አሁን ካለንበት ችግር ለመውጣት ትልቅ መፍትሔ ነው ያሉት ፓስተር ጻድቁ፣ አባቶችም «አይ እኔ በዚህ ዕድሜዬ ለምን ሰዎች ይናገሩኛል» ከሚል ስሜት በመውጣት በሕይወት ልምዳቸው አገርና ሕዝብን ከጥፋት መታደግ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
እንደ ፓስተር ጻድቁ ገለጻ፣ በተቻለ መጠን ሰዎች መጀመሪያ ከራሳቸው ጋር እንዲታረቁ ማድረግ፤ አባቶችም እውነትን ተናግረው መቀበል ያለባቸውን ሁሉ ለመቀበል ራሳቸውን ማዘጋጀት እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል።
ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ከስድብ የሰዎችን የግል ነገር ከመነካካት ይልቅ አገር አሁን ካጋጠማት ችግር እንዴት ነው መውጣት የምትችለው? የትኛውን መንገድ ብንከተል ነው መልካም ነገር የምናመጣው? የሚለውን ማሰብና ለደጋፊያቸውም ማሰማት እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል።
በወጣቶች ደም መኖር የሚፈልጉ ኃይላት አሉ ያሉት ፓስተር ጻድቁ፣ ይህንን በመገንዘብ ወጣቶች የሚያምኑትን ማወቅ። ያመኑት ነገር ትክክለኛ መሆኑንና ነገ ዕድሜያቸው ሲገፋና ሲያረጁ የማያፍሩበት እንደሆነ ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል ብለዋል።
ዛሬ ላይ የሚሰሩ ወይም የሚደርጉ ነገሮችና እንቅስቃሴዎች ለራሳቸውም ለአገርም ያለውን ፋይዳ በቅጡ መረዳትና መመርመር እንደሚያስፈልጋቸው ጠቁመው፣ ትክክለኛ ላልሆነ አላማ ዋጋ መክፈልም አስፈላጊ አይደለም ፤ ይህ ሁሉ የሚሆነው ግን በስሜት ሳይሆን ተረጋግቶ የዓለምን፣ የአፍሪካን እና የአገሪቱን ታሪክ በቅጡ ተገንዝቦ ትክክለኛውን መንገድ መከተል ሲቻልና ከአመጻና ሁከት መራቅ ሲቻል እንደሆነ አብራርተዋል።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 22/2013