
አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ ውስጥ የሚስተዋሉ ግጭቶች ኢትዮጵያን ከማፍረስ ውጪ ሌላ ዓላማ እንደሌላቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰብዓዊ መብትና የፌዴራሊዝም መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ሲሳይ መንግስቴ አስታወቁ፡፡
ዶ/ር ሲሳይ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፣ ኢትዮጵያ ያላትን ሀብት በአግባቡ ተጠቅማ እንዳታድግ፣ በዲፕሎማሲ ረገድ በምሥራቅ አፍሪካ አልፎም በዓለም ተጽዕኖ ፈጣሪ እንዳትሆን ከወዲሁ የውስጥና የውጭ ጠላቶቿ በስሌት እየሰሩ ነው፡፡
በተለየ መልኩ ግብጽና ሱዳን ኢትዮጵያ አባይ ወንዝን እንዳታለማ ከድሮ ጀምሮ ተጽዕኖ ሲያደርጉ እንደቆዩ የገለጹት ዶክተር ሲሳይ፣ አሁን ግን እነሱ ባልጠበቁት ሁኔታ ኢትዮጵያ ግዙፉን ፕሮጀክት በራሷ አቅም መገንባት ስትጀምር «ገና ለገና ኢትዮጵያ ከምሥራቅ አፍሪካ አልፋ በዓለም ተሰሚነቷ ይጨምራል» በሚል ስጋት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አክራሪና አኩራፊ ብሔርተኞችን በመደገፍ አገሪቱ እንዳትረጋጋ ከተሳካላቸው ደግሞ ለማፍረስ ከፍተኛ ተጋድሎ እያደረጉ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡
እንደ ምሁሩ ገለጻ፣ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ምን ጊዜም ተኝተው አያውቁም፣ በታሪክም ያልደገፉት የኢትዮጵያ ተቀናቃኝ ኃይሎችም የለም፡፡ ጊዜው ኢትዮጵያ ለሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ለማድረግ ዝግጅት ላይ በመሆኗ ወሳኝ ጊዜ ነው፡፡ ጠላቶቿም ባላቸውና በሌላቸው አቅም ሽብርና ግጭት ለመፈጠር ወሳኝ ጊዜ መሆኑን አምነው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
ሁለቱ ተቀናቃኞች በተሳሳተ ግምት በኢትዮጵያ ፈጽሞ አለመረጋጋት እንደሌለና ሕዝቦቿም ፈጽሞ የዓላማ አንድነት እንደሌላቸው እያስተጋቡ ይገኛሉ፡፡
ሱዳን ሰሞኑን በግብጽ አጋፋሪነት የቅኝ ገዥ ጎግል ካርታ ላይ በመመርኮዝ የኢትዮጵያን መሬት በመተማ በኩል መያዟን የተናገሩት ተመራማሪው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ አካባቢ የጀመረችው በጥቅል ሲታይ የጠብ አጫሪነትና ኢትዮጵያን የመቀራመት ዝንባሌ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ሱዳንና ግብጽ በትብብር እየሰሩ ያሉት ለእርስ በእርሳቸው ታሪካዊ ወዳጅ ስለሆኑ ሳይሆን የኢትዮጵያን ለም መሬቶችን በመውሰድ በኢኮኖሚ፣ በተፈጥሮ ሀብትና በዲፕሎማሲ ለማዳከም አስበው እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
«ሆኖም ግን ፖለቲከኛውም፣ የደህንነትና የፀጥታው መዋቅር እንዲሁም ሕዝባችን የተጋረጠብንን አደጋ በዚያው ልክ ለመከላከል አሊያም ለመጋፈጥ ያላቸው ዝግጁነት አጠያያቂ ሊሆን ይችላል» ያሉት ዶክተር ሲሳይ፣ በአገራችን የተፈጠሩት አለመግባባቶች ለጠላቶች ቀዳዳ ከመፍጠር ባሻገር በአገራችን የጠላት አጀንዳ ፈጻሚና አስፈጻሚዎች እየተበራከቱ መምጣታቸውንም ያሳያል ብለዋል፡፡
ጁንታውና ግልገሎቹም ዓለም አቀፍ ማህበረሰብን በማሳሳት ከኢትዮጵያ ተቃራኒ እንዲሰለፉ እያደረጉ ያሉት ጥረቶች እንደቀላል የሚታይ ጉዳይ እንዳልሆነና አንዱ የውስጣችን ጠላት ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ያም ሆኖ ግን «ትናንት በአንድነት በተለያዩ ጦርነቶች በተለየ መልኩ ደግሞ በአድዋ ወራሪውን ኃይል ላይ ድል ያጎናጸፈው ሕዝባችን ዛሬም ቢሆን እንደ ጠላት ስሌት አይደለም፡፡ እንዲያውም የሕዝባችን አንድነት በፈተና ጊዜ ከብረት እንደሚጠናከር ታሪክ ይነግረናል» ያሉት ምሁሩ፣ ብሔርን መሠረት የሚያደርግ ግጭት መዘዙ ከባድ በመሆኑ ለጉዳዩ ተገቢ ትኩረት መሰጠት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
ዋቅሹም ፍቃዱ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 22/2013