ታላቁ የስፖርት መድረክ ኦሊምፒክ በአራት አመት አንድ ጊዜ በመጣ ቁጥር የአለም አገራት ድምፃቸውን አጥፍተው ሲዘጋጁ ኢትዮጵያን በመድረኩ የሚወክሉ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች እርስ በርሳቸው እንዲሁም ከኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር መነታረካቸው እየተለመደ መጥቷል። ባለፈው በሪዮ ኦሊምፒክ ውድድር ወቅት በውሃ ዋና ፌዴሬሽን ውስጥ ትልቅ ውዝግብ ተከስቶ በታላቁ የስፖርት መድረክ አገርን ያሳፈረ ክስተት መፈጠሩ አይዘነጋም። ዘንድሮም የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ሊካሄድ ከሶስት ወራት ያነሰ ጊዜ በቀረው በዚህ ወቅት በውሃ ዋና ፌዴሬሽን ውስጥ የከረረ ንትርክና መከፋፈል ተፈጥሯል።
የኢትዮጵያ ውሀ ስፖርቶች ፌዴሬሽን ባለፈው ቅዳሜ ባካሄደው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ከኃላፊነት ታግደው የቆዩት የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ተሾመ ሶርሳን ማሰናበቱን አሳውቋል። ፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንቱን ያሰናበተው ባለፈው ወር ‹‹ሕገ ወጥ ነው ባለው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ስራ አስፈፃሚ ምርጫ›› ላይ ከፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ፍቃድና እውቅና ውጪ በራሳቸው ፍቃድ በመገኘታቸው መሆኑን ገልጿል።
ይህን ተከትሎም የኢትዮጵያ ውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አስቸኳይ ስብሰባ ጠርቶ ከተወያየ በኋላ ፕሬዚዳንቱ አቶ ተሾመ ሶርሳ ከስራ ታግደው እንዲቆዩ መወሰኑንና ውሳኔውንም ጉባኤው እንዲያፀድቀው አስቸኳይ ጉባኤ መጠራቱን ገልጸዋል።
የጉባኤው ተሳታፊዎችም በቀረበው አጀንዳ ላይ የፌደሬሽኑ መተዳደሪያና ሥነምግባር ደንብ መሠረት የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴዎች ያስተላለፉትን ውሳኔ በጥልቀት በመመርመርና ሰፊ ውይይት በማድረግ አቶ ተሾመ ሶርሳ ከውሃ ዋና ስፖርቶች ፕሬዚዳንትነት እንዲነሱ በአብላጫ ድምፅ መወሰኑን ገልጿል።
አቶ ተሾመ በበኩላቸው ሰኞ እለት በጊዮን ሆቴል በሰጡት መግለጫ፣ በአስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤው በኃላፊነት እንዲቀጥሉ ከ11 ድምፅ 5 ድምፅ እንዳገኙ፣ አራት ድምፅ በተቃራኒው እንደተሰጣቸውና ሁለት ድምፀ ታቅቦ እንደነበር በመግለፅ፣ በዚህ መሰረት በ50+1 ድምፅ ወደ ኃላፊነታቸው መመለስ ሲገባቸው ሥራ አስፈፃሚው ራሱ ከሳሽና ራሱ ፈራጅ ሆኖ ከሕግና ደንብ ውጪ ተጨማሪ ድምፅ ሰጥቶ ወደ ኃላፊነታቸው እንዳይመለሱ ማድረጉን ተናግረዋል።
በመጀመሪያም እንደ ፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት የኦሊምፒክ ኮሚቴ ምርጫም ይሁን ሌሎች ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት የስራ አስፈፃሚውን ይሁንታ የማግኘት ግዴታ እንደሌለባቸው አስረድተዋል። ‹‹ፕሬዚዳንቱ በማንኛውም ቦታ ፌዴሬሽኑን ይወክላል›› የሚለውን የፌዴሬሽኑን መተዳደሪያ አንቀፅ 29/1 በመጥቀስም ከሕግ አግባብ ውጪ እንደተሰናበቱ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።
ከኃላፊነታቸው የታገዱትም ይሁን ኋላ ላይ ከፕሬዚዳንትነታቸው የተነሱት ወደ ቶኪዮ ኦሊምፒክ የውሃ ዋና ቡድንን እየመሩ እንዳይሄዱና በእሳቸው ምትክ ሌላ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እንዲሄድ ታስቦ መሆኑንም ተናግረዋል። ለዚህም ፌዴሬሽኑ ወደ ኦሊምፒክ የሚጓዙ ሰዎችን ስም ዝርዝር ለኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እንዳስገባ በመጥቀስ ስማቸው የተላለፈውን ግለሰቦች ፓስፖርት ፎቶ ኮፒ አድርገው አቅርበዋል።
ይህን ውዝግብ ለመፍታት የበላይ አካል ለሆነው ስፖርት ኮሚሽን በደብዳቤ ጭምር አሳውቀው በጠቅላላ ጉባዔ ይፈታ ከሚል ምላሽ በዘለለ መፍትሄ እንዳላገኙ የሚናገሩት አቶ ተሾመ፣ ጉዳዩ በሕግና ሥርዓት ካልተፈታ ዓለም አቀፉ ውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን ድረስ ሄዶ አገርን እስከ ማሳገድ የሚደርስ አደጋ እንደሚያስከትል አብራርተዋል።
በዚሁ መግለጫ ላይ የተገኙት የፌዴሬሽኑ አሰልጣኝ አንተነህ ጎበዜ በበኩላቸው፣ ቢሾፍቱ ላይ በተደረገ የማጣሪያ ውድድር ውጤት መሰረት እሳቸውና የሚያሰለጥኗቸው አብዱልመሊክ ቶፊቅና ሊና አለማየሁ የተባሉ አትሌቶች ከወር በፊት ለኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ስም ዝርዝራቸው ተላልፎ በሆቴል ተቀምጠው ለኦሊምፒክ እየተዘጋጁ መክረማቸውን ይናገራሉ። ይሁን እንጂ በፌዴሬሽኑ ውስጥ በተፈጠረው ንትርክና አለመግባባት የተነሳ አሰልጣኙና አትሌቶቹ ሌላ የማጣሪያ ውድድር ማድረግ እንዳለባቸውና በሆቴል ተቀምጠው የሚያደርጉትን ዝግጅት እንዲያቋርጡ እንደተነገራቸው አመልክተዋል ።
ፌዴሬሽኑ ዝግጅታቸውን አቋርጠው ከሆቴል እንዲወጡ ከፈለገ ከኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር መነጋገር እንጂ አትሌቶቹ ላይ ተፅእኖ ማሳደር እንደማይገባው የሚናገሩት አሰልጣኙ፣ በዝግጅት ላይ የሚገኙት አትሌቶች በአለም አቀፍ ውድድሮች ጭምር ተወዳድረው ብቃታቸውን ያስመሰከሩ ባስመዘገቡት ውጤትና ሰአት መሰረትም የተመረጡ ስለመሆናቸው ተናግረዋል ።
በቶኪዮ ኦሊምፒክ በውሃ ዋና ስፖርት ለመሳተፍ ኢትዮጵያ አንድ ወንድና አንድ ሴት አትሌት፣ አንድ አሰልጣኝና አንድ ቡድን መሪን የሚያካትት ኮታ አላት። ፌዴሬሽኑ ወደ ቶኪዮ እንዲጓዙ ለኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አቅርቧል የተባሉት ሰዎች ቁጥር ከሚፈለገው ኮታ በላይ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቀልቤሳ ኤባ በተነሱት ቅሬታዎች ላይ ትናንት ከአዲስ ዘመን ጋር በነበራቸው ቆይታ ፕሬዚዳንቱ ‹‹ባልተፈቀደው የኦሊምፒክ ምርጫ›› ላይ በመገኘታቸው ከባድ የሥነ ምግባር ግድፈት መፈፀማቸው ታምኖበት ከ7ቱ ስራ አስፈፃሚዎች 6ቱ ከስራ እንዲታገዱ ወስኗል።
በፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብና የሥነ ምግባር መመሪያ አንቀፅ 19/33 እና አንቀፅ 19/35 መሰረት ‹‹ከባድ የሥነ ምግባር ጥሰት የፈፀመ በስራ አሥፈፃሚ ታግዶ ይቆይና በአስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲሰናበት ይደረጋል›› በሚለው መሰረትም ፕሬዚዳንቱ እንደ ተሰናበቱ ገልፀዋል።
‹እንዲያውም ጠቅላላ ጉባኤው ድምፅ መስጠት አይጠበቅበትም ነበር›› ያሉት አቶ ቀልቤሳ፣ ከጠቅላላ ጉባኤው 11 ድምፅ ፕሬዚዳንቱ በይቅርታ እንዲቀጥሉ 5 ድምፅ ማግኘታቸውን የገለፁ ሲሆን 5 ድምፅ በተቃራኒው እንዲሰናበቱ፣ በአንድ ድምፀ ታቅቦ እንዲሁም ሥራ የአስፈፃሚው ድምፅ ተደምሮ እንደተሰናበቱ አስታውቀዋል ። ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በምርጫ ላይ እንጂ በእንደዚህ አይነት ጉዳዮች ድምፅ አይሰጡም የሚል የስፖርት ማህበራት ማቋቋሚያ መመሪያም ይሁን የፌዴሬሽን ሕግና ደንብ የለም ፤ ስንብታቸው ሕጋዊ ሥርዓቱን ተከትሎ መፈፀሙን ያብራራሉ። በዚህ ላይ በፕሬዚዳንትነት እንዲወዳደሩ የወከላቸው የኦሮሚያ ክልል ውክልናውን እንዳነሳ አስታውቀዋል።
አቶ ቀልቤሳ አሰልጣኙ ባቀረቡት ቅሬታ ላይ ምላሽ ሲሰጡም፣ ቢሾፍቱ ላይ የተካሄደው ውድድር የመጨረሻ ማጣሪያ እንዳልሆነና ሌላ የማጣሪያ ውድድር እንደሚያስፈልግ ሥራ አስፈፃሚው ከተስማማ በኋላ ፕሬዚዳንቱ አቶ ተሾመ በገዛ ፍቃዳቸው ሆቴል ገብተው የሚዘጋጁትን አሰልጣኝና አትሌቶች እንዲሁም መታገዳቸውን እያወቁ ራሳቸውን ቡድን መሪ አድርገው ለኦሊምፒክ ኮሚቴ ስም ዝርዝር እንዳስተላለፉ ገልጸዋል።
ፌዴሬሽኑ ይህ ስህተት እንደሆነ ለማሳወቅ ወደ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ቢያቀናም እንዳልተሳካለት የሚናገሩት አቶ ቀልቤሳ፣ አሰልጣኙና አትሌቶቹ ከፌዴሬሽኑ እውቅና ውጪ ለኦሊምፒክ ዝግጅት ሆቴል ገብተው እንዳይዘጋጁና በፌዴሬሽኑ በኩል ቢሾፍቱ እየተዘጋጁ ከሚገኙ አሰልጣኞችና አትሌቶች ጋር ዝግጅት ካደረጉ በኋላ በሚካሄደው የማጣሪያ ውድድርና ውጤት መሰረት ተመርጠው የኦሊምፒክ ዝግጅታቸውን እንዲጀምሩ ማሳሰባቸውን አብራርተዋል። ይህም የተደረገው ለአትሌቶቹም ይሁን ለአሰልጣኞች እኩልና ፍትሐዊ እድል ለመስጠት ታስቦ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ቀልቤሳ፣ አሁንም ቢሆን ፌዴሬሽኑ ለአትሌቶቹ በሩ ዝግ እንዳልሆነ አስቀምጠዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 21/2013