
አዲስ አበባ፦ በቅርቡ የመከላከያ ሠራዊት ዩኒፎርም በመልበስ በተለያዩ የዕምነት ተቋማት ሲያመልኩ የሚያሳይ መረጃዎች በሚመለከታቸው የተቋሙ የፍትህ አካላት ተጣርቶ አስፈላጊው እርምጃ እንደሚወሰድ የመከላከያ ሠራዊት አስታወቀ፡፡
የመከላከያ ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የመከላከያ ሠራዊት ገለልተኛ ፣ የትኛውንም የሃይማኖት ተቋም እንደማይወክል ገልፀዋል፡፡
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ የማይወግን እና የማንኛውንም ዕምነት የማያራምድ መሆኑ በሕገ- መንግሥታቱም ይሁን በቅርቡ በጸደቀው የመከላከያ ስትራቴጂክ የግንባታ ሰነድና በአስተዳደራዊ ደንብ ላይ በማያሻማ ሁኔታ መቀመጡን አስታውቀዋል፡፡
ከዚህ በፊት የመከላከያን የደንብ ልብስ በመልበስ በተለያየ የዕምነት ተቋም ሲያመልኩ የተገኙ በቁጥጥር ስር ውለው እና ሪሀብሊቴሽን ማዕከል ገብተው ቅጣታቸውን ፈጽመው የወጡ መኖራቸውን ጠቁመዋል።
መሰል ድርጊቶችም በሠራዊቱ ውስጥ ሲከሰቱ የተለያዩ አስተዳደራዊ እርምጃዎች ሲወሰዱ መቆየታቸውን አመልክተዋል ፡፡
በቅርቡ በተለያዩ የዕምነት ተቋማት የጀግናውን እና የየትኛውንም እምነት የማይወክለውን ሠራዊት የደንብ ልብስ በመልበስ የታዩ ግለሰቦችን በማጣራት ክስ ይመሰረትባቸዋል ብለዋል።
በእንደዚህ ዓይነት ጥፋት የሚገኙ የሠራዊት አባላት እስከ አምስት ዓመት የሚደርስ የእስር ቅጣት እንደሚበየንባቸው ገልፀዋል።
መከላከያ ሠራዊት ዕምነትም ሆነ ሃይማኖት የማይወክል በመሆኑ በዚህ ድርጊት የተሳተፉ አባላት እንደዚህ ቀደሙም እርምጃም ይወሰድባቸዋል ብለዋል፡፡
የሠራዊቱ አባላት የፈለጉትን ዕምነት የመከተል መብት አላቸው ያሉት ኮሎኔሉ፣ ይሁን እንጂ የተከበረውን የኢትዮጵያ ሕዝቦች መመኪያ የሆነውን የደንብ ልብስ በመልበስ ማምለክ ፈጽሞ የተከለከለ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የዕምነት ተቋማቱም በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት በርካታ ሙያዎች ውስጥ ሠራዊቱን መርጠው በዚህ መልኩ ማሳየት የፈለጉበት ምክንያት ምን እንደሆነ መከላከያ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚከታተለው ገልፀዋል፡፡
በተጨማሪም በአንዳንድ ማህበራዊ ሚዲያ፤ የተቋሙን ዩኒፎርም የለበሱ እና በፓትሮል መኪና ሆነው ሰው እየደበደቡ የተላለፈው ዘገባ እውነተኛነቱ ተረጋግጦ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል።
ሆን ብለው የተቋሙን አልባሳት እያስመሰሉ የሚለቀቁ ምስሎች እንዳሉ እንረዳለን ያሉት ኮሎኔል ጌትነት፤ ይህን እና መሰል የስም ማጥፋት ዘመቻ ሲኖር ሕዝቡ እየተከላከለልን ውስጣችንን ደግሞ ራሳችን እያረምን እንሄዳለን ብለዋል።
ሕዝቡ መሰል የመከላከያ ሠራዊትን ክብር እና መልካም ስም ለማጉደፍ የሚደረጉ ጥረቶችን ሲመለከት ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 21/2013