
አዲስ አበባ፡- ሕገወጥ እርድ ላይ ተሰማርቶ የተገኘ ሰው እስከ 25ሺህ ብር አልያም በእስር እንደሚቀጣ የአዲስ አበባ አርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን አስታወቀ፡፡በ2012 ዓ.ም በተደረገ ጥናት ከተማዋ በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ በሕገወጥ እርድ ምክንያት 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ማጣቷም ይፋ ሆኗል፡፡
በትናንትናው ዕለት ኮሚሽኑ ከአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ጋር በመሆን በመጪው የፋሲካ በዓል ኅብረተሰቡ ከእርድ ጋር ተያይዞ ሊያደርግ ስለሚገባው ጥንቃቄ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል፡፡
መግለጫውን የሰጡት የአዲስ አበባ አርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወይዘሮ ፍቅርተ ነጋሽ እንደገለፁት፤ በሕገወጥ እርድ ላይ የተገኘ ሰው ከ15 እስከ 25ሺህ ብር አልያም ከሁለት እስከ ሦስት ወር በሚደርስ እስር ይቀጣል፡፡
እንደ ምክትል ኮሚሽነሯ ገለፃ ወንጀሉን ሲፈፅም የተገኘ ድርጅት የተጣለበት ቅጣት እስከሚተላለፍ ድረስም ሥራ የሚያቆም ሲሆን ድርጅቱም ይታሸጋል፡፡
ሕገወጥ እርድ መንግሥት ማግኘት ያለበትን ገቢ እንዳያገኝና ኅብረተሰቡም ንፅህናና ጤንነቱ ያልተጠበቀ ስጋ እንዲመገብ እንደሚያደርገው የገለፁት ምክትል ኮሚሽነሯ ከተማዋ በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ በሕገወጥ እርድ ምክንያት 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር እንዳጣች በ2012 ዓ.ም በተደረገ ጥናት ይፋ ሆኗል ሲሉም ገልፀዋል፡፡
እንደ ምክትል ኮሚሽነሯ፤ ሕገወጥ እርድ የሚደረጉባቸው ስፍራዎች በጥናት ተለይተዋል፡፡ከሕግና ከሰው እይታ ለመሰወርም በቆሻሻ ስፍራዎች፣ ሸለቆና አሳቻ ቦታዎች፣ የእንስሳት ማሳደርያ በረቶች እና ሆቴሎች ጀርባ ሕገወጥ እርድ የሚከወንባቸው ስፍራዎች መሆናቸውንም ምክትል ኮሚሽነሯ ተናግረዋል፡፡
ምክትል ኮሚሽነሯ ኅብረተሰቡ ሕገወጥ እርድ ከፍተኛ የጤና ችግር እንደሚያመጣ፣ መንግሥት ማግኘት የሚገባውን ገቢ እንደሚያሳጣ፣ አካባቢን እንደሚበክል፣ ከእንስሳት የሚገኝን ተረፈ ምርት እንደሚያባክንና የውጭ ምንዛሬን እንደሚያሳጣ በመገንዘብ መሰል ተግባራት ሲከናወኑ ሲያይ ለሕግ አካላት እንዲያሳውቅ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡
የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አታክልቲ ገብረሚካኤል በበኩላቸው ድርጅታቸው በመጪው የፋሲካ በዓል ጥራቱን የጠበ እርድ ለማከናወን ዝግጅቱን ጨርሷል ብለዋል፡፡
አቶ አታክልቲ እንዳሉት ድርጅቱ ከዚህ በፊት የነበሩበትን የትራንስፖርትና መሰል ችግሮችን በመቅረፍና ኮቪድ 19ን በሚመለከት የጤና ባለሙያዎች ያወጡትን ሕግ ተግባራዊ በማድረግ ጭምርም ነው የተዘጋጀው፡፡
እንደ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ከዚህ በፊት ካለው የበዓላት ልምድ በመነሳት 3ሺህ ትልልቅ እንስሳትን እንዲሁም ከ1500 እስከ 2ሺህ የሚደርሱ በግና ፍየሎችን እርድ ለማካሄድ አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
ዳግማዊት ግርማ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 21/2013