
ጌትነት ተስፋማርያም
አጣዬ ፡- በአጣዬና አካባቢው ተፈጥሮ በነበረው ግጭት የተፈናቀሉ ነዋሪዎችን ወደ ቀዬአቸው የመመለስ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ኮማንድ ፖስቱ አስታወቀ። መከላከያ ከገባበት ቀን ጀምሮ በአካባቢው ችግር ሲፈጥሩ የነበሩ አጥፊ ኃይሎችን በማስወገድ በአካባቢው ሰላማዊ እንቅስቃሴ መስፈኑንም ገለጸ።
በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን እና ደቡብ ወሎ ዞን የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል ደስታ አብቼ ትናንት በስፍራው ለተገኘው የጋዜጣው ሪፖርተር እንደገለጹት፤ በአካባቢው ያለው ኮማንድ ፖስት ሦስት አቅዶችን አውጥቶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። በመጀመሪያ ደረጃ በታቀደው መሠረት በግጭቱ ምክንያት ይደርስ የነበረውን ሞት እና የቤቶች ቃጠሎ ማስቆም ነው። ይህ በስኬት ተከናውኗል።
በሁለተኛው እቅድ የአካባቢው ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እንቅስቃሴ እንዲቀጥል ማድረግ እንደሆነ ያመለከቱት ሌተናል ጄኔራል ደስታ፣ በዚህም መንገዶች ክፍት እንዲሆኑ፣ የስልክ እና የመብራት አገልግሎቶች እንዲጀምሩ፣ የየአካባቢው አስተዳደሮች ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉን አስታውቀዋል።
ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የሚደረግበት የአዲስ አበባ -ደሴ- መቀሌ መንገድ ለቀናት ዝግ ሆኖ መቆየቱን ያስታወሱት ሌተናል ጄኔራል ደስታ፤ ኮማንድ ፖስቱ በአካባቢው ሥራ ከጀመረ በኋላ መከላከያ ሰራዊት ባከናወነው ሥራ መንገዱ ክፍት መሆኑን፤ ማንኛውም ተሽከርካሪ ያለምንም የጸጥታ ችግር መንቀሳቀስ እንደሚችል አመልክተዋል።
በአሁኑ ሰዓት ከአዲስ አበባ ወደ ደሴ እና ሌሎች ከተሞች የሚወስደው አገር አቋራጭ መንገድ ክፍት በመሆኑ የተለያዩ ከባድ እና ቀላል ተሽከርካሪዎች በየሰዓቱ ያለምንም የጸጥታ ችግር በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው ብለዋል።
መከላከያ ሰራዊቱ የጸጥታ ስጋት ያደረባቸውን ተፈናቃዮች በማነጋገር በየጊዜው ወደአካባቢያቸው እየመለሰ መሆኑንም ያስታወቁት ሌተናል ጄኔራል ደስታ፣ የአካባቢውን ነዋሪዎችን ወደ ቀዬአቸው የመመለሱ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።
መከላከያ ሰራዊት ከገባበት ቀን ጀምሮ በአካባቢው ችግር ሲፈጥሩ የነበሩ አጥፊ ኃይሎችን በማስወገድ አካባቢው የሰላም እንቅስቃሴ እንዲከናወንበት ማድረግ ተችሏል። ለአካባቢው ሰላማዊ እንቅስቃሴ መጓደል እና ለደረሰው ውድመት ተጠያቂ የሚሆኑ አካላትን ተለይተው ወደፊት ይፋ እንደሚደረጉ አመልክተዋል፡፡
በግጭቱ ወቅት በውጊያ የተሳተፉ ሰዎች መያዛቸውን እና ቆስለው በሆስፒታል እየታከሙ የሚገኙ ግለሰቦች በመከላከያ ሰራዊት ቁጥጥር ስር እንደሚገኙም አስታውቀዋል። ከጥቃት አድራሾቹ ጀርባ በአገር ውስጥ እና በውጭ አገራት ያሉ በርካታ ኃይሎች እጅ እንዳለ ጠቁመዋል።
በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ሆነውም ሆነ በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ሆነው ለግጭቱ መንስኤ የሆኑ ግለሰቦች ከሕግ አያመልጡም፤ ኮማንድ ፖስቱ ጥልቅ ምርመራ በማድረግ እና ማስረጃ በማደራጀት ከኋላ ሆነው ግጭቱን ሲመሩ የነበሩ አካላትን ለሕግ ያቀርባል ብለዋል።
በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን እና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ብዛት ያላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ቀዬአቸውን ጥለው ወደ ተለያዩ አካባቢዎች መሰደዳቸው ይታወሳል።
ጌትነት ተስፋማርያም
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 21/2013