
አዲስ አበባ፦ የህውሓት ሕገ ወጥ ቡድን ለወንጀል ድርጊት መፈፀሚያ ሊያውለው የነበረው ከ6 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ እንዳይንቀሳቀስና በሕገ-ወጥ መንገድ እንዳያሸሽ መከላከል መቻሉን የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አስታወቀ።
በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በወንጀል የተገኘ ሀብት ማስመለስ ዳይሬክቶሬት ጀነራል አቶ ዓለም አንተ አግደውን ምንጭ ያደረገው የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የህወሓት ሕገ-ወጥ ቡድን በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ከፈፀመበት ማግስት ጀምሮ ሕገ-ወጥ ቡድኑ ሲቆጣጠራቸው በነበሩና ገንዘብና ንብረታቸውን ለሕገ-ወጥ አላማው ሊጠቀምባቸው ይችላል በሚል በተጠረጠሩ ድርጅቶች እንዲሁም በጦርነት በተሳተፉ የጦር መኮንኖችና ሌሎች ባለሥልጣናት ላይ በተደረገ የሀብት ክትትልና ምርመራ ውጤታማ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡
“በዚህም መሠረት አገራቸው ኢትዮጵያን ከድተው ከህወሓት ጋር በመሰለፍ በጦርነት የተሳተፉ ዋና ዋና ተጠርጣሪዎች ገንዘብና ሀብት ላይ በተደረገ ክትትልና ማጣራት ሥራ አምሳ አራት ሚሊዬን ሁለት መቶ ሰላሳ ሰባት ሺህ አምስት መቶ ስልሳ አምስት ብር እንዲሁም ሌሎች ብዛት ያላቸው ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች በፍ/ቤት ትዕዛዝ እንዲታገድ ተደርጓል፡፡
በኤፈርት/ት.ም.ዕ.ት ሥር በሚተዳደሩ እና ተያያዥ የሆኑ የተለያዩ ድርጅቶች ላይ በተከናወነ የሀብት ክትትልና ምርመራ ሥራ አራት ቢሊዬን ሁለት መቶ አምስት ሚሊዬን ሰባት መቶ አስራ ሰባት ሺህ ስልሳ አንድ ብር በፍ/ቤት ትዕዛዝ በማሳገድ እና ግምታቸው ከ 2 ቢሊዬን ብር በላይ የሆኑ 179 የደረቅና የፈሳሽ ጭት ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ለማሸሽ ጥረት ሲያደርጉ የፍ/ቤት ትዕዛዝ በማውጣትና የጋራ የሕግ ትብብር ጥያቄ ለጅቡቲ መንግሥት በማቅረብ ወደ አገር ማስመለስ ተችሏል።
በተመሳሳይ በህወሓት ሕገ-ወጥ ቡድንና በዚህ ቡድን ሥር በነበሩ አመራሮች ቀጥተኛ ቁጥጥር ይደረግባቸው በነበሩና ቡድኑ የድርጅቶችን ገንዘብ ለወንጀል መፈፀሚያ ሊያውል ይችል የነበሩ ሦስት ስቪል ማህበራት ላይ በተደረገ የሀብት ክትትልና ምርመራ ሥራ አራት መቶ አምስት ሚሊየን አራት መቶ አምስት ሺህ አምስት መቶ ሃያ ሰባት ብር በፍ/ቤት ትዕዛዝ በማሳገድ እና ገለልተኛ አስተዳዳሪ በፍ/ቤት በማሾም የማህበራቱ ገንዘብ በህወሓት ቡድን ለሕገ-ወጥ ዓላማ እንዳይውል መከላከል ተችሏል፡፡
በወንጀል የተገኘ ሀብት ማስመለስ ዳይሬክቶሬት ጄነራል በተከናወነው የሀብት ክትትልና ምርመራ ሥራ የህወሓት ሕገ ወጥ ቡድን የሆነ ብር ዘጠና ሰባት ሚሊዬን አምስት መቶ ሰማንያ ሁለት ሺህ አንድ መቶ ስልሳ አራት ብር ለወንጀል ተግባር እንዳይጠቀምበት መደረጉንም አመልክቷል።
የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የህወሓት ሕገ-ወጥ ቡድን ታሳስ 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ከፈፀመበት ጊዜ ጀምሮ ባከናወነው የሀብት ክትትልና ምርመራ ሥራ ቡድኑ ለሕገ ወጥ አላማ ሊጠቀምበት የነበረውን ገንዘብ በሕግ አግባብ የውርስ ውሳኔ እንዲሰጥበት ለሚመለከተው አካል ተላልፏል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 19/2013