
አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በገንዘብ ኖት ቅየራ ሂደቱ ላይ ገንቢ ሚና ለተጫወቱና ለስኬታማነቱ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት እውቅና ሰጠ።የገንዘብ ኖት ቅየራው የባንኮችን የቁጠባ ሂሳብና ተቀማጭ ገንዘባቸውን በማሳደግና ፋይናንስ ነክ ወንጀሎች ደቅነውት የነበረውን አደጋ በመቀልበስ አገሪቱን ከኢኮኖሚ ቀውስ የታደጋት መሆኑንም አስታውቋል።
ባንኩ በትናንትናው ዕለት የገንዘብ ቅየራ ሂደቱ ስኬታማ እንዲሆን ወሳኝ ሚና ለተጫወቱ አካላት የዕውቅና አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት ባካሄደበት ወቅት የባንኩ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ እንዳስታወቁት፤ የገንዘብ ኖት ቅየራው 7 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች አዳዲስ የቁጠባ ሂሳብ እንዲከፍቱ፤ በዚህም 126 ቢሊዮን ብር መቆጠብ እንዲችሉ አድርጓል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ አዲሱ የገንዘብ ኖት በፋይናንስ ሥርዓቱ ውስጥ በህቡዕ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ፣ በገንዘብ እጥበትና በጥቁር ገበያው ውስጥ ተሳታፊ የነበሩ ወንጀለኛ ግለሰቦችን በመለየት አገሪቱ ገጥሟት የነበረውን ገንዘብ ነክ ወንጀሎች እንድትዋጋ አስችሏታል።አዳዲስ ቀለሞችን፣ ምልክቶችንና የደህንነት ማስጠበቂያ ዘዴዎችን አካትቶ ጥቅም ላይ የዋለው አዲሱ የገንዘብ ኖት የዕይታ ችግር የነበረባቸው ግለሰቦች የብር ኖቶቹን በቀላሉ መለየት እንዲችሉና የአገሪቱን የተፈጥሮ ሀብት ለማስተዋወቅ አጋዥ ሆኖ መገኘቱንም የብሔራዊ ባንክ ገዥው ዶክተር ይናገር ጨምረው ገልፀዋል፡፡
በሌላ በኩል ወደ ገንዘብ ሥርዓቱ የገባው አዲሱ የሁለት መቶ ብር ኖት የሕዝብን ፍላጎት ከማርካቱ ባሻገር ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን የባንክ ኖቶችን ለማተም መንግሥት የሚያወጣውን ወጭ ለመቀነስም ማገዙንም አመላክተዋል።
ሕብረተሰቡ በላያቸው ላይ ባለመጻፍና እንዲጨማደዱ አድርጎ ባለመያዝ የአገልግሎት ጊዜያቸው እንዳያጥር ለገንዘብ ኖቶቹ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግም ዶክተር ይናገር ጥሪ አቅርበዋል።
ባንኩ እውቅና ከሰጣቸው ተቋማት መካከል የጠቅላይ ሚንስቴር ቢሮ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የኢትዮጵያ ሚዲያ ባለሥልጣንና የአነስተኛና ጥቃቅን የገንዘብ ተቋማት ይገኙበታል።
ይበል ካሳ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 20 ቀን 2013 ዓ.ም