ትውልድና ዕድገታቸው ሻሸመኔ አካባቢ ከሚገኝ የገጠር ወረዳ ገበሬ ማህበር ውስጥ ነው። ከቤተሰባቸው ባገኙት መጠሪያ‹‹ ደርጉ ቱሌ›› በመባል ይታወቃሉ። በሥራቸው አካባቢ የሚያውቋቸው በርካታ ሰዎች ደግሞ ምንተስኖት ወይም ምንቴ ፈርኒቸር ተብሎ በሚታወቀው የድርጅታቸው ሥም ያውቋቸዋል። ከዚህ በተጨማሪም ሚሊዬነር የሚል መጠሪያ እራሳቸው ለራሳቸው ሰይመዋል። ‹‹ብዙዎች እገሌ ሚሊየነር ነው ሲሉ እሰማለሁ ታድያ እኔ ሚሊዬነር የማልሆነው ለምንድን ነው በሚል ሚሊዬነር የሚል ሥያሜ ለራሴ ሰጥቻለው። በመሆኑም ዛሬ ሚሊዬነር ሆኛለሁ›› የሚሉት የዛሬው የስኬት እንግዳችን የምንቴ ፈርኒቸር ባለቤት እና በሆቴል ቱሪዝም ዘርፍ አሻራቸውን ያሳረፉት – አቶ ደርጉ ቱሌ ናቸው፡፡
አቶ ደርጉ በስፋት ከሚታወቁበት የፈርኒቸር ዘርፍ ባለፈ በሆቴል ኢንዱስትሪውም ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረጉ ይገኛሉ። በመሆኑም አዳማ የባ ኢንተርናሽናል ሆቴል ከፍተው ሥራ የጀመሩ ሲሆን፤ በቅርቡ ሻሸመኔ ላይ የገዙት አዲስ ሪዞርት ሆቴልም ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅቱን አጠናቋል። በቀጣይ የሆቴል ኢንዱስትሪውን ለማስፋት ዕቅድ ያላቸው አቶ ደርጉ የፈርኒቸር ዘርፉ ሙሉ ለሙሉ መሰረት የያዘና የሚመራው የራሱ አስተዳደር ያለው ነው ይላሉ፡፡
ዛሬ ላይ በስፋት ወደታወቁበት የፈርኒቸር ዘርፍ ከመግባታቸው አስቀድሞ በትናንሽ የንግድ ሥራዎች ላይ ተሰርተዋል። በተለይም ሻሸመኔ ሞቅ ደመቅ ያለች የንግድ ከተማ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ ተወልደው ካደጉበት የገጠር ገበሬ ማህበር የእንሰት ቅጠል (ኮባ) ቅጠል እያመጡ ሻሸመኔ ላይ ይሸጡ ነበር። ኮቦ የዳቦና የቆጮ መጋገሪ ቅጠል በስፋት የሚሸጠው በባዕላት ሰሞን እንደነበር ያስታውሳሉ። ኮባ በሚሸጡበት አካባቢ ደግሞ ያገለገሉ የቤትና የቢሮ ዕቃዎች ሲሸጥ አስተውለዋል። ከኮባ ንግድ ይበልጥ አዋጭ ይሆናል ብለው በማመንም በቀጥታ ያገለገሉ የቤትና የቢሮ እቃዎች ሽያጭ ስራ ውስጥ ዘው አሉ።
አቶ ደርጉ ሰው የቻለውን ሁሉ እኔም እችላለው ብለው የሚያምኑና እይታቸው ሰፊ በመሆኑ በኮባ ንግድ ያገኙትን ሁለት ሺ ብር ይዘው ርብራብ አልጋ አንድ ሁለት እያሉ መነገድ ጀመሩ። ኮባ ሽጠው ከሚያገኙት ትርፍ ይበልጥ ከአልጋ የሚገኘው ትርፍ ጠርቀም እያለ የመጣ መሆኑን አስተውለዋል። የተሰራውን ገዝቶ መሸጥ ይህን ያህል ውጤታማ ማድረግ ከቻለ ለምን አላመርትም የሚል ሌላ ጥልቅ ሀሳብ ወጥነው ለማምረት ዝግጅት አደረጉ። በወቅቱ ምንም እንኳን የእጅ ሙያ ባይኖራቸውም ‹‹መልክ ሥጠኝ እንጂ ሙያ ከጎረቤት›› እንደሚባለው በዘርፉ ሙያው ያላቸውን ሁለት ሰራተኞች ቀጥረው ወደ ማምረት ገቡ። በዚህ ጊዜ ሙያውን ከባለሙያዎቹ መቅሰም ችለዋል።
ሥራው እንዳሰቡት ውጤታማ እየሆነ ሲመጣ በወቅቱ አነስተኛ ማሽን ከቻይና መግዛት አስችሏቸዋል። የሰው ልጅ በሚፈልገው የሥራ ዘርፍ ላይ በቂ ጥረት ካደረገና መሆን የሚፈልገውን አውቆ በዕምነት በአንደበቱ እሆናለሁ ብሎ መናገር ከቻለ ይሆናል ፤ይደረግለታል ብለው የሚያምኑት አቶ ደርጉ፤ ዕድልና አጋጣሚው ተገጣጥሞላቸው በወቅቱ ጥቃቅንና አነስተኛ የሚል ፕሮግራም መንግስት መጀመሩ ትልቅ ዕድል የፈጠረላቸው እንደሆነ ያስታውሳሉ። በዚህ ጊዜ ወንድምና እህታቸውን ጨምረው አዳማ ከተማ ላይ በመደራጀት የዕድሉ ተጠቃሚ ሆነዋል።
ጥሩ አጋጣሚ የሆነላቸው የመንግስት ፕሮግራም የጀመሩትን የፈርኒቸር ምርት በስፋት ለመሥራት በር ከፍቶላቸዋል። በወቅቱ ከመንግስት ያገኙትን ሼድ ተጠቅመው ሲሰሩ ሰራተኞቻቸውን ከሁለት ወደ አራት፤ ከአራት ወደ ስምንት አሳድገዋል። በጊዜው ማህበረሰቡ በስፋት የሚፈልገው ብፌዎች(ባለመስታወት የእቃ መደርደሪያ) ነበር እነሱን በማምረት ለገበያ ያቀርባሉ። በተጨማሪም አልጋዎች ሶፋና ሌሎች የቤት ውስጥ ዕቃዎችን ከደንበኞቻቸው በሚቀርብላቸው ትዕዛዝ መሰረት እያመረቱ ለገበያ አቅርበዋል። መንግስት ባመቻቸላቸው ዕድል ተደራጅተውና የማምረቻ ቦታ ተጠቅመው ከሚያመርቱ አምራቾች መካካል ጥሩ አደረጃጀትና አፈጻጸም የነበራቸው በመሆኑና በወቅቱ ከ20 በላይ ለሚደርሱ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር በመቻላቸውና አጠቃላይ ለሥራ ባላቸው ተነሳሽነት በዘርፉ ከአዳማ ከተማ የዋንጫ ተሸላሚ ሆነዋል።
በሥራዬ ውጤታማ ሆኜ ለመሸለሜ አስተዳደጌ የመጣሁበት የገጠር ገበሬ ማህበር አስተዋጽኦ አለው የሚሉት አቶ ደርጉ፤ ዝቅ ብሎ መስራት ከፍ ያደርጋል የሚል ዕምነትም አላቸው። ከዚህ አለፍ ሲልም ለራስ ብቻ ሳይሆን በዙሪያችን ላሉ ሰዎች ማሰብና በግልጽነት መስራትም ውጤታማ ያደርጋል። ዕድገት ግልጽ ከመሆንና ቀና እያሰቡ ከመስራት ይመጣል። አንድ ሰው ብቻውን ቢሰራና ቢሳካለት ምንም ትርጉም የለውም። በዙሪያችን ያሉ ሰዎች ሁሉ የዕድገትና የስኬት መሰረቶችን አውቀው እንዲተጉ ማድረግ ያስፈልጋል። ይህን ማስተማር ደግሞ ከተሳካላቸው ሰዎች ይጠበቃል። ያካልሆነ ግን የራስን ዕድገት እየገቱ እንደመሄድ ይቆጠራል።
‹‹ቀና አመለካከት የስኬት ቁልፍ ነው›› ያሚሉት አቶ ደርጉ፤ ከአስተዳደጋቸው ጀምሮ አብሯቸው ያለው ቀና አስተሳሰብ አሁን ለደረሱበት ስኬት አድርሶኛል በቀጣይም ከዚህ በበለጠ የስኬት ማማ ላይ ያወጣኛል ብለው ያምናሉ። ገና ከልጅነታቸው እራስን ለመለወጥ፣ ለማደግና ለመሻሻል ብለው ከትውልድ ቦታቸው የገጠር ሥፍራ ወደ ሻሸመኔ ከተማ ሲመላለሱ ቤተሰብ ከተማ ገብቶ ይበላሻል የሚል ስጋት የነበራቸው መሆኑን ያስታውሳሉ። ይሁንና እርሳቸው በንግድ ከተማነቷ በምትታወቀው ሻሸመኔ ከተማ ላይ ኮባ ከመሸጥ ጀምሮ ርብራብ አልጋም ሲሸጡ የነበራቸው ልበ ቀናነት ዛሬም አብሯቸው እንዳለና ለስኬት ያበቃቸው መሆኑን በኩራት ይናገራሉ። በተለይም የገጠር ልጅ መሆናቸው በርካታ መሰናክሎችን በጥንካሬ ማለፍ እንዲችሉ ረድቷቸዋል። ለዚህም የገጠር ኑሮ በራሱ ፈተና በመሆኑ ወደ ከተማ ገብተው በሥራ ላይ የገጠሟቸውን መሰናክሎች በቀላሉ በማለፍ ችለዋል፡፡
ከአስር ዓመት በፊት የተጀመረው ምንቴ ፈርኒቸር ምርቶቹን አምርቶ ለገበያ የሚያቀርብባቸው የተለያዩ ቦታዎች አሉት። ምርቱ መነሻውን ያደረገው አዳማ ከተማ ላይ እንደመሆኑ በከተማዋ በስፋት ይመረታል፤ ይሸጣልም። ምርቶቹ አዳማ ከተማ ቀበሌ 03 ውስጥ ከመንግስት በተገኘው አራት ሺ ካሬ ሜትር ስፋት ለገበያ ይቀርባል። ከአዳማ ውጭ ደግሞ ሻሸመኔ ከተማ ላይም እንዲሁ የመሸጫ ቦታ በመኖሩ ምርቶቹ በስፋት ለገበያ ይቀርባሉ። ከአዳማ እና ከሻሸመኔ በተጨማሪም ምንቴ ፈርኒቸር አዲስ አበባ ከተማ መካኒሳ አካባቢ የማምረቻ ቦታ ሲኖረው ቃሊቲ አካባቢ ያለውን የመሸጫ ቦታ ጨምሮ አራት የመሸጫ ስፍራዎች አሉት።
ምንቴ ፈርኒቸር ከሚያመርታቸው ምርቶችም መካከል ሶፋ በስፋት ሲሆን፤ ብፌዎች፣ ቁምሳጥኖች፣ የምግብ ጠረጴዛዎች፣ አልጋዎችና የተለያዩ የቤት ውስጥና የቢሮ ዕቃዎች ይገኙበታል። ለምርቶቹ ግብዓት የሚሆነው በዋናነት እንጨት ሲሆን ከሀገር ውስጥ ይገኛል። ነገር ግን አልፎ አልፎ የማጠናቀቂያ ቁሳቁሶች ለአብነትም ለሶፋ አልባሳት የሚሆኑ የተለያዩ ጨርቃ ጨርቆችን እና የተለያዩ መገልገያ ቁሳቁሶችን ከቻይና ያስመጣሉ። አልፎ አልፎም በሀገር ውስጥ በጥራት የማይገኙ ቁሳ ቁሶችን ያስገቡ ነበር። ይሁንና በአሁን ወቅት 90 በመቶ ያህል ቁሳቁሶችን ከሀገር ውስጥ በመጠቀም ጥራት ያላቸውን የቤትና የቢሮ ዕቃዎችን እያመረተ ለገበያ ያቀርባል፡፡
ማንኛውም ነገር በፍላጎትና በጥራት ቴክኖሎጂን ተጠቅመን መስራት ከቻልን ከሀገር ውስጥ አልፈን የውጭ ገበያን መሸፈን የሚያስችል አቅምና የታደለ ተፈጥሮ ስለመኖሩ የሚናገሩት አቶ ደርጉ፤ ከውጭ ሀገር የሚገቡ የፈርኒቸር ምርቶች ምንም የተለየ ነገር የሌላቸው መሆኑን ይናገራሉ። በውጭ ሀገር ካለው ሰው ጋር እኩል ነን፤ እነሱ የሰሩትን ሁሉ እንሰራለን። እስካሁን ያልተጠቀምነውን ቴክኖሎጂ አሁን ላይ በመጠቀም በሚመረቱ ምርቶች ተወዳዳሪ መሆን ተችሏል። ከዚህም በላይ ከውጭ ከሚገቡ ምርቶች በበለጠ በጥራት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተለይም በአሁን ወቅት ሀገሪቷ ባለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት የምርት እጥረት ያጋጠመ በመሆኑ እና የሀገር ውስጥ ምርት ያለውን ጥራትና ጥንካሬውን በማየት አብዛኛው ሰው ወደ ሀገር ውስጥ ምርት እየመጣ ነው። ይህን መልካም አጋጣሚ በመጠቀምም አምራቾች ጥራት ያለውን ምርት የደንበኞችን ፍላጎት መሰረት በማድረግ በስፋት በማምረት ገበያውን መቆጣጠር ተችሏል። ስለዚህ በቀጣይም ይህንኑ በማስቀጠልና ከውጭ የሚገባውን ምርት በማስቀረት በምትኩ ወደ ውጭ የመላክ ዕቅድ ይዞ መስራት ያስፈልጋል። ይህ በዋጋም ይሁን በሚፈጠረው የስራ ዕድል ለሀገር ኢኮኖሚ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላል።
በአሁኑ ወቅት በድርጅታቸው ሥር አጠቃላይ ከ600 ለሚልቁ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻሉ ሲሆን፤ ለሥራቸው አስፈላጊ የሆኑና አብረዋቸው የሰሩ በርካታ ሰዎችንም ራሳቸውን ችለው ለሌሎች የሥራ ዕድል መፍጠር እንዲችሉ አድርገዋል። ማህበራዊ ሀላፊነትን ከመወጣት አንጻርም እንዲሁ ለሰዎች ሀሳብ ከማካፈል ጀምሮ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ በማድረግ ይታወቃሉ። በተለይም ገንዘብ ከመስጠት ይልቅ ሥራ በመፍጠር ዜጎች ራሳቸውን የሚችሉበትን መንገድ በማመላከት ማህበራዊ ሀላፊነታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ።
ዛሬ ላይ የፈጠሩትን 600 የሥራ ዕድል በቀጣይ ስድስት ሺ እና ከዛም በላይ ለማድረስ ዕቅድ ያላቸው አቶ ደርጉ፤ ይህ ዕቅድም ሊተገበርና ሊሳካ የሚችል ነው። ምክንያቱም አንድ ጊዜ ስርዓቱ ተዘርግቷልና እራሱ የሥራ ዕድሉን እየፈጠረና እየሰፈ ይሄዳል። በዚህም በርካታ ዜጎች ተጠቃሚ ይሆናሉ። ሰዎች ሰርተው ገቢ ከማግኘት ባለፈ መለወጥና ለሌሎች መትረፍ ይችላሉ። ለዚህ ግን በቅድሚያ እችላለሁ ብሎ ማመንና በቁርጠኝነት መነሳት ያስፈልጋል ብለው የሚያምኑት አቶ ደርጉ፤ በዚህ አመለካከታቸውም በዙሪያቸው ባሉ ሰዎች ይታወቃሉ።
ሰዎች ስለራሳቸው ዳቦ ጠግበው መብላት ብቻ ካሰቡ ለሌሎች መኖር አይችሉም። ስለሌሎች ሰዎች እያሰብን በቅንነትና በግልጽነት መኖር ያልቻለ ሰው ደግሞ ስኬታማ መሆን አይችልም። ስለዚህ ከራስ አለፍ ብለን ስለ አካባቢ፣ ሲቀጥልም ሀገራዊ የሆነ አስተሳሰብ ማራመድ ያስፈልጋል። ሲቀጥል ደግሞ ዓለም አቀፍ መሆን ይቻላል። ያን ጊዜ ሰዎች የሚያስቡትን ሀሳብ በማሳካት ስኬታማ መሆን ይቻላሉ። ይህ ደግሞ ውስጣዊ ደስታን ያጎናጽፋል በማለት ሰዎች ሁል ጊዜ እንደ ንስር አሞራ እይታቸውን ማስፋት እንዳለባቸውም ይመክራሉ፡፡
ለዚህም የእኛ ሀገር ሰው ድህነትን ተላምዶ በቅርበት እየተመለከተው ይኖራል። ነገር እንደ ንስር አሞራ እይታውን በማስፋት እንዴት አድርገን ከድህነት እንላቀቅ ብለን ማሰብና ሀሳብን ወደ ተግባር መቀየር ከተቻለ ስኬታማ መሆን ይቻላል። ሁል ጊዜ አዕምሮን ለበጎ ነገር በማዘጋጀት እችላለሁ ይሳካል ብሎ በማመን መነሳት ያስፈልጋል። ያን ጊዜ ሁሉም ነገር ጥሩ ከመሆን ውጭ ምንም አማራጭ አይኖረውም። ማንኛውም ነገር ለአዕምሯችን በነገርነው ልክ ነው የምንሆነው። ኑሮ በራሱ ከባድ ነው ካልነው ይከብዳል። ‹‹ሰው የአፉን ፍሬ ይበላል›› እንዳለው ታላቁ መጽሐፍ እኛም መልካም ነገር እያሰብን ከሥራ ጋር በአንደበታችን መልካም ነገሮችን በማውጣት ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻልም የህይወት ልምዳቸውን አጋርተዋል።
በየጊዜው እዚህ ጋር እደርሳለሁ እያሉ ዕቅድ የሚያዘጋጁት አቶ ደርጉ፤ ከዛሬ አስር ዓመት አስቀድመው ሚሊየነር ነኝ ብለው ለሰዎች ይናገሩ እንደነበርና ያኔ በዙሪያቸው ያሉ ሰዎች ጉረኛ ይሏቸው እንደነበር አስታውሰዋል። ይሁን እንጂ እርሳቸው ያኔ እሆናለሁ ያሉት ዛሬ ላይ ሆነው ተገኝተዋል። ለዚህም ሰዎች በአስተሳሰባቸውና በፈለጉት መጠን መኖር የሚችሉ እንደሆነ ተምሬበታለሁ በማለት ለሌሎችም ይህ አስተሳሰብ ቢጋባባቸው መልካም ነው በማለት ሀሳባቸውን ቋጭተዋል። እኛም ተሞክሯቸውን ወስደን ብንጠቀመው ውጤታማ መሆን ያስችላል በሚል ነው እንግዳችን ያደረግናቸው።
ፍሬህይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 19/2013