ራስወርቅ ሙሉጌታ
የነገ አገር ተረካቢ የሆኑ ወጣቶችን በስነ ምግባር የታነጹ ይሆኑ ዘንድ የቤተሰብ ብቻ ሳይሆን የማህበረሰብ፤ የእምነት ተቋማትና የመንግሥት ሚና ከፍተኛ ነው። ወጣቶች በለጋ ዕድሜያቸው የሚደረግላቸው እንክብካቤና ጥበቃ ለራሳቸው ጥሩ ሕይወት እንዲመሩ ብሎም ለአገርና ለሕዝብ አሳቢና ሰላማዊ ዜጎች እንዲሆኑ የሚያበቃቸው ይሆናል። ወጣቶችን ከትምህርታቸው እንዲዘናጉና ካሰቡት አላማ እንዳይደረሱ እንቅፋት እየፈጠሩባቸው ከሚገኙና የቤተሰብ፤ የሃይማኖት አባቶችን፣ የመንግሥትን ክትትልና ድጋፍ ከሚሹ ችግሮች መካከል ለተለያዩ ሱሶች ጥገኛ መሆን ቀዳሚውን ቦታ ይይዛል።
እስከ ቅርብ ጊዜ እንደ ማህበረሰብ የሱስ ነገር ሲነሳ ወደ አእምሯችን የሚመጡት እንደ መጠጥ፣ ጫት፣ ሲጋራ፣ ሀሺሽና ሺሻ ያሉት ናቸው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በአገራችን እምብዛም ያልተለመዱት ነገር ግን በአውሮፓና አሜሪካ በከፍተኛ ደረጃ የተስፋፉት የኤሌክትሮኒክስ የኳስ ውድድር ጨዋታዎች በርካታ ወጣቶችን ሱሰኛ እያደረጉ ይገኛሉ። ለመሆኑ አነዚህ የኤሌክትሮኒክስ ውድድር ጨዋታዎች በወጣቶች ላይ ምን ዓይነት የሥነ ልቦና ጫና ያሳድራሉ ስንል የሥነ ልቦና ባለሙያ አነጋግረን የሚከተለውን ይዘን ቀርበናል።
ወይዘሮ ሙሉ መኮንን በኢምፓክት ኢትዮጵያ የሳይኮሎጂካል አገልግሎቶችና የማኅበረሰብ ጤና ማማከር ማኅበር የሥነልቦና አማካሪና የማኅበረሰብ ጤና ባለሙያ ናቸው። ባለሙያዋ እንደሚያብራሩት፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመዲናችን አዲስ አበባ በሕጋዊ መንገድ እውቅናና ፈቃድ አግኝተው የኳስ ጨዋታን በመንተራስ ውድድር የሚያካሂዱ ሱቆች እየተበራከቱ መጥተዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1981 የውርርድ
ጨዋታዎችን አስመልክቶ በወጣው ሕግ መሠረት ፈቃድ የመስጠት ሥልጣን በተሰጠው መሠረት ለእነዚህ ተቋማት ፈቃድ ሰጥቷቸዋል። በዚህም አግባብ በሕጋዊ መንገድ የንግድ ፈቃድ አውጥተው ቤት ተከራይተው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ። በሌላ በኩል እንደነዚህ መሰል ጨዋታዎች ማህበረሰቡ ላይ ጫና ይፈጥራሉ ተብሎ ስለሚታሰብ እስከ ቅርብ ጊዜ በሚዲያ ማስተዋወቅ ይከለከሉ ነበር። አሁን ግን ይህንን ማስተዋወቅ በመጀመራቸው የተጠቃሚው ቁጥር እየጨመረና ውድድሩንም እንደ መልካም የማየቱ ነገር እየተስፋፋ መጥቷል። በአሁኑ ወቅትም «ስፖርት ቤቲንግን» በርካታ ወጣቶች እየተጠቀሙት የሚገኝ ሲሆን አብዛኛዎቹ ለተለያዩ ችግሮች እየተጋለጡ ይገኛሉ።
በመጀመሪያ ደረጃ ጨዋታ የሚባለው «ውድድር» ሳይሆን «ውርርድ» ነው። ውድድር የአንድን ሰው አካላዊ ወይንም አእምሯዊ ብቃት በመጠቀም የሚደረግ ፉክክር ሲሆን ውርርድ ግን በሌሎች ሁለት አካላት ፉከክር ላይ ተመስርቶ የሚገኝ ውጤትን መነሻ የሚያደርግ ነው። እንደዚህ ዓይነት ፉክክሮች ደግሞ ሱሰኛ የማድረግ አቅማቸው ከፍተኛ ነው። በመሆኑም ይህ ውድድር ቁማር እንደማለት ነው። አንደዚህ ዓይነት ውርርዶችን የሚያደርጉ ወጣቶች በአንድ ወገን ያለ ሥራ፤ ያለ ልፋት ገንዘብ የማግኘትን ልምድ እያዳበሩ እንዲመጡ የሚያደርጋቸው ሲሆን በሌላ በኩል በቀጣይ ሕይወታቸው እንደ ሱስ ሆኖ ወደ ሌሎች የቁማር ጨዋታዎችም እንዲሳተፉ በር የሚከፍት ይሆናል።
ይህም ከትምህርታቸው እንዲዘናጉ፤ ያላቸውን አቅም ለማውጣት የሚኖራቸውን በራስ የመተማመን መንፈስ የሚያጠፋና በሕይወታቸው አቋራጭ መንገዶችን በመጠቀም የሚፈልጉትን ነገር ለማግኘት የሚንቀሳቀሱ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። ምንም እንኳን የውድድሩ ቦታ ላይ የሚገኙት አንድ ጊዜ ገንዘብ ከፍለው ትኬት ለመቁረጥ ቢሆንም የውድድሩ ውጤት እስኪጠናቀቅ ድረስ ያሉትን ጊዜያቶች የሚያሳልፉት ሙሉ የኳስ ጨዋታውን በመከታተልና ስለሱ በማሰብ ይሆናል። በዚህም አጠቃላይ ትኩረታቸው ወደ ጨዋታው ስለሚሆን በትምህርታቸው ደካማ እንዲሆኑ ውሸታምና በባህሪያቸው ነጭናጫ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። ይህም ከቤተሰብ ጋር እንዳይስማሙ በማህበረሰቡ ዘንድ ያላቸው ተቀባይነትና ተአማኒት አንዲጎድልና ማህበራዊ ኃላፊነት ለመቀበል እንዳያስችላቸው ያደርጋል።
የዚህ ዓይነቱ ውርርድ ደግሞ ትኬት ቆርጠው ቢያሸንፉ የሚያገኙት ገንዘብ ስለሚጥማቸው መቀጠላቸው የማይቀር ሲሆን ባይወጣላቸውም እልህ ስለሚገቡ መደጋገማቸው አይቀርም። እናም አዙሪት ውስጥ ለመግባት ይገደዳሉ። በአሁኑ ወቅትም ጥቂት የማይባሉ ወጣቶች በቀጥታ ከቤተሰብ ብር እየጠየቁ በመውሰድ ሳያገኙ ሲቀሩ ደግሞ ወደመስረቅ እየገቡ ይገኛሉ። ከዚህ በተጨማሪ ምንም እንኳን አንዳንዶቹ ቤቶች «ከአስራ ስምንት ዓመት በታች ብቻ ለሆኑ» የሚል ነገር ቢለጥፉም አገልግሎቱን ግን የሚሰጡት በአንደኛ ደረጃ ለሚማሩ ሁሉ ነው።
በቀጣይም ይህ ያለ ልፋት የሚገኝ ገንዘብ እንደ ግለሰብ ተወዳዳሪዎቹን ሱስ እያስያዘ እንዲደጋግሙ ከማሰሩ ባሻገር ተጠቃሚዎቹ በቀላል ኢንቨስትመንት ከፍተኛ ገቢ የሚያገኙበት በመሆኑ ሥራው እየተስፋፋ መምጣቱ አይቀርም። ይልቁንም ዛሬ እኛ አገር ያልገቡ ነገር ግን በአውሮፓ እየተስስፋፉ ያሉ የተለያዩ የቁማር ዓይነቶች በአገሪቱ እንዲስፋፉ በር የሚከፍትም ይሆናል። ይህ ደግሞ በግለሰብና በቤተሰብ ደረጃ ከሚያስከትለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንደ ተጠበቀ ሆኖ እንደ አገር ደግሞ ባለ ሀብቶችች በርካታ አሴት ተጨምሮባቸው ለአገርና ለሕዝብ የሚበጁ የሥራ ዕድል የሚፈሩ ሥራዎችን ከመጀመር ይልቅ በቀላሉ የሚበለጽጉበትን እንዲመርጡ ይገፋፋቸዋል። በመሆኑም ለጥቂት ሰዎች የሥራ ዕድል ከፍቶ የማህበረሰቡን ግንኙነትና ሞራል የሚነካ ስለሚሆን ከፍተኛ ጥበቃና ጥንቃቄ የሚፈልግ ነው። በዚህ ረገድ ከማስተማርና ከመቆጣጠርም ባለፈ ሕጉን ዘመኑን በሚዋጅና አሁን ያለውን የቴክኖሎጂ ደረጃና ወደፊትም ከቴክኖሎጂ እድገትና መራቀቅ ጋር ሊፈጠሩ የሚችሉትንም ከግምት በማስገባት መፈተሽ እንደሚገባ ባለሙያዋ ያሳስባሉ።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 19/2013