ግርማ መንግሥቴ
በዘመነ ደርግ በ”ሶስቱ ሥላሴዎች” ስያሜ የሚጠሩትን በዘመኑ የኖረ ሳያውቃቸው (ሳያስታውሳቸው) አይቀርም። ይህ አይነቱ ታሪክና ባህል፣ ፖለቲካውንና ሃይማኖቱን በአንድ የማስተባበር፤ አስተሳስሮም ለአንድ አገራዊና ማህበራዊ ፋይዳ ሲባል ጥቅም ላይ ማዋል በራሱ እንደ አንድ ማህበረ-ባህላዊ እሴት ተወስዶ ተገቢውን ቦታ ሊገኝ ይገባል።
ፈጠራውም ሆነ አጠቃቀሙ የተለመደ ሳይሆን የሚቀር አይመስልም። ለምን? በዘመነ ኢህአዴግም እውቋ ዳንኪረኛ ቢዮንሴ በሚሊነየማችን መግቢያ ብቅ ብላ ነበር። ብቅታዋንም ተከትሎ “በሰባት ሥላሴ በዘጠኝ ቢዮንሴ” የምትል ነገር ጣል ተደርጋ ታልፋለች። ወደፊት ከማነጋገርና ማወያየት አልፋ ማመራመሯ አይቀርምና ነው እዚህ ጠቀስ አድርገናት ማለፋችን። (ደ’ሞም በየስያሜዎቹ የ”ሥላሴ” ቋሚነት።)
ከ”ሶስቱ ሥላሴዎች” ሌኒን (1870-1924) ዓለማችን ካፈራቻቸው እውቅ (ኤሚነንት)፣ ቀዳሚና ተፅእኖ ፈጣሪ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር፣ አንቂ፣ አደራጅና መሪ ነው። በመሆኑም በእነዚህ ተግባርና ሃላፊነቶቹ ሁሉ ዓለም ከማወቅም አልፎ የ20ኛው ክ/ዘ ቁንጮ ለመሆኑ አረጋግጦለታል። አረጋግጦም አድንቆታል፤ አድንቆም አምልኮታል፤ ተከትሎታልም። ከተከታዮቹም አንዷ በአብዮተኞቿ አማካኝነት ኢትዮጵያ ነበረች።
በተለይ በአገርና ወገኖቹ እይታ ቭላድሚር ኢሊች ሌኒን “ታዋቂ” የሚለው ነጠላ ቃል የሚገልፀው አንድ ታዋቂና መልካም ስራ የሰራ ግለሰብ ብቻ ሳይሆን አገር – ሩሲያ ነው። እንደ ብዙዎች የጥናትና ምርምር ስራዎችም ይሁን ፖለቲካዊ ትንታኔዎች ያለ ሌኒን የዛሬዋ ራሺያ ባልኖረች ብቻ ሳይሆን ባልታሰበችም ነበር። ለዚህም ነው በሩሲያ በስሙ ያልተሰራ (ኢትዮጵያን ጨምሮ – ሌ. ጀነራል ተስፋዬ፣ ‘የአንድ ቀን ስልጣን ቢኖርህ ምን ታደጋለህ?’ እንደሚለው የልጅነት ጨዋታ፣ ሳምንት ባልሞላ የመሪነት ዘመናቸው አፈረሱት እንጂ (ነገሩ ለመጪው መንግስት እጅ መንሻ ነበር ብለው ያሚያሟቸው አሉ) ሀውልት ነበረው) ነገር የሌለው። ስራዎቹ የሚነበቡበት፣ የሚመረመሩበትና የሚከማቹበት ‘Leniniana’ በሚል ስያሜ የተቋቋመ ቤተመጻሕፍትም ተሰይሞላታል።
“ተፈረካከሰች” ከተባለች በኋላ ለዳግም ልደት የበቃችውን የአሁኗን ሩሲያ የቭላድሚር ፑቲን ውጤት መሆኗን የክሬምሊን አባላት ሳይቀሩ “Without Putin – no Russia.” በማለት እንደሚገልፁት ሁሉ፤ የጥቅምት አብዮት ባይከሰት ኖሮ ሩሲያ ባልነበረች፤ የጥቅምት አብዮት ፈጣሪ አባትና ወላጅ እናት (“mastermind” ነው የሚሉት) ደግሞ እሱ (Vladimir Il’ich Lenin) ነው።
ይህ ጽሑፍ የሌኒን አዋቂነትና አዋቂነቱ ያጎናፀፈውን ታዋቂነት ለመግለፅ አይደለም የተነሳው። ጽሑፉ ከሌኒን ጋር በተያያዘ በራሺያ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ በሚባሉት አማካኝነት የነበረውን ክፍተት ተጠቅሞ በ1990ዎቹ ብቅ ያለውን ጉንጭ አልፋ ክርክርና ተያይዞም ለዓመታት የዘለቀው እሰጥ አገባ ሲሆን እሱም “ሌኒን ማን ነው?” የሚለውና የዘር ቆጠራና የደም ስሌቱን (“genealogy”) የሚመለከት ነው። በመሆኑም በቀጥታ ወደ እሱው እናምራ።
በዘመነ ደርግ ለ17 ዓመታት ከነገሱት ማርክስና ኤንግልስ ጋር በ”ሰላም፣ መሬት፣ ዳቦ” (Peace, Land, Bread) የሚለው የዓላማና ግብ ማራመጃ መሪ ቃሉና እምነቱ የሚታወቀው ሌኒን ተለይቶ አያውቅም። በወቅቱ ባለስልጣናትና የሌኒን አስተምህሮ በሚገባ ገብቶናል ከሚሉ ወገኖች ዘንድም “ሌኒን እንዳለው …” በማለትና ከፈጣሪ ቃል አስቀድሞ መጥቀስ የተዘወተረ ብቻ ሳይሆን የተጠናወተ ልምድ ሁሉ እስኪመስል ድረስ ስራ ላይ ውሏል። “ሌኒን እንዳለው …”፣ “ማርክስ እንዳለው …”፣ “ኤንግልስ እንዳለው …” ወዘተ የእውነቶች ሁሉ ማረጋገጫ፣ የስራዎች ሁሉ መለኪያና የምሁርነት ሁሉ ቁና፤ እንደ “በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተጠቀሰው …” የማያስጠይቅ ነበር። (“ያ” የተባለው ትውልድም እንዲሁ ከማርክሲዝም-ሌኒኒዝም ጋር በፍቅር ወድቆ የነበረ ሲሆን፤ የግንዛቤ ይሁን የተግባራዊነት እጦት (ብዙዎች የግንዛቤ እጦት ነው ነው የሚሉት) በፈጠረው ክፍተት እርስ በእርስ መተላለቁ የአገራችን አንዱና ጉልሁ ታሪካችን አካል ነው።)
የሌኒንም ሆነ ማርክሲዝም-ሌኒኒዝም ጉዳይ ደርግ ላይ የቆመ ይምሰል እንጂ አልቆመም። በስፋት ሲሰነዘሩ ከነበሩት አስተያየቶች እንደምንረዳው ውስጥ ውስጡን በኮሚኒስትነቱ የሚታማው ኢህአዴግ ወደ ስልጣን መጥቶ ከሰነባበተ በኋላ በይፋ ከቪ.አይ. ሌኒን ስራዎች (“What is to be done?”፣ “State and Revolution” እና “April Theses” (የሚያዚያ 1917 ንድፈ ሐሳቦችን)) ጨምቆ የ”ልማታዊ መንግስት” ስራ ማስኬጃ የሆነውን “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” ማወጁን፤ ከስራ መመሪያም ባለፈ የገዥው ፓርቲ ርእዮት ማድረጉን ተከትሎ ሲሰነዘሩ የነበሩት አስተያየቶችና ሂሶች ፓርቲው አሁንም ከማርክሲስት ማእቀፍ ውስጥ ያልወጣ መሆኑን ሹክ የሚሉ ናቸው።
እንደ አንዳርጋቸው አሰግድና ሌሎችም ከሆነ የሌኒን ሃሳብ ያለአውዱ ተተርጉሞ ያለ ዓላማው ውሏል። ይህንንም “የአብዮታዊ ዴሞክራሲን አስተሳሰብ አመጣጥ በጥቅሉ ለማቅረብ ብንሞክር አመንጪው ሌኒን ነው። ይሁንና አብዮታዊ ዴሞክራሲ ለሌኒን በራሱና ለራሱ ግብ አልነበረም፣ ወይም የሥልጣን መጠበቂያና የመግዣ መሣሪያ አልነበረም። ሌኒን አብዮታዊ ዴሞክራሲን የተጠቀመበት የሩሲያን የጥቅምት አብዮት በቀደመው የየካቲት 1917 ዓ.ም አብዮት ሥልጣን የጨበጠውን ክፍል ለማስወገድና ሥልጣንን ለመያዝ በመደራጃና መታገያ መሣሪያነቱ ነበር።” ይህ ደግሞ በሃሳቡ አመንጪና ተቀባዩ በኩል ያለው ልዩነት የሰማይና የመሬት ያህል መሆኑን ያሳያሉ። (ይህን እዚህ መጥቀስ ያስፈለገው የአሁኑ ዘመን የዘር ፖለቲካ (racial politics) ሰለባ የሆነውን ሌኒንን ከስራዎቹ ጋር አያይዞ ለመግለፅ መሆኑ ደግመን እናስታውሳለን።)
ይህ ብቻም አይደለም፣ ማርክስና ሌኒንን በአንድ የሚያስተሳስረውና ወደ አንድ ወጥ ፍልስፍና የሚያሸጋግረው “ማርክሲዝም-ሌኒኒዝም” የፖለቲካ ፍልስፍናና ርእዮቱ ወደ ሰፊው ህዝብ ይሰርፅ ዘንድ ውድም/ግድም ነበርና ይህንኑ ለማድረግ ድርጅቶች (ለምሳሌ “ኢማሌድኅ” – የኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች ኅብረት) ሁሉ ተቋቁመው የማጥመቁ (ኢንዶክትሪኔሽን) ስራ ይሰራ ነበር። ይህ እንግዲህ የመንግስት መዋቅርንና የማህበረሰቡን አደረጃጀት ተከትለው ከላይ እስከ ታች የተዋቀሩትን የውይይት ክበባት ሳይጨምር ነው።
በአይነቱ የመጀመሪያውም የመጨረሻውም በሆነውና በራሺያ ግዛት በ1897 በተካሄደው የህዝብና ቤቶች ቆጠራ (Imperial Census) መሰረት በወቅቱ የነበረው የራሺያ (ፊንላንድን ሳይጨምር) ህዝብ ቁጥር 126 ሚሊዮን ሲሆን ከዚህ ውስጥ በዘር ሀረጉ (ብሄሩ?) ሩሲያዊ፤ የአፍ መፍቻ ቋንቋው ራሺኛ የሆነው ህዝብ 56 ሚሊዮን (44%) ሲሆን ቀሪዎቹ (56%) በባህላዊ መስተጋብር ምክንያት በተፈጠረው የባህል ውርርስ ምክንያት የተዋሀዱና የዛሬይቱን ሶቪየት ህብረት የፈጠሩ ናቸው።
በዚሁ በጠቀስነው 1897 ሩሲያ በርካታ የዘር ሀረግ ያላቸው ዜጎችን ያስተናገደች ሲሆን፤ 8 ሚሊዮን (6%) ፖሊሾች (ፖላንዳዊያን)ን፣ 5 ሚሊዮን (4%) ጁዎችን፣ 5 ሚሊዮን (4%) ታርስ እና ባሽኪርሶችን (Tatars and Bashkirs)፣ 3 ሚሊዮን (2.4%) ባልቲኮች (Baltic nations)፣ እንዲሁም 2 ሚሊዮን (1.6%) የሚሆኑት ደግሞ ጀርመኖችና ስዊድኖች ነበሩ።
የወቅቱ እውነታ (genealogical fact) ይህ ሲሆን የዛሬዋ ሩሲያም የእነዚህ ሁሉ ውሁድና ድምር ውጤት ነች እንጂ “እኔ ንፁህ … ነኝ” ብሎ አካኪ ዘራፍ ማለት ዓላማው አገር ለማፍረስ፤ ትርፉም ኪሳራ ከመሆን ሊያልፍ አይችልም። እዚህ ላይ አንድ ነገር አንስቶ ማለፍ ጠቃሚ ሲሆን እሱም የእኛው የኢትዮያን ወቅታዊ ሁኔታ በትክክል ልስለሚያሳይ ብቻ ሳይሆን ከላይ ካልነውም ሆነ ከሚቀጥለው ጋር አብሮ ስለሚሄድ ነው።
ነፍሱን ይማረውና የጉዳዩ ባለቤት ገጣሚውና የሥነፅሁፍ መምህሩ ሰለሞን ደሬሳ ነው። ሪፖርተር ባነጋገረው ወቅት ካነሳቸው ጥያቄዎች አንዱ “ብሄርህ ምንድነው?” የሚል ነበር፤ ደስ የሚለው ብቻ አይደለም የሚያስተምረው መልሱ ነው – በሴት አያቶቻችን በር ላይ ማን እንዳለፈ አውቀን ነው እኔ እንዲህ ነኝ እኔ እንዲህ ነኝ የምንለው?
የተፈጠረውንና ሩሲያን ተገጠማትን መደነቃቀፍ ተጠቅሞ በ1990ዎቹ ብቅ ያለውና በሌኒን አስታኮ ሪክን እንደገና ለመፃፍ፣ ነባር እሴቶችን ከስራቸው ነቅሎ ለመጣል፣ ወጣቱን አቅጣጫ በማሳት በአገሩ ጥቅም ላይ እንዲነሳና የተሳሳተ ትርክት ባለቤት እንዲሆን፣ የስነምግባርና ሞራል ድንበሮች እንዲጣሱ ወዘተ (የ Daniel Staetsky “Was Lenin Jewish?”ን ይመልከቱ) የገጠማት ችግር የድሮውን ወደ አሁኑ ዘመን በማምጣት ጠብ ያለሽ በዳቦ የሚለው መብዛቱ ብቻ ሳይሆን አላስፈላጊ ውዝግብ፣ መከፋፈልና አገርን የማፍረስ እንቅስቃሴ መታየቱ ነው። በዚህ ተቃራኒ ያሉት ወገኖች ደግሞ የሚሉት ቢኖር “አሁን ይህን (ሌኒን ጁው ነው የሚለውን) ምን አመጣው?” ነው። ሌኒን ማድረግ ያለበትን አድርጎ፣ ለሩሲያና ወገኖቹ የሚበጀውን አበርክቶ ወደማይቀረው ሄዶ ሳለ ይህን (Jewish Lenin) ምን አመጣው? በተለይ ጊዜ ያመ(የሰ)ጣቸው የፖለቲካ ፓርቲ ነን የሚሉትስ ይህ አይነቱን ከፋፋይና የጥንቱን ተግባር በአሁኑ ሚዛን የመለካት እኩይ አስተሳሰብስ አጀንዳ አድርጎ መንቀሳቀስ ፋይዳው ምንድን ነው? አስፈላጊነቱስ?” የሚለው፤ እንዲሁም ለአጠቃላይ አገሪቷና ህዝቧ ብቻ ሳይሆን ለዓለም ባለውለታ የሆነን ታላቅ ሰው “ጁ ሌኒን” (Jewish Lenin) የሚል ታርጋ (tagline) መለጠፉና ይህን የሩሲያ አብዮት መሪ “ሩሲያዊ አይደለም” የሚል አፍራሽ ሃሳብ ማምጣቱ ለምን ሲባል? የሚለው ነው። (“ጁ ሌኒን” “Lenin’s Jewish Question” በሚለው የYohanan Petrovsky-Shtern መጽሐፍ ውስጥ በዋናነት መጠቀሱና የሽፋን ሥእል ሁሉ ሆኖ መምጣቱ ለውዝግቡ መጧጧፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል።)
ታይም መጽሄት የ20ኛው ክፍለ ዘመን ተፅእኖ ፈጣሪ ከሆኑት 100ዎቹ አንዱ አድርጎ የመረጠው፤ ሕግ አዋቂና የተመሰከረለት ጠበቃ፣ አብዮተኛ፣ የቮልሼቪክ ፓርቲ እና የጥቅምት አብዮት ጠንሳሽ መሪ፣ አብዮቱ ያስገኘውንም ውጤት/ድል ተከትሎ የሩሲያ የመጀመሪያው መሪ፤ በኋላም ሃሳቡ ለሰው ልጆች ሁሉ ጠቃሚና ለፍትህ፣ እኩልነትና ሰብአዊነት ከፍተኛ ዋጋ አለው በሚል ሃሳቡ ወደ “—ism” የተሸጋገረለትና ፍልስፍናዊ ይዘቱን እንዲይዝ በማድረግ ወደ “Leninism” ያደገለት ሰው፤ ከዛ ሁሉ መስዋእትነቱ፣ አስተሳሰቡ፣ እንቅስቃሴና ተግባሩ፣ ህዝባዊነቱ ወዘተ ደረጃ አውርዶና ወደ ምስራቅ አውሮፓ አጓጉዞ “ጁ ነው/አይደለም” የሚል እሰጥ አገባ ውስጥ ማስገባት አገሪቱን ለማፍረስ ካልሆነ ፋይዳው ምን ላይ ነው? ብለው ከሚጠይቁት አንዱ “Was Lenin Jewish?” በሚል ጠንካራ ትንታኔና ማብራሪያ ያቀረቡት ዳንኤል ስቴትስኪ (2020) ሲሆኑ ከላይ ያቀረብነውን የአገሪቱን የብሄር ስብጥር በመረጃነት በመጠቀም ማንም “ንፁህ … ነኝ” ማለት እንደማይችልና ሁሉም የተቀላቀለ ሊሆን እንደሚችል አውቆ ከእንደዚህ አይነቱ ፋይዳ ቢስ ውዝግብ ሊወጣ እንደሚገባ፤ ሌኒንም ከደሙ አንድ አራተኛው ብቻ ጁ እንደሆነ የገለፁ ሲሆን ይህንንም ከሚናፈሰው ጋር ምንም እንደማይገናኝና ማብራሪያቸውም ከጄኔቲክ (ዘረመል) አኳያ ብቻ እንደሆነ genetically speaking በማለት ነው ያብራሩት።
ጸሐፊው ይህን ካሉና ጭቅጭቁንም ከአንድ እድሜ የለሽ ነጠላ ዜማ (እሳቸው “fanfare” ነው ያሉት) ጋር ካወዳደሩ በኋላ፣ በማጠቃለያቸው ያሉት ነገር ቢኖር “ምንም ሆነ ምን ሌኒን ምንም ሊወጣለት የማይችል ሩሲያዊ ነው። “አይደለም” የሚሉት ወገኖች ያንን የሩሲያ ታላቅና ከፍተኛ የሽግግር ዘመንና ያስገኘውን ዓለምን ያስደመመ ታሪክ ለማቆሸሽ፤ ከሁሉም በላይ እችን የተባረከች አገር (Holy Russia) ለማፈራረስ፤ ህዝቡንም እርስ በእርሱ ለማጫረስ ነው። ይሁን እንጂ አይሳካላቸውም።” የሚለው ነው።
የእነዚህ ተማርን የሚሉ ፖለቲከኞች ዋና ዓላማ ሩሲያ የአንድ ብሄር የበላይነት የነገሰባትና የብሄረሰቦች እስር ቤት የሆነች አገር አድርጎ ለማቅረብ፤ የሩሲያ (ኦክቶበር 1917) አብዮትንም ሆነ አጠቃላይ እንቅስቃሴውንም የጁዎች (Judeo-Bolsheviks)፣ ለውጡም በሩሲያውያን የመጣ ለውጥ ሳይሆን በጁዎች የተገኘ አድርጎ ለመሳል፤ ሩሲያዊያን ጁዎችን እንደሚጠሏቸው አድርጎ ለማቅረብ የታሰበ ነው። እውነቱ ግን እሱ ይደለም። እውነቱ ራሺያ የበርካታ ብሄረሰቦች አገር መሆኗ (Russia was a multinational entity) ነው፤ እንደ ተመራማሪው ዳንኤል ስቴትስኪ መደምደሚያ።
እየሆነ ያለውም ሆነ የታሰበው የ(nihilism) አውዳሚነት (በተለይም የአገርና ህዝብ ህልውናን የማውደም (existential nihilism)፤ ወጣቱን ከማንነቱ የመንቀል (sunny nihilism)) ተግባር ነው፤ ይሁን እንጂ ይህ በዘላቂነት የሚሳካ አይደለም።
አጥኚው በጥናታቸው ከርእሰ ጉዳዩ ጋር ከተያያዙ በርካታ ሃሳቦችን አንስተው የሞገቱ ሲሆን በምክረ ሃሳቦቸውም ይህ አይነቱ የዘር ስሌት (racial calculation)ም ሆነ ዘርን መሰረት ያደረገ የፖለቲካ ቀመር ምንም አይነት ፋይዳ የሌለው መሆኑን “This, in my view, was, and remains, imprecise and unnecessary, unhelpful political hysterics.” ሲሉ ይገልፁታል። ለተለያዩ ተደጋጋፊና ተቃራኒ ሃሳቦች “Times of Israel” እና ሌሎችን መመልከት ይቻላል።)
የታሪክ ተመራማሪው አልበርት ሬሲስ የ20ኛ ክ/ዘ አቻ የለሽ የፖለቲካ መሪ መሆኑን “the century’s most significant political leader” በማለት የገለፁት፤ ድብን ያለ ማርክሲስት (devout Marxist)ና የስራዎቹ ተንታኝ መሆኑ የሚነገርለት፣ አራት ቋንቋዎች (ራሺኛ፣ ጀርመንኛ፣ ፈረንሳይኛና እንግሊዝኛ)ን ጠንቅቆ የሚያውቀው ሌኒን በፖለቲከኞች፣ ምሁራን፣ ገበሬዎች (ፒዛንትስ)፣ ሰራተኞች/ፕሮሌታሪያት ወዘተ ዘንድ ከሚታወቀው እኩል በወጣቱ ልብ ውስጥ ሰርስሮ በመግባት ልዩ ስፍራን ያገኘ ሲሆን ለዚህም ኦክቶበር 2/1920 ለወጣቱ ያደረገው ምድርን ያንቀጠቀጠ፣ ዓለምን ያናወጠ ንግግሩ ይጠቀስለታል።
(እኛም ጆሮ ያለው ይስማ፤ አይን ያለው ይመልከት፤ ህሊና ያለው ያገናዝብ …” በሚለው መሰረት ጉዳዩን ለጥቅስ አብቅተነዋልና ክፍለ ዘመናትን ወደ ኋላ መሄድና ጉንጭ ማልፋትም ሆነ የአሁኑ ዘመን ላይ ቆሞ “ዐብይ አማራ ነው/አይደለም” ማለት ህዝብን ከመናቅና ዋናውን ጉዳይ ትቶ በማይረባ አጀንዳ እንዲጠመድ ከማድረግ፣ በሃሳብ ድርቀት ከመመታት፣ ጊዜ ከማባከንና ውሃ ከመውቀጥ የተለየ አይደለምና ልክ እንደ ተመራማሪው ጉዳዩን “የማይረባ” ብለን ልናልፈው እንገደዳለን። “የማይረባ …”) የማይረባ መሆኑንም በተከበረው የቭላድሚር ኢሊች ሌኒን ፊርማ እናረጋግጣለን።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 19/2013