
አዲስ አበባ:- በምርጫ ቅድመ ዝግጅት ላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና መገናኛ ብዙሃን ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ገለልተኛ ሆነው ህዝቡን እንዲያገለግሉ አዲስ ትውልድ ፓርቲ ጥሪ አቀረበ።
የፓርቲው ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን ታፈሰ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፣ እስካሁን ያለው የሚዲያዎች እንቅስቃሴ መልካም የሚባል ነው። ሚዲያዎች ለሕዝብ ዓይን በመሆናቸው በዚህ ምርጫ ላይም ልዩ ትኩረት ሰጥተው በገለልተኝነት መሥራት ይጠበቅባቸዋል።
በተመሳሳይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምርጫው ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ሕዝባዊ ወገንተኝነታቸውን እንዲያሳዩ የጠየቁት አቶ ሰለሞን፤ በዘንድሮው የቅድመ ምርጫ ሂደት ላይ እየታዩ ያሉ እንቅስቃሴዎች በአንፃሩ ከባለፉት ምርጫዎች የተሻሉ ናቸው ብለዋል።
ከምርጫ ቅስቀሳ እና ደህንነት ጋር በተገናኘ ከዚህ ቀደም በደቡብ ኢትዮጵያ እና በሌሎችም አንዳንድ አካባቢዎች በመዘዋወር ምልከታ ማድረጋቸውን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፤ የሰላም ሁኔታ አሳሳቢ ቢሆንም ክብደቱ ግን በማህበራዊ ሚዲያ እንደሚናፈሰው እንዳልሆነ አስታውቀዋል።
“በምርጫው በንቃት እየተሳተፍን ነው። የምርጫ ቅስቀሳ በምናደርግበት ወቅትም ሕዝቡ ተመዝግቦ የመራጭነት ካርዱን በእጁ እንዲይዝ እየሰራን ነው። አስካሁን ባለው ሁኔታ “ሕዝቡ በሰላም እና በፍቅር ነው የተቀበለን፤ ምንም አይነት ችግር አልገጠመንም” ብለዋል።
የሱፍ እንድሪስ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 19/2013