
ወሊሶ፡-በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን 47 አርሶ አደሮች ወደኢንቨስትመንት መሸጋገራቸውን ዞኑ አስታወቀ። በገበታ ለሀገር መርሃግብር ተይዞ በመገንባት ላይ የሚገኘው የወንጪ ፕሮጀክትም ለዞኑ ዕድገት ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው ተጠቁሟል።
የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መገርሳ ድሪብሳ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት መንግሥት ለሀገር በቀል ኢኮኖሚ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ዞኑም የውስጥ አቅምን በአግባቡ ለመጠቀም ባደረገው ጥረትና ድጋፍ 47 አርሶአደሮች ወደ ኢንቨስትመንት መሸጋገራቸውን ገልፀዋል።
እነዚህ አርሶአደሮች የኢንቨስተርነትን ስም ብቻ የያዙ አይደሉም ያሉት አቶ መገርሳ፤ በተጨባጭ አቅማቸውን ያጎለበቱና ከራሳቸውም አልፈው ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዞኑ ውስጥ ከሚገኙ ወረዳዎች አብዛኞቹ በመስኖ ሥራ ተጨማሪ ምርት እንዲያመርቱ በማድረግ በዞኑ የግብርና ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር መደረጉንና በዚህም በርካታ አርሶ አደሮች መስኖን በመጠቀም የበጋ ስንዴና ልዩ ልዩ አትክልቶችን ማምረት መጀመራቸውንም አስተዳዳሪው ጠቁመዋል።
በሌላም በኩል ዞኑ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ መነቃቃት እየታበት ይገኛል ያሉት አቶ መገርሳ፤ በተለይ በገበታ ለሀገር የወንጪ ልማት ፕሮጀክት በዚህ ዞን ተግባራዊ ሊሆን መቃረቡ የአብዛኛውን የአካባቢው ነዋሪ ተስፋ ያለመለመ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ወንጪ በተፈጥሮ የተገኘ፣ በተራሮች የተከበበ እና ሰፊ የቱሪስት መስህብ አቅም ያለው ሐይቅ ነው ያሉት አቶ መገርሳ፤ የአካባቢው ህብረተሰቡ ሐይቁን ልክ እንደራሱ ንብረት ሲጠብቅና ሲንከባከብ መቆየቱን አስታውሰዋል።
የወንጪ አካባቢ ከመልማቱ በፊትም ጀምሮ ከአፍሪካም ሆነ ከአውሮፓ እንዲሁም ከሌሎች የዓለም ክፍሎች የሚመጡ ቱሪስቶችን ሲያስተናግድ እንደነበር እና በቀጣም የወንጪ አገራዊ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ የበለጠ ጎብኚ እና ልማት ያመጣል ተብሎ እንደሚታመንም ጠቁመዋል።
አቶ መገርሳ እንደገለፁት፤ ቀደም ሲል የወንጪ ኢኮቱሪዝም በሚል ማህበረሰቡ ተደራጅቶ 365 ሰዎች ሥራ አግኝተውበታል። አርሶ አደሮች እና የአርሶ አደር ልጆች ቱሪስቶችን በማመላለስ፣ የቱር ጋይድ እና የጀልባ አገልግሎት በመስጠት የራሳቸውን ገቢ ለማሳደግ ሲጠቀሙበት ነበር። አሁን በሐይቁ ላይ የተጀመረው ልማትም ሥራቸውን የበለጠ ስለሚያሳድግላቸው በተስፋ እየተጠባበቁ ይገኛሉ።
እንደ አቶ መገርሳ ገለፃ፤ የወንጪ ፕሮጀክትን ለየት የሚያደርገው ህብረተሰቡን የሚያፈናቅል ሳይሆን ሁሉንም አሳታፊ ባደረገ መልኩ ተገንብቶ ለአገልግሎት የሚበቃ በመሆኑ በደስታ ተቀብለውታል። ከዚህም በተጨማሪ የመሰረተ ልማት ጥያቄያቸውንም የሚፈታ ስለሆነ ደስተኛ ናቸው። ቱሪስት ወደቦታው ሲመጣ ተሽከርካሪ አቁሞ ረጅም እርቀት በፈረስ ነበር የሚጓዘው። አሁን ግን መንግሥት እስከ ሐይቁ ድረስ መንገድ እንዲገባ ለማድረግ ግንባታውን ለኮንትራክተሮች ሰጥቷል።
ከዚህ በተጨማሪ ከፕሮጀክቱ ጋር ተያይዞ የመብራት፤ የጤና፤ የቴሌኮም እና ሌሎች ልማቶች እንደሚሻሻሉለት ህረተሰቡ ተገንዝቧል ያሉት አቶ መገርሳ፤ ሐይቁን በማይረብሽ ሁኔታ ዙሪያው የሚለማበት ሁኔታ አለና ህዝቡ በሥራ ዕድሉም ሆነ ገቢውን በማሳደግ ረገድ ሰፊ ዕድል ይዟል ብለዋል። ወንጪ በመሰረቱ ከማዕድን ውሃ አንስቶ ለጀልባ ጉዞ እና የደሴት ጉብኝት የተመቸ ብዙ ድብቅ ሀብቶችን የያዘ እንደሆነም አብራርተዋል።
ወንጪ ፕሮጀክት ከአምራች ኢንዱስትሪ ጋር በተያያዘም ከቀርከሃ የሚሰሩ ምርቶችን በማቅረብ የተለያዩ የእጅ ሥራዎችን ለገበያ በማቅረብ ረገድ ትልቅ የምርት ማቅረቢያ ቦታ ሆኖ እንደሚያገለግልም አቶ መገርሳ ጠቁመዋል። የአካባቢው ህዝብ ሥራ የማይንቅ እና ታታሪ ከመሆኑ ጋር ተያይዞም ከወንጪ ፕሮጀክት ጋር ተያይዞ ትልቁን ዕድል ለመጠቀም ይችላል ብለዋል።
እንደ አቶ መገርሳ ማብራሪያ፤ በዞኑ የሚገኙትን ከሰበታ ጀምሮ እስከ ወንጪ ድረስ ያሉ ከተሞች ከቱሪስት ጋር በተያያዘ የእራሳቸውን ገበያ በመፍጠር ረገድ ይጠቀማሉ ተብሎ ይታሰባል። ደንዲን እና ወንጪ ሐይቆችን የሚያገናኘው የ12 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር መንገድ በዚሁ ፕሮጀክት ሥር ይገነባል።
ቱሪስቶች ሁለት አማራጭ መንገዶችን ሊጠቀሙ ይችላሉ ያሉት አቶ መገርሳ፤ አንድም በአምቦ በኩል ደንዲን ዞሮ ወንጪንም ሊያይ ይችላል፤ አልያም በወሊሶ በኩል አድርጎ ቀጥታ ወደ ወንጪ ሊጓዝ ይችላል ብለዋል።
ወርቁ ማሩ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 19/2013