ከሀገራችን ወላጆች በእማሆይ ዘውዲቱ ውድነህ የተተረከውን ተረት አንብቡልኝ።
አንድ አባት ሶስት ልጆች ነበሩት። ልጆቹንም ሰብስቦ “እኔ አሁን አርጅቻለሁና ሞቴን የምጠብቅ ሰው ነኝ። አሁን የምነግራችሁን ነገር እኔ እንዳልኳችሁ መፈፀም አለባችሁ። ትዕዛዜንም አክብሩ። አላቸው። ልጆቹም በሃሳቡ ተስማሙ።
ከዚያም እነርሱ ሳያውቁ ሶስት ሳጥኖች አምጥቶ በአንድ ሳጥን ውስጥ ገንዘብ አስቀምጦ አሸገው። በሁለተኛውም ውስጥ አፈር ጨምሮ አሸገው። በሶስተኛው ሳጥን ውስጥ ደግሞ ወርቅ አስቀምጦ አሸገው። ይህንን ሁሉ ያደርግ የነበረው ልጆቹ ሳያዩት ነበር።
ሶስቱንም ሳጥኖች ካሸጋቸው በኋላ በሞተ ጊዜ ቀብሩ ከተከናወነ በኋላ አዛውንቶች ተሰባስበው ስለኑዛዜው መወያየት ጀመሩ። ሰውየውም የሶስቱን ልጆች ስም በሳጥኖቹ ላይ ፅፎ ስለነበረ እያንዳንዳቸው ሳጥኖቹን በየስማቸው ከወሰዱ በኋላ ሳጥኑ ውስጥ ያገኙትን ነገር ሲያዩ ተገርመው ነበር።
“ለምንድነው ይህንን ያደረገው? በርግጥ አትቃወሙ ብሎን ስለነበረ መቃወም አንችልም።” ከዚያም ወደ አንድ ብልህ ሰው ዘንድ ለመሄድ ወስነው ሲጓዙ በመንገዳቸው ላይ ከአንድ ወንዝ አጠገብ አንድ አዞ ጤዛ ሲልስ አይተው ተገረሙ።
“ይህ ምን ማለት ነው?” ብለው መንገዳቸውን ቀጠሉ። ከዚያም በጣም ለምለም ከሆነ መስክ አጠገብ ደረሱ። በለምለሙም መስክ ላይ ያልተለጎመና ሳር መብላት የሚችል ግን በጣም የከሳ ፈረስ አዩ። በዚህም ተገርመው “የሚደንቅ ነው። ይህ ፈረስ ይህንን የመሰለ ለምለም ሳር ከፊቱ እያለ እንዴት ሊከሳ ቻለ?” ብለው አሁንም መንገዳቸውን ቀጠሉ።
ለሶስተኛም ጊዜ ከአንድ ጠፍ ወይም ደረቅ መሬት ሲደርሱ አንድ ግዙፍ ወፍራም አህያ አይተው በሁኔታው በመገረም “ይህ ምን ማለት ነው? ጤዛ የሚልስ አዞ፣ ከሲታ ፈረስ በለምለም መስክ ላይ፣ ወፍራም አህያ በደረቅ መሬት ላይ፤ ይህ ለእኛ የተላከ እንቆቅልሽ ነው።” አሉ።
በመጨረሻም ወደ አዋቂው (አስማተኛውና)
የሰዎችን ችግር ከሚፈታ ሰው ዘንድ ደረሱ። አዋቂውም ሰው “ችግራችሁ ምንድነው?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም “እነሆ አባታችን ተናዞልን ነበር። ለአንደኛችን ገንዘብ፣ ለአንደኛችን አፈር፣ ለአንደኛችን ደግሞ ወርቅ ተናዞልን ሞተ። ከመሞቱም በፊት እንዳንጣላ ቃል አስገብቶን ስለነበረ አልተጣላንም። ለዚህ ነው ወደዚህ የመጣነው።” አሉት።
አዋቂውም ሰው “ሄዳችሁ ታላቅ ወንድሜን አግኙት።” አላቸው። እነርሱም የመጀመሪያው አዋቂ ሰው እጅግ በጣም ያረጀ ስለነበረ ታላቅ ወንድም እንዳለው ሲያወቁ ተገረሙ። ወደ ታላቅየውም ሰው ዘንድ ሄደው ችግራቸውን ነገሩት። ታላቅ ወንድሙ ግን የመሃከለኛ እድሜ ጎልማሳ ስለነበረ ተገረሙ። ታናሽ ወንድሙ የጎበጠና በከዘራ የሚሄድ ሰው ነበር።
እርሱም “ይህንን እኔ መፍታት አልችልምና ሄዳችሁ ታላቅ ወንድሜን አማክሩት።” አላቸው። እነርሱም ወደ ታላቅ ወንድማቸው ሲሄዱ ያርስ የነበረ በጣም ወጣት ሰው ሆኖ አገኙት። “ይህ ተዓምር ነው።” አሉ። በጣም ተገረሙም።
እርሱም ወደቤቱ ወስዷቸው ምግብ እንዲበሉ፣ ሰውየው ሚስቱ ምግብ እንድታቀርብ አዘዛት። በባህሉ መሰረት ስጋ የሚበላው መጨረሻ ላይ ነው። መጀመሪያ የሚበላው መረቅ በእንጀራ ነው። አጥንቱ የሚበላውበመጨረሻ ላይ ነው።
ሰውየው ግን ተቃራኒውን ነው ያደረገው። መጨረሻ መብላት ያለበትን አጥንት መጀመሪያ ከበላ በኋላ መጨረሻ ላይ መረቁን መጠጣት ጀመረ።
በመጨረሻም “ተመስገን!” አለ። “እንዴት እንደበላሁ አያችሁ?” አላቸው።
እነርሱም “አዎ” አሉት።
ሰውየውም እንደገና “አጥንቶቹን በሙሉ ከመረቁ በፊት በላሁ። ይህም የእኛ ባህል አይደለም። አይታችኋል?” አላቸው።
እነርሱም “አዎ” ሲሉት “ለምን እንደዚያ እንዳደረኩ ታውቃላችሁ?” ብሎ ሲጠይቃቸው “አናውቅም።” አሉት።
እርሱም “ምክንያቱም እግዚአብሔር ወደ እናንተ መቼ እንደሚመጣ ማለትም መቼ እንደምትሞቱ አታውቁም። ይህንን ማንም አያውቅም። ስለዚህ በቅድሚያ አጥንቱን በላሁ። የምንኖረው አጭር ጊዜ ሲሆን መሞቻችንን በፍፁም አናውቅም። የእግዚአብሔርን መምጫ ማንም አያውቅም። ነፍሳችንንም መቼ እንደሚወስዳት አናውቅምና በመጀመሪያ ምርጡን ነገር በላሁ። ድንገት ቢመጣስ ብዬ ስለሰጋሁ ነው።
ነፍሴን አንዴ ከወሰዳት መልሼ አላገኛትም። እኛ ሰዎች ወዲህ ወዲያ ስንባዝንና ብዙ ስናስብ እንውላለን፣ ውሳኔው ግን የእግዚአብሔር ነው። ምንም ያህል ብንለፋ፣ የህይወታችንን ምርጫ ለማሟላት ምንም ያህል ብንጥር በመጨረሻ የሚሆነው የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው።” ብሎ ነገራቸው።
ከዚያም ለምን ወደ እርሱ እንደመጡ ሲጠይቃቸው ነገሩት። ጉዳያቸውን እንደገና ሲተርኩለት ከሰማ በኋላ አዋቂው ሰው “አባታችሁ ጥሩ ኑዛዜ ነው የተወላችሁ። “አንተ” ብሎ ወደ አንደኛው እየጠቆመ “ያንተ ዕጣ ፈንታ ግብርና ነው። ስለዚህ ነው አባትህ አፈር (መሬት) የሰጠህ። “አንተ ደግሞ” አለ ወደ ባለ ወርቁ እያመላከተ “አንተ ዕጣ ክፍልህ ንግድ ነው። ወርቅ የተሰጠህም ለዚህ ነው። “አንተ ሶስተኛው ደግሞ የከብቶች መንጋ ማርባት እድልህ ነው። ለዚህ ነው ከብቶች እንድትገዛ ገንዘብ የተወልህ። ከዚህ በተጨማሪ ሁላችሁም ገንዘብ እንደምታገኙ አመላክቷችኋል።” አላቸው።
እነርሱም “እንዴት?” አሉት።
“አሁን ዝም ብላችሁ ወደመንደራችሁ ተመለሱና በኋላ ይገባችኋል።” ሲላቸው ተነስተው ሄዱ።
ድርሻቸውንም ወሰዱ፤ አንደኛው ከብቶች ገዛ፣ አንደኛው መሬት፣ ሶስተኛውም ወርቁን ወሰደ። ባለከብቱ ከብቶቹን የሚያበላቸው የግጦሽ መሬት ስላልነበረው ሌላኛውን ወንድሙን ጠየቀ።
ወንድሙም “አይሆንም! መሬቱ የእኔ ነው። አንተ ከብቶች ስላሉህ መሬት እንድሰጥህ ከፈለክ የተወሰኑ ከብቶች ስጠኝ።” አለው።
ባለከብቱም የተወሰኑ ከብቶች ለወንድሙ ሰጥቶት መሬቱን አገኘ። ነጋዴውም ንግዱን አካሂዶ ገንዘብ አገኘ። ሆኖም ቤት መስሪያ ቦታ ስላልነበረው ወደ ወንድሙ ዘንድ ሄዶ ሲጠይቀው ወንድሙም “አባቴ ለእኔ መሬት ሲሰጠኝ ለአንተ ገንዘብ ሰጥቶሃል። እኔ ግን ገንዘብ የለኝም።” አለው።
ነጋዴውም ለወንድሙ ገንዘብ ሰጥቶት ገበሬው ወንድሙ መሬት ስለሰጠው ተስማሙ።
ከሁሉ በጣም ተጎድቶ የነበረው ልጅ አፈር (መሬት) ያገኘው ልጅ ነበር። ከብቶች ያገኘው ከብቶቹን መሸጥ ይችላል። ሌላኛውም ወርቅ ነበረው። ሶስተኛው ግን መሬት ብቻ ስለነበረው ተበድሎ ነበር። ነገር ግን ገንዘቡንና ከብቶቹን ከወንድሞቹ አገኘ። በዚህ ዓይነት ሶስቱም የሚፈልጉትን አግኝተው በሰላም መኖር ጀመሩ። ተረቴን መልሱ አፌን በዳቦ አብሱ።
ከአስርቱ ትእዛዛትም አንደኛው “አባትህን አክብር” የሚል ነው። ድሮ ልጆች መልካም ነበሩ። የወላጆቻቸውን ምክር የሚሰሙና በፍፁም የማይጣሉ ስለነበረ በደስታ ይኖሩ ነበር። አሁን ግን ሰዎች እርስ በርሳቸው አይስማሙም፣ በራሳቸውም ላይ መዓት ያመጣሉ። ስለሆነም ልጆች ሰላም ወዳድ ሁኑ እሽ፣ ቻው።
ምንጭ፡- የኢትዮጵያ ተረቶች ስብስብ ድረገፅ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17/2013