ኃይለማርያም ወንድሙ
መጋቢት 30 ቀን በእንጦጦ ፓርክ የኢትዮጵያ የኪነጥበብ ባለሙያዎች የእውቅና መርሐግብር ተካሂዷል።በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተገኝተው ለአንጋፋ የጥበብ ሰዎች የክብር ሜዳይ ሰጥተዋል። በአጠቃላይ 157 የኪነጥበብ ሰዎች ተሸላሚዎች የነበሩ ሲሆን፣ በዚህም አንጋፋ የቴአትርና የፊልም ባለሙያዎች ፣ ደራሲያን፣ የሙዚቃ ባለሙያዎች እና 29 አንጋፋ ሰዐሊያን ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
የዛሬው ትኩረታችን ወደ ስዕሉ ነው።አቶ አገኘሁ አዳነ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአለ የስነጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ናቸው።እሳቸው እንዳሉት፤ ትምህርት ቤቱ ከተቆረቆረበት ከ1950 ጀምሮ በ1951 በትንሽ ቤት አለፈለገ ሰላም በሚል ስያሜ አንድ ቦታ በሁለት የትምህርት ዓይነት ተማሪዎችን እያስተማረ ያስመርቅ ነበር። ዛሬ ላይ ሰባት የትምህርት ፕሮግራሞች አሉት።
ትምህርት ቤቱ ብዙ መምህራንን አፍርቷል፤እነዛም ተተኪ ሙያተኞችን እያፈሩ የነሱን ፈለግ እየተከተሉ ሰርኩሌት (ዑደት) እያደረገ በታሪክ ቅብብሎሽ ላይ የበኩሉን አስተዋፅኦ አድርጓል ሲሉ አቶ አገኘሁ ይናገራሉ።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ በስነጥበብ በቀረው ዓለም ከዚህ ትምህርት ቤት የተመረቁ ሰዐሊያን ወይም የጥበብ ሰዎች በጀርመን፣ በኦስትርያ፣ በፈረንሳይ፣ በስፔንና በአሜሪካ በጣም ስምና ዝና ያላቸው በዓለም የስነጥበብ እንቅስቃሴ ውስጥ የራሳቸው ጉልህ ድምፅና ተቀባይነት ያላቸው ሰዐሊያን አሉ።
በተለይ ሰለጠነ በሚባለው ዓለም በሙያ መሥራት እጅግ ከባድ ነው የሚሉት አቶ አገኘሁ፣ ታዳጊ አገር ሄዶ የህክምና ሙያተኛ እንኳን ሆኖ በህክምና ሙያ ለመስራት በጣም እንደሚያስቸግር ይገልጻሉ።ߵ ከዚህ የተመረቁ የኛ ትልልቅ ሰዐሊያን ሀገራቸውን የሚያስጠሩ በሙያቸው የተመሰገኑ ለዓለም ስነጥበብ የራሳቸውን ግብአትና አስተዋፅኦ ማድረግ የቻሉ ሰዐሊያን አሉ ሲሉ ያብራራሉ።
እነ ወሰኔ ኮሶሮፍ ፣ፕሮፌሰር አቻምየለህ ደበላ፣ ከበደች ተክለአብ፣ ተገኔ ኩንቢ፣ እንግዳጌጥ ለገሰ ከእነዚህ መካከል ይጠቀሳሉ ይላሉ።በጣም ትልልቅ ሰዐሊያን እነ ደረጀ ደምሴ በሌላ ዓለም ተበትነው ግን ትርጉም ያለው ሥራ ይዘው ወደፊት የወጡ ብዙ ሰዐሊያን አሉ፡፡እነዚህ ሰዐሊያን መቀመጫቸው በሌላው ዓለም ሆኖ ይሄንን ውጤት ያመጡ ናቸው፡፡ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
ዳይሬክተሩ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያም ሆነው ከወጣት እስከ ትልቅ ዓለም አቀፍ ሰዐሊያን፤ ሌላው ዓለም የበለጠ የሚገነዘባቸው እስኪመስል ድረስ የስነጥበቡ ዓለም ሰዎች ውጪ በጣም ይጓዛሉ፤ የተለያየ ዐውደ ርዕይ ያሳያሉ።የሀገራቸውን ፍልስፍና፣ አስተምህሮ፣ ባህል፣እምነት፣ መልክ ይዘው በቀረው ዓለም ይንቀሳቀሳሉ።ለምሳሌ ከነዚህ መካከል እነ ዳዊት አበበ ፣ ሄኖክ መልካም ዘር፣ በቀለ መኮንን ፣በኃይሉ በዛብህ ጥበበ ተርፋ፣ ወርቁ ጎሹ፣ ዘሪሁን የትምጌታ በጣም ዓለም አቀፍ ሰዐሊያን ናቸው።እነዚህ በሙሉ የዚህ ትምህርት ቤት ውጤት ናቸው ሲሉ በኩራት ይናገራሉ፡፡
ሀገራችን የዕይታዊ ጥበብ ባህል የረጅም ዘመን ታሪክ አላት።በስዕል የጎንደርን ጥንታዊ ቤተ እምነቶች በጣም አስደናቂ የቀለም ቅብ ሥራዎች የተሞሉ ናቸው ፤የሰሜን ጥንታዊ ሀውልቶች ከአክሱም ላሊበላ ጀምሮ እነዚህ የዕይታዊ ጥበብ ባህላዊ ውጤቶቻችን ናቸው፡፡ረጅም የስነጽሁፍና ስነጥበብ የስነስዕል ታሪክ አለን ሲሉ ያስረዳሉ።
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ ከዚህ በፊት ያልነበሩ የትምህርት ክፍሎች እየበዙ ነው። በጌጣ ጌጥ ዲዛይን በዘመናዊ ደግሞ ሳይንስ የዲጂታል ፋብሪኬሽን ዩኒት አለ፤ ይሄም ሳይንስንና አርትን አጋብቶ ለመሥራት ታስቦ የተቋቋመ ስቱዲዮ ወይም ዩኒት ነው።
በጌጣ ጌጥ ዲዛይን ረጅም ታሪክ አለን ፡፡ግን በባህላዊ መንገድ እዛው ዳዴ ሲል ነው የሚገኘው።ስለዚህ ኢማጅኔሽን (ዐይነ ህሊና) እና ኤክስፐርመንቴሽን ተጨምሮበት ከፍ ወዳለ ደረጃ እንዲደርስ አሁን በማቋቋም ፤ ትምህርት መስጠትም ጀምረናል ይላሉ ፡፡በዚህም ሀገራችን ነባሩን ሀብቷንና ባህሏን በማደራጀት በሳይንሳዊ መንገድ በመዋቀር በመመርመርና ወደፊትና ወደ ዋናው ዐውድ በማምጣት የተገፋውን ባህላዊ ብለን የናቅነውን ወደ ማዕከል በማምጣት ነባሩን ሀብታችንን ማበልፀግ መገልገል እና ከፍ ያለ ደረጃ ላይ የማምጣት ሥራ እየተሠራ ነው፡፡
ያጋጠማችሁ ተግዳሮት ብለን ጠይቀናቸውም ሲመልሱ እኛ ከችግር ውጪ አይደለንም ሀገሪቱ ታዳጊ ናት ፤በምጣኔ ሀብት ዝቅ ያለች።ሁሉም ተቋማት ጋር ብትሄድ ይሄ ጎደለኝ ማለቱ አይቀርም ፤ እየቻሉ መሥራት እንጂ የሌለንን ብንቆጥር ማለቂያ የለውም፤ ግን ትኩረት ማድረግ ያለብን ያለን ላይ እጃችን ላይ ባለው ሀብት ተጠቅሞ ውጤት ማምጣት ላይ ይሻላል ብለዋል፡፡
ስለ ተቋሙና ሃይማኖታዊ ጥንታዊ ስዕሎች ሲያብራሩም ትምህርት ቤቱ ሃይማኖታዊ ስዕል የምናስተምርበት ተቋም አይደለም፡፡ይሁንና የአሳሳል ፈሊጡና ፍልስፍናው ላይ አተኩረን ተማሪዎቹ እንዲያውቁት እናደርጋለን ይላሉ።የራሱ የአሳሳል አስተምህሮና ፍልስፍና አለው።ያንን ዲስከርሲቭ የሆነ ሀቲታዊ ጉዳይ አወካከል አመሳሰል ቀለም አጠቃቀም እንዲሁም ቴክኒካዊ የሆነውን ክፍል በዚህ ዘመን እንዲሳል ነበር፤ያኛው ተለውጦ እዚህ ደረሰ እያልን እናስተምራለን።…ሰዐሊያኑ ከእነዚህ ነባር የአሳሳል ፈሊጦቻችን የሳባቸውን ይጠቅመኛል ያሉትን መርጠው ማለቂያ የለውም ብዙ ሀብት ነው ያለን።ከዘመናዊው ጋር እያቀላቀሉ እንደ ሰዐሊው ፍላጎትና ዝንባሌ ይጠቀሙባቸዋል ይላሉ፡፡
ነባሩንና አዲሱን እያጋጩ አዲስ ስነጥበባዊ ጣዕም መዐዛ ለመስጠትና ለማምጣት ጥረት በማድረግ ረገድ ዘሪሁን የትምጌታ እስክንድር ቦጎሲያ ከቤተክርስቲያን ነባር አሳሳሎች ከአፍሪካ ሜቶሎጂ ኤለመንቶች ወስደው ከዘመናዊ ስዕል ጋር አዋህደው አዲስ ቃና ፈጥረው በዓለም ላይ ዝነኛ ሰዐሊ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ።ወርቁ ጎሹም እንደዚህ ናቸው ።በዚህም የራሱ ኢትዮጵያዊ መልክና ቃና ባለው የዓለም የስነጥበብ መድረከ ላይ ስምና ዝና ያገኙበት መንገድ ነው ብለዋል ።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የስዕል ትምህርት ለመስጠት ሙከራ እየተደረገ ነው።በተደራጀ ስፋትና ይዘት ባይሆንም ፤ በእንጦጦ ቴክኒክና ሙያም የስዕል ትምህርት ጉዳይ ሆኖ መሰጠት ከጀመረ ወደ አስር ዓመት ይጠጋዋል።እንደዚህ ሙከራዎች አሉ በግልም እንደዚሁ፤ነገር ግን ሀገሪቱ የብዙ ባህል ቋንቋ ብሄር ሃይማኖት ባለቤት እንደመሆኗ ሊታይ ሊመረመር የሚገባው ብዙ ሀብት አለ፡፡
የስነጥበብ ትምህርቶች ሰብዓዊ ልማት ለማምጣት በጣም መሠረቶች ናቸው፡፡ሌላው የምታየውን መልክና ቁመና የያዘው ገናናነት ያገኘው የስነጥበብ ትምህርት ጉዳይ ከልጅነት ጀምሮ ስለሠራ ነው።የሰው ልጅ አእምሮ የሚለማው በእነዚህ የስነጥበብ ዘርፎች አማካይነት ነው።በልጅነት የስነጥበብ ትምህርት ያልተማረ ማኅበረሰብ አይለማም ፤አይሰማም።ይሄንን ለማምጣት የትምህርት ተቋማት በጣም መሠረቶች ናቸው።ስለዚህ ታስቦበት ታቅዶ ሊሠራበት የሚገባ ትልቅ ክፍተታችን ነው በማለት ይገልጻሉ።
ዶ/ር ዐቢይ ይሄን ት/ቤት ጎብኝተዋል።በጣም ትልቅ ዜና ነበር።መጥተው ጋርደኑን እሳቸው ናቸው ያሠሩት።ት/ቤቱ አሁን ጥሩ ነው ውብ ሆኗል።እንጦጦ ጋለሪ ላይ ዓለምአቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሠርተው ሰጥተውናል።ይሄ ትልቅ ዕድል ነው።በቀን እስከ 6ሺ ሰው እናስተናግዳለን ስዕል የሚያይ ግፊያ ያለበት።ግፊያውን አልቻልነውም።ሰዉ ያያል ፤አጥቶ ነው እንጂ።እንደዚህ ዓይነት ተቋማት ብታደራጅለት ብትከፍትለት ሰዉ እኮ ለካ ለስዕል ትልቅ ፍላጎት አለው።ሄዳችሁ ብታዩት ትደነቃላችሁ።ስለዚህ ባህሉ ያድጋል፤ ይመጣል ይለወጣልም፡፡ሁሉ ነገር ጥሩ ይሆናል ብለዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17/2013