ዳግም ከበደ
የዛሬው የዝነኞች የእረፍት ውሎ እንግዳችን አቶ ኤርሚያስ አየለ ይባላል፤ የታላቁ ሩጫ ስራ አስኪያጅ ነው። ላለፉት በርካታ ዓመታት ተወዳጁን የጎዳና ላይ ሩጫ በብቃት እንዲካሄድ የራሱን ድርሻ ተወጥቷል። የዝግጅት ክፍላችንም በእነዚህና በመሰል ጉዳዮች ላይ ጥቂት ጭውውት አድርጓል። መልካም ንባብ!
ወደ ህልም ጉዞ
የኤርሚያስ አስተዳደግ ከስፖርት ጋር ትስስር አለው። አካባቢው ጃንሜዳ እንደመሆኑ መጠን ስፖርታዊ ጨዋታዎች ከጓደኞቹ ጋር የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዎቹ ነበሩ። በተለይ እግር ኳስ ያዘወትር ነበር። ይህ የልጅነት ልምዱ ትምህርቱን ጨርሶ በስራ ላይ እያለም ሙሉ ለሙሉ አልተቋረጠም ነበር። ጤንነቱን ለመጠበቅም ሆነ እግረ መንገዱን ለመዝናናት በአጋጣሚ በሚያገኛቸው ስፖርታዊ ዝግጅቶች ላይ ይሳተፍ ነበር። ከዚህ ውስጥ የታላቁ ሩጫ ይጠቀሳል።
እንደ አጋጣሚ ሆኖ የታላቁ ሩጫ አዘጋጆች በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ አንድ ማስታወቂያ አወጡ። ዝግጅቱን በተለያየ መንገድ የሚያስተናብሩ ሰዎች ይፈለጉ ነበር። የአትሌት ሻለቃ ሀይሌ ገበረስላሴ አድናቂ የሆነው ኤርሚያስ ይሄ እድል እንዲያልፈው አልፈለገም። በማስታወቂያው መሰረት በትርፍ ጊዜው በጎ ፍቃደኛ ለመሆን ተወዳደረና አለፈ። በአስተባባሪነት 4ኛውን መርሀ ግብር ከቡድን አጋሮቹ ጋር በስኬት አጠናቀቀ።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነበር ኤርሚያስ የታላቁ ሩጫ አዘጋጅ ቡድን አባልነትን የተቀላቀለው። በ1997 ዓ.ም አስረኛው የማንችስተር የጎዳና ሩጫ በእንግሊዝ አገር ይካሄድ ነበር። በውድድሩ ላይ አትሌት ሻለቃ ሀይሌ ገብረስላሴም ተሳታፊ ነበር። ኤርሚያስም በማንችስተሩ ዝግጅት ላይ የመሳተፍ አጋጣሚውን አገኘ።
በርካታ ሺ ሰዎችን የሚያሳትፉት ይህን አይነት የጎዳና ላይ ሩጫዎች በጥንቃቄ እና በከፍተኛ ወጪ የሚዘጋጁ ናቸው። እሱም በማንችስተሩ የጎዳና ላይ ውድድር
ተገኝቶ የተመለከተውም ይሄንኑ ነው። ከአዘጋጅ ቡድኖቹ በርከት ያሉ ልምዶችን ተመልክቶ ወደ አገሩ መጣ። ወደ አገሩ እንደተመለሰ የማርኬቲንግ ማኔጀርነት ቦታውን ይዞ እንዲሰራ ተመደበ።
ውድድሮችን የማስተባበር ወይም «event organize» የማድረግ ፍላጎቱ ስለነበረው ከቡድን አጋሮቹ ጋር በማርኬቲንግ ማኔጅመንት መስራት ጀመረ። ለሶስት አመታት በዚህ ስራ ቆየ። ኤርሚያስ ፈጣን የመግባባት አቅም፣ የጎዳና ላይ ሩጫን የማሰናዳት ልምዱ ከጊዜ ወደ ጊዜ በይበልጥ እየጎለበተ እና እያደገ መጣ።
በዚህ ላይ ደግሞ በ2000 ዓ.ም በስፖርት እና ሌዤር ማኔጅመንት በእንግሊዝ አገር የትምህርት እድል አግኝቶ ለሁለት አመታት ተከታተለ። ይህ ሂደትም የኢትዮጵያ ታላቁ ሩጫን እስከ ስራ አስኪያጅነት እንዲመራ አስችሎታል።
አቶ ኤርሚያስ በቡድን ስራ ያምናል። «ሃላፊነትን የሚጋራ ባለሙያ አብሮህ ካለ የምታዘጋጀው መሰናዶ ጥራቱ የተጠበቀ ይሆናል» ይላል። ታላቁ ሩጫ በየጊዜው በዝግጅት የላቀ ውጤት እንዲያመጣ የተለያየ እውቀት ያላቸው ባለሙያዎችን አንድ ሆነው የሚሰሩበትን መንገድ መመቻቸት መቻሉ የስኬቱ ቁልፍ ሚስጢር ነው።
የአቶ ኤርሚያስ ስፖርታዊ ተሳትፎ በታላቁ ሩጫ ላይ ብቻ የተገደበ አልነበረም። ለዓመታት በኢትዮጵያ ሞተር ስፖርት ማህበር ላይ የቦርድ ፕሬዚዳንት በመሆን ማህበሩ ተሳትፎው በኢትዮጵያ ስፖርት ላይ የጎላ እንዲሆን ጥረት አድርጓል። በዚህ ማህበር ላይ ተሳታፊ እንዲሆን እና ውድድሩ ላይ ልክ እንደ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጣ በሚል ነበር በአባላቱ ፍላጎት ተመረጠው።
አዝናኝ አጋጣሚ
ታላቁ ሩጫ በባህሪው አዝናኝ ትእይንቶች ይስተዋሉበታል። ኤርሚያስም ከማዘጋጀት ባለፈ የዚህ ቀጥተኛ ተሳታፊ ሆኖ ያውቃል። በውድድሩ ላይ የነበሩ ተሳታፊዎች እሱን እሽኮኮ አድርገው በሙዚቃ ጨፍረዋል። በነሱ ምክንያት መንገድ ለተወሰነ ጊዜ ቢዘጋም በጎዳናዎች ላይ የውድድሩን ዋና ስራ አስኪያጅ
አንከብክበው ወደ ላይ ከፍ በማድረግ ጭፈራውን አቅልጠውት ነበር። ለኤርሚያስ ይህቺ ቀን የማትረሳ ነች። እነሱም ይህን መሰል ውድድር በሚያምር ድባብ ከቡድን አጋሮቹ ጋር ማሰናዳቱ አዝናንቷቸው ምስጋና ለማቅረብ ያደረጉት ትእይንት ይመስላል።
ማህበራዊ ድረ- ገፅን ለመልካም
ኤርሚያስ በስራ አስኪያጅነት ከሚመራው የኢትዮጵያ ታላቁ ሩጫ ውጪ የማህበረሰብ ለውጥ ያመጣሉ ብሎ በሚያምንባቸው የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ይሳተፋል። ከዚህ ውስጥ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ስፖርትን ለሰላም እንዲሁም ለጤንነት ልንጠቀምበት ይገባል ሲል መልክት ያስተላልፋል።
በተለይ የስኬት ምንጭ
አቶ ኤርሚያስ «ለስኬቶቼ ቤተሰቤ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል›› ይላል። ባለቤቱ ለስራው ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ የተለያዩ ጫናዎችን ትቀንስለታለች። ውድድሮችን ማሰናዳት ከሚፈጥረው ውጥረት አንፃር ቤተሰቡ ከጎኑ መኖሩ እጅጉን እንደጠቀመው ይናገራል። ከዚህ ሌላ አትሌት ሻለቃ ሀይሌ ገብረስላሴ እንደ ታላቁ ሩጫ መስራችነቱ እና የቦርድ ዳይሬክተርነቱ ለስኬቱ ትልቅ
ድርሻ እንዳለው ይገልፃል። ሁሉም ተባብሮ በቀናነት መስራቱም ለዝግጅቱ እና በግሉ ለደረሰበት ስኬት ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል ይላል።
የእረፍት ጊዜ ውሎ
አቶ ኤርሚያስ ስፖርትና የእረፍት ጊዜው በእጅጉ የተገናኙ ናቸው። ደስታና ጤንነቱ ከስፖርት ጋር የተቆራኙ ናቸው። በትርፍ ጊዜው ተራሮችን መውጣት “ሃይኪንግ” ይወዳል። በቡድን ከጓደኞቹና ባልደረቦቹ ጋር የእግር ጉዞ እንቅስቃሴ ያደርጋል። ከዚያ በተረፈ የሚወዳቸውን መፅሃፍት በማንበብ ከቤተሰቡ ጋር በመጨዋወት ማሳለፍ ምርጫው ነው። ቀለል ያሉ ስፖርታዊ ትጥቆችንና አልባሳትን በነዚህ የእረፍት ቀናቱ ማድረግም ይወዳል።
ኤርሚያስ ወጣቶች የእረፍት ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙበትና ጤንነታቸውን እንዲጠብቁበት ይፈልጋል። ሁሉም ሰው የሚዝናናበት የራሱ መንገድ ቢኖረውም ግን ራስንና ማህበረሰብን ይጎዳሉ ከሚባሉ ጉዳዮች በመራቅ፣ በንባብ በመታነፅና በስፖርትዊ እንቅስቃሴዎች በመታጀብ ጥሩ የመዝናኛ ጊዜን መፍጠር ይቻላል ይላል። በመጨረሻም ለኢትዮጵያና ለዜጎቿ ሰላምን በመመኘት ሃሳቡን ይቋጫል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17/2013