አብዛኞቹ ሴቶች በተፈጥሮ የተሰጣቸውን ፀጋ እንደማይጠሉት ይናገራሉ። በነበረው አስተሳሰብ ምክንያት ሴቶች ላይ የሚደርሰውን ተፅእኖ ደግሞ ሁሉም በሚባል ደረጃ አይቀበሉትም። የባህል ተፅእኖን ለመቃወም የሚነሱ ሴቶችን ደግሞ “ፌሚኒስት” ወይም “ለሴቶች የወገነ አስተሳሰብ አራማጅ” ተብለው ይፈረጃሉ።
የወንዶች አለም በሆነችው ሀገራችን “በቃኝ እንደ ተፈጥሮዬ እንጂ እንደ እናንተ ሀሳብ መኖር አያሻኝም” በማለት ከመቶ ሀምሳ አመታት በፊት የመብት ጠያቄ ያነሳች ሴት መኖሯን ስንመለከት ምን ያህል አርአያ የሚሆኑና ከጊዜው የቀደሙ ሰዎች እንደነበሩና የአሁኑ ዘመን አስተሳሰብ አስቀድሞ እንደተገለጠላቸው እንገነዘባለን።
ዛሬ ለዘመናችን የሴቶች መበት ይከበር ትግል የቀደሙ ኢትዮዽያዊያን እናቶቻችን ፈር ቀዳጅ መሆናቸውን ለማሳየት የሴቶች የነፃነት ምልክት የሆነችው የቃቂ ወርድወትን ታሪክ ይዤላችሁ ቀርቤያለሁ። ጊዜው በአፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግስት በ1830ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ነው። ይህ ዘመን ህግ እንደ ውሃ የቀጠነበት፤ ተፈጻሚነቱም ኃያልና ጠንካራ የሆነበት ብርቱ ዘመን ነበር። በተለይ በሴቶች ላይ የሚወጡ ባህላዊ ህጎች በወንዶች የበላይነት ብቻ የሚመሩ በመሆናቸው ሴቶች በጭቆና ቀንበር የመውደቃቸውን እውነታ ግድ ይል ነበር።
የቃቄ ወርድወት የጉራጌ ምድር ያፈራቻት ውብና ጠንካራ ሴት ነበረች። በዘመኑ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን የባህል ተፅዕኖና የወንዶች የበላይነትን በመቃወም ከአስር በላይ የመብት ጥያቄዎችን ይዛ የታገለች የለውጥ አርበኛ ስለመሆኗም ታሪኳ ይመሰክራል። ወርድወት አባቷ ቃቄ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ፤ የወለኔ ቤተ ጉራጌ ተወላጅ፤ እናቷ አጀት አሚና ደግሞ ከሙስሊም የዘር ሀረግ የሚመዘዙ ሴት ናቸው።
የቃቄ ወርድወት የራሷን ህይወት መነሻ በማድረግ ትግልን ከቤቷ ጀምራ አደባባይ በመውጣት «በደል ይብቃ» ስትል ሌሎች አቻዎቿን ጭምር ለለውጥ አነቃንቃለች። ይህ ታሪክ በዛ ዘመን ይፈፀማል ተብሎ በማይታመንበት አጋጣሚ ውርድወት በርካታ ሴቶችን አስከትላ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን፣ የጋብቻ ተፅዕኖንና በሴቶች ላይ የሚደርስን ጥቃት ከመታገል አኳያ ብርሃን ፈንጥቃለች። የሚደርስባቸውን የመብት ጥሰት ለማስቆምም የሰላማዊ አመፅ ንቅናቄን መርታለች።
ከ150 ዓመታት በፊት በጉራጌ ምድር የሴቶችን መብት ለማስከበር በመንቀሳቀስ ዝናን ያተረፈችው የቃቄ ወርድወት የሕይወት ታሪክ ከክልሉ አልፎ የብዙዎችን ቀልብ ከሳበ ሰነባብቷል፡፡ የቃቄ ወርድወት በወቅቱ ካነሳቻቸው የስርአተ ጾታ እኩልነት ጥያቄዎች መካከል ሴት ልጅ የፍቺ ጥያቄ ማቅረብ ይፈቀድላት፣ ሴቶች እንደ ወንዶች በአካባቢው ሸንጐ ተሰብስበው ይምከሩ፣ ሴት ልጅ ከቤተሰቦቿ የሚገኝን ውርስ ከቀሪው ቤተሰቧ እኩል ትካፈል የሚሉት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
የቃቄ ወርድወት ባለቤት ከእሷ በተጨማሪ ሁለት ሚስቶች ያሉት መሆኑን ከመቃወም ተነስታ ሌሎችም በሴት ላይ የሚደርሱ ጭቆናዎችን ለማስቆም ስትታገል የነበረች ጠንካራ እንስት ነች፡፡ እንደ እሷ የተጨቆኑ ሴቶችን አሰባስባ በአካባቢው ባህላዊ ሥርዓት አማካኝነት ሴት ያለባሏ ፈቃድና ምርቃት ባሏን ፈትታ እንዳትሄድ የሚያስረውን ባህል አምርራ ተቃውማለች። ተቃውሞዋም ፍሬ ያፈራና የጨቋኝ ስርአትን ቀንበር በጣጥሶ ለመጣል የሚያስችለውን መሰረት የጣለ በመሆኑ ለታሪክ ምስክርነት በቅቷል።
የቃቄ ወርድወት በርካታ ተከታይ ሴቶችን አፍርታ በአካባቢው ታይቶም ሆነ ተሰምቶ የማይታወቅ ንቅናቄን ስትፈጥርና የሴቶችን ጥያቄ አንግባ በቤተ-ጉራጌ ጠቅላይ ሸንጐ የምትቀርበውን የቃቄ ወርድዎት ታሪክ የማኅበረሰቡን ባህላዊ ሥርዓትና አኗኗር በሚገልጹ ግብዓቶች የታጀበ ቴአትርም በስሟ በአንጋፋው ብሄራዊ ቲያትር ቤት አማካኝነት ተሰርቶላታል።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17/2013