ዘለዓለም የሳጥን ወርቅ (የእፀ ሳቤቅ አባት)
ከብዙ አመታት በፊት የአለም እውቅ ሳይንቲስቶች የሰው ልጅ እዚህ ምድር ላይ በህይወት ሲኖር እጅግ የሚያስፈልገው ምንድነው የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ተሰባስበው ነበር። የጥያቄያቸውን መልስ ለማግኘት ሲሉም ለሰባ አምስት አመታት ጥናት አካሄዱ። ከሰባ አምስት አመታት በኋላ አንድ እውነት ላይ ደረሱ…ፍቅር የሚለው እውነት ላይ…ከሰባ አምስት አመታት በኋላ ፍቅር ለሰው ልጅ ሁሉ እጅግ አስፈላጊ ነገር ሆኖ ተገኘ።
አሁን ሁላችንንም ስለሚያግባባ አንድ እውነት እናወራለን፤ በእኔና በእናንተ በሙልአተ ፍጥረቱ ውስጥ ስላለ አንድ እውነት…እኔ ከዚህ የሚበልጥ እውነት አላውቅም፤ እርግጠኛ ነኝ እናተም አታውቁም፤ ብታውቁ እንኳን ስህተት ናችሁ። እርሱ የሁላችን የጋራ እውነት ነው…እርሱም ፍቅር ይባላል። ከፍቅር ውጪ ያሉ አብዛኞቹ የሰው ልጅ ደስታዎች ጊዜያዊና በትንሽ ነገር የሚበረዙ ናቸው።
ፍቅር ግን ከእኛ እውቀትና ጥበበ በላይ በሆነ በማይመረመር ድንቅ ችሎታ የተገኘ ነው። በዚህም በፍጹምና ይኖራል። ፍቅር ፈጣሪ ራሱን በሰው ልጅ ነፍስ ውስጥ የተወበት ጥበብ ነው። ፍጹምናችንን ሳቅ ፈንጠዝያችንን የሸሸገበት ስፍራ እንዲህም ነው። የሚወዱ የሚያፈቅሩ ሁሉ ወደ አምላክነት የተጠጉ ናቸው። ፍቅር የመጨረሻው ድንቅ ሳቃችን የመጨረሻ ድንቅ ሰላማችን ነው። ፈጣሪ አምላክ ሰማይና ምድርን የሚታየውንና የማይታየውን ሁሉ ፈጥሮ ያን የሚያክል ታላቅ እውነት በአንድ ቃል አሰረው…በፍቅር። አመንም አላመንም ሁላችንም በፍቅር በታሰረ አለም ውስጥ ነው የምንኖረው…በፍቅር ታስረን ነው ወደዚህ አለም የመጣንው። እንረክስ ዘንድ ክፉ እንሆን ዘንድ አልተፈቀደልንም።
ከሰዎች ሁሉ ጋር በፍቅርና በመተሳሰብ እንድንኖር ነው የተፈጠርነው። ከተፈጥሮአችሁ አትውጡ ህይወት ምንም ያክል መራራ ምንም ያክል አስቸጋሪ ብትሆንብንም ራሳችንን ለመጥፎ ነገር አሳልፈን እስካልሰጠን ድረስ ጥሩዎች ነን። በህይወት ውስጥ ያሉ መጥፎ ነገሮች ሁሉ ከፍቅር ማጣት የሚመጡ ናቸው። ልባችሁ ውስጥ ብዙ ፍቅርን አስቀምጡ። ማሸነፊያችን ፍቅር ነው…ፍቅር ጋሻና ጦራችን ነው። በፍቅር የሚኖሩ ነፍሶች በድህነት ውስጥ ባለፀጋ ናቸው።
የእስካሁኑ ድህነታችን፣ የእስካሁኑ ኋላቀርነታችን፣ የእስካሁኑ ሰላም ማጣታችን ፍቅር አልባ መሆናችን ያመጣብን ጣጣ ነው። ከተፈጥሮ ስንርቅ፣ ከእውነታችን ስንወጣ፣ መጥላት ስንጀምር ያኔ ራሳችንን እናጣዋለን። ያኔ ወደማንፈለግበት ሰይጣናዊ አለም እንሄዳለን። ያኔ ክብራችንን…ሰውነታችንን እንነጠቃለን። መኖራችን ትርጉም ያጣል።
አንዲት ልጅ እናቷን ‹እማ ፍቅር ምንድነው?› ስትል ጠየቀቻት።
እናትም ‹በእኔና በአንቺ መካከል ያለው ነው።› ስትል መለሰችላት።
አንድ ቀን ሚስት የባሏን አይን እያየች ‹ፍቅር ግን ምንድነው?› ስትል ትጠይቀዋለች።
ባልም ‹ልክ አንቺ በእኔ እንደምትሰቃይው ሁሉ እኔም በአንቺ የምሰቃየው ደስ የሚል ስቃይ ነው› ሲል መለሰላት።
ፈጣሪም ተጠየቀ…‹ፍቅር ምንድነው?›
እንዲህም አለ ‹በልባችሁ ውስጥ የኔ በዝቶ መኖር ነው›።
እመኑኝ በፍቅር በታሰረ አለም ውስጥ ነን…አናውቀውም እንጂ ሄደን…ሄደን መድረሻችን ፍቅር ጋ ነው። አናውቀውም እንጂ በፍቅር ተወልደን በፍቅር ነው የምንሞተው። ስንወለድ በደስታ እልል ተብሎልናል፤ ያም ይኼም እያቀፈ ስሞናል፣ ስንሞትም በእንባ እንሸኛለን። አናውቀውም እንጂ በፍቅር ህግ ውስጥ ነው። ጥላቻን ተፈጥሮአችን አያውቀውም። በተፈጥሮ ልክና መልካም ሆነን ነው ወደዚህ ምድር የመጣነው።
ለመጥላት ክፉ ለመሆን ሰው አልሆንም። ጥላቻን መጥፎ መሆንን ከተወለድን በኋላ የምንለምደው ነገር ነው። ነፍሶቻችን መጥላት እንዳይችሉ ሆነው ነው የተሰሩት። እኛ ግን ከተፈጥሮ በወጣ ህግ እንጠላለን። እንበድላለን። አለም አሸንፋናለች…ለማናውቀው ግብራችን ላልሆነ ባዕድ ነገር እየተገዛን ነው። መጥላት በማያውቅ ምህረቱ ብዙ በሆነ ፍቅርን በሚያውቅ አምላክ ነው የተፈጠርንው…ለሀጢያት አልተፈጠርንም። ለሌሎች ደስታ፣ ለሰው ዘር ሁሉ መልካም እንድንሆን ለዚህ ነው ሰው የሆነው።
አሁን… አሁን እማ ጭራሽ ፍቅር የለም ወደማለት መጥተናል። የድፍረታችን መዐት…የክፋታችን ጥግ አይሎ በፍቅር ላይ መዘባበት ጀምረናል። ፍቅር እኮ ሌላ አይደለም፤ የእኔና የእናንተ ሰው መሆን…የእኔና የእናንተ ተፈጥሮ ነው። ፍቅር እኮ የእኔና የእናንተ ንጹህ ልብ፣ የእኔና የእናንተ ብሩካን ነፍሶች ናቸው። አንድታችን ህብረታችን እኮ ነው። ፍቅር በእኛ ውስጥ ነው ያለው…በጥላቻችሁ ሸፍናችሁት ፍቅር የለም እያላችሁ አታብሉ። ፍቅር የትም ሁሌም አለ…ፍቅር የለም እያላችሁ አትሳቱ።
ብዙዎቻችን ፍቅር የለም እያልን የምናፈቅር ነን። እየጠላን እየገፋን ሰው የሚርበን ነን። እኔና እናተን ጨምሮ ይኼ አለም እየተገዛ ያለው በፍቅር ሀይል ነው። የአለም ፍጻሜ እንኳን በፍቅር ማጣት የሚመጣ ነው። ፍቅር መጀመሪያችንም መጨረሻችንም ነው። በፍቅር ቀመር ሰው የሆንን ነን…ልባችሁን የማይችለውን አታልምዱት፣ የማያውቀውን አታሳውቁት…የመፈጠራችን ሰው የመሆናችን የመጀመሪያውም የመጨረሻም አላማ መውደድ ነው። ጎረቤቶቻችሁን፣ ጓኞቻችሁን በዙሪያችሁ ያሉትን ትንሽ ትልቅ ሳትሉ በማፍቀር ያጣችሁትን ፍቅር መልሱት። የዚህ አለም መከራዎቻችን ሁሉ በጥላቻችን፣ በራስ ወዳድነታችን የመጡብን ናቸው። የመጨረሻው አለም ምጻት እንኳን ፍቅርን ባጡ ልቦች አማካኝነት የሚመጣ ህልፈት ነው። የመውደቅ ሁሉ ምንጩ የፍቅር የአንድነት የመተሳሰብ አለመኖር ነው። ልዕልናችን ደግሞ ባፈቀርን ሰሞን የምናገኘው በረከታችን ነው። አሁን ላለችው ሀገራችን ከምንም በላይ የህዝቦች ፍቅር ያስፈልጋታል።
እስካሁን ፍቅርን ረስተን ከሙላታችን ጎለናል። ከከፍታችን ወርደናል። የሚገባንን ክብር፣ የሚገባንን ስልጣኔ ሳናገኝ ኋላ ቀርተናል። ፍቅርን የማያውቅ ሰው በልቡ አምላክ የለም። ፍቅር የለም የሚል ልብ ለሌሎች የሚሰጠው አንዳች ነገር የለውም። ፍቅርን የማያውቅ ሰውነት የተራቆተ ነው። በብዙ ማጣት በብዙ ውጣ ውረድ የተሞላ። ፍቅርን የማያውቅ ልብ ሐዘንተኛ ነው…ሁሌም ህመምተኛ። በዙሪያችን ለምልመውና አብበው የምናያቸው እነርሱ በፍቅር ተወልደው በፍቅር ያደጉ ናቸው። እነርሱ ለሌላው የሚሆን ብዙ ነገር አላቸው። ለቀረባቸው ሁሉ አስደናቂዎች ናቸው። ምክንያቱም ፍቅርን ያውቃሉና።
በህይወታችን እንደ ፈጣሪ የሆንበት ጊዜ ቢኖር ያፈቀርንበት ጊዜ ነው። የወደድንበት ከሌሎች ጋር ተስማምተን የኖርንበት ጊዜ በመኖራችን ውስጥ የተከሰተ ከሁሉም ድንቅ ጊዜችያን ነው። ፍቅር ለዚህች መከራዋ ለበዛ አለም እንስቅበት ዘንድ የተሰጠን ህብስታችን ነው። እመኑኝ በትክክል የኖራችሁት እድሜያችሁ ሌሎች የተጨነቃችሁበት፣ ከሌሎች ጋር በፍቅር የኖራችሁበት፣ በመስጠት በመረዳዳት የኖራችሁት ነው። ህይወት ያለፍቅር ምንም ነው…ላምባ እንደሌለው ፋኖስ እንደዚያ። ፍቅር ሙላታችን ነው፣ ሳይነጥፍ የሚፈስ የደስታ ባህር። ፍቅር ትንሳኤችን ነው…ከሞት ወደ ህይወት መሸጋገሪያችን።
ምንም ብታጡ…ምንም ቢጎድላችሁ ግድ አይስጣችሁ፤ የፍቅር ድሀ ሆናችሁ ራሳችሁን እንዳታገኙት፤ ግን አደራ እላችኋለሁ። እዚህ አለም ላይ ሁሉ ሞልቶት ፍቅር እንደተራበ ሰው ድሀ የለም። ሀብት፣ ዝና፣ እውቀትና ጥበብ ቢኖራችሁ ውድ መኪና ብትነዱ ውድ ቤት ውስጥ ብትኖሩ ስልጣንና አለቅነት ጌትነትም ብትታደሉ ፍቅርን እስካላወቃችሁ ድረስ ጎደሎዎች ናችሁ።
በአሁኑ ጊዜ አብዛኞቻችን በፍቅር ርረብ የምንሰቃይ ነን…በመጥላት፣ በመግፋት በተንኮል የምንኖር እንደዚህ ነን። ሁሉ ሞልቶን ምንም እንደሌለን ይሰማናል፤ በሰው ተከበን ሰው ይርበናል፤ በባዶነት እንማቅቃለን…ታላቅ ሆነን ተፈጥረን ትንሽ ሆነን እንኖራለን…ለሌሎች ደስታ ከመሆን ይልቅ የሐዘናቸው ምክንያት በመሆን እየኖርን ነው፣ እየሰረቅን፣ እየቀማን በጉልበታችን እየታበይን ነው…ይኼ የሰውነት መገለጫ አይደለም። ይኼ የደጋግ ነፍሶች ባህሪ አይደለም። ከዚህ ውጡ፣ ራሳችሁን አድሱ። ተፈጥሮአችሁን ተረዱ…በምክንያት ነው የተፈጠራችሁት…በምክንያትም መኖር አለባችሁ። በፍቅር ሞታችሁን ግደሉት…ፍቅር የሰላማችሁ ስፍራ ነውና።
የማይሞት…የማያረጅ ዘለአለማዊ ሰውነትን ፍጠሩ። ሞት የፍቅር አለመኖር ነው። የምንሞተው መጥላት ስንጀምር ነው…መጥላት ስንጀምር ያኔ በነፍሳችንም፣ በስጋችንም እንሞታለን። ስንወድ ስናፈቅር ደግሞ እንለመልማለን። በደስታ እንከበባለን። እድሜያቸው ከመቶ አመት በላይ በሆኑ አረጋዊያን ላይ ጥናት ያደረገ አንድ ተቋም ነበር። ከሁሉም አዛውንቶች ቃለ መጠይቅ ላይ ፍቅር የሚለውን ቃል እንዳገኘ ገልጧል። ጥናቱ አያይዞም በህይወታቸው ሁሉን አጥተው በድህነትና በጉስቁልና የሚኖሩ እንዲሁም በየሆስፒታሉ ታመው የአልጋ ቁራኛ ሆነው የምናያቸው ሕመምተኞች ከህይወታቸው ውስጥ ከሁሉም ትልቁን ፍቅርን ያጎደሉ እንደሆኑ ደርሼበታለሁ ብሏል።
አያችሁ የፍቅርን ዋጋ? ፍቅር እስከ እለተ ሞታችን ድረስ የሚከተለን ፀጋችን ነው…አብሮን ካለ እናሸንፋለን አብሮን ከሌለ ደግሞ ከንቱ እንሆናለን። እዚህ አለም ላይ ሁሉን አግኝተን ሞልቶን እንኖር ዘንድ አንድ መንገድ ብቻ ነው ያለን…እርሱም ፍቅር ነው…እርሱም ሌሎችን መውደድ ነው። እርሱም ከሰዎች ሁሉ ጋር ተስማምቶ መኖር ነው። ክፉ ነገር ሁሉ የተቀመጠው ለሚጠላ ልብ ነው። በፍቅር ውስጥ ስትሆኑ አሁን ከሆናችሁት ሌላ ናችሁ። ደስ በሚል እንግዳ አለም ውስጥ ትሰወራላችሁ፤ ራሳችሁ ለራሳችሁ እስኪገርማችሁ ድረስ በሀይል በብርታት በአዲስነትም ትሞላላችሁ። ወደ ህይወታችሁ ዳግመኛ የማይመጣ ርህራሄና ደግነት፣ ትህትናና መታዘዝ ጽድቅናም ባፈቀራችሁ ሰሞን የምታገኟቸው በረከቶቻችሁ ናቸው።
ስለዚህ ከሁሉም በፊት ግን ራሳችሁን አፍቅሩ። ለሌሎች የሚሆን ብዙ ፍቅር ይኖራችሁ ዘንድ አስቀድማችሁ ራሳችሁን አፍቅሩ። ራስን ማፍቀር ሌሎችን ለማፍቀር ቀዳሚው ጥበብ ነው። አብዛኞቻችን ግን ለራሳችን የምንሰጠው ዋጋ አነስተኛ ስለሆነ ሌሎችን መውደድ ምን እንደሆነ አናውቀውም። አይደለም ሌላውን ማፍቀር ይቅርና ከራሳችንም ጋር ተግባብተን መኖር ያቃተን ነን። ራሳችሁን ካልወደዳችሁ ለራሳችሁ ክብርና ፍቅር ከሌላችሁ መኖራችሁ ዋጋ የለውም። ሁሉም ነገር ራስን ከማወቅ የሚጀምር ነው።
ፍቅር ከክፉ፣ ከተንኮል ባጠቃላይ መጥፎ ከሆኑ ነገሮች የምትከለከሉበት የህይወታችሁ ትክክለኛ ጊዜ ነው። ግሪካዊው ባለቅኔ ሶፎክለስ ‹አንድ ቃል ከህይወት ሸክምና ስቃይ ሁሉ ያነጻናል፤ እርሱም ፍቅር ነው የሚል አባባል አለው። ሌሎችን እስካልወደዳችሁ ድረስ በህይወታችሁ ፈልጋችሁ የምታገኙት፣ ተመኝታችሁ የሚሳካላችሁ አንዳች ነገር የለም። ጥሩ ነገር ሁሉ በፍቅር ቀመር ለሚያፈቅሩ ልቦች የተቀመጠ ነው። የምትፈልጉት ሁሉ በፍቅራችሁ ልክ የምታገኙት ነው።
አሁኑኑ ከጥላቻ…ከአሉባልታ ጥቅም ከሌለው ዋጋ ቢስ ልማድ ውጡ። ርምጃችሁ፣ ስኬታችሁ፣ ሁሉ ነገራችሁ ውስጣችሁ ባለው መልካምነት ልክ የምታገኙት ነው። እየጠላችሁ ለሌሎች ክፉ በመሆን የምታገኙት ጥሩ ነገር የለም። ደግሜ እላችኋለሁ። እያፈቀራችሁ ኑሩ፣ በነፍሳችሁም በስጋችሁም ርኩሰት አይግባ። ራሳችሁን በማወቅ በመፈለግም ዛሬያችሁን ጀምሩ። ራሳችሁን በመውደድ በማክበርም ከእንቅልፋችሁ ንቁ። ከፍቅር ውጪ መደሰቻ አልተሰጠንም…እያሳቁን እያስደሰቱን ያሉ ነገሮች ሁሉ የፍቅርን ያክል ጉልበት የሌላቸው ነገሮች ናቸው። አሁን ላይ በደስታ እየኖሩ ያሉ ፍቅርን የሚያውቁ በፍቅር የተባረኩ ነፍሶች ናቸው።
ፍቅርን ካላወቃችሁ ገና መኖር አልጀመራችሁም…መኖር የምንጀምረው ማፍቀር ስንጀምር ነው። የሌሎችን ህመም ስንታመም በሌሎች መከራ እንባችን ሲመጣ ያኔ መኖር ጀምረናል። እኛ ለሌሎች እንደምናስፈልግ ሌሎችም ለእኛ እንደሚያስፈልጉ ስናምን፣ ይቅርታን ስናውቅ…ሰውነትን ስንረዳ ያኔ ሰው ነን ማለት ነው። ፍቅርን ያወቅን እለት ያኔ ነው የምንፈጠረው። አብረውን ላሉ እናስፈልጋለን። አንዳችን ያላንዳችን ምንም ነን። የቆምነው ተደጋግፈን ነው…ከመካከላችን የአንዱ መጉደል ጉዳት አለው። በነፍሣችሁ በሥጋችሁም ላይ ፍቅርን አትሙ። ፍቅርን የሚያውቅ ከጠቢብ ሁሉ ይበልጣልና። ቸር ሠንብቱ።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17 ቀን 2013 ዓ.ም