ኢያሱ መሰለ
ስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ከአምስተኛ በር ፊት ለፊት ቁልቁል ወደ መንደሮቹ በሚወስደው የኮብል ስቶን መንገድ ላይ አንድ ወጣት ጀሪካን የተደረደረበት የብረት ጋሪ እየገፋ ወደ አስፋልቱ ለመውጣት ይታገላል። ወጣቱ በጋሪው ላይ ጭኖ የሚገፋው ነገር ከባድ ስለመሆኑ ግንባሩ ላይ የተገተረው ደምስሩና ፊቱን እያጠበ የሚወርደው ላብ ይናገራል። የንግግር ርዕስ ለመክፈት ያህል ‹‹በርታ ወንድሜ፤ ላግዝህ እንዴ?›› አልኩት። ‹‹አመሰግናለሁ›› አለኝ።
ሰውነቱ ሞላ ያለ ትሁት ወጣት ነው። ትንፋሽ ለመሰብሰብ ይመስላል የሚገፋውን ጋሪ ተደግፎ ትንሽ እንደመቆም ሲል ምን እንደጫነ ጠየቅኩት። እያንዳንዳቸው ሃያ ሊትር ውሃ የያዙ ስድስት ጀሪካኖች መሆናቸውን ነገረኝ። ወጣቱ ውሃ ካለበት ሰፈር እየገዛ ወደሌለበት ሰፈር በመውሰድ እየሸጠ ኑሮውን የሚገፋ ነው። ቀን ቀን ውሃ ይሸጣል፤ በወር አስራ አምስት ቀን ማታ ማታ ደግሞ የጥበቃ ስራ ይሰራል።
አባቱን በህይወት ካጣበት የልጅነት እድሜው ጀምሮ ጠላ፣ እንጀራና ዳቦ እየሸጡ ሰባት ልጆቻቸውን ሲያስተዳድሩ ከነበሩት እናቱ ጥንካሬን እንደተማረ ይናገራል። የወጣቱ ተሞክሮና የስራ ትጋት የዚህ አምድ እንግዳ እንዳደርገው ስላነሳሳኝ ፈቃደኝነቱን ጠይቄው እሺታውን ከገለጸልኝ በኋላ ወደ ወጋችን ገባን።
በሃይሉ ሲሳይ ይባላል። የተወለደው በአዲስ አበባ ከተማ ደጃች ውቤ ሰፈር ነው። የአምስት ዓመት ልጅ እያለ አባቱ በስራ ምክንያት ከአዲስ አበባ ወደ ደብረ ዘይት ይዛወራሉ። በዚህን ጊዜ ቤተሰባቸውን በሙሉ ይዘው ደብረ ዘይት ይገባሉ። በሃይሉ ነፍስ እስኪያውቅ ድረስ በደብረ ዘይት ከተማ ከሰፈሩ ልጆች ጋር እየተጫወተ ማደጉን ያስታውሳል። ሶስት እህትና ሶስት ወንድሞች እንዳሉት የሚናገረው በሃይሉ ለወላጆቹ አምስተኛ ልጅ ነው።
ቤተሰቡ የአባቱን የወር ደመወዝ ብቻ እየጠበቀ የሚኖር በመሆኑ አስተዳደጉ ድሎት እንዳልነበረው ይገልጻል። በዚህም ላይ ገና በጨቅላ እድሜው አባቱ ከእናቱ ጋር በመለያየታቸው እና ኋላም ከዚህ ዓለም በሞት በመለየታቸው ያችው ለቤተሰብ መጽናኛ የነበረችው የወር ደመወዝ ከነአካቴው እንደተቋረጠች ይናገራል። ከዚያ በኋላ ያለምንም የወር ገቢ ሰባት ልጆችን የማሳደግ ሃላፊነት በእናቱ ጫንቃ ላይ ያርፋል።
እናቱ ወይዘሮ ቀለሟ ጠላ፣ ዳቦና እንጀራ እየሸጡ ልጆቻቸውን ሊያሳድጉ ቢጥሩም እንዳሰቡት ሳይሆንላቸው ይቀራል። በሃይሉና ቤተሰቦቹ ችግር ይፈትናቸዋል። በዚህም ምክንያት ትምህርቱን ከሰባተኛ ክፍል አቋርጦ ቤተሰቡንና እራሱን እየረዳ ለመኖር ይወስናል። ነፍስ ያወቁ ወንድሞቹና እህቶቹም እራሳቸውን ለማውጣት ተመሳሳይ ርምጃ ይወስዳሉ። ሁሉም በተለያዩ ስራዎች ተሰማርተው እራሳቸውንና እናታቸውን ለማኖር መሯሯጥ ይጀምራሉ።
በ15 ዓመቱ ትምህርቱን አቋርጦ ወደ ስራ ለመግባት የተገደደው ታዳጊ በመጀመሪያ ብስክሌት እያከራየ ለመኖር ይጥራል። በሚያገኘው ገቢም እናቱን መርዳት ይጀምራል። ከወንድሞቹና እህቶቹ ጋር እየተጋገዘ የቤት ኪራይ እና የተለያዩ ወጪዎችን በመሸፈን ከኑሮ ጋር መጋፈጡን ይያያዛል።
የእለት ተእለት ስራ በማከናወን የእለት ጉርሱን ለመሸፈን የሚጥረው ወጣት ኑሮው እየከፋ ሲሄድበትና እራሱን ታግሎ ለማውጣት ሲጥር ያቋረጠውን ትምህርት ለመቀጠል ሳይችል ይቀራል። በሃይሉ ብስክሌት በማከራየት የሚያገኘው የቀን ገቢ በየጊዜው እየጨመረ ከሚሄደው የኑሮ ውድነት ጋር አልጣጣም ይለዋል። ቀኑን ሙሉ አከራይቶ የሚያገኘው ገንዘብ የእለት ጉርሱን ለመሸፈን ይገዳደረዋል።
በሃይሉ ከደብረ ዘይት ወደ ትውልድ ስፍራው አዲስ አበባ ይመጣል። የስራ ዘርፉን ለመቀየር በማሰብ ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር ተደራጅቶ በኮብል ስቶን ስራ ላይ ይሰማራል። አዲስ ሙያ የተካነው ወጣት ህይወቱን በአዲስ ምእራፍ መምራት ይጀምራል። በኮብል ስቶን ስራ ከተሰማራ ወዲህ ገቢው መጠነኛ መሻሻል ቢታይበትም ኑሮው ከእጅ ወደ አፍ ከመሆን አልዘል ይለዋል።
ታታሪው ወጣት እራሱን እየጎዳ ከሚያገኛት ጥቂት ገንዘብ ላይ እየቆነጠረ ማጠራቀም ይጀምራል። ለጥቂት ዓመታት ህይወቱን በዚህ መልክ ከመራ በኋላ የኮብል ስቶን ስራው በበጀት እጥረት ምክንያት ድንገት መቋረጡን ተከትሎ በሃይሉ ስራ አጥ ይሆናል።
በዚህን ወቅት በሃይሉ ትዳር መስርቶ አንድ ልጅ ወልዶ ነበር። ባለቤቱ ስራ የላትም። በድንገት ስራ ያቋረጠው ወጣት ለችግር ይጋለጣል። በአንድ በኩል የመሰረተው ቤተሰብ በሌላ በኩል የወላጅ እናቱ ጉዳይ ያስጨንቀውና ጊዜያዊ ስራ ያፈላልጋል። ኋላም በአንድ ግለሰብ ቤት በጥበቃ ስራ ይቀጠራል።
ወጣቱ ማታ ማታ የጥበቃ ስራ እየሰራ ቀን ቀን በሚኖረው ነጻ ጊዜ ሌላ ስራ ለመስራት ሁኔታዎችን ማጥናት ይጀምራል። አንድ ቀን በአንዲት አነስተኛ ኮንቴነር ውስጥ ቁጭ ብሎ ሻይ ሲጠጣ ያስተዋለው ነገር ዛሬ ለሚሰራው ስራ መነሻ እንደሆነው ይናገራል።
ጉዳዩ እንዲህ ነው። የካቲት 12 ሆስፒታል ጀርባ በተለምዶ ፍርፍር ሰፈር ከሚባለው ቦታ ነው። በሃይሉ በኮንቴነር ውስጥ ምግብ እያበሰሉ የሚሸጡ ሰዎች ለምግብ መስሪያ የሚሆን ውሃ በአቅራቢያቸው ስለማያገኙ እየገዙ መጠቀማቸውን ያያል። ውሃ የሚሸጡላቸው ሰዎች አንድ ጀሪካን ውሃ በሁለትና ሶስት ብር እየገዙ አምስትና ስድስት ብር እንደሚሸጡላቸው ይመለከታል። በአንድ ጊዜ ሁለትና ሶስት ጀሪካን በጋሪ እየጫኑ መሸጥ ቢቻል የተሻለ ገቢ ሊገኝ እንደሚችልም ያስባል።
በሃይሉ በዚህ የስራ መስክ መሰማራት ይፈልግና ለመጠባበቂያ ያስቀመጣትን አምስት ሺህ ብር ይዞ የሚገፋ ጋሪ የሚሰሩ ሙያተኞችን ያነጋግራል። እንዳሰበውም በአንድ ጊዜ ከአስር በላይ ጀሪካኖችን መሸከም የሚችል ባለአራት ጎማ ጋሪ ያሰራል። ጋሪውን ካሰራ እና ጀሪካኖችንም ከገዛ በኋላ ውሃ የሚሸጡለትንና የሚገዙትን ደንበኞች ማግኘት ደግሞ ሌላ ፈተና ይሆንበታል።
ለስራ ቆርጦ የተነሳው ወጣት በጋሪ ላይ የጫናቸውን ባዶ ጀሪካኖች እየገፋ በየሰፈሩ በመዞር ውሃ እንዲሸጡለት ሰዎችን ማግባባት ይሞክራል፤ ውሃ መሸጥ ነውር የሚመስላቸው ሰዎች ፊታቸውን ሲያጠቁሩበት ጥቅሙን የተረዱ ደግሞ ይፈቅዱለታል።
በሃይሉ ሀሳቡ ተሟልቶ በስድስት ጀሪካኖች ውሃ ቀድቶ ወደ ምግብ ቤቶቹ አካባቢ እየገፋ ይወስዳል። ለጊዜው ምንም አይነት ደንበኛ ስላላፈራ እዚያው ፍርፍር ሰፈር በየኮንቴነሮቹ በር ላይ በማቆም እያግባባ መሸጥ ይጀምራል። ቀስ በቀስም ሌሎች ከሚሸጡበት ዋጋ እየቀነሰ በመሸጥ የአካባቢውን ገበያ መቆጣጠር ይጀምራል። በሃይሉ በምግብ ቤቶቹ አካባቢ ታዋቂ እየሆነ በመምጣቱ ስልክ እየተደወለለት ውሃ እንዲያቀርብ እስከመጠየቅ ይደርሳል።
ውሃ በየሰፈሩ የሚመጣው ተራ በተራ በመሆኑ በሃይሉ አንዳንድ ጊዜ ከስድስት ኪሎ አፍንጮ በር፤ አንዳንዴም ምኒልክ ሆስፒታል ድረስ እየሄደ መቅዳቱን ይናገራል። ይህ ደግሞ ጊዜውን እንደሚበላበትና በቀን የሚያገኘውን ጥቅም እንደሚያሳጣው ይገልጻል። ውሃ አለ በተባለበት ሰፈር እየሄዱ መቅዳቱ ብቻ ሳይሆን በየጊዜው አዳዲስ ሰዎችን ውሃ እንዲሸጡለት ማግባባቱ አስቸጋሪ እንደሆነበት ይናገራል። አሁን ግን በርካታ ውሃ የሚሸጡ ደንበኞችን በማፍራቱ እነርሱንም ጭምር ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን ይገልጻል።
በሃይሉ አንዳንድ ቀን እራቅ ወዳለ ሰፈር ሄዶ ሲቀዳ ከአስራ አምስት እስከ ሃያ ኪሎ ሜትር ይመላለሳል። የስራ ጋሪውን እየገፋ ከመንቀሳቀሱ በፊት የት የት ሰፈር ውሃ እንዳለ ማወቅ የመጀመሪያ ተግባሩ ነው። እንደ ትእዛዙ ብዛት በአንድ ጊዜ እስከ አስር ጀሪካን እንደሚጭን የሚናገረው ወጣቱ ስራው አድካሚና የተለያዩ ፈተናዎች እንዳሉበት ይገልጻል፤ በበጋ የፀሐዩ ሃሩር እንደሚያደክመው፤ በክረምት በአብዛኛው አካባቢ የውሃ አቅርቦት ስለሚኖር የደንበኞቹ ቁጥር እንደሚቀንስበት ይናገራል።
ያም ብቻ ሳይሆን ዝናቡ እንደልብ ስለማያናቀሳቅስ የተገኘችውን ስራ እንኳን ለመስራት እንደማያስችለው፤ በዚህም ምክንያት የድካሙን ያህል እንደማያገኝ ይገልጻል። በሃይሉ ድካሙ ‹‹ውሃ ቅዳ፣ ውሃ መልስ›› እንደሆነበት ቢገልጽም በትግሉ የቤተሰቡን የዕለት ጉርስና የቤት ኪራይ ሸፍኖ መኖሩ አልቀረም። አንዳንዴም የተወሰነች ነገር ለእናቱ ጣል ማድረጉን ይናገራል።
ቀደም ሲል በሃይሉ ሰርቶ የሚያገኘውን አብዛኛውን ገንዘብ የሚያወጣው ለቤት ኪራይ እንደሆነ ይናገራል። በቤት ኪራይ ወጪ የተማረረው ወጣት የመኖሪያ ቦታውን ከመሃል አዲስ አበባ ወደ ቦሌ አራብሳ ለማዛወር መገደዱን ይገልጻል። በወር ሰባት መቶ ብር እየከፈለ በትንሽ ክፍል ቤት ከቤተሰቦቹ ጋር መኖር ቢችልም አሁንም ከቦሌ አራብሳ ስድስት ኪሎ በሚያደርገው ምልልስ ለትራንስፖርት የሚከፍለው ብር ኑሮውን እንዳቆረቆዘው ይገልጻል።
በሃይሉ ከሌሊቱ አስራ አንድ ሰዓት ከቦሌ አራብሳ ተነስቶ ማለዳ ስድሰት ኪሎ ይደርሳል። ደንበኞቹ ጠዋት ቁርስ ሲሰሩ ውሃ እንዳይቸገሩ ቀድሞ ተገኝቶ ማቅረብ ይጠበቅበታል። ካልሆነ ግን ሌላ ደንበኛ ይይዙና ከስራ ውጭ ያደርጉታል። ስራው ጉልበት የሚጠይቅ በመሆኑ ጠንክሮ ለመስራት በደንብ መመገብ አለብኝ የሚለው ወጣቱ ብዙውን ጊዜ ምሳውን ከቤቱ ይቋጥራል፤ አንዳንድ ቀን ግን ከእለት ገቢው ላይ እየቆነጠረ እዚያው በሚሰራበት ቦታ ይመገባል።
በሃይሉ ማታ ስራውን ጨርሶ ወደ ቤቱ ሊሄድ ሲል የሰራበትን ገንዘብ ከደንበኞቹ ላይ ይሰበስባል። አንዳንዴ ሃምሳ፣ አንዳንዴ ሰባ፣ ጥሩ የሰራ ቀንም እስከ ዘጠና ብር ያገኛል። ከዝችም ላይ እንደአቅሙ የእለት እቁብ ይጥላል። በቀረችውም የሚያስፈልገውን የቤት ፍጆታ እየገዛ ይገባል። በሃይሉ በወር አስራ አምስት ቀን ማታ ማታ በግለሰብ ቤት የጥበቃ ስራ ይሠራል። ይችንም የልጁን የትምህርት ቤት ወጪ እንደሚሸፍንባት ይናገራል።
የጉልበት ስራ ከአቅም ጋር የሚሄድ በመሆኑ አቅም እየደከመ ሲሄድ አስተማማኝ ገቢ ምንጭ ሊሆን አይችልም የሚለው ታታሪ ወጣት ወደፊት ከዚህ የተሻለ ስራ ለመስራት እቅድ እንዳለው ይገልጻል። በሚያደርገው ጥረት ላይ የሚያግዘው አካል ቢያገኝ ባለቤቱን ወደ ስራ በማስገባትና እራሱም ጠንክሮ በመስራት የተሻለ ህይወት የመኖር ምኞት እንዳለው ያስረዳል። ነገ ሌላ ሰው ሆኖ እንደምናገኘውም ያለውን ተስፋ ገልጾልን ተሰነባብተናል።
በሃይሉ ስራ የለም ብሎ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ ተገቢ እንዳልሆነ ያምናል። ማንኛውም ሰው በአካባቢው ያሉትን ሁነቶች ወደ ገንዘብ የሚቀይርበትን እድል መፍጠር እንዳለበት ይመክራል። በአሁኑ ጊዜ ያልተማረ ሰው ቀርቶ የተማረውም ቢሆን እራሱ የስራ እድል እንዲፈጥር ይጠበቃል የሚለው ወጣቱ የስራ ፍላጎትና ፈጠራን አጣምሮ እራስን መቻል እንደሚያስፈልግ ይገልጻል።
ዛሬ ቀንና ሌሊት እየሰራ ኑሮው ጠብ እንዳላለለት የሚናገረው ወጣቱ ያሰበበት ደረጃ ላይ እስከሚደርስ ድረስ ጠንክሮ መስራቱን እንደሚቀጥል ይገልጻል። አንድ ቀን ይህን የህይወት ውጣ ውረድ ተሻግሮ ስኬት ላይ እንደሚደርስ ባለ ሙሉ ተስፋ መሆኑንም ይናገራል።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 16/2013