ባለንበት ዘመን የመንግስትን ህጋዊነት ማጽኛ ዋነኛው መንገድ ምርጫ ነው። በምርጫ ወደ ስልጣን የሚመጣ መንግስት ወደ ስልጣን ከመምጣቱ ባለፈ ሂደቱ ለአንድ አገር ሁለንተናዊ ዕድገት በራሱ አስቻይ ሁኔታ እንደሆነ ይታመናል ።ከዛም ባለፈ ሕጋዊነቱ በራሱ የሚሠጠው አቅምና ጥንካሬም ከፍ ያለ ነው።
በአገራችን በህዝቦች ምርጫ ላይ የተመሰረተ ህዝባዊ መንግስት ለመፍጠር ባለፉት 60 አመታት ዜጎች ብዙ መስዋዕትነት ከፍለዋል። በየወቅቱ የተፈጠሩ እና ወደ ፖለቲካ ስልጣን የመጡ ኃይሎች የዜጎችን በመስዋዕትነት የተደገፈ ተስፋ አምክነው ዛሬም ህዝባችን በምርጫ ላይ የተመሰረተ መንግስት ተስፈኛ ሆኗል።
ከዚህም ባለፈ አምባገነን ቡድኖች ህዝብ ተስፋ ያደረጋቸውን አጋጣሚዎች የቅዠት ያህል በሚታሰቡ ተስፋ አስቆራጭ የጭካኔ ተግባራት ያመከኑበት የትናንት እውነት አስከዛሬ የምርጫ ጉዳይ የስጋትና የአለመረጋጋት ምንጭ ሆኖ እንዲታሰብ እና እንዲታይ ያሳደረው ስነ ልቦናዊ ተጽእኖ ከፍ ያለ ነው።
ስለህዝባዊ መንግስትና ስለ ምርጫ ፖለቲካ ትናንት አደባባይ የሞሉ ድምጾች በአምባገነኖች የጭካኔ በትር የጠፉ ያህል ቢታሰቡም፣ በብዙ የህይወት መስዋዕትነት ወደስልጣን በመጣው የለውጥ ኃይል ዳግም ሕይወት ዘርቶ ለትንሳኤ በሚበቃበት የመጨረሻ የታሪክ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን።
የለውጥ ሀይሉ አገራዊ የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ተቃዋዊ የፖለቲካ ድርጅቶችን ወደተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅነት መለወጥ የሚያስችላቸውን የአስተሳሰብ መሰረት መጣል ያስቻለ ነው ። በዚህም ባለፉት ሶስት ዓመታት የተመዘገቡ ስኬቶች ከፍ ያሉ ናቸው ።
በዚህ ታሪካዊና አገርና ህዝብን አሻጋሪ በሆነ የለውጥ መሰረት ላይ ራሳቸውን ማዋቀር ያልቻሉ ፣ በፖለቲካ ገበያ ውስጥ አሸናፊ የሚያደርግ ተመራጭ አስተሳሰብም ሆነ ለዚህ አስተሳሰብ ፍጥረታዊ መሰረት የሌላቸው ቡድኖች በታሪክ አጋጣሚ በብዙ መስዋዕትነት የተገኘውን ይህንን ዕድል ለማምከን ገና ከጠዋቱ ብዙ ጥረዋል ፤ በዚህም አገርና ሕዝብን ዋጋ አስከፍለዋል፣ እያስከፈሉም ነው።
የምርጫ ፖለቲካ በዚህች አገር ጠንካራ መንግስት ለመፍጠር ትልቁ አቅም መሆኑን ቀድመው የተረዱ የውጪ ኃይሎችም እንደለመዱት በምርጫ ጉዳይ እየከሰሱ ጥንካሬውን የሚፈታተኑት አይነት መንግስት ለመመስረት ፣ በዚህም ያልተገቡ ጥቅሞችን ለማትረፍ እየሰሩ ይገኛሉ ። እነዚህ ሀይሎች በተለይም በኢትዮጵያ በምርጫ ሊመጣ የሚችለው መንግስትና በጥቅሞቻቸው ላይ ሊፈጥር የሚችለው ተግዳሮት ከወዲሁ አሳስቧቸዋል።
እነዚህ ኃይሎች በአንድ በኩል ዓለም አቀፍ ጫና በመፍጠር ምርጫው እንዳይካሄድ በግልጽና በስውር እየተንቀሳቀሱ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ፍላጎቶቻቸውን ሊፈጽሙላቸው የሚችሉ ሀይሎችን በማስተባበርና በመደገፍ ምርጫውን ለማደናቀፍ በየአቅጣጫው እየሰሩ ነው።
ይህ እውነታ በአፍሪካ ጠንካራ መንግስት እንዳይፈጠር ከነጻነት ማግስት ጀምሮ በስፋት፣በተደራጀና በተጠና መልኩ ሲካሄድ የነበረና ያለ ሴራ አካል ነው። ፣ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የእነሱን ፍላጎትና ጥቅም ተሸክሞ የሚጓዝ ደካማ መንግስት በመፍጠር ተጠቃሚነታቸውን አስጠብቀው የመጡበት እውነታም አካል ነው።
ይህ እውነታ የአፍሪካውያንን ትኩረት የሚሻ ከፍ ያለ ጉዳይ ስለመሆኑ አጠያያቂ አይደለም ። በተለይ ኢትዮጵያውያን በቀደመው ታሪካቸው የአፍሪካውያንን ዓይን ያስከፈቱ ፣ ያነቁና ለተሻለ ህይወት ከፍ ባለ መስዋዕትነት ያነሳሱ የታላላቅ ታሪኮች ባለቤቶች ከመሆናቸው አንጻር ለጉዳዩ ከፍ ያለ ትኩረት ሰጥተን ልንንቀሳቀስ ይገባል። ያለንበት ታሪካዊ ምዕራፍም ለዚህ ወሳኝ ጊዜ ነው።
ከቀደመው አፍሪካዊ ታሪካችንም ሆነ ኢትዮጵያዊ እውነታችን አገራችን ጠንካራ ሆና ለመውጣት ባደረገቻቸው እልህ አስጨራሽ ትግሎች ታሪካዊ ጠላቶቻችንም ሆኑ ከእነሱ ጎን የተሰለፉ የጥቅም ተጋሪ ኃይሎች ምን ያህል ፈተና እንደሆኑብንና ስንት ጊዜ አበቃላቸው ብለውን ቆመን መሄድ እንደቻልን የቅርቡም የሩቁም ታሪካችን ምስክር ነው።
በተቃርኖ የተሞሉ ቡድኖችን በህዝባችን ላይ በመጫን እንደአገርም ሆነ እንደ ህዝብ ባእድ ለሆኑ አስተሳሰቦችና አስተሳሰቦቹ ለወለዷቸው ጥፋቶች ተላልፈን እንደተሰጠን ፤ ከሚያጠነክረን ይልቅ የሚያላላን ፣ አንድ ከመሆን ይልቅ የሚከፋፍለን አስተሳሰብ ሰለባዎች እንደሆንም የዛሬ ህይወታችን ማሳያ ነው ።
በብዙ ተግዳሮትና መስዋዕትነት ዛሬ ላይ ጠንካራ መንግስት መመስረትና የህዝባችንን የዘመናት የመልማት ፍላጎት እውን ለማድረግ የሞት ሽረት ትግል ውስጥ ባለንበት በዚህ ወቅት የምናደርገው ምርጫ ምን ማለት እንደሆነ የገባቸው ታሪካዊ ጠላቶቻችንም ብዙ የሴራ ገመድ ገምደው በእጃችን ያስገባነውን የስኬት ዕ ጣ ፋንታችን ለማክሰም የሚችሉትን ሁሉ እያደ ረጉ ይገኛል።
እነዚህ ኃይሎች በረጅሙ የታሪክ ምዕራፋችን ውስጥ ብዙ ጥቁር ጠባሳዎችን መጣል ቢችሉም አሁን ግን እውነታው እንደቀደሙት ዘመናት አይደለም። መላው ሕዝባችን ከትናንት ሴረኞች የሴራ ትብታብ ውስጥ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመውጣት ከፍ ባለ አገራዊ መነቃቃት ውስጥ ይገኛል።
ከዚህም በላይ እስካሁን በመጣንበት መንገድ ያጋጠሙንን እና በከፍተኛ ጽናት የተሻገርናቸው ችግሮቻችን ከፊታችን ከቆሙት የሚበልጡ አይደሉም። ችግሮች በፈጣሪዎቻቸው ከአቅማቸው በላይ አደባባዮችን ይሙሉ እንጂ ከጀመርነው የለውጥ መንገድ የሚያቆሙን አይደሉም።
ህዝባችን የቀደሙትንም ሆኑ አሁን ያሉ የሴራ ትብታቦች በፊታችን በሚጠብቀን ምርጫ የመጨረሻ ሞታቸውን እንደሚሞቱና አገራዊ ትንሳኤያችን ከፍ ባለ አቅም ሕያው የሚሆንበት መሆኑን በአግባቡ መረዳት ይጠበቅበታል። ከመረዳትም በላይ የአገራዊ ትንሳኤውን ምጥ አብረው ማማጥና ህያው ተስፋን የመውለዱን ብስራት ተጨባጭ ማድረግ ይኖርበታል።
መጪው ምርጫ የጠንካራ መንግስት ተስፋችን ከዚህ የሚመነጨው ሰላማችን ከሰላማችን የሚቀዳው ብልጽግናችን መሰረት፤ አልፋና ኦሜጋ በመሆኑ በአገሩ ባለተስፋ የሆነ ዜጋ ሁሉ የመራጭነት ካርዱን ወስዶ ለመምረጥ ራሱን ሊያዘጋጅ ይገባል። ከሴራ ፖለቲካ ትብታብ መውጪያና ማረፊያችን በመሆኑም በቂና ከበቂ በላይ ትኩረት ልንሰጠው ይገባል።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 16/2013