ለምለም መንግሥቱ
ወይዘሮ ቢልጮ አህመድ በስልጤ ዞን ዳሎቻ ወረዳ ነዋሪ ናቸው።በዕድሜ ጠና ያሉ ቢሆኑም ላለፉት 12 ዓመታት የአካባቢያቸውን ሴቶች በገንዘብ ቁጠባ በማስተባበር መርተዋል።የአካባቢው ሴቶች የገንዘብ ቁጠባውን ሲጀምሩ የባንክ ሂሳብ ደብተር ከፍተውና የሂሳብ አያያዝ ሥርዓትን ተከትለው በዕውቀት በመመራት አልነበረም።ቁጠባውም የተጀመረው በሳንቲም ደረጃ በማሰባሰብ እንደነበር ወይዘሮ ቢልጮ ያስታውሳሉ።
በመንደራቸው ተሰባስበው በባህላዊ የቁጠባ ዘዴ ሲጠቀሙ የነበሩ ሴቶች ዘመኑ ወደሚጠይቀው የገንዘብ ብድርና ቁጠባ ማህበር ተሸጋግሯል።‹‹አፍረን መሊቅ›› የገንዘብ ብድርና ቁጠባ ማህበር በሚል የማህበር ስያሜ ተደራጅተው እንቅስቃሴ ከጀመሩ ወደ 13 ዓመታት ተቆጥሯል።
ወይዘሮ ቢልጮ እንደነገሩኝ ቁጠባቸው ወደ ዘመናዊ የገንዘብና ብድር ቁጠባ ማህበር በመሸጋገሩ በባህላዊ መንገድ የሰበሰቡትን ገንዘብ ቤታቸው ውስጥ ሲያስቀምጡ የነበረባቸውን ስጋት ቀርፎላቸዋል።በዘመናዊው የገንዘብ ብድርና ቁጠባ አሠራር ደስታ ቢሰማቸውም ቅሬታ ግን ነበረባቸው።
በእስልምና እምነት ወለድ የሚፈቀድ ባለመሆኑ በአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለመሆን አላስቻላቸውም።አባላትም እየሸሹ በመሆናቸው ማህበሩም ተዳክሞ ቆይቷል።እንደ ሀገር የሙስሊሙን ማህበረሰብ ማዕከል ያደረገ ከወለድ ነፃ ወይንም ወለድ አልባ የገንዘብ ብድርና ቁጠባ አገልግሎት ተግባራዊ መሆን በመጀመሩ የአፍረን መሊቅ የገንዘብ ብድርና ቁጠባ ህብረት ሥራ ማህበር እንደገና መነቃቃት ጀምሯል።
የወይዘሮ ቢልጮ የረጅም ጊዜ የመሪነት ምስጢር ጥንካሬያቸው እንደሆነ በነበረን የአጭር ጊዜ ቆይታ ለመረዳት ችያለሁ።ንግግራቸውም በሳል ነበር።‹‹እኔ በቃኝ።ካለእኔ ሌላ ሴት መሪ የለችም ወይ በማለት ኃላፊነቱን ለማስረከብ በተደጋጋሚ ጠይቄያለሁ።አንድ አመራር ከሁለት ጊዜ በላይ ምርጫ መሥራት እንደማይችልና ህጉ እንደማይፈቅድ ነግሬያቸዋለሁ።አባላቱ አንቺ ከሌለሽ ማህበራችን ይበተናል እያሉ እስከአሁን ቆየሁ።አንዳንዶች ተምረሻል ወይ ብለውይጠይቁኛል።
አልተማርኩም እላቸዋለሁ።መጥፎ እረኛ ከብቱን በአግባቡ ካልጠበቀ ለባለቤቱ አያስረክብም።ከብቶቹን በትኖ ወደቤት ይመለሳል።ትምህርትም እንዲሁ ነው።ጭንቅላት ካልሠራ ትምህርት ብቻውን አይሠራም።ማህበራችንም የአቅም ግንባታ ያስፈልገዋል።›› በማለት በምሳሌያዊ አነጋገር አስደግፈው ነው ጠንከር ያለ ሀሳብ የሰጡት። በከተማ ውስጥ የተሻለ ተሞክሮ ያላቸው ማህበራት ልምድ እንዲያገኙ እንዲመቻችላቸውም ጠይቀዋል።
የማህበሩ አባል በመሆናቸው ብዙ ጥቅም እንዳገኙ የነገሩኝ የማህበሩ አባል ወይዘሮ ጁባሌ ሱርሞሎ የሁለት ልጆች እናት ሲሆኑ፣ባለቤታቸው በሞት ስለተለዩዋቸው ለብቻቸው ነው ያሳደጓቸው።ባለባቸው የአካል ጉዳት እና በገንዘብ አቅም የከበዳቸውን ኑሮ መቋቋም የቻሉት በማህበራቸው እንደሆነ
ይገልጻሉ።የማህበሩ የማበደር አቅም ሦስት መቶ ብር በነበረበት ጊዜ ብድር ወስደው በግ ገዝተው አርብተው ሸጠው ወደ ወይፈን መቀየር ችለዋል።በድጋሚም አምስት መቶ ብር ተበድረው ጥጃ ገዝተው በማርባት ተጠቃሚ ሆነዋል።በሌላ ጊዜም ሰባት ሺህ ብር ተበድረው የእርሻ መሬት በመግዛት እህል አምርተዋል።መኖሪያ ቤታቸውንም አሻሽለዋል።ብድሩ በዓይነት በዓመት ስለሚመለስ አልተቸገሩም።ማህበራቸው ከዚህም በላይ ተጠናክሮ ቢቀጥል ይመኛሉ።
የዳሎቻ ወረዳ የህብረት ሥራ ጽህፈትቤት ኦዲተር አቶ በህረዲን ከዳሙ፤ስለ የአፍረን መሊቅ የገንዘብ ብድርና ቁጠባ ህብረት ሥራ ማህበር አመሰራረትና አሁን ስላለው እንቅስቃሴ እንዳስረዱት ማህበሩ በ2001 ዓ.ም ነው የተቋቋመው።ካፒታላቸው ከ12ሺ ብር
ወደ 71ሺ ብር አድጓል።እስከአሁን ያለው ቁጠባቸውም 80ሺ ብር ደርሷል።የማህበሩ አባላት ተጠቃሚ መሆናቸው ማሳያው ብዙ ነው የሚሉት አቶ በህረዲን አንድ ከብት እንኳን ያልነበረው ከብት መግዛት ችሏል።ቤታቸው በላያቸው ላይ ሊወድቅ ደርሶ የነበሩ የማህበሩ አባል በብድሩ ችግራቸውን ለመፍታት ችለዋል።
በወለድ አገልግሎት በሚሰጥበት ጊዜና ከወለድ ነፃ አገልግሎት ስላለው ልዩነትም አቶ በህረዲን እንዳስረዱት፤ ወለድ አልባ አገልግሎቱ በወለድ ይሰጥ የነበረውን አገልግሎት አያስቀረውም።ዘንድሮ አንድ ኩንታል ስንዴ በሁለት ሺ ብር ዋጋ ሰባት ሺ ብር ብድር ቢሰጥ የስንዴው ዋጋ በሚቀጥለው ዓመት 2 ሺ 500 ብር ዋጋ ሊያወጣ ስለሚችል ማህበሩ ትርፋማ ነው።ሰባት ሺ ብር የተበደረ አባል በበቆሎ እህል ከሆነ አስር ኩንታል መመለስ ይኖርበታል።ይህ ማለት አንድ ኩንታል በቆሎ በሰባት መቶ ብር ተተምኖ ነው።ማህበሩ በዚህ መንገድ አምና የሰበሰበውን በቆሎ በአንድ ሺ አንድ መቶ ብር ሸጦ ገቢ አግኝቷል።ዘንድሮ የሚሰበሰበው ደግሞ ከዚህም በላይ ዋጋ ሊያወጣለት ይችላል።
በተለያየ መንገድ ምርት ተጎድቶበት ችግር ውስጥ የወደቀ ተበዳሪ ቢኖር ችግሩ እንዴት ሊፈታ እንደሚችል አቶ በህረዲን ላቀረብኩላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ ችግሩ ያጋጥማል።በአካባቢው በዘንድሮ የምርት ዘመን በረዶ እህል አጥፍቶ ነበር።ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ በሽታም በግብርና ሥራው ላይ ተጽዕኖ በማሳደሩ ተደራራቢ ችግሮች አጋጥመዋል።በማህበሩ ተካፎሎ የሚባል የሁለት በመቶ የብድር አመላለስ ሥርዓት በመጠቀም ብድሩ እንዲመለስ ስለሚደረግ ችግሩ ይፈታል ብለዋል።ማህበሩ በአሁኑ ጊዜ እየተጠናከረ መሆኑንና የስልጤ ኑር የህብረት ሥራ ዩኒየን አባልም ለመሆን ችሏል።
ማህበሩ ከአባላት የሚሰበስበውን ገንዘብ የሚያከማችበት መጋዘን ባለመኖሩ ትልቅ ተግዳሮት እንደሆነበት የማህበሩ ሰብሳቢም ኦዲተሩም ተናግረዋል።ችግሩ እንዲፈታላቸው ለስልጤ ኑር የህብረትሥራ ማህበር ዩኒየንና ለስልጤ ዞን አመልክተው ምላሽ በመጠበቅ ላይ እንደሆኑ ገልጸዋል።ማህበሩ የአባላት ቁጥር ወደ 103 አድጓል።ለአባላቱ የሚሰጠው የብድር ገንዘብም ወደ ሰባት ሺ ብር ከፍ ብሏል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15/2013