መላኩ ኤሮሴ
በሀገሪቱ የመሠረታዊ ሸቀጦች አቅርቦት እና ፍላጎት ባለመጣጣሙ ምክንያት የዋጋ ንረት እየጨመረ መጥቷል።አቅርቦትን ለመጨመርና በአቅርቦትና ፍላጎት መካከል ያለውን ክፍተት በማጥበብ የዋጋ ንረት ማረጋጋት እንዲቻል መሰረታዊ የምግብ ሸቀጦች ያለ ውጭ ምንዛሬ ፈቃድ (በፍራንኮ ቫሉታ) እንዲገቡ መወሰኑን መንግሥት በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
ያለ ውጪ ምንዛሬ ፈቃድ እንዲገቡ የተፈቀዱት ምርቶች ዘይት፣ ስንዴ፣ ስኳር፣ የህጻናት ወተት እና ሩዝ ሲሆኑ፤ ይህ ፈቃድም ለቀጣይ ስድስት ወራት የሚቆይ መሆኑን በመግለጫ ተጠቅሷል።ለዚህም መጠኑ ከ250 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ወይም ተመጣጣኝ የውጭ ሀገር ምንዛሬ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ እየተረጋገጠ እንዲፈቀድ ተወስኗል።
በሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት የሚስተዋለውን የመሠረታዊ ሸቀጦች አቅርቦት እና የፍላጎት አለመጣጣም ችግር ለመቅረፍ መንግሥት የወሰደው እርምጃ ችግሩን በጊዜያዊነት ለመቅረፍ የሚረዳ አንድ አማራጭ መሆኑን የምጣኔ ሀብት ምሁራን ይናገራሉ።ነገር ግን እርምጃው ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እንደማያስችል ያብራራሉ። መንግሥት ዘላቂ መፍትሄዎች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት እንዳለበት ሳይጠቁሙ አላለፉም ።
በሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ሞላ አለማየሁ እንደሚሉት፤ ዘይት፣ ስንዴ ስኳር የህጻናት ወተት እና ሩዝ የመሳሰሉ የምግብ ሸቀጦች የሚያስገቡ አካላት ለቀጣይ ስድስት ወራት ያለ ውጭ ምንዛሬ ፈቃድ እንዲያስገቡ መፈቀዱ የመሠረታዊ ሸቀጦቹን ዋጋ መናር ለመቆጣጠር የአጭር
ጊዜ መፍትሄ ነው።አስመጪዎች የውጭ ምንዛሬ ያለ እንግልት እንዲያገኙ እድል ስለሚፈጥርላቸው ሸቀጦቹን በብዛት እንዲያቀርቡ እድል ይፈጥርላቸዋል።ይህም በሀገሪቱ ውስጥ የሚስተዋለውን የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም ለማስተካከል ይረዳል።
ሆኖም መሠረታዊ ሸቀጦችን ያለ ውጭ ምንዛሬ ፈቃድ (በፍራንኮ ቫሉታ) መቅረቡ በራሱ ግብ አይደለም፤ ችግሩንም ለመቅረፍ ላይረዳ ይችላል።የሰው ልጅ በአጠቃላይ ነጋዴ ደግሞ በተለይ የሚፈለገውን ከማድረግ ይልቅ ጥቅም የሚያስገኝለትን ወደ ማድረግ የማዘንበል ባህሪይ አለው የሚሉት ዶክተር ሞላ ነጋዴዎቹ እንዲያስገቡ ከሚፈለገው ሸቀጣ ሸቀጥ ይልቅ ጥቅም የሚያስገኝላቸውን ወደ ማስገባት የሚገቡ ከሆነ የበለጠ ችግሩ ሊባባስ ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል።
በመሆኑም መንግሥት በፍራንኮ ቫሉታ ባቀረበው የውጭ ምንዛሬ ሸቀጣ ሸቀጦቹን ከውጭ ሀገራት በሚያስገቡ አካላት ላይ ቁጥጥርና ክትትል መደረግ አለበት።በቀረበላቸው ምንዛሬ የትኞቹን ሸቀጦች አስገቡ፣ ምን ላይ አዋሉት የሚለው በየጊዜው ጥብቅ ክትትል ይፈልጋል።ይህንን ለማድረግ ቁጥጥር ማድረጊያ ስርዓት ሊኖር ይገባል።አዳዲስ ቁጥጥር ስርዓቶችን መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።
አንዳንድ ስግብግብ ሰዎች በፍራንኮ ቫሉታ ያስገቡትን ምርት በጥቁር ገበያ የማዋል እድሎች ሊኖሩ ስለሚችሉ እነዚህን እና መሰል ጉዳዮችን መንግሥት በከፍተኛ ጥንቃቄ ሊመለከተው ይገባል ያሉት ዶክተር ሞላ፤ ከዚህ ቀደም በሀገሪቱ ውስጥ የውጭ ምንዛሬ ያለፈቃድ ወስደው የተለያዩ ሸቀጦችን እንዲያስገቡ የተፈቀደላቸው አካላት ያልተፈቀደላቸው ሸቀጦችን
በማስገባት ተጨማሪ ችግሮችን ሲፈጥሩ እንደነበር በማስታወስ አሁንም ቁጥጥር ያስፈልጋል ሲሉ አሳስበዋል።በተለይም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ የሚያቀርብላቸው አካላት ላይ ቁጥጥር ማድረግ አለበት።
ዶክተር ሞላ እንደሚሉት፤ መንግሥት የወሰደው እርምጃ ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ አይረዳም።እርምጃው እንዲያውም ሀገሪቱ የሚያስፈልጓትን ሸቀጦች በሀገር ውስጥ በራሷ ለማሟላት ጥረት እንዳታደርግ ያደርጋታል፤ መንግሥትንና አምራቾችንም ያዘናጋል።ሁሉም አካላት ከዘላቂ ይልቅ የአጭር ጊዜ መፍትሄ ላይ እንዲያተኩር ያደርጋል፣ ያ ደግሞ የረጅም ጊዜ መፍትሄዎች እንዲዘነጉ መንገድ ይከፍታል።በአጠቃላይ አሁን መንግሥት እየወሰደ ያለው እርምጃ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ላይ አሉታዊ ጫና አለው።
በመሆኑም መንግሥት የአጭር ጊዜ መፍትሄ ለመስጠት እያደረገ ካለው ጥረት ጎን ለጎን ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ መፍትሄዎች ላይ ማተኮር ያስፈልጋል።ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ለአስመጪዎች ድጋፍ ከማድረግ ይልቅ ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ላይ ለተሰማሩት አስፈላጊውን እገዛ ማድረግ ይገባል ይላሉ።
በተለይም የገንዘብ፣ እውቀትና የቴክኖሎጂ እገዛ ማድረግ፣ ለኢንቨስተሮቹ አስፈላጊውን የመስሪያ ቦታ ማቅረብ፣ ምቹ የስራ ከባቢን መፍጠር እና ማበረታቻዎችን ማቅረብ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ሊያመጣ እንደሚችል ያብራሩት ምሁሩ፤ በዘርፎቹ ለሚሰማሩት አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል የማድረግ ተግባር ልዩ ትኩረት ይሻል ብለዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15/2013