ዘለዓለም የሳጥን ወርቅ (የእፀ ሳቤቅ አባት)
በሰው ልጅ የዘመናት ታሪክ ውስጥ ብዙ ኩነቶች ይሄዳሉ ይመጣሉ። ሁሉም ኩነቶች ግን በሰው ልጅ ቁጥጥር ስር ሆነው የሚያልፉ ናቸው። አንድነትና መተባበርን ባህል ላደረገ ማህበረሰብ የትኛውም ችግር ከአቅሙ በላይ አይሆንበትም።
በዘመናት የሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ከሰው ልጅ አቅም በላይ ሆነው ያለፉ ችግሮች ሁሉ በአንድንትና በተባበረ ክንድ ስላልተመከቱ ነው ባይ ነኝ። የህዝቦች አንድነት ማጣት ትንሹን ችግር ትልቅ የማድረግ ኃይል አለው። አንድነት ለሌለው ማህበረሰብ የትኛውም ችግር የሚጥለው ነው የሚሆነው። በተቃራኒው ደግሞ በአንድነት ለቆመ ህዝብና ሀገር ምንም ዓይነት ችግር ቢመጣ ሊፈትነው ይችላል እንጂ አይጥለውም።
ከዛሬ መቶ ሃያ አምስት ዓመት በፊት ኢትዮጵየዊያን በተባበረ ክንድ ወራሪውን ጣሊያንን ድል መተው ስማቸውን በወርቅ ቀለም የጻፉበት ታሪክ ነበር። በኡጋዴን፣ በአንባላጌ፣ በካራማራ ያስመዘገብናቸው ድሎች ሁሉ የአንድነታችን ውጤቶች ሆነው ያለፉ ናቸው። ልክ እንደትላንቱ ሁሉ ዛሬም የአሁኑ ትውልድ የጥንቱን የአባቶቹን የአልሸነፍባይነት ባህል ሊደግመው በአባይ ላይ ዘምቶ ይገኛል።
እችላለሁ ብሎ ለተነሳ ሀገርና ህዝብ የማይቻል ነገር የለም። ታላላቅ ነገሮች ሁሉ በእችላለሁ መንፈስ የተሠሩ ናቸው። ታላቁ የህዳሴ ግድብም በኢትዮጵያዊያን የእንችላለን መንፈስ እየተገነባ ያለ የታላቅ ህዝቦች ታላቅ ቅርስ ነው። አባይ ለዚህኛው ትውልድ የተጋድሎ፣ የመስዋዕት የአርበኝነት ጥግ ነው።
ስለ አባይ እያሰቡ ኖረው እያሰቡ የሞቱ አባቶች ነበሩን። ስለ አባይ እያሰቡ ተወልደው እያሰቡ ያረጁ ብዙ ናቸው። ዛሬ ግን በዚህኛው ትውልድ አባይ ከወንዝነት ወደ ግድብነት፣ ከግድብነትም ወደ ኃይል ማመንጫነት ሊሸጋገር የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ይገኛል። አባይ ወንዝ ብቻ አይደለም…ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን ታሪካችን፣ ዓርማችን መታወቂያችንም ጭምር ነው። በላባችን ወዝ የቆመ፣ በአጥንትና በደማችን የገነባንው የማንነታችን ወጋግራ ነው።
ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ በብዙ ልዩነት ውስጥ አንድነትን ያስተማረን፣ በብዙ መለያየት መካከል መተሳሰብን ያሳየን፣ ፍቅርን መተሳሰብን የሰጠን በትውልድ መካከል የተሰመረ በኩራችን ነው። የህዳሴ ግድባችንን በተመለከተ እንዲህ ነው የሚሰማኝ።
ይሄ የአብሮነት ስሜት እስከመጨረሻው አብሮን እንደሚዘልቅ ጥርጥር የለኝም። ብንለያይ ያኔ እንለያይ ነበር። ብንሰለች ያኔ ይሰለቸን ነበር። ብዙ ነገር እየሰማን ብዙ ነገር ችለን ወደ ፊት መሄድን የመረጥንው ከዛሬ ይልቅ ብሩህ ነገን ናፍቀን ነው። በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ አባይ በዝቶና ተትረፍርፎ አለ። በብዙ ማጣት ውስጥ ቆመን ለአባይ ግድብ ስንባል እጃችንን የምንዘረጋ ብዙዎች ነን። በብዙ ድህነት በብዙ ችግር ውስጥ ሆነን የተሻለ ነገን ለማየት ስንል ቦንድ የገዛን እልፎች ነን።
በትምህርት ቤት፣ በሥራ ቦታ፣ በሰፈር፣ በቀበሌ ለአባይ ግድብ ድምፃችንን ያሰማን ሞልተናል እውነት እላችኋለሁ እናንተ የዚች ሀገር ጀግኖች ናችሁ። መጪው ትውልድ በኩራትና በሞገስ ሲያስታውሳችሁ ይኖራል። በእናንተ ነፍስ ውስጥ የአባቶቻችሁ ነፍስ እንደሚያርፉ ስነግራችሁ ከልቤ ነው። በእናንተ ዛሬ ውስጥ ተስፋ ያጡ በርካታ ትላንቶች ፍሬ እንዳፈሩ ስነግራችሁ በታላቅ እውነት ነው።
አባይ በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ የተሳለ ህብራዊ ሀቅ ነው። በደስታና በኀዘን ያጌጡ፣ በውጣ ውረድ የተፈተኑ አስርት ዓመታትን ከአባይ ጋር አሳልፈናል። ከአፋችን ላይ ሳይጠፋ፣ ከልባችን ሳይሰወር እንሆ አስረኛ ዓመት ልደቱን አክበረናል። እኛ እኮ በብዙ ነገር ተለያይተን በአባይ ጉዳይ ግን አንድ ነን። ተኮራርፈን ተቀያይመን እንኳን ስለ አባይ ሲነሳ ኩርፊያችንን ትተን አንድ ላይ የምንቆም ህዝቦች ነን።
ለዚህም ነው አባይ ከወንዝነት ባለፈ ብዙ ነገራችን ነው ያልኩት። ዛሬ ብቻ አይደለም ከአባይ ጋር ብዙ ነገዎች አሉን። ብዙ ቀናት፣ ብዙ ዘላለማት፣ እልፍ አዕላፍ ዓመቶች ከአባይ ጋር ይጠብቁናል። እርሱ በአባቶቻችን ልብ ውስጥ የነበረ ባለ ብዙ ውበት፣ ባለ ብዙ ቁንጅና ባለቤት ነው። ከዚያኛው ትውልድ የተረከብንው የአባቶቻችን የአደራ ሰነድ ነው። ውሃ ብቻ አይደለም ከእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ የሚፈስ የቁጭት ዕንባ ነው።
በእያንዳንዳችን ነፍስ ውስጥ ያለ የህላዊ ደም እንዲህም ነው። አባይ እያንዳንዳችንን ነው። የእያንዳንዳችን መልክ፣ የእያንዳንዳችን ውጣ ውረድ ማስታወሻ ነው። በአባይ ውስጥ እኛ አለን። አባይ ሲነሳ እኛ ሁላችንም እንነሳለን። አባይ የመቶ ሃያ ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ወዘና ነው። የሰማኒያ ብሄር ብሄረሰብ ቀለም ነው። ባህላችን፣ ታሪካችን እንዲህም ነው። ለዘመናት ከደጃችን እየፈለቀ የእትብቱ ማደሪያ የሆነውን ቀዬ ግን ውሃ እያስጠማ ባዕድ ሀገራትን ሲያረሰርስ ኖሯል።
“የማያረጅ ውበት የማያልቅ ቁንጅና” እያልን በዜማና ግጥም በወቀሳና በሙገሳ አዚመንለታል። ያ ሁሉ አልፎ ዛሬ ላይ እንደተመኘንው ብርሃን ሊሆነን፣ ከድህነት ሊያወጣን የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ይገኛል።
ነገን እያሰብን የህልማችን ፍጻሜ የሆነውን የግድቡን መጠናቀቅ እያሰብን በተስፋ ቆመናል። ከሳቅን ከእንግዲህ ነው…ከበረታን… ከደመቅን ከእንግዲህ ነው። ከጊዮን ማዶ ሊስቁ ያሉ በርካታ ፊቶች ይታዩኛል። ኀዘን የረሳቸው… የሚፍነከነኩ ጸዐዳ ልቦች ፈገግ ብለው ይታዩኛል። ዘለዓለማዊ ፈገግታ።
ስለ አባይ እያዜምን በአንድ ልብ በአንድ ሃሳብ አስር ዓመታትን ተጉዘናል። ከሌለን ላይ እየሰጠን፣ ካለን ላይ እየቀነስን ከድሀ መቀነት በተሰጠ አምስትና አስር ሳንቲም እንሆ የፍጻሜው መጨረሻ ላይ ደርሰናል። ከእንግዲህም በአባይ ጉዳይ ላይ የሚያቆመን የለም። አባይ ብሄራዊ መዝሙራችን ነው። ተኝተን በተነሳን ቁጥር፣ በኖርናት በእያንዳንዷ ንጋት ልክ የምናስበው የመኖራችን ዋስትና ነው።
ጥንት አባቶቻችን በዓድዋ ላይ እንዳስመዘገቡት ድል ሁሉ እኛም የዚህ ዘመን ትውልዶች አባይን ገድበን መጪውን ትውልድ ከድህነት ማውጣት እንፈልጋለን። አባይ ትኩሳታችን ነው..ከዚያ እስከዚህ ድረስ በብዙ ችግር ውስጥ አልፈና ከመጣንበት ይልቅ የምንሄድበት ቅርብ ነውና ከእንግዲህም ለሚገጥሙን ማናችውም ችግሮች እጅ አንሰጥም። የሁላችንም ህልምና ምኞት አባይ አልቆ ኃይል ማመንጨት ሲጀምር ማየት ነው። ከጨለማ ወጥተን ወደሚደነቅ ብርሃን መሄድ ነው። ከድህነትና ከኋላ ቀርነት መውጣት ነው።
ይሄ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ምኞት እንደሆነ አውቃለሁ። ይሄ ሁሉ የሚሆነው ግን የእኛ አንድነትና አብሮነት መቀጠል ሲችል ነው። ቀደም ሲል እንዳልኳችሁ አባይ የእኔና የእናንተ የቁጭት ዕንባ ነው። የአባቶቻችን የአደራ ቃል ኪዳን ነው። በአባይ ወንዝ ላይ እኔና እናንተ በስውር አለን። ከመሰረቱ ጀምሮ አብሮ የመጣው አንድነታችን እስከ ፍጻሜው ድረስ መቀጠል አለበት። አትችሉም ያሉንን ከፍጻሜ አድርሰን ማሳፈር አለብን።
የሳቁብንን የተሳለቁብንን ጎረቤት ሀገራት በአንድነት በመቆም እንደምንችል ማሳየት ግድ ይለናል። ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ከቆሙ የሚችላቸው የለም። ለዚህ ደግሞ ዓድዋ አንዱ ምስክር ነው። የህዳሴ ግድባችን ደግሞ ሁለተኛው ዓድዋ ሆኖ ወደ ታሪካችን እየመጣ ነው። በአባይ ጉዳይ እስከመጨረሻው ሽር ጉዳችን ይቀጥላል።
ልክ እንደ ዓድዋ ሁሉ በአንድ የተገመድንበት፣ በአንድ የተቋጠርንበት የአንድነታችን ካርታ ነው። አባይ ሳንበላ ጾም እያደርን የገነባንው፣ ከድሀ እናት መቀነት ላይ በተሰጠ የደግነት መባ የቆመ ዕንባና ሳቃችን ነው። ማንም ቢሆን ሊያቆመን አይችልም። በድህነት፣ በማጣት በችግር በዚህ ሁሉ ውስጥ ያቆምንው የታሪካችን ፊተኛ ነው።
ምንም ዓይነት ምድራዊ ኃይል ሊያቆመን አይችልም። እንደምታውቁት እቅዳችንን ሊያሰናክሉብን ግብጽና ሱዳን በአንድ አብረው ተነስተውብናል። በየቀኑ የተለያዩ አሉታዊ ወሬዎችን እንሰማለን። የሀሰት ወሬ እየፈጠሩ በአባይ ጉዳይ ላይ የጸና አንድነታችንን ለማላላትና የተለየ አቋም እንዲኖረን ለማድረግ ብዙ ነገር ያወራሉ።
መቼም ከጠላት መልካም ነገር የለምና አሁንም ቢሆን በአንድነታችን በመበርታት ብልጽግናችንን ለሚጠሉ ጎረቤት ሀገራት አልሸነፍባይነታችንን ማሳየት ይኖርብናል። ብታምኑም ባታምኑም የህዳሴ ግድባችን የነገ ትልቅ ተስፋችን ነው። ከድህነት ወደ ብልጽግና፣ ከኋላ ቀርነት ወደ ዘመነች ኢትዮጵያ የምናደርገው ጉዞ ነው።
ለጋራ ጥቅም በገንዘብ፣ በጉልበት በእወቀት እየሠራን አስር ዓመታትን ተጉዘናል አሁንም የተስፋችን ጥግ ከሆነው ታላቁ የፍጻሜ ቀን እንደርስ ዘንድ እንደትላንቱ ሁሉ በአንድነት መቆም አለብን። ከፊታችን ከአባይ ጋር ብዙ የፍሰሐ ዘመናት አሉን። ከእንግዲህ በአባይ ብቻ አንቆምም በተባበረ ክንድ የምንገነባቸው ብዙ የህዳሴ ግድቦች ይኖራሉ።
የነገዋ ኢትዮጵያ አዲስ ተስፋ በእያንዳንዳችን እጅ ውስጥ ነው። እጆቻችንን ለልማት ካፍታታን፣ ልባችንን ለፍቅር፣ ነፍሶቻችንን ለይቅርታ ካስገዛን ወደ ፊት በአንድነት የምንቆርሰው ወፍራም እንጀራ አለን።
ስለ አባይ እያዜምን፣ ስለ አባይ እየተጨነቅን መቼ ይሆን የሚያልቀው እያልን በታላቅ የእኔነት ስሜት እስከአሁን ተጉዘናል ልክ እንደ ትላንቱ ሁሉ ዛሬም በአንድነት በመቆም ቀጣይ የሀገራችንን የልማት እቅዶች ማስፈጸም ይኖርብናል። በህዳሴ ግድባችን ላይ የታየው የህዝቦች አንድነትና መነቃቃት በሌሎች የልማት ሥራዎች ላይም መታየት ይኖርበታል። የህዝቦችን አንድነትና ህብረት የሚሹ ሌሎች በርካታ ሀገራዊ ጉዳዮች ከፊታችን አሉ።
ልክ ግድቡ የኔ ነው ብለን በጋለ ሀገራዊ ፍቅር እንደተነሳን ሁሉ በሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች ላይም በአንድነት መቆም አለብን። አባይ በአንድ ያስተሳሰረን የአስር ዓመት የአንድነት ጉዞ ድርና ማግ ነው። ነገ ለምትፈጠረው አዲሲቷ ኢትዮጵያ ታላቅ ተስፋ ነው። የህዳሴ ግድባችን ለእኛ ብዙ ትርጉም አለው። ግብጽና ሱዳን እንደሚሉት የውሃ እጥረትን ስለሚያመጣ አይደለም።
ግብጽና ሱዳን ከመሬት ተነስተው ለምን እንዲህ የሚሆኑ ይመስላችኋል? ቅናት እኮ ነው…ነገ ላይ በሁሉ ነገሯ የበረታችውን ኢትዮጵያ ላለማየት ሲሉ እኮ ነው። በአፍሪካ በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚው ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገር ሆና ከፊት ሆና ማየት ስላልፈለጉ እኮ ነው። የህዳሴ ግድባችን ለእኛ ብዙ ትርጉም አለው። ይሄን መቼም እንዳትረሱ።
የግብጽና ሱዳን ዛሬ ላይ እንዲህ መሆን ነገ ላይ በህዳሴ ግድባችን በረከት ታላቋን ኢትዮጵያ ማየት ስላልፈለጉ ብቻ ነው እንደዚያማ ባይሆን ሰማኒያ ስድስት ፐርሰንት የውሃው ባለቤት የሆነችን ሀገር በዚህ ልክ ሽንጣቸውን ገትረው ባልተሟገቷት ነበር። ስለዚህ የህዳሴ ግድባችንን በተመለከተ ከመቼውም ጊዜ በላይ ወደ ፊት የምንሄድበት ጊዜ ላይ ነው።
አባይን ገድበን እንደ ዓድዋ ድል ሁሉ በአንድነት የምንጨፍርበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም። በአንድነት ከተነሳን የሚሳነን የለም…አይደለም አንድ ግድብ ቀርቶ ሌላም ነገር መሥራት እንችላለን። አይደለም ግብፅና ሱዳንን ቀርቶ ለሌሎች ሀገራትም የማንበገር ህዝቦች ነን። ትንሽ ብቻ ነው የቀረን የአባይን ትንሳኤ የምናይበት ጊዜ ሩቅ አይደለም። የድካማችንን ፍሬ የምንበላበት ብሩህ ጊዜ እየመጣ ነው።
ደግሜ እነግራችኋለው በአባይ ጉዳይ የሚያቆመን ማንም የለም። የውስጥ አንድነታችንን ካጠነከርን የሚደፍረን ማንም የለም። ግብፅና ሱዳን አፋቸውን የሚከፍቱብን አንድ ሆነን ስላልቆምን ነው። ወደፊት ለምትፈጠረው አዲስ ሀገር አንድነታችን ግድ ይላታል። አንድ ሁኑ። አበቃሁ…ቸር ሰንብቱ::
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15/2013