አስመረት ብስራት
አዲስ አበባ፡- ዜጎች ለቀጣይ አምስት ዓመታት የሚመራቸውን መሪ ለመምረጥ በመራጭነት ተመዝግበው ካርድ መያዝ እንደሚኖርባቸው የኦሮሞ ነፃነት ንቀናቄ (ኦነን) የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አሳሰቡ።
የኦሮሞ ነፃነት ንቅናቄ (ኦነን) የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ተሰማ ሁኑዱማ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት ፣ እያንዳንዱ ዜጋ ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ይመራኛል፤ ያሻሽለኛል፤ ሀገሬን ይለውጣል፤ ብሎ የሚያስበውን መሪ ለመምረጥ እንዲችል የመራጭነት ካርዱን በጊዜ ወስዶ መጠበቅ ይኖርበታል።
̋የኢትዮጵያ ህዝብ መሪውን ሊመርጥ የሚችለው በምርጫ ነው፣ እኛን ወደ ፊት የሚያራምደን ወደ ስልጣኔ የሚያሻግረን አንድ አማራጭ ምርጫ ብቻ በመሆኑ ሌሎች አማራጮችን ወደ ጎን በመተው የመራጭነት ምዝገባ ማካሄድ ይኖርብናል ̋ ብለዋል።
ህብረተሰቡ በበቂ ሁኔታ የመራጭነት ካርዱን እንዳይወስድ ማህበራዊ ሚዲያዎች ባልተገባ ሁኔታ ግራ መጋባት ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል የሚሉት አቶ ተሰማ ፣ዜጎች የጠራ መረጃ በተገቢው መልኩ ስላላገኙ ካርዱን ለመውሰድ ተነሳሽነት እያሳዩ አለመሆኑን ጠቁመዋል። ሁሉም ዜጋ ሀገሩ ወደፊት እንድትቀጥል ትክክለኛ መረጃን በማስተላለፍ መስራት እንደሚኖርበትም አሳስበዋል።
ለቀጣዮቹ አምስት ዓመት መሪያችሁ ማን እንደሚሆን የምትወስኑበትን ካርድ መውሰድ ይኖርባችኋል ̋ የሚሉት አቶ ተሰማ፣ መላው ህዝብ ድምፁ ዋጋ እንዳለው ተረድቶ ፈጥኖ ካርድ ሊያወጣ እንደሚገባ አመልክተዋል።
የተፈጠረውን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የሚስማማንን ሰው በመምረጥ የሀገሪቱን የወደፊት እድል መወሰን ይገባላል የሚሉት አቶ ተሰማ፣ የጠራ እድገት፤ ሰላም የሰፈነባት ሀገር እንድትኖረን ዋናው አማራጫችን ምርጫ ብቻ መሆኑን አውቀን የመራጭነት ካርድ መውሰድ ይኖርብናል ብለዋል።
ህብረተሰቡ እገሌ ያገለግለኛል፤ ቀጣይ አምስት ዓመታትን ከዚህኛው ፓርቲ ጋር ብቀጥል ለሀገሬ ለውጥ በአጭር ጊዜ አመጣለሁ ብሎ የሚያስበውን ለመምረጥ ጊዜው ሳይረፍድ የምርጫ ካርድ መውሰድ ተገቢ ነው ብለዋል።
የመራጮች ምዘገባ በመላው ሀገሪቱ በተዘጋጁ የምዝገባ ጣቢያዎች ከመጋቢት 16 እስከ መያዚያ 15 ድረስ የሚካሄድ መሆኑ ይታወሳል።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 15/2013