የግብርናውን ዘርፍ ዲጂታላይዝ የማድረግ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው

አዲስ አበባ፡የግብርናውን ዘርፍ ዲጂታላይዝ የማድረግ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡

የዲጂታል ግብርናን ለማሳደግ የባለድርሻ አካላት ውይይት ከትናንት በስቲያ ተካሂዷል፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፍሬው ተገኝ( ዶ/ር) በውይይቱ ወቅት እንዳሉት፤ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የግብርናው ዘርፍ ዲጂታላይዝ መደረግ አለበት፡፡

የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን ዋናው ዘዴ ዲጂታላይዝ ማድረግ ነው ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ ዘርፉ ዲጂታላይዝ ሲደረግ አርሶአደሩ በቀላሉ የሚፈልገውን መረጃ ፣የምክር አገልግሎት እንደሚያገኝና የግብዓት ጥያቄውም ይሟላለታል ብለዋል፡፡

በዘርፉ በተለይም በግብዓት አቅርቦት ላይ የተጀመሩ የዲጂታል ሥራዎች እጅግ አበረታች ውጤት እንደታየባቸው የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ሥራዎቹ ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመሆን በስፋት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የዲጂታል ግብርና ከፍተኛ ዳይሬክተር ጪሚዶ አንጫላ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ “ኢ ቮቸር” የግብዓት አቅርቦትን ለማሻሻል ታስቦ የተሠራ ሥራ ነው፡፡ ሥርዓቱ ማዳበሪያ ስርጭት ላይ የነበሩ ችግሮችን ለመቅረፍ ጥቅም ላይ ውሏል ብለዋል፡፡

በተለይ የገንዘብ መጭበርበር እንዳይፈጠር ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸው፤ኢቮቸር አርሶ አደሩ ተንቀሳቃሽ ስልኩን ተጠቅሞ ማዳበሪያ ግዥ መጠየቅ እንዲችል በማድረግ የማዳበሪያ ግዢ ሂደቱንም ያሳጥረዋል ብለዋል፡፡

የግብርናው ዘርፍ ዲጂታላይዝ መሆን አርሶአደሩ ቤቱ ሆኖ በተንቀሳቃሽ ስልክ የሚፈልገውን የምክር አገልግሎት እንዲያገኝ ያስችለዋል የሚሉት ከፍተኛ ዳይሬክተሩ፤ በውጤቱም ምርታማነት በመጨመር አርሶአደሩ ውጤታማ እንዲሆን ያስችለዋል ብለዋል፡፡

ኢቮቸር ትልቁ የግብርና ማነቆ የነበረውን የግብርና ኤክስቴንሽን ሥርዓት ይቀርፋል ያሉት ጪሚዶ(ዶ/ር)፤ የኢንተርኔት ግንኙነት በሌለበት አካባቢ አርሶአደሩ ዳታ በማስገባት የኢንተርኔት መሰረተ ልማት ባለበት አካባቢ በመምጣት ሲስተም ውስጥ ማስገባት እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

የሙከራ ትግበራው በአማራ፣ትግራይ፣ሲዳማ እና በኦሮሚያ ክልሎች መጀመሩን ተናግረው፤ የሙከራው ትግበራ እየሰፋ ይሄዳል ብለዋል፡፡

የልማት ሰራተኞች የዲጂታል እውቀት አነስተኛ መሆን ችግር እንደሚያጋጥም ተናግረው፤ በቀጣይ የሠራተኞቹን ክህሎት ማሳደግ ላይ ይሠራል ብለዋል፡፡

በተባበሩት መንግሥታት የካፒታል ዴቨሎፕመንት ፈንድ የኢትዮጵያ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ኢብራሂም ማማ ፈንዱ የኢቮቸር አገልግሎት ላይ ከግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ አሁን በኢትዮጵያ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የኢቮቸር ሲስተም ይበልጥ እንዲፋጠን እና ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ዓላማው በአርሶአደሩ ደረጃ ምርትን ለማምረት የሚያስችሉ ሂደቶችን እና በምርት ስብሰባ ሂደቶች ላይ ያለውን ችግር ማቃለል እንደሆነ ጠቁመው፤ አርሶ አደሩ በገቢ ደረጃ የሚያገኘውን ጥቅም ለማሳደግ መታቀዱንም አመላክተዋል፡፡

በመድረኩ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት አመራሮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡

መዓዛ ማሞ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 24 ቀን 2016 ዓ.ም ገጽ

Recommended For You