የሱዳን ጦርነት በአፍሪካ ቀንድ ያስከተለው ተጽዕኖና መፍትሔ

ዜና ትንታኔ

በሱዳን እየተካሄደ ያለው ጦርነት ኢትዮጵያን ጨምሮ በቀጣናው በሚገኙ ሀገራት ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን ምሁራን ይገልጻሉ፡፡

በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ ተመራማሪ በፍቃዱ ቦጋለ (ፕ/ር) እንደሚሉት፤ ይህ ጦርነት ለአፍሪካ ሀገራት በተለይም ለቀጣናው ሀገራት ያለው ጫና ከፍተኛ ነው፡፡

ፕሮፌሰር በፍቃዱ እንደሚሉት፤ ከሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት ጀርባ የተለያዩ ሀገራትና ተቋማት ድብቅ አጀንዳ አለ፤ በመሆኑም ጦርነቱን በቀላሉ ለመቋጨት አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ ያም ሆኖ ግን በተለይ ኢትዮጵያ በሀገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን ያደረገችው ጥረት አበረታች ነው፡፡

ሁለቱን ኃይሎች በተለያዩ ሀገራት ለማሸማገል ጥረት ሲደረግ ቆይቷል ያሉት ፕሮፌሰር በፍቃዱ ፤ ኢጋድ፣ አፍሪካ ኅብረትና ደቡብ ሱዳን በሀገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን ጥረት ካደረጉት መካከል ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል፡፡

በዩክሬንና በራሽያ ጦርነት፣ በጋዛ ጦርነት ምክንያት ለሱዳኑ ጦርነት ትኩረት መነፈጉ እንዲሁም አረብና ጥቁር አፍሪካዊያን ነን የሚል የሱዳን ዜጎች የሃሳብ ክፍፍል ጦርነቱን የማይጨበጥ ማድረጉም ተጨማሪ ምክንያቶች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

እንደ ፕሮፌሰሩ ገለጻ፤ በሀገሪቷ የተፈጠረው አለመረጋጋት ከሰላም መደፍረስና ቀጣናዊ ትብብርን ከማቀጨጭ አንጻር አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል። በተለይ ሱዳን ከሕገ-ወጥ የሰዎችና የጦር መሳሪያ ዝውውር አንጻር መሸጋገሪያ በመሆኗ በቀጣናው ላይ ከፍተኛ ችግር ማስከተሉን ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም በቀጣናው ያሉ ተቋማት እንዲዳከሙ፣ የተጠናከረ ትብብር እንዳይኖር እንዲሁም ሽብርተኝነት በጋራ መዋጋት እንዳይቻል ማድረጉንም ነው ፕሮፌሰር በፍቃዱ ያመላከቱት፡፡

ጦርነቱ ከኢትዮጵያ ጥቅም አንጻር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ግንኙነት ቢኖረውም በኢትዮጵያ በኩል ባለው ከፍተኛ ጥንቃቄ እስካሁን ከሌሎች የተለየ ተጽዕኖ ያሳደረባት ነገር አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡

መሰል ጦርነቶች በቀታናው ሀገራት እንዳይከሰቱ ሀገራዊ የተቋማት ግንባታ ማጎልበት፣ የልዩነት ምንጮችና አድሎአዊ አሰራሮች ከመሰረታቸው በፊት ማድረቅ እንዲሁም የውጭ ጣልቃ ገብነት ማስወገድ አስፈላጊ ነውም ብለዋል፡፡

በተለይ ጦርነቱ የሚቀጥል ከሆነ ሱዳን ከደቡብ ሱዳን ጋር በድንበር ውዝግብና ከነዳጅ ማስተላለፊያ

መስመር ጋር ተያይዞ ያልተቋጩ ጉዳዮች በመኖራቸው ለቀጣናው ሌላ ራስ ምታት እንዳይሆን የሚል ስጋት እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡

የሱዳኑ ጦርነት ወደ ሰላም እንዲመጣ ኢትዮጵያ ከአረብ ሊግና ከሌሎች ሀገራትና ተቋማት በላይ ጥረት አድርጋለች ያሉት ደግሞ ኢት-አረብ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት የጥናትና የምርምር ባለሙያ ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል ናቸው፡፡

ጦርነቱ ለአፍሪካ ሀገራት ለከባድ ችግር እየዳረገ ነው ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ ኢትዮጵያ ባላት በሳል ዲፕሎማቲክ አካሄድ ከፍተኛ ተጽዕኖ መፍጠር ትችላለች ብለዋል፡፡

እንደ ረ/ፕሮፌሰር አደም ገለጻ፤ የአፍሪካ ኅብረት፣ የአረብ ሊግ፣ ኢጋድ እንዲሁም የቀጣናው ሀገራት ያደረጉት ርብርብ ፍሬ እንዳያፈራ ያደረገው የሌሎች ሀገራት ድብቅ አጀንዳ እንዲሁም ሀይ ባይ ያጣው የመሳሪያ ንግድ ነው፡፡

በሀገሪቱ የወደሙ መሰረተ ልማቶች መልሶ ለመገንባት ከመቶ ዓመት በላይ ይወስዳል ያሉት ረ/ፕሮፌሰር አደም፤ አሁንም ከዚህ በላይ ጉዳት እንዳያስከትል ሁሉም ተረባርቦ ተዋጊ ኃይሎች ከስምምነት እንዲደርሱ የበኩሉን መወጣት ይጠበቅበታል ብለዋል።

ምሁራኑ እንደሚሉት፤ የሱዳን ጦርነት በጊዜ ካልተቋጨ በአፍሪካ ቀንድ ብሎም በአፍሪካ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ግንኙነቶች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ይኖረዋል፡፡ በመሆኑም በሀገሪቱ ሰላም የሚሰፍንበትን ሁኔታ መፍጠር ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም፡፡

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You