ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ አበባ ፡- ባለፉት ሰድስት ወራት ከአዲስ አበባ ከተማ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ምስክር ነጋሽ ከትናንት በስቲያ ከኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ጋር በመሆን በከተማዋ የተጀመረውን የገቢ ማሰባሰብ መርሃ ግብር አስመልክተው በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት ፣ በተያዘው በጀት ዓመት ከአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች 734 ሚሊዮን ብር እንዲሁም ከመንግስታዊ ተቋማት 55 ሚሊዮን ብር በድምሩ 789 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ እቅድ ተይዞ ሲሰራ ቆይቷል።
በዚህም በግማሽ ዓመት ወስጥ ብቻ ከእቅዱ በላይ ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ማሰባሰብ መቻሉን ያመለከቱት አቶ ምስክር፣ ከ2010 ዓ.ም ፊት በስልጣን ላይ የነበረው ቡድን በፈጠረው ችግር ግንባታው በተያዘለት ጊዜ አለመጠናቀቁና በየወቅቱ የነበሩ ሌሎች ችግሮች የህብረተሰቡን የድጋፍ ተነሳሽነት አቀዛቅዘውት መቆየታቸውን ጠቁመዋል።
ባለፈው ዓመት ሀምሌ 2012 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አራት ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ሜትር ኪዩበ ውሃ ሙሌት መከናወኑን መግለጻቸው፤ እንዲሁም አጠቃላይ የለውጥ አመራሩ ያለፈውን ስህተት በማረም ግድቡ በፍጥነት ተጠናቆ ሃይል ማመንጨት እንዲጀምር እያደረገ ያለው ጥረት ተቀዛቅዞ የነበረውን የህዝቡን የድጋፍ ስሜት እንደ አዲስ ማነሳሳቱን አመልክተዋል።
በአሁኑ ወቅትም የተጀመረውን ድጋፍ ለማስቀጠል የተለያዩ የህዝብ ንቅናቄዎች እየተከናወኑ ነው ያሉት ሃላፊው፣ በሁሉም ክፍለ ከተሞች የተጀመረው የጉዞ መርሃ ግብርም የዚሁ አንድ አካል መሆኑን ገልጸዋል።
መርሃ ግብሩ ህዝቡ በቦንድ ግዢ፤ በ8100 እና በሌሎችም አማራጮች ለግድቡ ግንባታ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ በማስቀጠል የግድቡን ግንባታ ከግብ ለማድረስ ያለመ እንቅስቃሴ እንደሆነም ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15 ቀን 2013 ዓ.ም