ዋቅሹም ፍቃዱ
አዲስ አበባ፦ መንግስት ያለውጭ ምንዛሬ ፍቃድ መሰረታዊ ሸቀጦች እንዲገባ / ፍራንኮ ቫሉታ / መወሰኑን ተከትሎ የሂደቱ ተሳታፊ ባለሀብቶች እንዲሁም መሰረታዊ ሸቀጦቹ በተሻለ ዋጋ የሚገኙበት ሁኔታ ከዓለም ገበያ የማፈላለግ ስራ እየተከናወነ መሆኑን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እሸቴ አስፋው አስታወቁ።
አቶ እሸቴ አስፋው በተለይ ለአዲስ ዘመን በሰጡት አስተያየት፣ መንግስት እየሰፋ የመጣውን የአቅርቦትና ፍላጎት ልዩነት ለማጥበብ ብሎም በአጠቃላይ ገበያን ለማረጋጋት በተለየ ሁኔታ ደግሞ መሰረታዊ የምግብ ሸቀጦችን ፍላጎት ለማሟላት የአጭርና የረጅም ጊዜ መፍትሄዎችን በማበጀት ላይ ነው።
የአጭር ጊዜ መፍትሄዎቹ በብዛት ውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሚያሳትፍ ከ250ሺ የአሜሪካን ዶላር ወይም ከዚህ ጋር የሚመጣጠን ገንዘብ ያላቸው ባለሀብቶች ከባንክ ውጪ በራሳቸው ገንዘብ ያለውጭ ምንዛሬ ፍቃድ /ፍራንኮቫሉታ/ መሰረታዊ ሸቀጦች ወደ አገር እንዲያስገቡ መወሰኑ አንዱ ነው ብለዋል።
ከዚህ በፊት ኮሮና በአገሪቱ በተከሰተበት ወቅት መንግስት የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመቅረፍ ፍራንኮቫሉታና የዲያስፖራ አካውንት ሥርዓት በመዘረጋቱ የተመዘገበው ውጤት አመርቂ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ጠቀሜታውን በጥናት በማስደገፍ ለገንዘብ ሚኒስቴር ቀርቦ መጽደቁን አስታውቀዋል።
በሂደቱ ተሳታፊ ለመሆን በአገርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያስመዘገቡት ገንዘብ 250ሺ የአሜሪካ ዶላር በላይ መሆኑን ማረጋገጫ ለብሔራዊ ባንክ ማቅረብ እንደሚያስፈልግ ያመለከቱት አቶ እሸቴ ፣ በአሰራር ሂደቱ ተሳታፊዎች ከየትኛም ገበያ ስኳር፣ ስንዴ፣ ዘይትና የህጻናት ወተት በተመጣጣኝ ዋጋ ወደ አገር እዲያስገቡ የሚፈቅድ ነው ብለዋል።
ከዚህ በፊት መንግስት የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍ የዳያስፖራ አካውንት ለመክፈት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደሚያስፈልግ እንደአሰራር አስቀምጦ እንደነበር ያስታወሱት አቶ እሸቴ፣ ዳያስፖራው የገንዘቡ መጠን ከፍተኛ ሆኗል በሚል ባቀረቡት ቅሬታ መነሻውን ወደ 500ሺ የአሜሪካን ዶላር ዝቅ በማድረጉ ከፍራንኮ ቫሉታ ጎን ለጎን የተሻለ የውጭ ምንዛሪ እየተገኘ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ለመቆጣጠር፣ ባለሀብቶቹ ከጥቁር ገበያን ዶላር ገዝተው አየር በአየር የሂደቱ ተሳታፊ እንዳይሆኑ የግል አካውንታቸው በጥንቃቄ ይፈተሻል። በቁጥጥር ሂደቱ ጉዳዩ የሚመለከታቸው እንደ ጉሙሩክ ባለስልጣን ያሉ የተቆጣጣሪ አካላት የሚሳተፉ ይሆናል። ስጋት አይኖርም ማለት ሳይሆን ስጋቶች የሚቀንሱ አሰራሮች ተዘርግተዋል።
በሸቀጦቹ ላይ የዋጋ ማጭበርበር እንዳይ ፈጸም፣ ለህብረተሰቡም በተገቢው መንገድ እንዲደርሱ ግልጽ አቅጣጫ መቀመ ጡንና በዚያውም ልክ ጥብቅ ክትትል እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
ለዘላቂ መፍትሄ ስንዴ፣ስኳርና ዘይት ትኩረት ተሰጥቶ በአገር ውስጥ እየተመረቱ ቢሆንም አሁን ካለው ፍላጎት ጋር ባለመጣጣማቸው ምክንያት ገበያውን ለማረጋጋት ከውጭ የማስገባቱ ሂደት እንደ ጊዜያዊ አማራጭ መወሰዱን የገለጹት አቶ እሸቴ፣ ለዘላቂ መፍትሄ ግን ስንዴን በበጋ መስኖ፣ ስኳርና ዘይት የአገሪቱ ፍጆታ በሚሸፍኑ ደረጃ ለማምረት ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
መንግስት የኑሮ ወድነት ለመቅረፍ በህብረት ስራ ማህበራት በዩኒየኖች ምርት ካለው አካባቢ የምርት እጥረት ያጋጠሙ አካባቢዎች እያቀረበ ይገኛል። መሰረታዊ ሸቀጦቹን ማለትም ስንዴ አውስትራሊያ፣ ከራሺያና ከሌሎች አገራት እንዲሁም ዘይት ደግሞ ከማሌዥያና ከኢንዶኔሺያ ለማስገባት እንቅስቃሴ ተጀምሯል ብለዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15 ቀን 2013 ዓ.ም