አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ለውጡን በመደገፍና ለውጡ የሁሉም ኢትዮጵያውያን እንዲሆን በሚያስችል ሁኔታ መረጃዎችንና ዘገባዎችን በማቅረብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አስተባባሪ ሚኒስትር ዶክተር ቢቂላ ሁሬሳ ገለጹ፡፡
ዶክተር ቢቂላ ሁሬሳ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ያዘጋጀውን የመንግስት መረጃ ዳይሬክተሪና በአዲስ መልክ የተዘጋጀውን የድርጅቱን ድረገጽ ባስመረቀበት ወቅት እንዳስታወቁት ፤ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ባለፉት 80 ዓመታት ለአገር ግንባታ የተጫወተውን ሚና ባለፉት ሶስት ዓመታትም ለውጡን በመደገፍና ለውጡ የሁሉም ኢትዮጵያውያን እንዲሆን በሚያስችል ሁኔታ መረጃዎችንና ዘገባዎችን በማቅረብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ለዚህም መንግስት ከፍተኛ አድናቆትና አክብሮት አለው፡፡
በተለይ ባለፉት 3 ዓመታት የተደረጉ የለውጥ እንቅስቃሴዎችን በመዘገብና ወደፊት በማምጣት ከፍተኛ የሆነ የህዝብና የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እንዲኖር አድርጓል ያሉት ዶክተር ቢቂላ ፣ ህብረተሰቡ ሃሳቡን የሚገልጽበት ፣ የህዝብ ስሜቶች የሚንጸባረቁበት መድረክ ሆኖ በማገልገል ለውጡ እዚህ እንዲደርስና ኢትዮጵያውያን የወደፊት እጣፋንታቸውን በጋራ ሆነው የሚመሰርቱበትን መድረክ በመፍጠር የራሱን አሻራ ያኖረ ድርጅት መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
የኢትጵያ ፕሬስ ድርጅት የሚማርና የሚመጡ አዳዲስ ክስተቶችንና አዳዲስ ግኝቶችን ከግምት ያስገቡ ለውጦችን እያመጣ የሚሄድ ድርጅት መሆኑን ያመለከቱት ዶክተር ቢቂላ፤ የመንግስት የመረጃ ዳይሬክተሪ የለውጥ አካል ሆኖ በአንድ መጽሐፍ በአገሪቱ ያሉ ቁልፍ መረጃዎችን በአንድ ቦታ ልናገኝ በምንችልበት ሁኔታ በማዘጋጀቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ አዲሱ የፕሬስ ድርጅት ድረ ገጽም አዳዲስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማድረስ በሚያስችል ሁኔታ የተዘጋጀ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጌትነት ታደሰ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት 80 ዓመቱን እያከበረ ያለ አንጋፋ ድርጅት መሆኑን አመልክተው፤ በርካታ ውጣውረዶችን አልፎ እዚህ መድረሱ ትልቅ ድል መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በተሻሻለው የድርጅቱ ማቋቋሚያ አዋጅ ከተሰጡት ተጨማሪ ተልዕኮዎች አንዱ አጠቃላይ ሀገራዊ የመረጃ ክፍተት መሙላት መሆኑን የጠቀሱት አቶ ጌትነት፤ ለዚህ ደግሞ የመንግስት መረጃ ዳይሬክተሪ ለመጀመሪያ ጊዜ አዘጋጅተን ለምርቃት ማብቃታችን ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ዳይሬክተሪው ላይ ያሉ መረጃዎችን በቀላሉ ማግኘት የሚቻልበትን በራስ አቅም የተሰራ አዲስ ድረ ገጽ ለምርቃት ማብቃት መቻሉን አመልክተዋል። ስራዎቹ ተቋሙ በቀጣይነት ለሚያከናወናቸው ዘርፈ ብዙ የለውጥ ስራዎች መንገድ ከፋች እንደሚሆኑም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
በህትመት ካለው ተደራሽነት በተጨማሪ በዲጅታል ሚዲያው ላይ በስፋት ለመስራት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቅሰው፤ ራስን ከዘመን ጋር ለማዋሃድ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴም በተምሳሌትነት የሚታይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በቀጣይም ድርጅቱ የጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ አጠናክሮ በመቀጠል የኢትዮጵያውያን ሁሉ ድምጽ ለመሆን እንደሚሰራ አስታውቀዋል። የመንግስትና የሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍና ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናታን ተስፋዬ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በመንግስታት መቀያየር ውስጥ በፈተናና ጫና ውስጥ ተቋምነቱን ይዞ ዛሬ መድረስ የቻለ መሆኑን አመልክተዋል። በብዙ የታሪክ ሂደት ውስጥ አልፎና ራሱ የታሪክ ቤተመዘክር ሆኖ ከዚህ መድረሱ ያስደስታል ብለዋል፡፡
ከዚህ በኋላም ጊዜው በሚፈቅደውና ባለው ምቹ ሁኔታ ተጠቅሞ የሚጠበቅበትን ድርሻ ያበረክታል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸው፤ ሚዲያዎች በህዝብና በመንግስት መካከል ያላቸው ድልድይነት ከፍተኛ በመሆኑ ዘገባን ከማቅረብ ባለፈ ድርጅቱ ያጠራቀማቸውን ተቋም በመገንባት ሂደት ውስጥ ያለፋቸውን ድክመቶችና ጥንካሬዎች ወስዶ በአገሪቱ የዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ግንባታ የድርሻውን እንደሚወጣ እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለአንድ አገር ሁለንተናዊ እድገት የመገናኛ ብዙሃን ሚና ከፍተኛ መሆኑን ያመለከቱት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ጠንካራ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት እንዲፈጠሩ ለማድረግ ከተቋማቱ ጋር በቅርበት እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በአራት የአገር ውስጥና በሁለት የውጭ ቋንቋዎች አገር ቋንቋዎች የህትመት ውጤቶችን እያሳተመ ለህዝብ ተደራሽ እያደረገ የሚገኝ አንጋፋ የህትመት ሚዲያ ሲሆን፤ አሁን ላይ ደግሞ ፕሬስ ኦንላይን በሚል ስያሜ ተደራሽነቱን ለማስፋት በመስራት ላይ ይገኛል ፡፡
በመጪው ግንቦት 80 ዓመት የሚደፍነው ተቋሙ፤ ካለፈው መስከረም ወር ጀምሮ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች 80ኛ አመት በዓሉን እያከበረ ይገኛል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15 ቀን 2013 ዓ.ም