በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ አበባ ፦ የ6ኛው ብሔራዊ ምርጫ ሂደት ነጻ፣ ፍትሐዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ሰላማዊ እንዲሆን መንግስት በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ አስታወቁ። ምርጫው ስኬታማና ሰላማዊ እንዲሆን ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት የሚቻላቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ ጥሪ አቀረቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት ከክልል ፕሬዚዳንቶች እና ከብሔራዊ የምርጫ ቦርድ አመራሮች ጋር ያደረጉትን ስብሰባ አስመልክቶ በማህበራዊ ድረ ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት እንዳስታወቁት፣ የ6ኛው ብሔራዊ ምርጫ ሂደት ነጻ፣ ፍትሐዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ሰላማዊ እንዲሆን መንግስት በቁርጠኝነት እየሠራ ነው።
ምርጫ የዴሞክራሲያዊ ባህል ግንባታ አንዱ ማሳያ ነው፣ ልዩነቶች በጥይት ሳይሆን በምርጫ ካርድ አማካኝነት የሚፈቱበት ነው። በምርጫ ሂደት፣ ዜጎች የተማመኑበትን በሙሉ ልብ ለመምረጥ እና ዴሞክራሲያዊ ሂደትን ለመገንባት ንቁ ተሳትፎ የማድረግ ዕድል የሚያገኙበት እንደሆነ አስታውቀዋል።
መጪው ምርጫ ኢትዮጵያን ወደ ፊት የሚያስፈነጥር እንደ መሆኑ፣ በጋራ የዜግነት ግዴታችንን መወጣት ያስፈልገናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ “ነገን እንዲወስኑ፣ ዛሬ ይመዝገቡ!” ሲሉ ለመራጩ ህዝብ መልእክት አስተላልፈዋል።
በተመሳሳይ ዜና 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት ወሳኝ በመሆኑ ምርጫው ስኬታማና ሰላማዊ እንዲሆን ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት የሚቻላቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ጥሪ ማቅረባቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
ጽህፈት ቤቱ ትናንት ከክልል ፕሬዚዳንቶች እና ከብሔራዊ የምርጫ ቦርድ አመራሮች ጋር ያደረጉትን ስብሰባ አስመልክቶ በማህበራዊ ድረገጹ እንዳስታወቀው ፣ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት ወሳኝ በመሆኑ ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ምርጫው ስኬታማና ሰላማዊ እንዲሆን የሚቻላቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ከወቅታዊ የጸጥታ እክሎች ጋር በተያያዘም ዜጎች በስሜት እርምጃ ከመውሰድ ታቅበው ለሰላምና ለመረጋጋት በጋራ እንዲሰሩ ፣ ከዚህ አንጻር፣ ወጣቶች አገልግሎት ለመስጠት በመመዝገብ እና የሲቪክ ግዴታዎቻቸውን በመወጣት የሀገራችንን የጸጥታ ዘርፍ በማስተባበር እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።
ባለፈው ሳምንት በተደረገ ስብሰባ የምርጫ ቦርድ ያቀረበው ሪፖርት ብዙ የምርጫ ጣቢያዎች አገልግሎት መስጠት ያለመቻላቸውን ያሳየ እንደነበር ፣ ክልሎች አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ የምርጫ ጣቢያዎች በፍጥነት ተቋቁመው አገልግሎት ለመስጠት እንዲችሉ ለማድረግ ቃል መግባታቸውን አስታውሷል ።
በተገባው ቃል መሰረትም ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ሆነ ክልሎች ባለፈው ሳምንት የምርጫ ጣቢያዎች ተከፍተው መራጮችን መመዝገብ መጀመራቸውን ማሳወቃቸውን ጠቁመዋል።
በየምርጫው ሂደት ሰላማዊ እና በነውጥ ሃይሎች የማይደናቀፍ እንዲሆን በሁሉም ክልሎች የተደረገውን የጸጥታ ማስከበር ዝግጁነት በስብሰባው የተዳሰሰ መሆኑን አመልክቶ። በዚህ ረገድ፣ ብሔራዊ የጸጥታ አማካሪ/ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው በሀገር አቀፍ የምርጫ ደህንነት ኮሚቴው የተዘጋጀውን ግምገማ በማቅረብ፣ ከጥቂት ግጭት ከሚስተዋልባቸው አካባቢዎች በስተቀር በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች በሰላማዊ ሁኔታ ምርጫውን ለማስተናገድ መዘጋጀታቸውን ማስታወቃቸውን ገልጿል።
በስብሰባው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ የክልል ፕሬዚዳንቶች ቀሪ የምርጫ ጣቢያዎችን አጠናቅቆ በመክፈት፣ በሚቀጥለው ሳምንት ሙሉ በሙሉ ሥራቸውን እንዲያከናውኑ እንዲያደርጉ ማሳሰባቸውን አስታውቋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15 ቀን 2013 ዓ.ም