ለምለም መንግሥቱ
አዲስ አበባ ከተማ ስያሜዋን ያገኘችው በአንዲት ውብ ተክል የተነሳ መሆኑን የታሪክ ድርሳናት ይገልጻሉ። ስያሜውንም የሰጧት እቴጌ ጣይቱ ሲሆኑ፣ እቴጌዋ በአሁኑ ጊዜ ለብዙ የከተማዋ ነዋሪዎችና እንግዶች አገልግሎት በመስጠት ላይ በሚገኘው ፍልውሃ አካባቢ ሲደርሱ ነበር ከዚህ ቀደም አይተውት የማያውቁት ውብ የሆነች የአበባ ተክል ያጋጠማቸው።
አይተውም ያደንቃሉ። አበባዋ በጣም ስለማረከቻቸውም አካባቢውን አዲስ አበባ ብለው ሰየሟት። ከተማዋ በአንዲት የአበባ ተክል ስያሜዋን ታግኝ እንጂ እንደ ዛሬው ዙሪያዋን ጨምሮ በመኻል ከተማዋ ከአረንጓዴ ልማት ይልቅ ግንባታ ጎልቶ መታየት ከመጀመሩ በፊት ብዙ የተክል ዓይነቶች የነበሯትና በአረንጓዴ የተከበበች ከተማ መሆኗ አይዘነጋም፡፡
በተለይ በአሁኑ ጊዜ በከተማዋ ማስፋፊያ ተብለው በሚጠሩ አካባቢዎች ኮሽም፣ቀጋ የተባሉ የፍራፍሬ ዓይነቶች ሲበሉ ያደጉ ሰዎች አጋጥመውኛል።መንደሮቹም በጣም ጥቂት ስለነበሩ የትራንስፖርት አገልግሎቱ ተደራሽ ባለመሆኑ ግማሹን መንገድ በእግር በመጓዝ ወደ ቤታቸው ይገቡ እንደነበርም አጫውተውኛል።
አካባቢውም እርሻ ስለሚበዛው ከተሜው አነስተኛ እንደነበር ልጅነታቸውን የሚያስታውሱ ብቻ ሳይሆኑ ከጊዜ በኋላም በማህበር ቤት ሠርተው የገቡ ሰዎችም ከመንደራቸው ሲወጡና ወደ መንደራቸው ሲመለሱ የሚያደርጉት ሁለት ጫማ ይዘው ነበር የሚወጡት።በክረምት ጭቃው ፣ በጋ ሲሆን ደግሞ አቧራው ስለሚያስቸግራቸው ሁሌም በዚህ መልኩ ነበር የሚመላለሱት።
ታሪኩን ለሰማ ሰው እነዚህ ሰዎች አዲስ አበባ ከተማ ነው ወይንስ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ነው የኖሩት? ብሎ መጠየቁ አይቀሬ ነው። ያጫወቱኝ ሰዎች እንዲህ በትውስታ ካነሷቸው መካከልና ማስፋፊያ ከሆኑት ንፋስልክ ላፍቶ ክፍለከተማ ይጠቀሳል። ዛሬ መንገዱ በኮብል ስቶንና በአስፓልት ተሸፍኖ ጭቃው ጠፍቷል።እነ ቀጋ፣ ኮሽምና ባህር ዛፎች በሕንፃ ተተክተዋል።
አረንጓዴ ሥፍራዎች በግንባታ እየተዋጡ መምጣታቸውና ለአረንጓዴ ልማት ትኩረት የማይሰጥ ማህበረሰብ እየተፈጠረ ነው ብለው የሚሰጉ አንዳንድ ሰዎች የከተማዋ ስያሜ ታሪክ ብቻ ሆኖ እንዳይቀር ሲሉ ይደመጣሉ።በከተማዋ ዙሪያ በከፍታ ቦታ ላይ ሳይቀር ግንባታዎች በመቅረባቸው በአረንጓዴ የተሸፈኑ ቦታዎች ተመናምነዋል፡፡
በከተማዋ መኻልም የአዲስ አበባ ከተማ ተፋሰስና አረንጓዴ አካባቢዎች ልማት ኤጀንሲ በህብረተሰብ ተሳትፎ በመንገድ አካፋይና ቁርጥራጭ ቦታዎች ላይ የአረንጓዴ ልማት ሥራ እየተከናወነ ቢሆንም አብቦና አምሮ ለከተማዋ ውበትም ሆነ ጥሩ የሆነ የአየር ፀባይ በመፍጠር አስተዋጽኦ እያበረከቱ ያሉት ውስን በሆኑ የከተማዋ አካባቢዎች የተከናወኑት የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች ናቸው።ተገቢውን እንክብካቤ በማጣት፣በጎዳና ላይ ውለው በሚያድሩ ሰዎችና የቤት ውስጥ እንስሳትና በተለያዩ ምክንያቶች በመንገድ አካፋይና ቁርጥራጭ ቦታዎች የተተከሉት እፅዋቶች ደርቀው ይጠፋሉ።
በአንዳንድ ቦታ የተተከለው አበባ ከአረንጓዴ ሳር ጋር ልዩ ውበት ተጎናጽፎ እይታን ይስባል።በአንዳንድ ቦታ ደግሞ ወደ መፀዳጃነት ተለውጦ ይመለከታሉ።በ35ኪሎ ሜትር ርዝመት ውስጥ በተዘረጋው የባቡር ሃዲድ ሥር የሚስተዋለውን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል።
እንደእኔ ታዝባችሁ ከሆነ ወደ ቦሌ ሚካኤል በሚወስደው የባቡር ሃዲድ ሥር አረንጓዴ ለብሶ በውስጡ ደግሞ የተለያዩ ሥዕሎች ተደርገው የአላፊ አግዳሚውን ትኩረት ይስባሉ።በተቃራኒው ደግሞ በስቴዲየም አካባቢ ለማየት ቀርቶ መጥፎ ሽታው አያሳልፍም።
ኑሯቸውን በጎዳና ያደረጉ መዋያ ፣ ማደሪያና መፀዳጃ ሆኗል።በአንድ ከተማ ሊያውም በአንድ መስመር ላይ እንዲህ የተለያየ ነገር ሲያጋጥም ለተመልካቹ ግራ ያጋባል።እንዲህ ዥንጉርጉር የሆነ የልማት ሥራ ሲያዩ ከተማዋ ስንት አስተዳደር ነው ያላት ያስብላል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ በቅርቡ ደግሞ በአረንጓዴ ልማቱ በተለይም በመንገድ አካፋዮች መነቃቃት እየፈጠረ ይገኛል።ቸርችር ጎዳናን ይዞ ቁልቁል የተለያዩ እፅዋቶች በመተከል ላይ ናቸው። ቀድሞ በተተከሉበት ሥፍራዎችም ለእፅዋቶቹ የሚውል ውሃ በአቅራቢያ እንዲኖር የውሃ ማጠራቀሚያ ታንከር(ሮቶ) የማስቀመጥ ሥራ ተከናውኗል። ብቻ ከተማዋን በተለያዩ እፅዋቶች የማስዋብ ሥራ በስፋት በመከናወን ላይ ነው፡፡
በአረንጓዴ ልማት የማስዋብ ሥራ በመሳተፍ ላይ ከሚገኙት የከተማዋ ነዋሪዎች በቂርቆስ ክፍለከተማ ወረዳ ሰባት ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ አባይነሽ በየነ አንዷ ናቸው። እርሳቸው እንደነገሩኝ ‹‹አባይነሽ እዝራና ጓደኞቻቸው›› በሚል ስያሜ 10 ሆነው በአረንጓዴ ልማት በማህበር ተደራጅተው በከተማ የባቡር ትራንስፖርት ሥር የማስዋብ ሥራ ለማከናወን ቦታ ተረክበው በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛሉ።
ሥራው አንድ የሕንፃ ባለሙያ ወይንም ተቋራጭ የግንባታ ሥራ ወስዶ በገባው ውል ገንብቶ አጠናቅቆ እንደሚያስረክበው ሁሉ ‹‹አባይነሽ እዝራና ጓደኞቻቸው›› ማህበርም ለአረንጓዴ ልማት የተረከበውን ቦታ አልምቶ ወይንም አስውቦ ያስረክባል።ማህበሩ ለልማቱ ሥራ መነሻም 53ሺህ ብር አግኝቷል፡፡
ወደዚህ ሥራ የገቡበትን አጋጣሚ ፣ ስለ ሥራ መነሻ የገንዘብ ምንጫቸውና አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴያቸውን በተመለከተ ወይዘሮ አባይነሽ እንዳሉት የማህበሩ አባላት በወረዳቸው በከተማ የምግብ ዋስትና ወይንም በምግብ ዋስትና የሴፍቲኔት ፕሮግራም ለሦስት ዓመታት ተጠቃሚ ነበሩ፣ አካባቢያቸውን በማጽዳትና የተለያዩ ዕፅዋቶችን የመትከል ሥራዎች በማከናወን በወር ክፍያ ሲያገኙ ቆይተዋል።ክፍያውም አንደኛና ሁለተኛ ዓመት በሚል ተከፋፍሎ ሲፈጸም የቆየ ሲሆን፣ እያንዳንዱ ተጠቃሚም የሚያገኘው ክፍያ ይለያያል። አንደኛ ዓመት ላይ ያለው አንድ ሺህ ሁለት መቶ ብር ነበር የሚያገኘው።
ከሚያገኙት ገንዘብ ላይም የባንክ ሂሳብ ከፍተው ይቆጥባሉ።በዚህ መልኩ ሲከናወን የነበረው የሦስት ዓመት የምግብ ዋስትና ሴፍቲኔት ፕሮግራም በመጠናቀቁ ወደ ማስዋብ ሥራ ተሸጋግረዋል። ማህበራቸው ሥራ ከጀመረ ገና ሁለት ወሩ በመሆኑ አባላቱ አልምተው ከሚተርፋቸው ገንዘብ ነው ወደፊት ተጠቃሚ የሚሆኑት። የማህበሩ አባላት ለማስዋብ ቦታ ከመረከባቸው በፊት ወረዳቸው ባመቻቸላቸው የሥልጠና ማዕከሎች የአጭር ጊዜ ስልጠና አግኝተዋል።
ወይዘሮ አባይነሽ በከተሞች የምግብ ዋስትና ፕሮግራም (ሴፍቲኔት) ታቅፈው ወደዚህ ሥራ ከመግባታቸው በፊት ሥራ አልነበራቸውም፤ የባለቤታቸውን እጅ ነበር የሚጠብቁት። ሥራ ስለተፈጠረላቸው ደስተኛ ናቸው። ካልደከሙ የሚገኝ ነገር እንደሌለም ያምናሉ። በመሆኑም ክህሎቱም የሥራ ገንዘቡም በመገኘቱ ጠንክሮ በመሥራት ውጤታማ ከመሆን ውጪ ሌላ አማራጭ የላቸውም።
አረንጓዴ ልማት ወይም ማስዋብ ለእርሳቸው ትልቅ ትርጉም አለው።በአንድ በኩል ኑሯቸውን የሚደጉሙበት ገቢ ያገኙበታል።በሌላ በኩል ደግሞ የሚኖሩባት ከተማ አምራና ተውባ ለእይታም ሆነ ለኑሮ ተስማሚ መሆኗ ያስደስታቸዋል።እርሳቸው ደግሞ የዚህ አካል ለመሆን በመቻላቸው ዕድለኛ እንደሆኑ ይሰማቸዋል፡፡
እንዲህ እንደነ ‹‹አባይነሽ እዝራና ጓደኞቻቸው›› በማህበር ተደራጅተው በአረንጓዴ ልማት ላይ እንደተሰማሩት የከተማዋ ነዋሪዎች ሁሉ እንደምርጫቸው በተለያየ የሙያ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ በምግብ ዋስትና ሴፍቲኔት ፕሮግራም ታቅፈው ለሚሠሩ የአጭር ጊዜ ሥልጠና በመስጠት እገዛ ካደረጉላቸው የሥልጠና ማዕከላት በቂርቆስ ክፍለከተማ የሚገኘው ማንፋክቸሪንግ ኮሌጅ ይጠቀሳል።
የኮሌጁ ዲን ወይዘሮ ዳግማዊት ግርማ እንደነገሩኝ ቴክኒክና ሙያ እንዲህ በተለያየ ዘርፍ የሥራ ዕድል ለሚፈጠርላቸው ዜጎች በአጭር ጊዜ ሥልጠና በማብቃት ከሥራ ጠባቂነት ወደ ሥራ ፈጣሪነት እንዲሸጋገሩ በአጠቃላይ በተፈጠረላቸው አቅም የምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረጋግጡ የሚያስችላቸውን ክህሎት እንዲያገኙ በማድረግ ቴክኒክና ሙያ ሚናውን ተወጥቷል ብለው ያምናሉ።ኮሌጁ ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ በሽታን ታሳቢ ባደረገ ሥልጠና በመስጠት ለዚህ እንዳበቃቸውም ተናግረዋል።
ሥልጠናውም እንደየሚሰማሩበት የሥራ ዘርፍ እንደሚለያይና የወሰዱት ሥልጠናም በምዘና ፈተና ተረጋግጦ ወደ ሥራ እንደሚሰማሩ አስረድተዋል። በሥልጠናው በተለያየ የዕድሜ ክልልና በጾታም ስብጥር ቢኖርም በዕድሜ ጠና ያሉ ሴቶች በቁጥር የበዙ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።ልማቱም እነዚህን አካላት የሚያሳትፍ በመሆኑ ዓላማውን ያሳካ ነበር ብለው ያምናሉ።ሥልጠናው የመቀበል ችሎታቸውን ባገናዘበ ፣ በተግባር የተደገፈ በዘጠኝ ዘርፎች ወደ ሦስት ሺ ሰባት መቶ ሰልጣኞችን ለማሰልጠን መቻሉን የኮሌጁ ዲን ተናግረዋል፡፡
ለልማቱ ሥራ መነሻ ስለሚውለው የገንዘብ ምንጭ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመገናኛ ቅርጫፍ ዲስትሪክት አቶ ቴዎድሮስ ታደሰ፤ ባንኩ ከልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም ጅምሮ አንስቶ ሲንቀሳቀስ የቆየ ሲሆን፣ ከፌዴራል የምግብ ዋስትና ኤጀንሲና ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር የሦስትዮሽ የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም ነው ወደ ሥራው መግባታቸውን የተናገሩት።
በባንኩ በኩል ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም ሂሳብ በልዩ ሁኔታ የባንክ ሂሳብ እንዲከፈትና ተጠቃሚዎችም ከሚያገኙት ገቢ 20 በመቶ እንዲቆጥቡ በማድረግ ልማቱን የማገዝ ሥራ መሠራቱን አመልክተዋል። ባንኩ ወደተጠቃሚዎች በመሄድ የባንክ ሂሳብ እንዲከፍቱና በየወሩ ከሚያገኙትም እንዲቆጥቡ ተከታትሎ በማስፈጸም እንዲሁም ግንዛቤ በመፍጠር እገዛ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ ቴዎድሮስ ማብራሪያ የሴፍትኔት ልማት ፕሮግራም ተጠቃሚዎች የሚውለው የሥራ ማስኬጃ ገንዘብ በዓለም ባንክ የ350 ሚሊየን ዶላር፣የኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ 150 ሚሊየን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ነው በመከናወን ላይ የሚገኘው፡፡
በዓለምአቀፍና በመንግሥት ቅንጅት እየተከናወነ ያለው የከተሞች የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ወደ ሥራ መገባቱንና በፕሮግራሙም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙና ለምግብ ዋስትና ተጋላጭ የሆኑ የከተማዋ የማህበረሰብ ክፍሎች እንደሆኑ የተናገሩት ደግሞ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ አቶ ጃንጥራር አባይ ናቸው። እንደርሳቸው ገለጻ፤ በፕሮግራሙ የመጀመሪያ ዙር በ10 ክፍለከተሞች በተመረጡ 37 ወረዳዎች የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ተተግብሮ 23ሺ948 በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ሆነዋል።በ2010 ዓ.ም በ58 ወረዳዎች 200 ሺህ፣በ2011 ዓ.ም ደግሞ በ26 ወረዳዎች 92ሺ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ የተቻለ ሲሆን፣ በዚህም ወደዘላቂ የኑሮ ማሻሻያ እንዲሸጋገሩ የማድርግ ሥራ ተሠርቷል።ዕድሉ የተመቻቸላቸው ዜጎችም በመረጡት የሥራ ዘርፍ ንግድ ሥራ ዕቅድ አዘገጃጀት ስልጠና የወሰዱና ከሚያገኙት ገቢም 20 በመቶ መቆጠብ የቻሉ መሆናቸው ደግሞ የምግብ ዋስትና የማረጋገጥ ፕሮግራሙን የበለጠ ስኬታማ ያደርገዋል፡፡
ከከተማ አስተዳደሩ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የከተማዋን የማህበረሰብ ክፍል የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል እየተከናወነ ያለውን ተግባር በማስቀጠል መቶ በመቶ የማሳካት ሥራ ይጠበቃል።ከአንዱ ምዕራፍ ወደ ሌላው እየተሸጋገሩ በተሻለ ውጤት ላይ የሚገኙትንም ደግፎ የላቀ ደረጃ ላይ የማድረሱን ተግባር የከተማ አስተዳደሩ የሚገፋበት ተግባር ነው።
ወደሌላኛው ምዕራፍ የተሸጋገሩትም ተግተውና ጠንክረው አርአያነታቸውን እንዲያስመሰክሩ መልዕክት አስተላልፈዋል። አቶ ጃንጥራር ይህን መልዕክት ያስተላለፉት በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ተዘጋጅቶ በልዩ ሥነሥርዓት በተከናወነው በከተሞች የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ለሦስት ዓመታት ተጠቃሚ የነበሩ ከድህነት ወለል በታች የሚገኙ የከተማዋ ነዋሪዎች ወደ ቀጣይ የሥራ ፕሮግራም የማሸጋገር መርሐግብር ላይ ነው፡፡
ከድህነት ወለል በታች ሆኖ መኖር ምን ያህል ከባድ እንደሆነ የኖረው ብቻ ሳይሆን የተጋራውም ያውቀዋልና እያስዋቡ ድህነትን ለማሸነፍ የሚተጉ እጆች ለሥራ መነቃቃታቸው ጥቅሙን ዘርፈ ብዙ እንደሚያደርገው መገንዘብ ይቻላል።በተለይም እንደ አዲስ አበባ ከተማ ዙሪያዋን በኢንዱስትሪ ለተከበበችና በውስጧ ከሚርመሰመሱ መኪኖች በሚወጣው ጭስና ሌሎች በካይ ነገሮች ንጹሕ አየሯን ላጣች እጅግ ወሳኝ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 14/2013