አስቴር ኤልያስ
ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ሊካሄድ የቀረው ጊዜ ጥቂት ነው፡፡ ይሁንና ምርጫውን እውን ሊያደርጉ የሚችሉ መራጮች የመራጭነት ካርዳቸውን በመውሰዱ ረገድ እያሳዩ ያለው እንቅስቃሴ አነስተኛ ነው፡፡
በእስካሁኑ ሂደት የተመዘገበውን የመራጭ ቁጥር ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ባያደርግም በአንዳንድ ቦታዎች ግን የጸጥታ ችግር መኖሩን አልሸሸገም፡፡ ምርጫንና የአገሪቱ የሰላም ሁኔታን በተመለከተና በሌሎች ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ከፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ዶክተር ዲማ ነገዎ ጋር ቆይታ አድርገን እንደሚከተለው አጠናቅረናል፤ መልካም ንባብ ይሁንልዎ፡፡
አዲስ ዘመን፡– በአሁኑ ወቅት አገራችን በአንድ በኩል ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት የሚያስችል ምርጫ ለማካሄድ ከጫፍ ደርሳለች፤ በሌላ በኩል ደግሞ ዛሬም የፀጥታና የሰላም ችግሮች አሉ፤ መፈናቀል፤ የሰው ህይወት መጥፋትና የመሳሰሉት ችግሮች ዛሬም ያልተቀረፉ ናቸው፤ ከዚህ አንጻር መጪው ጊዜ ምን ይሆናል ብለው ያስባሉ?
ዶክተር ዲማ፡– ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ከሚገለጽባቸው መንገዶች አንዱ ነው። የዴሞክራሲ ስርዓት መገለጫዎች ብዙ ናቸው። ለምሳሌ ያህል ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት፣ የመጻፍና ነጻነትና የመሳሰሉት ተጠቃሾች ናቸው።
በመሰረቱ ምርጫ አገርን ለተወሰነ ጊዜ የሚያስተዳድሩ ሰዎች የምንመርጥበት ሂደት ነው። እንደሚታወቀው በአገራችን ብዙ ጊዜ ምርጫ ተካሂዷል። ነገር ግን የተካሄዱ ምርጫዎች ምን ያህል ዴሞክራሲያዊ ነበሩ? ምን ያህልስ የሕዝቡን ፍላጎት አንጸባርቀዋል? ብለን ከጠየቅን ብዙ የሚጎድላቸው ነገሮች ነበራቸው። አንድ ተስፋ የማደርገው ነገር ቢኖር የአሁኑ ምርጫ ቀደም ሲል ከነበሩት ምርጫዎች የተሻለ እንደሚሆን ነው።
ይሁንና ሌሎች ደግሞ ያልተሟሉ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ። ማንኛውም ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የሚያሳየው ምርጫ የውድድር መድረክ መሆኑን ነው፤ ከተወዳዳሪዎቹ ውስጥ ህዝቡ የእኔን ችግር ሊፈታ ይችላል ብለው ያመኑበትን ፓርቲ የሚመርጡበት ሂደት ነው። ምን ያህል ፓርቲዎች አሉ? ምን ያህሉስ ለዚህ ተዘጋጅተዋል? ምን ያህልስ አማራጭ ለህዝቡ አቅርበዋል? ብለን ከጠየቅን ብዙ አይደለም የሚል ምላሽ ነው የሚገኘው።
ለማንኛውም ግን ባለፉት ሶስት ዓመታት ኢትዮጵያ የሽግግር ሂደት ውስጥ ነበረች። በተለይ ለረጅም ጊዜ አገሪቱን ሲያስተዳድር የነበረው አመራር ተለውጦ ሌላ አመራር ተተክቷል። እናም የተተካው አመራር ቅቡልነት ለማግኘት ወደህዝቡ መሄዱ አጠያያቂ ነገር አይደለም።
እንደእኔ አስተሳሰብ ግን ኢትዮጵያ ብዙ ውስብስብ ችግር ያለባት አገር ናት። ምርጫ ደግሞ ብቻውን እነዚህን ሁሉ የኢትዮጵያ ውስብስብ ችግሮች ይፈታል ብዬም አልገምትም። ምርጫ ሊፈታ የሚችለው ማን አገሪቱን ለተወሰነ ጊዜ ያስተዳድር የሚለውን ብቻ ነው። በአገራችን ከመንግስት ውጪ፣ ከአስተዳደሩ ውጪ እንዲሁም ከዚያም በላይ ብዙ ውስብስብ ችግሮች አሉ። የአገረ መንግስቱ ቅቡልነት በራሱ ጥያቄ ውስጥ ያለባት አገር ናት።
አንቺም እንደጠቀስሽው ሰው የሚጠፋበት ሁኔታ በጣም ብዙ ነው፤ ለዚህ ሁሉ መንስኤው ምንድን ነው የሚለውን ማጤን ተገቢ ነው እንጂ ለእነዚህ ሁሉ ችግሮች ምርጫ ብቻውን መፍትሄ ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም መፈታት ያለበት በሌላ ዘይቤ ነው። ከዚህ ውጭ በራሱ የአገረ መንግስቱን አወቃቀር የሚመለከቱ እንዲሁም የመንግስት ስርዓትን በሚመለከት ብዙ ጥያቄዎች አሉ።
ስለዚህም እነዚህ ጥያቄዎች በምርጫ አይፈቱም። በእኔ አስተሳሰብ በአገራዊ ውይይት መፈታት አለባቸው ብዬ ነው የማምነው። ይህ ውይይት ደግሞ ሊሆን የሚችለው ከምርጫ በፊትም ሆነ ከምርጫ በኋላ ነው። ውይይቱ ሰፊና ሁሉንም አካታች ቢሆን ተመራጭ ነው።
በተለይም ልዩ ልዩ በሆኑ ውስብስብ ችግሮች ላይ ተወያይቶ ለእነሱ እልባት ለመስጠት ስምምነት ላይ የመድረስ አገራችንን ወደፊት እንዴት አድርገን እናስቀጥል? ምን አይነት አገረመንግስት እናዋቅር? ምንስ አይነት የመንግስት ስርዓት ይኑረን? ህገ መንግስቱ የት ቦታ ቢሻሻል ጥሩ ነው? የሚለውና ሌሎች መሰል ችግሮች አሉ።
አሁን አሁን በአካባቢ ስም ሁሉ ስንጨቃጨቅ ነው የምንታየው። ለሰንደቅ ዓላማችን ሳይቀር የተለያየ ትርጉም ስንሰጥ ነው የምንስተዋለው። እነዚህ ሁሉ ችግሮች በጣም በርካታ በመሆናቸው ሰፊ የሖነ አገራዊ ውይይት ይፈልጋሉ። ውይይት ተደርጎም ስምምነት ላይ መድረስ ያስፈልጋል። በዚህ መልኩ ከተጓዝን የተፈጠሩት ችግሮች ሊፈቱ ይችላሉ የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡– ዘንድሮ የሚካሄደው 6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ትንሽ ተስፋ የሚጣልበት ነው ብለዋልና ከምን አኳያ ነው?
ዶክተር ዲማ፡- አንደኛ ነገር ከአካሄዱ ነው፤ አካሄዱ ምን ያህል ነጻ ነው፤ ህዝቡስ ምን ያህል በነጻነት የፈለገውን ሰው ያለምንም ተጽዕኖ መምረጥ ይችላል የሚለው አንድ ነገር ነውና ይህን ከአካሄዱ ማስተዋል ይቻላል። በፊት ይደረጉ በነበሩ ምርጫዎች ብዙ ተጽዕኖ ነበር ሲደረግ የነበረው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ማስፈራራትም ይታከልበት እንደነበር ይታወሳል። ስለዚህ በአሁኑ ምርጫ ይህ እንዳይሆን ተስፋ አደርጋለሁ። ሙሉ በሙሉ ይቀራል ብዬ በማሰብ ራሴን የማሞኝ ሰው ባልሆንም መጠነኛ እንደሚሆን ነው የማስበው።
በተለይ አንድ ፓርቲ ብቻ አብዛኛው የመንግስት መዋቅር ከላይ እስከታች በተቆጣጠረበት አገር ውስጥ በልዩ ልዩ መንገድ ተጽዕኖ ማድረጉ ይቀራል ብዬ አልገምትም። ነገር ግን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ከማየው አያያዝ ተነስቼ የተሻለ ነው የሚል እምነት አሳድሮብኛል። ሌላው ደግሞ ሁሉም በነጻነት መወዳደር ይችላል ብዬ እገምታለሁ። ሂደቱ ራሱ ይህን አመላካች ነው።
ለምሳሌ ምርጫውን የሚያስፈጽመው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ከዚህ ቀደም እንደነበረው አይነት ሳይሆን የተሻለ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ስለመሆኑ አንዱ ማሳያ ነው። ምክንያቱም ቦርዱ ስልጣን ላይ ላሉ አካላት ብቻ የማይወግኑ ሰዎች የተካተቱበት ነው ብዬ ነው ተስፋ የማደርገው። ስለዚህ ይህ አካል ምርጫን በገለልተኛነት ያስፈጽማል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
ከዛ ውጭ ደግሞ ምርጫውን በሚመለከት ውዝግብ ከተፈጠረ፣ ፓርቲዎች ችግር ካጋጠማቸው እንዲህ አይነቱን ችግር መፍታት የሚችለው የፍትህ ስርዓቱ ነው። ከዚህ በፊት የነበረው የፍትህ ስርዓቱ ጥሩ አይደለም። ስለዚህ አሁን ችግር እንኳ ቢከሰት በገለልተኝነት ፍትህ ይሰጣል ብዬ አምናለሁ። ቀደም ሲል የምርጫ ቦርድ አሰራርና የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ አንድ ነበር ማለት ይቻላል።
አሁን ግን ከዚህ አይነቱ አሰራር ወጥተናል ብዬ ስለማምን የተሻለ አሰራር ይኖራል ብዬ አስባለሁ። በዚህም ይህ ምርጫ አንድ እርምጃ ወደፊት ይወስደናል ብዬ አምናለሁ። ቀጣዩ ምርጫ ደግሞ ዘንድሮ ከሚካሄደው ይልቅ በተሻለ መንገድ ይሆናል የሚል ተስፋ አለኝ። በሂደቱ በቀጣዮች አስርና አስራ አምስት ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንደሚሰፍንበት አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡– ከምርጫ በፊት ወይም ደግሞ ከምርጫ በኋላ አገራዊ የሆነ ውይይት መደረግ አለበት ብለዋል፤ በውይይቱ ይፈታሉ ብለው የሚያስቡት የትኞቹ አይነት ችግሮች ናቸው?
ዶክተር ዲማ፡- እንዳልኩት ያሉት ችግሮች ብዙና ውስብስብ ናቸው። የአገራዊ ውይይቱ ዋና አካል መንግስት ነው። ሌሎች ደግሞ ፓርቲዎች ናቸው። እንዲሁም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው። ስለዚህ በቀጣይነት ውይይቱ መካሄድ ያለበት ነው። ከዚሁ ጎን ለጎን ከሌሎች አገሮች ልምድ መቅሰም ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡– ለምሳሌ ከየትኞቹ አገሮች…?
ዶክተር ዲማ፡– እንግዲህ ለውጥ የተካሄደባቸው አገሮች ብዙ ናቸው። ከእነዚህም መካከል ደቡብ አፍሪካ አንዷ ናት። በምክክርና በውይይት አንዳንድ ችግሮቻቸውን መፍታት ችለዋል። ኬኒያም ሆነች ቱኒዚያ በተመሳሳይ ሂደት ውስጥ አልፈዋል። በዚህ ውስጥ ያለፉ ብዙ አገሮች ቢሆኑም የሁሉም ችግር አንድ አይነት ነው ማለት አይቻልም። እያንዳንዱ አገር የራሱ ችግር አለው። እናም እኛም የአገራችንን ችግር እንዴት አድርገን እንፍታ በሚለው ላይ መጀመሪያ በራሱ ስምምነት ላይ መድረስ የግድ ይለናል።
በዚህ ዙሪያ በተለያየ መንገድ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ አካላት አሉ። ለነገሩ የሰላም ኮሚሽን ተቋቁሞ እንቅስቃሴ እንደተጀመረ ነው የሚታወቀው። ይሁንና እስካሁን ድረስ ምን ያህል እንደሰራ ብዙ አናውቅም። ነገር ግን አንዱ ስራው ይህ ነው ለማለት ነበር። እናም በቀጣይ ይሰራል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።
አዲስ ዘመን፡– በአሁኑ ወቅት ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ ግብጽና ሱዳን ከፍተኛ ተጽዕኖ ለማድረግ ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ ይገኛሉ፤ ይህ በኢትዮጵያ ላይ ምን ተጽዕኖ ይኖረዋል ብለው ያስባሉ?
ዶክተር ዲማ፡- እንደሚታወቀው ከውጭ በኩል ኢትዮጵያ ላይ ብዙ ተጽዕኖ አለ። የህዳሴ ግድብ ላይ ብቻ አይደለም ተጽዕኖ እየደረሰብን ያለው፤ እሱ አንዱ ሊሆን ይችላል። ከዚህ ውጭ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ የሰብዓዊ መብት ተቋማት የመሳሰሉት በአገራችን ላይ ከፍተኛ የሆኑ ተጽዕኖ እያደረሱብን ነው።
በግብጽና በሱዳን በኩል እየመጣብን ያለው ተጽዕኖ በአንድ በኩል ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በአገር ውስጥ ተወጥራ የተያዘች አገር ናት። ስለዚህም የውጪው ኃይል እድሉ ያለን አሁን ነው በሚል ነው ተጽዕኖውን እያደረሱ ያሉት። ይህም ከረጅሙ ትግል ውስጥ የሚካተት ነው። ይህን ግን ኢትዮጵያ ትወጣዋለች ብለን እናምናለን።
ኢትዮጵያ በራሷ የተፈጥሮ ሀብት የመጠቀም መብቷ በማንኛውም የተፈጥሮ ህግ የተጠበቀ ነው። ሀብቷን ህጉን ተከትላ በመጠቀሟም ማንም ሊጠይቃት አይችልም። ነገር ግን ይህ ማለት ሌሎችን ለመጉዳት ሳይሆን ፍትሃዊ አጠቃቀም ላይ በመመስረት ነው። ግብጽና ሱዳን የቱንም ያህል ተጽዕኖ ለመፍጠር ቢጥሩም ኢትዮጵያን በሀብቷ እንዳትጠቀም ለማድረግ አይቻላቸውም። ይህን ለማድረግ መብትም ችሎታም የላቸውም።
እንዲህም ሆኖ በኢትዮጵያ በኩል አንዳንድ ድክመቶች መኖራቸው አይካድም። ከዚህም አንዱ በውጭ ግንኙነት ላይ ብዙ ያልተሰራ ስራ አለ። በመሆኑም እሱ ላይ ጠንከር ያለ ስራ መስራት ያስፈልጋል። የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስጠበቅ በውጭ አገር የተሰማሩ ዲፕሎማቶቻችን ተጠቃሾች ናቸው። ዋና ስራቸው የአገራችንን ጥቅም ማስጠበቅ ነው። ስለዚህ በዚህ ላይ በአግባቡ መስራት ያስፈልጋል።
ሁለተኛው ደግሞ አገር ውስጥ ያሉትን ውስብስብ ችግሮች በጊዜ መፍታትና እልባት መስጠት ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ችግር ካለ እና የእርስ በእርስ አለመግባባት ካለ የውጭ ኃይሎች የሚጠቀሙበትን መንገድ እንደማበጀት ይቆጠራል። ይህ እንዳይኖር ለእነዚህ ሰዎች ምንም አይነት ቀዳዳ አለመክፈት ነው። ቀዳዳ ካለ ቀዳዳውን ቶሎ መድፈን ነው።
አዲስ ዘመን፡– በተለይ የውጪውን እና የግብጽን ጫና እንዴት ያዩታል?
ዶክተር ዲማ፡– ግብጽ የተለያዩ አገራት መንግስታት አጠገቧ እንዲቆሙ የተለያየ ተግባር ስትፈጽም ቆይታለች። በተለይ ደግሞ ያለውን እውነት በማዛባት ታቀርባለች። ኢትዮጵያ ግብጽ ውሃ እንዳታገኝ አድርጋለች በሚልም ጭምር ነው እውነትን አዛብታ የምታቀርበው። እንደሚታወቀው ግብጽ በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ ከእኛ የተሻለ ሰዎች አላት። የቱንም ያህል ከምዕራባውያን አገራት የተሳሰረች ቢመስልም የትኛውም የዓለም አቀፍ ህግ ግን የአባይን ውሃ ለግብጽ ነው የሚል የለም።
እንዲህም አይነት ውጣ ውረድ ሊመጣ የቻለው በኢትዮጵያ በኩል መሰራት የተገባው ስራ ባለመሰራቱ ነው። ከእርሷ ጎን ናቸው በሚባሉ አገራት ላይ እንኳን እውነታውን በመግለጽ ተጽዕኖ ማሳደር ስንችል ስራ ግን አልተሰራም ብዬ ነው የምገምተው።
አዲስ ዘመን፡– በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት እየተከሰተ እንደሆነ ይታወቃል፤ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
ዶክተር ዲማ፡– የኑሮ ውድነት ችግር የመነጨው ከየት ነው የሚለውን መሰረት አድርጎ ጥናት ማካሄድ ጠቃሚ ይመስለኛል። ለምሳሌ የኑሮ ውድነቱ የመጣው ከምርት ጉድለት ነው ብሎ መጠየቅም መልካም ነው። ዋጋ የጨመረው አገር ውስጥ የሚመረቱ ግብዓቶች ላይ ከሆነ የምርት ጉድለት በመኖሩ ነው ማለት ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ ምርትን ማሳደግ የግድ ይላል ማለት ነው። ዋጋ የጨመረው ከውጭ አገር ከሚመጡ እቃዎች ላይ ከሆነ እንደሚታወቀው ከውጭ የሚመጣ እቃ ወደአገር ውስጥ ሲገባ የውጭ ምንዛሬን የሚጠይቅ ነው።
ከረጅም ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ የውጪና የገቢ ንግድ ሚዛኑ ከውጪ የምናስገባቸው ምርቶች ላይ ያዘነበለ ነው። ወደውጭ የምንልካቸው እቃዎች የተወሰኑ ቢኖሩም የምናስገባቸው ግን ይበዛሉ። እንደዛም ሆኖ ግን ወደውጭ የምንልካቸው ምርቶች ቀንሰዋል። በዚህም ምክንያት የውጭ ምንዛሬያችን እንዲሁ ዝቅ እያለ ነው የሄደው። በመሆኑም ይህ በገበያ ላይ የራሱ የሆነ ተጽዕኖ አለው።
ለምሳሌ የውጭ ምንዛሬን በሚመለከት ያለው ሁለት አይነት ገበያ ነው። በግልጽ በባንክ የሚደረገው ግብይት አንዱ ሲሆን፣ በድብቅ ጥቁር ገበያ የሚባለው ሌላው ነው። ይህን መንግስት ሊያጠናው ይገባል። ይህ ሁሉ በኑሮ ውድነት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር ነው። በመሆኑም በአንድ በኩል የዚህን ችግር መንስዔ መንግስት አጥንቶ እልባት መስጠት አለበት። መፍትሔ መፈለግ ይኖርበታል። በሌላ በኩል ደግሞ በተጨማሪ ነጋዴዎች ዋጋ እየጨመሩ ያሉት ያለአግባብ ከሆነ በዚህ ዙሪያም ቁጥጥር ማድረግ ያስፈልጋል ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡– ከህብረተሰቡስ ምን ይጠበቃል?
ዶክተር ዲማ፡– በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ስናየው
ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ ሙስና ተንሰራፍቷል። ይህን ሙስና ለመቆጣጣር ተቀባዩን ብቻ ሳይሆን ሰጪውንም ነው ከግምት ውስጥ ማስገባት የሚገባው። በዚህ ጉዳይ በተለይ ህብረተሰቡ መተባባር አለበት። ህጎች መከበር አለባቸው። የፍትህ ስርዓቱ በጥቅሉ በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት አለበት። አብዛኛው ችግር ናቸው የምንላቸው ነገሮች ሁሉ የተያያዙ ናቸው። በመሆኑም በአንድ አይነት አካሄድ ብቻ መቅረፍ አይቻልም። ሁሉም በትብብር መስራት ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን፡– በቅርቡ እርስዎ ያሉበትና በርካታ ምሁራንን ያቀፈው የኢትዮጵያ ገለልተኛ ብሄራዊ የኢኮኖሚ ምክር ቤት መቋቋሙ ይታወሳል፤ ለመሆኑ ይህ ማህበር ምን እየሰራ ነው፤ እሰካሁንስ ምን ተግባራትን አከናወነ?
ዶክተር ዲማ፡– ገና በመደራጀት ላይ ያለ ምክር ቤት እንደመሆኑ ብዙ ሰራን ማለት አይቻልም። እኔ እስከማስታውሰው የመጀመሪያውን ስብሰባ ብቻ ነው ያካሄድነው። የተወሰኑ ኮሚቴዎች ተቋቁመው እንዴት እንደራጅ በሚሉ ጉዳዮች ላይ አንዳንድ ዝግጅት እንዲደረግ ተደርጓል። ሁለተኛው ያደረግነው ስብሰባ ደግሞ እነዚህ የተዋቀሩ ኮሚቴዎች ሪፖርታቸውን ባቀረቡበት ጊዜ ነው።
ለማንኛውም ምክር ቤቱ በመደራጀት ላይ ያለ ነው። አብዛኛዎቹ የምክር ቤቱ አባላት ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉ ሰዎች ናቸው አገር ቤት ያሉት ውስን ናቸው ስብሰባውም በኦንላይን ነው እንዲያም ሆኖ አብዛኛው አባል ባለሙያዎች በመሆናቸው በምጣኔ ሀብት ብቻ ሳይሆን በተለያየ መስክ የተሻለ ሐሳብን ማፍለቅ የሚችሉ ናቸው።
ከዚህ ምክር ቤት የሚጠበቀውም አጠቃላይ የሆነ ምክርና ሐሳብ ነው። ለምሳሌ የአስር ዓመት የኢኮኖሚ ፕላን የመሳሰለው ላይ ነው ምክር የሚሰጠው። ለምሳሌ ይህ ፕላን ምን ያህል ወደፊት ሊሄድ ይችላል፤ ምን አይነት እንቅፋት ሊያጋጥም ይችላል፤ በመንግስትስ በኩል ምን ያልታዩ ችግሮች አሉ፤ ይህን ችግር ለመወጣትስ መንግስት ምን ማድረግ አለበት። ያልታሰቡ ነገሮች ደግሞ በመሃል ሊያጋጥሙ ይችላሉና ያንን መወጣት የሚቻለው እንዴት ነው የሚለውንና ሌሎች ጉዳዮች ላይ በምክርም በሐሳብም ሙያዊ እንቅስቃሴ የምናደርገው።
አዲስ ዘመን፡- ምክር ቤት ከተቋቋመ ወራት ተቆጥረዋልና አንዴ ብቻ ዘገያችሁ አያስብለውም? ፈጥናችሁ ያልተገናኛችሁበት ምክንያትስ ይኖር ይሁን? ወይስ ትክክለኛው አካሄድ ላይ ናችሁ?
ዶክተር ዲማ፡- የምክር ቤቱ ሴክሬቴርያት የፕላን ኮሚሽን ነው። የመጀመሪያውንም ስብሰባ የጠራው ይኸው ኮሚሽን ነው። እስኪጠራን ድረስ መዘግየቱ የታወቀ ነው ሁለተኛው ደግሞ የመጀመሪያው ስብሰባ ከተደረገ በኋላ እንዳልኩሽ የተቋቋመው ኮሚቴ ነው። ጊዜውም ለስብሰባ ትንሽ ከበድ የሚል ነው ወረርሽኙም አንዱ ሳንካ ነበር።
በቀጣይ በግልም ሆነ በቡድን የተለያዩ ጥናቶች ይካሄዳሉ ብዬ አስባለሁ፤ እነዚህ ጥናቶች ላይ ሁሉም የምክር ቤቱ አባላት ሐሳባቸውን ሰንዝረው ጉዳዩ ተመርምሮ ለወደፊት ለኮሚሽኑ ማቅረብ ነው።
አዲስ ዘመን፡– እንደምክር ቤት አባልነታችሁ በኢኮኖሚው ዘርፍ ያልታዩ ጉዳዮችን ከመካከላችሁ ተነሳሽነቱን ወስዶ ለመንግስት ጠቆም ያደረገስ አካልይኖር ይሆን?
ዶክተር ዲማ፡– ሊኖር ይችላል፤ ምክንያቱም አብዛኞቹ በውጭ አገርም ያሉ ሆነ በአገር ውስጥ ያሉ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ናቸውና ስብስቡ የባለሙያተኞች ነው። አብዛኞቹ ባለሙያዎች ቀደም ብሎም በዘርፉ በምርምር ስራ ላይ የተሰማሩ በመሆናቸው የአገሪቱን የኢኮኖሚ ችግር ያውቁታል። ስለዚህ ለአገሪቱ ይጠቅማል የሚል ሐሳብ ከማቅረብ አይቦዝኑም፤ የምክር ቤቱ አባላት አገልግሎቱን የሚሰጡት በነጻ ነውና ህጸጽም ካለ እንዲሁም ጠቃሚ የሆነ ነገርም ካለ ከማመላከት አይቦዝኑም ማለት እችላለሁ ስራዎች ግን በመሰራት ላይ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡– ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ሃገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ማሻሻያ አድርጋ እየሰራች ነው፤ ለመሆኑ ይህ ለሃገራዊ እድገት የሚኖረው ፋይዳ ምንድነው?
ዶክተር ዲማ፡– ዝርዝር እቅዱን አላየሁም፤ ጠቅላላ ግንዛቤ ነው ያለኝ። አብዛኛው የአገራችን ችግር የሚመነጨው ከአገሪቷ ኋላቀርነት የተነሳ ነው። እንዲህም ስል ለምሳሌ የምርት አለማደጉ አንዱ ተጠቃሽ ነው። ሌላው ደግሞ የቴክኖሎጂ ኋላቀርነት አለ። በአገራችንም አሁንም ድረስ እህል የሚመረተው ኋላቀር የአስተራረስ ዘዴ በመጠቀም ነው። አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን ሲያርሱበት በነበረ እቃ ነው ዛሬም እየተገለገልን ያለነው። ይህ ደግሞ ምርታማነትን መጨመር ስለማይችል ቴክኖሎጂው መቀየር አለበት። በአገራችን በነፍስ ወከፍ የሚመረተው ምርትም በጣም አነስተኛ ነው።
አገሪቱ ምርታማ ብትሆን ፋይዳው ብዙ ነው። ኢኮኖሚያችን አደገ ማለት በማህበራዊ ዘርፍ፣ በኢኮኖሚ ዘርፍና በፖለቲካው ዘርፍ ያለው ችግር ሁሉ ሊፈታ ይችላል። ሰው በበቂ ሁኔታ አምርቶ የተደላደለ ኑሮ መኖር ከቻለ ላልተገባ አካሄድ ሊያጋልጥ አይችልም። ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በዘርፉ ያቀደችው የኢኮኖሚ እቅድም ዋና ዓላማ አገሪቱን በተወሰኑ ዓመታት ውስጥ ከድህነት አውጥቶ ወደመካከለኛ ገቢ ወዳላቸው አገሮች ተርታ ለማሰለፍ ነው። ዋናው ነገር የታቀደውን እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ መረባረብ ነው። በንጉሰ ነገስቱም ጊዜ የዚህን ያህል ዓመት የኢኮኖሚ ፕላን እየተባለ እቅድ ይታቀዳል፤ ነገር ግን ምን ያህል ተግባራዊ ሆነ ወደሚለው ሲመጣ ችግር ነው። እናም በየጊዜው አሁን የታቀደውን ፕላን የየዓመቱንም ቢሆን መገምገሙ ያለንበትን ደረጃ ያመላክተናል።
አዲስ ዘመን፡- ምርጫውን አስመልክተው መልዕክት ካልዎት?
ዶክተር ዲማ፡- ምርጫው ወሳኝ የሚሆነው ህዝቡ ተሳታፊ መሆን ሲችል ነው። ስለዚህም ይህ ምርጫ ህዝቡን ምን ያህል አነሳስቷል ብሎ መጠየቁ ተገቢ ይመስለኛል። እየተመዘገበ ያለውስ ምን ያህሉ ነው፤ አንዳንድ አገሮች ላይ አንድ ሰው የአገሪቱ ዜጋ እስከሆነ ድረስ የምርጫው ካርድ በየቤቱ ይደርሰዋል። እኛ አገር ደግሞ ለመራጭነት ተሰልፎ መመዝገብን ይጠይቃል። ያልተመዘገበ ሰው አይመርጥም። ስለዚህም በኋላ ላይ ያልፈለኩት ፓርቲ ነው የተመረጠው ብሎ ከመጸጸት የቀረው ጊዜ በጣም ጥቂት እንደመሆኑ ለመምረጥ የሚያስችለውን የመራጭነት ካርድ መያዙ መልካም ነው።
በእርግጥ በእስካሁኑ ሂደት ምን ያህል ሰው እንደተመዘገበ የሚታወቅ ነገር የለም። ይህን መረጃ ሊነግረን የሚገባው ምርጫ ቦርድ ነውና ሊነግረን ይገባል። እንደሚገባኝ ብዙ ሰው መመዝገብ እንዲችል ማበረታታትና ማነሳሳት አስፈላጊ ነው። ሰው የፈለገውን አካል ይምረጥ እያንዳንዱ ፓርቲ ግን ህዝቡን ማነሳሳት ይጠበቅበታል። በከተማዋ ውስጥ እንኳ እስካሁን የሚያነቃቃ ፓርቲ አላስተዋልኩም። አብዛኛው በከተማው ውስጥ የሚታየውም ጽሁፍ የብልጽግና ፓርቲ ነው። ፓርቲዎቹ ቢያነቃቁም እኔን ምረጡኝ በሚል ሐሳብ የተጠመዱ ናቸው እንጂ ለመራጭነት የሚያስችላችሁን ካርድ ውሰዱ ሲሉ አይደመጥም።
ዋናው ግን ምርጫውን ዴሞክራሲያዊ ማድረጉ ላይ ነው መበርታት የሚጠበቀው። ያለፉት ምርጫዎች ችግር ያለባቸው መሆኑ ታውቆ የአሁኑ ግን የተሻለ ልምድ ሊወሰድበት የሚችል ምርጫ ማድረጉ ላይ ቢሰራ መልካም ይሆናል። በአገራችን ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያምም ምርጫ አድርጎ ነበር፤ ነገር ግን ስድስተኛ እየተባለ የሚቆጠረው ከኢህአዴግ ጀምሮ ያለው ነው። እንዲያም ሆኖ ግን ምርጫዎቹ ዴሞክራሲያዊ ባለመሆናቸው የሚያመሳስላቸው ናቸው ማለት ይቻላል። አሁን ለሚካሄደው ምርጫ ግን ሁሉም ለዴሞክራሲያዊነቱ የየራሱን አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡኝ ማብራሪያ በጣም አመሰግናለሁ።
ዶክተር ዲማ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 11/2013