አዲስ አበባ፡- የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በቅርቡ ያደረገውን የንግድ ቤቶች ኪራይ ዋጋ ተከትሎ የተነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት የወሰደው እርምጃ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ አሁንም ከደንበኞች የሚቀርቡ ጥያቄዎችን በመመርመር በድጋሚ ሦስት ማሻሻያዎችን ማድረጉን ገለጸ፡፡
ኮርፖሬሽኑ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ባደረሰው መረጃ እንዳስታወቀው፤ ኮርፖሬሽኑ ያደረገውን የኪራይ ማሻሻያ ውሳኔ በመቀበል በሁሉም ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ አብዛኛዎቹ ደንበኞች ውል እየፈጸሙ ይገኛሉ፡፡ በሂደቱም ከአፈጻጸምና አተገባበር ዙሪያ ደንበኞች የሚያቀርቧቸውን ቅሬታዎችም ለመፍታት ከሚሰራቸው ተግባራት በተጓዳኝ ከደንበኞች የቀረቡ ጥያቄዎችን በመመርመር በሦስት ጉዳዮች ላይ ማሻሻያዎችን አድርጓል፡፡
ከእነዚህ መካከል አንዱ፤ የድርጅት ወይም የቢሮ ቤት ተከራዮች ካላቸው የሥራ ባህርይና ከሚሰጡት አገልግሎት አኳያ ያደረገው ማሻሻያ ሲሆን፤ በእነዚህ ላይ የተደረገው ማሻሻያ በራሱ በሦስት ምድብ ተቀምጧል፡፡ የመጀመሪያው፣ ለትርፍ ያልተቋቋሙ ከሚሰጡት አገልግሎት መነሻነት ገቢ የማያመነጩና በአባላት መዋጮ የሚተዳደሩ ተቋማትና ማህበራትን የሚመለከት ሲሆን፤ ገቢ የሌላቸው የሙያ ማህበራት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ሲቪክ ማህበራት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የአካል ጉዳተኛ ማህበራት፣ ህዝባዊ መሰረት ያላቸው የልማት ማህበራት፣ የሕዝብ ትምህርት ቤቶች እና የመንግሥት የጤና ተቋማት የተካተቱበት ነው፡፡
እነዚህ ተቋማትም፣ ገቢ እንደሌላቸው ወይም በአባላቶቻቸው መዋጮ እንደሚተዳደሩ መረጃ እያቀረቡ ቀድሞ ይከፍሉ በነበረው የኪራይ ተመን መሰረት እየከፈሉ እንዲቀጥሉ ኮርፖሬሽኑ ወስኗል፡፡ የእዚህ ምድብ ሁለተኛዎቹ ደግሞ በመንግሥት በጀት የሚተዳደሩ መንግሥታዊ ተቋማት፣ ለትርፍ ቢቋቋሙም የትርፍ ሕዳግ ተበጅቶላቸው በውስን ትርፍ ሕዝብ የሚያገለግሉ፣ ተቋማትና ማህበራት ሲሆኑ፤ እነዚህ በካሬ ሜትር በብር 140 የኪራይ ተመን እንዲቀጥሉ ተወስኗል፡፡
ሦስተኛው ምድብ ደግሞ፣ መነሻቸው የንግድ ባህርይ ያለውና ለትርፍ የተቋቋሙ መንግስታዊ የልማት ድርጅቶች፣ የግል ድርጅቶች፣ ኢንዶውመንቶች፣ አምራች ድርጅቶች፣ በአማካሪ ስራ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች ሲሆኑ፤ በአዲሱ በተወሰነው የንግድ ቤቶች የኪራይ ተመን መነሻ መሰረት እንዲቀጥሉ ተወስኗል፡፡
በመረጃው እንደተመላከተው፤ ሌላው ማሻሻያ የተደረገበት ጉዳይ ለንግድ አገልግሎት የዋሉ ቤቶችን አከረያየት ላይ የተሰጠ ሲሆን፤ ማሻሻያውም በማንኛውም ዘርፍ ላይ ቢሆን ለንግድ አገልግሎት የዋሉ ቤቶችን የተከራዩ ነጋዴዎች ባለው በአዲሱ የኪራይ ተመን መነሻ መሰረት ክፍያው የሚቀጥል ሆኖ በአከፋፈሉ ላይ የተደረገ ነው፡፡
በዚህ መሰረት፤ ከዚህ በፊት የኪራይ አፈጻጸሙ በ3 ዓመት ጊዜ ውስጥ ተከፋፍሎ በመጀመሪያው ዓመት 35 በመቶ፣ ሁለተኛው ዓመት 70 በመቶ፣ የመጨረሻው 3ኛ ዓመት 100 በመቶ ተከፋፍሎ ውል እንዲፈጽሙ የተወሰነው እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ከዝግጁነትና ከአቅም ጋር ተያይዞ በተዘጋጀው መስፈርት መሰረት ደንበኞች በሚያቀርቡት መረጃ ላይ መሰረት በማድረግ በመጀመሪያው ዓመት ላይ የክፍያ መጠኑ 20 በመቶ እንዲሆን፣ በ2ኛው ዓመት ዘንድሮ ያልተከፈለው 15 በመቶ እና የቀጣዩን ዓመት 50 በመቶ ተጨምሮ 85 በመቶ እንዲሆን፣ የ3ኛውና የማጠቃለያው ዓመት ላይ 15 በመቶ ጨምሮ 100 በመቶ አጠቃሎ እንዲከፍሉ ይደረጋል፡፡
ሆኖም ለእዚህ ውሳኔ አፈጻጸም፣ የደንበኛው ጥያቄ በጽሁፍ ማቅረብ፣ በሚቀርበው ውሳኔ መሰረት ለመጠቀም በቅድሚያ የውል ስምምነት መፈጸም፣ ከገቢዎች ሚኒስቴር እና ከአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ዓመታዊ ገቢ (የቀን ገቢ) ማስረጃ እና የንግድ ፈቃድ የካፒታል መጠን መቅረብ ይጠይቃል፡፡ የቀረበውን መረጃም ኮርፖሬሽኑ በራሱ መንገድ የሚያረጋግጥ ይሆናል፡፡
ማሻሻያ የተደረገበት ሦስተኛው ጉዳይ ከህንፃ ከፍታ ጋር ተያይዞ የቀረቡ ቅሬታዎችን አስመልክቶ የተደረገ መሆኑን የሚያሳየው መረጃው፤ ህንፃዎች ከፍታቸው በጨመረ ቁጥር ኪራይ ተመኑ መቀነስ እንደሚገባው የቀረበው ጥያቄ በኮርፖሬሽኑ በኩል ተቀባይነት ማግኘቱን ያመላክታል፡፡ የስፋትና የአካባቢ ደረጃ መቀነስ እንደተጠበቀ ሆኖ የስፋት መጠናቸው ተመሳሳይ እና ልዩነት ያላቸው እየተለዩ የኪራይ መጠኑ የህንፃዎቹ ከፍታ በጨመረ ቁጥር የኪራይ ተመኑም እንዲቀንስ የሚደረግ እንደሆነ እና የኪራይ መጠኑ በየቤቱ አድራሻ ተዘርዝሮ በቀጣይ ለደንበኞች ይገልጻል፡፡
ከዚህ ባለፈ ያሉ ማናቸውም ቅሬታዎችን በተመለከተ ግን በማናቸውም ሁኔታ ሕጉንና መመሪያውን አክብረው በተናጠል የሚቀርቡ ቅሬታዎችን ኮርፖሬሽኑ የሚቀበል መሆኑን፤ ለጥያቄዎቹም በቅድሚያ በቅርንጫፍ፣ በመቀጠልም በማእከል በጽሁፍ ምላሽ እንዲሰጥ እንደሚደረግ ተመላክቷል፡፡ በተለይም የካሬ ሜትር ልዩነቶች፣ የአካባቢ ቅንስናሾች፣ የቤት ደረጃ ጥያቄዎች፣ የስሌት ጥያቄዎችና ሌሎች ማንኛውንም አይነት ቅሬታዎችን በተናጠል በማስተናገድ አስፈላጊ ምላሾች እንዲሰጡ እንደሚደረግም አረጋግጧል፡፡
ይሁን እንጂ እነዚህ የማሻሻያ ውሳኔዎች ተፈጻሚ እንዲሆኑ፤ ማንኛውም ደንበኛ ውሉን እስከ የካቲት 14 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ባሉት የሥራ ቀናት መፈጸም እንዳለበት እና በተሰጠው ውሳኔ ውሉን ያልፈረመ ደንበኛን ኮርፖሬሽኑ ጥያቄውን እንደማያስተናግድ ተገልጿል፡፡ ይህ እድል መንግሥትና ኮርፖሬሽኑ የደንበኞችን ጥያቄ በትእግስት በማድመጥ ለመጨረሻ ጊዜ የተሰጠ ምላሽ መሆኑን በመረዳት በተሰጠው ውሳኔና በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ውላቸውን የማይፈጽሙ ደንበኞች በደንበ ኝነታቸው ለመቀጠል እንዳልፈለጉ ታወቆ ኮርፖሬሽኑ ውለታቸውን የሚያቋርጥ መሆኑም ተመላክቷል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 7/2011
ወንድወሰን ሽመልስ