አስናቀ ፀጋዬ
የከበሩ ማዕድናትን ጨምሮ ሌሎች ለግንባታና ለኢንዱስትሪ ግብአትነት የሚውሉ ማዕድናት በስፋት እንደሚገኙበት ይነገራል። የኮንስትራክሽን ማዕድናት በተለይ ደግሞ ጥቁር ድንጋይ በሁሉም አካባቢዎች ላይ አቅፎ መያዙ በዚህ የማዕድን ሃብት የታደለ አሰኝቶታል። በጥቂቱም ቢሆን የአሸዋ ሀብትም አለው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የብረትና የድንጋይ ከሰል ማዕድናትን በጥናት ፈትሾ በተለይ የብረት ማዕድኑን በባህላዊ መንገድም ቢሆን እያመረተ ይገኛል።
ይሁን እንጂ በክምችት ደረጃ አለኝ የሚላቸው ሌሎች የከበሩ ማዕድናት ከጥቂቶቹ በስተቀር ጥናት ያለያቸው ባለመሆኑ ጥቅም ላይ እየዋሉ አይደለም። የኮንስትራክሽን ማዕድናቶቹ ግን ከከበሩ ማዕድናቶቹ በተሸሻለ መልኩ ጥቅም ላይ እየዋሉ በመሆናቸው መፅናኛዎቹ ሆነዋል- በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የሚገኘው የከፋ ዞን።
የከፋ ዞን ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ ሃላፊ አቶ አፈወርቅ አለሙ እንደሚገልፁት በዞኑ እስካሁን ድረስ በጥናት ተረጋግጦ ጥቅም ላይ የዋለ የከበረ ማዕድን ሃብት የለም። ይሁንና በብረት ማዕድን ላይ የአዋጭነት ጥናት ተጠንቶ ናሙና ተገኝቷል። ጠና ወረዳ ላይ 35 ከመቶ የብረት ማዕድን ያለ መሆኑም ተረጋግጧል።
በተመሳሳይ በጠሎ ወረዳም የድንጋይ ከሰል መኖሩ በክልል ባለሙያዎች ታውቋል። በጠና ወረዳ ላይ ያለው የብረት ማዕድንም በዘመናዊና በቴክኖሎጂ በተደገፈ መልኩ እየተመረተ ባይሆንም የአካባቢው ሰዎች በባህላዊ መንገድ ማዕድኑን በማውጣት እየተጠቀሙበት ይገኛሉ። የድንጋይ ከሰል ማዕድኑን ጥቅም ላይ ለማዋል ግን በሂደት ላይ ይገኛል።
ከብረትና ድንጋይ ከሰል ውጪ ያሉና በዞኑ አሉ ተብለው የሚታሰቡ ሌሎች የከበሩ ማዕድናትን በጥናት አውቆ ጥቅም ላይ ከማዋል አኳያ ውስንነቶች አሉ። ለዚህም በዘርፉ የሰለጠነ ባለሙያ፣ የማዕድን መፈለጊያ መሳሪያዎች በበቂ ሁኔታ አለመገኘትና የሃብት ማነስ በምክንያትነት ይጠቀሳሉ። መምሪያው በዞኑ ያሉ ማዕድናት በጥናት ተለይተው ጥቅም ላይ እንዲውሉ ፍላጎት ያለው ቢሆንም ያሉትን ችግሮች በተደጋጋሚ ለክልሉ አሳውቋል። በብረትና በድንጋይ ከሰል ማዕድናት ላይ የተሰራው ጥናትም በመምሪያውተደጋጋሚ ግፊት የተከናወነ ነው።
እንደ ኃላፊው ገለፃ ከብረትና ከድንጋይ ከሰል ማዕድናት ውጪ ገፀ መሬት ላይ ያሉና ለግንባታ ግብአትነት የሚውሉ የድንጋይና አሸዋ ማዕድናት በስፋት እየተመረቱ ጥቅም ላይ ይውላሉ። በተለይ ጥቁር ድንጋይ በዞኑ ባሉ አስራ ሁለት ወረዳዎችና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች ውስጥ ይገኛል።
በእነዚህ አካባቢዎች ላይም ወጣቶች ተደራጅተው በባህላዊ መንገድ ጥቁር ድንጋይ እያመረቱ ለገበያ ያቀርባሉ። ከዚህ ማዕድን ምርት ከሚገኘው ገቢም አራት ከመቶ ያህሉ በሮያሊቲ የአገልግሎት ክፍያ ለዞኑ ገቢ ይሆናል።
የአሸዋ ምርትም በዞኑ እንደልብ ባይገኝም በየአካባቢው ከወንዞች የሚወጣ የአሸዋ ምርት አለ። የአሸዋ ምርቱ ከወንዝ ሲወጣ የብዘሃ ህይወቱን ይጎዳል የሚል እምነት ስላለም ምርቱ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ሆኖም ውሃውን በማይጎዳ መልኩ አሸዋው ጥቅም ላይ የሚውልበት ሁኔታም አለ። በዚህም ወጣቶች በተመሳሳይ ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ።
ይሁንና የኮንስትራክሽን ማዕድን አውጪዎቹ የሮያሊቲ አገልግሎት ክፍያ ከመፈፀም አኳያ መጠነኛ ክፍተቶች ይታይባቸዋል። በመንግስትም በኩል በተለይ የመሰረተ
ልማቶችን ለመገንባት የኮንስትራክሽን ማዕድናትን ሲጠቀም የሮያሊቲ አገልግሎት ክፍያዎችን ያለመክፈል ችግሮች ይታያሉ። ከዚህ ባሻገር ግን የኮንስትራክሽ ማዕድናቱ በሚወጡባቸው አካባቢዎች ላይ የጎላ የመንገድ መሰረተ ልማት ተደራሽነት ችግር አይታይም።
በዚሁ የኮንስትራክሽን ማዕድን ማምረት ስራ በማህበር ተደራጅተው ተጠቃሚ እየሆኑ ያሉ ወጣቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መጥቷል። ይሁንና በዞኑ የውሃ፣ ማዕድንና ኢንርጂ መምሪያና ከወጣቶች ስራ እድል ፈጠራ ፅህፈት ቤት ጋር ተቀናጅቶና ተናቦ ከመስራት አኳያ ውስንነቶች ይታያሉ። ወጣቶቹ ከኦሞ ማይክሮ ፋይናስ ጋር በመሆን ገንዛባቸውን እንዲቆጥቡ ግን አበረታች ስራዎች እየተከናወነ መሆኑን ይናገራሉ።
የንግድና ኢንዱስትሪ ፅህፈት ቤት በዞኑ የሚገኘውን የብረት ማዕድን በስፋት በማስተዋወቅ ኢንዱስትሪዎች እንዲጠቀሙበት ከማድረግ አኳያም ክፍተቶች ይታዩበታል። ከመንግስት ሰራተኞች መዋቅር ጋር ተያይዞም መዋቅሩ ባለሙያ ለማግኘት እንቅፋት በመሆኑ ከክልል ባለሙያ ወደዞኑ ያለመምጣት ውስንነት መኖሩን ነው ያስታወቁት።
በቀጣይም የሰራተኞች መዋቅር ተስተካክሎ ሲመጣ የዞኑ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ ያለበትን የባለሙያ እጥረት ይፈታል ተብሎ ይጠበቃል። በሌላ በኩል ደግሞ ዞኑ ከደቡብ ምእራብ ጋር በመደራጀት ክልል የመመስረት ተስፋ ያለው በመሆኑ የማዕድን ሃብቱን በቅንጅት ለመስራት ያስችለዋል። በይበልጥ ደግሞ መዋቅሩ ሲስተካከል ከዩኒቨርስቲዎች በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን ቀጥሮ የማሰራት እድል ይኖረዋል።
መምሪያውን ጨምሮ ሌሎች ከማዕድን ዘርፉ ጋር በተያያዘ የሚመለከታቸው አካላትም ተናበው የመስራት ፍላጎት አላቸው። ይህንንም በእቅድ ጭምር አስቀምጠዋል። በአሁኑ ወቅት የሚታዩ ችግሮችን መፍታት ከተቻለም በተለይ ያሉትን የብረትና የድንጋይ ከሰል ማዕድን ሃብቶችን በስፋት የመጠቀም እድል ይኖራል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 11/2013