“የአገራት አንድነት የተገነባው በጸረ አንድነት ውድቀትና መቃብር ላይ ነው።” ይህ የፖለቲካ አካሄድ የሀገረ መንግስት ግንባታቸውን በተጠና እና አንድነትን በጠበቀ መልኩ ለማስኬድ በሚተጉ አንድነትን ለሀገረ መንግስት ግንባታ እንደ ዋና ካስማነት የሚጠቀሙ ናቸው።ከዚህም በተጨማሪ በዚህ የፖለቲካ መስመር የተሰለፉ ፖለቲከኞች ተከታዮቻቸውን በሃሳብ እንጂ በዘውግ የረቱ አይደሉም።
በአሁኑ ወቅት ያሉ የጎሳ ድርጅቶችን በሁለት መልክ ከፍለው የሚያዩ አንዳንድ ግለሰቦች፣ ምሁራን እና ቡድኖች አሉ።ከዚህ አንጻር አንደኛው ክንፍ ጎሳን መሰረት ያደረጉ ድርጅቶችን በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ የሀገር አንድነትን መገንባት ይቻላል የሚሉ ሲሆን ሌላኛው ክንፍ ደግሞ የጎሳ አደረጃጀት አንዱን ለአንድነት የቆመ፣ ሌላውን በጸረ አንድነት ጎራ የተሰለፈ በማድረግ ላይ ያተኮረ በመሆኑ የፖለቲካ ምህዋሩ እና መሮጫ ሜዳው የፖለቲካ መሆኑ ይቀር እና ወደ ማንነት የሚወሸቅ ይሆናል የሚል ነው።
እንደኔ የጎሳ የፖለቲካ ድርጅት አገር አጥፊ እንጂ አገርን ሊገነባ አይችልም።ምክንያቱም በማንኛውም አግባብ ጎሰኛ ጎሰኛ ነው። ከራሱ ቋንቋ ተናጋሪና ስሜት ላይ ብቻ በመቸንከር የሌሎች ጎሳዎችን ሁለተናዊ ፍላጎት ካስማ ሊያውቅ አይችልምና።
ለማወቅም አይፈልግም።ይህ ከሆነ ደግሞ በጎሳዎች መካከል የሚፈጠሩ ተቃርኖዎችን በቀላሉ ማስታረቅ አይቻለውም።ስለሆነም ሁሌም አንድ ነገር ይቀናቸዋል።እንገንጠል የሚል የልጅ ጨዋታ።በዚህም ሃገርን እና ህዝብን ያተራምሳሉ።ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ ጠላቶች ሰርግ እና ምላሽ ነው።ለኢትዮጵያዊያን ግን እሳትን በብብት ውስጥ አቅፎ እንደመተኛት የሚቆጠር ነው።
ፕሮፌሰር ተስፋጽዮን መድሃኔ (ብሬመን ዩኒቨርሲቲ፣ ጀርመን) “ኤርትራ እንደ እናት አገር፣ ችግሮችና ፈተናዎች ትናንትም ዛሬም” በሚለው መጽሃፋቸው ላይ እንደጠቀሱት የትግራይ ተወላጆችን በሚመለከት በአጼ ዮሐንስና በአሁኖቹ የህወሃት መሪዎች መካከል ስለእናት አገር ያላቸው ግንዛቤና አመለካከት የተለያየ መሆኑንና የዛሬዎቹ ቅድሚያ የሚሰጡትም ለማንነታቸው እንደሆነ እንዲህ ሲሉ አቅርበዋል።
” የዛሬው የትግራይ ፖለቲከኞች ወይም የፖለቲካ ተዋንያን እናት አገራችሁ ማነች? ለሚለው ጥያቄ የሰጡት መልስ በመንፈስም በአስተሳሰብም አሳሳቢ በሆነ መጠን ይለያል። በጥያቄው ከተሳተፉት የትግራይ ፖለቲከኞች መሃል እናት አገራችን ኢትዮጵያ ነች ብለው የመለሱ 3 ነጥብ 6 በመቶ ብቻ ናቸው ። አብዛኛዎቹ
በጥያቄው የተሳተፉ የህወሃት ፖለቲከኞች ግን እናት አገራችን ትግራይ ነች ነበር ያሉት፤ ኢትዮጵያ አላሉም። አቶ ስብሃት ነጋ ይህንን ጥያቄ ሲጠየቅ ለአንድ አፍታ አሰብ አድርጎ ካመነታ በኋላ ሲመልስ እናት አገር ሲባል በአዕምሮው ውስጥ ድቅን የምትልበት ትግራይ መሆኗን ገልጿል።
የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት የነበረው አቶ ጸጋዬ በርሄ እናት ሃገርህ ማን ናት ተብሎ ተጠይቆ ነበር።ለዚህ ጥያቄ ምንም ሳያመነታ በቀጥታ እናት ሀገሬ ትግራይ ነች ብሎ መለሰ።ሌሎችም እንዲሁ እናት ሃገራችን ትግራይ እንጂ ኢትዮጵያ ናት አላሉም። ”
እነኚህ ሰዎች የጥበታቸው መጠን ገዝፎ ሂዶ…ሂዶ የኢትዮጵያን ጦር ሰራዊት በመበተን ሃገሪቱን ለማጥፋት ከኢትዮጵያ ጠላቶች ከነ ግብፅ፣ አረብ ሀገራት፣ እና ምዕራባዊያን በባሰ የሄዱበትን አግባብ ለሚመለከት እና አሁን በሃገሪቱ ውስጥ ያለው እዚያም እዚህም የሚፈጠረው የዜጎች መፈናቀል እና መሞት ወዘተ…በህወሃት የዛር ውላጆች የተፈጠሩ በጸረ አንድነት እርኩስ መናፍስት የተለከፉ፣ ትኩስ እብድ የዘር ፖለቲካ አራማጅ ፖለቲከኞች የስራ ውጤት መሆኑ ለአፍታም አያጠራጥርም።
ብዙ ጊዜ በሃገሪቱ ለሚፈጠሩ ዘውግ ተኮር ችግሮች የዘውግ ፖለቲካ አራማጆች እጅ ከፍተኛ መሆኑን በተደጋጋሚ ተመልክተናል።ይሁን እንጂ ራሳችው ለሚፈጥሩት ችግር ራሳቸው መፍትሄ ማበጀት ሲገባችው መንግስት ላይ ጣት ሲቀስሩ ይስተዋላል።ይህ አካሄድ ትክከልም፤ አዋጭ አይመስለኝም።ይህን ስል ማንም ችግሩን ይፍጠረው ማን መንግስት ዜጎችን የመጠበቅ ኃላፊነት የለበትም እያልኩ አይደለም።
ፖሊሱ፣ ደህንነቱ፣ መከላከያው ወዘተ…ትዕዛዝ የሚሰጠው ከመንግስት መሆኑን ዘንግቼም አይደለም።ነገር ግን የዘውግ ፖለቲካን በሚያራምዱ አካላት በአንድ የስልክ ጥሪ ስንት እና ስንት ሰላማዊ ሰልፎችን፣ የመንጋ ጥፋቶችን፣ ወዘተ… ማድረጋቸውን በተለያዩ አጋጣሚዎች በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች አይተናል።
ታዲያ አቅማቸው ይህን ያህል ሆኖ ሳለ ችግርን ለመፍታት ሲሆን ይህን አቅማቸውን ከመጠቀም ምድንነው ጠፍንጎ የያዛቸው? ያም ሆነ ይህ ለሚፈጠሩ ችግሮች ሁሉ መንግሥት ላይ ብቻ ጣታችሁን መቀሰሩን ትታችሁ የራሳችሁንም ታሪካዊ ሃላፊነት ብትወጡ ባይ ነኝ።አለበለዚያ እሳትን በብብት ውስጥ አቅፎ እንደመተኛት ይቆጠራል።ይህ ደግሞ ዞሮ ዞሮ ጉዳቱ ለሃገርና ለወገን ነው።
አሁን በአገራችን የሚታየው ምስቅልቅል ሁኔታና አለመረጋጋት የመጣው ምዕራባዊያን እና የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች በፈጠሩት የጎሳ ድርጅቶች ምክንያት መሆኑን መካድ አይቻልም። ይህን ለማወቅ የአውሮፓና የአረብ አገሮችን የቆዬና እስከአሁንም ድረስ የዘለቀ ጸረ ኢትዮጵያ ታሪክ መመልከቱ በቂ ነው።
እነኚህ የኢትዮጵያ የውጭ ጠላቶች ኢትዮጵያን የማፈራረስ ሴራ የሚከናወነው ደግሞ በጎሰኞች ጫንቃ መሆኑን ያምናሉ። ቀደም ሲል በርበራና ዘይላ ቀጥሎ ጂቡቲ ከዚያም በኤርትራ የአሰብ፣ የምጽዋና አዶሊስ የባህር በሮችና ወደቦችን ማጣት የዚህ ውጤቶች ናቸው።
”ለዝሆን መጥፊያው የራሱ ጥርሱ ነው” እንዲሉ አገራችን ኢትዮጵያ ያላት የተፈጥሮ ሃብት እና አቀማመጧ ጠላት እየገዛላት መሆኑ በግልፅ ይታያል። ይህን ተከትሎ አሁን አገራችን ኢትዮጵያ ዙሪያዋ በውጭ ሃይሎች ጦር የተከበበች የጦር ዒላማ ሆናለች። የቀድሞ ወደቦቿ ለአረብና ለሃያላን መንግስታት የጦር ሰፈሮች ሆነው በሚፋጠጡበት የጦር ቀጠናው ውስጥ ገብታለች። ይሁን እንጂ ከስልጣናቸው ባሻገር የወደፊቱን አደጋ አርቆ ማየት የሚሳናቸው የዘውግ ፖለቲከኞች በዘረኝነት ታውረው፣ ክብርና ድንበራቸውን ለገንዘብ እየሸጡ እንመራዋለን / እንወክለዋለን የሚሉትን አገርና ህዝብ ለአደጋ አጋልጠውታል።
ራሳቸውንም ለምዕራባዊያን፣ ለአረብ አገራት ወዘተ…ለባርነት እያጫረቱ ለመሸጥ ግልጽ ጨረታ አውጥተው ለመጥፋት እየኳተኑ ነው።”አልሞትም ብሎ ሂዶ ከማይቀበርበት ሃገር ደረሰ” እንዲሉ ምዕራባዊያንን ማመን የመጨረሻው ጥፋት እና እልቂት መሆኑንም የዘነጉ ይመስላል።
”ሞኝን ሁለት ጊዜ እባብ ነደፈው፤ አንድ ጊዜ ሳያየው በሁለተኛው ደግሞ ለሰዎች ሲያሳይ ”እንዲሉ በጎሳ የተደራጁ ስብስቦችን ለዴሞክራሲ እንደቆሙ አድርጎ በመቁጠር መጃጃል ላለፉት ሃምሳ ዓመታት የተሰራውን ስህተት እና የነቀዘውን ስርዓት ቀደው እየሰፉ እና እየደረቱ እንደመጓዝ አይነት ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዚህ በፊት በነበሩት የትኛውም ስርዓት የተጎዳና የተበደለ ህዝብ ነው። ስለሆነም ከእንክርዳድ የተጠመቀ ጠላ እንደጣጣ ሰው በአዙሪት ውስጥ መሽከርከሩን ትተን በየቦታው የሚፈጠሩ ቸግሮችን ተባብሮ ለማጥፋት አንድ ላይ ብንቆም መልካም ነው። አለበለዚያ የአንድነታችንን ማጥበቂያ ቁልፍ መላላትን ለሚጠባበቁ ተኩላዎች ራሳችንን አሳልፈን መስጠት ነው።
ስለዚህ ለሚፈጠሩ ችግሮች በሙሉ መንግስት ላይ ጣታችንን መቀሰሩን አቁመን ከመቼውም በላይ በአንድነት የምንቆምበት ወሳኝ ወቅት ላይ እንገኛለን።አለበለዚያ አሁን ባለው የምዕራባዊያን ሴራ ተታለን እና ለጊዜያዊ ጥቅም ተደልለን የሃገርን ሰላም ማወክ እሣትን አቅፎ እንደመተኛት የሚቆጠር መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 11/2013