ለምለም መንግሥቱ
በቡታጅራ ከተማ ሰሞኑን በነበረኝ ቆይታ በመሠረተ ልማት ግንባታ ብዙ ለውጦችን ለመታዘብ ችያለሁ:: የውስጥ ለውስጥ መንገዶች በኮብል የድንጋይ ንጣፍ፣ ዋና ዋና መንገዶች ደግሞ በአስፓልት ደረጃ ተሰርተው ከመንገድ ዳር መብራቶች ጋር ከተማዋ ውበትን ተላብሳለች:: አበረታች የሆነው የመሠረተ ልማት ግንባታ ይበል የሚያስብል ቢሆንም መታረም ያለባቸውንም ነገሮች መታዘብ ችያለሁ::
በአንዳንድ የከተማዋ አቅጣጫ የተሰራው የአስፓልት መንገድ የእግረኛ መንገድን ታሳቢ ያደረገ አይደለም:: ከአስፓልቱ ዳር ቀጥሎ የሚገኘው የቆሻሻ ውሃ መውረጃ ቱቦ ነው:: እግረኛው ከቁጥጥር ውጭ የሆነ መኪና ቢያጋጥመው እንኳን በቀጥታ የቆሻሻ ማስወገጃው ቱቦ ውስጥ ነው የሚገባው:: መልሶ ለማረም በማይቻልበት በሚመስል መልኩ የተሰራው እግረኛውን ያላገናዘበ የአስፓልት መንገድ ባለሙያውንም አሰሪውንም አካል የሚያስወቅስ ሆኖ ነው ያገኘሁት:: የታዘብኩት መንገድ የተሰራው ደግሞ ወደከተማ አስተዳደሩ በሚወስደው አቅጣጫ ነው::
በህንጻ ግንባታው በኩል አብዛኞቹ በጅምር ህንጻ ላይ አገልግሎት እየሰጡ ቢሆንም ሆቴል ቤቶችና የተለያዩ የንግድ መስጫ ህንጻዎች ግንባታ በመስፋፋት ላይ ይገኛል:: የአንድ ከተማ ገጽታን በመላበስ ላይ በምትገኘው ቡታጅራ በከተማዋ ዋና አስፓልት ዳር አገልግሎት በመስጠት ላይ ከሚገኙ የሆቴል ቤቶች አንዱ እይታዬ ውስጥ ገባ::
ስለሆቴሉም የአካባቢው ሰዎች እንደነገሩኝ ደቡብ አፍሪካ ሀገር የሚኖሩ አንዲት የአካባቢው ተወላጅ ሰርተው ለአገልግሎት ያበቁት ሆቴል ነው:: የሆቴሉ መጠሪያ ስያሜ ‹‹ሳውዘርን ሳን›› ስለነበር ምናልባት ባለቤቷ በሚኖሩበት ሀገር ደቡብ አፍሪካ ሰይመውት ይሆን ብዬ ጠረጠርኩ::
የከተማዋን ነዋሪዎች ጨምሮ እንዲህ በሀገራቸው ውስጥ የተለያየ ግንባታ ለማካሄድ ፍላጎት ላላቸው በውጭ ሀገር ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የከተማው ማዘጋጃ ቤት ስለፈጠረው ምቹ ሁኔታ፣ እንዲሁም በግንባታ ግብአት አቅርቦትና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ለመጠየቅ ወደ ሆቴሉ ጎራ ባልኩበት ወቅት ነበር ስያሜው ግጥምጥሞሽ መሆኑን እንጂ የሆቴሉ ባለቤት ከሚኖሩበት ከደቡብ አፍሪካ ሀገር ጋር ተያያዥነት እንደሌለው ለመረዳት የቻልኩት::
ባለቤቷን ሳይሆን የሆቴሉን የሰው ኃይል አስተዳዳሪና የሂሳብ ሠራተኛ አቶ ትግሉ ዳባን ነበር ያገኘኋቸው:: እርሳቸውም ስያሜው ኢትዮጵያዊ መሆኑን ነበር ያረጋገጡልኝ:: አቶ ትግሉ የሆቴሉ ግንባታ ተጠናቅቆ ሥራ ሲጀምር ነበር የተቀጠሩት:: እርሳቸውም ሆቴሉም እኩል ሥራ የጀመሩ በመሆናቸው ሁለተኛ ዓመታቸውን ይዘዋል::
በቆዩባቸው የሥራ ጊዜያቶችም ባለቤቷ ለከተማዋ ጥሩ ገጽታ የሚሰጥ ህንፃ መገንባት በመቻላቸውና ለአካባቢው ነዋሪዎችም የሥራ ዕድል የሚፈጥር የንግድ አገልግሎት መስጫ መሆኑ ከሆቴሉ ከሚያገኙት ገቢ በላይ እንደሚያስደስታቸው እንዳጫወቷቸው ነግረውኛል:: በንግድ ውስጥ በስፋት የመንቀሳቀስ ፍላጎት ያላቸው ጠንካራ ሴት እንደሆኑም መስክረውላቸዋል:: በአሁኑ ጊዜም የማስፋፊያ ግንባታ ለማከናወን በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ይገልጻሉ::
አቶ ትግሉ እንደነገሩኝ፤ የሆቴሉ ባለቤት አሁን በአገልግሎት ላይ ያለውን ሆቴል ገንብቶ ለማጠናቀቅ ረዘም ያለ ግዜ ወስዶባቸዋል:: ሆቴሉ በሚገኝበት ሥፍራ ላይ ይኖሩ ከነበሩ ግለሰቦች ቦታውን ገዝተው ስለነበር ነዋሪዎቹ ከቦታው እስኪነሱና በየተለያዩ ምክንያቶች ግንባታው ጊዜ ወስዷል::
አሁንም የማስፋፊያ ግንባታውን ለማከናወን ቦታቸውን ለመሸጥ ከተስማሙ ግለሰቦች ላይ በመግዛት ነው ለግንባታ ሥራ የተዘጋጁት:: የከተማ ማዘጋጃ ቤቱ በዚህ ረገድ እያደረገ ስላለው ድጋፍም እንደገለጹት ባለሀብቱም እንዲበረታታ፣ የሻጩንም ተጠቃሚነት ባማከለ ማዘጋጃ ቤቱ አገልግሎት ለመስጠት ጥረት እያደረገ መሆኑን ነው የሚናገሩት::
ለግንባታ የሚውል የመሬት ዝግጅቱ ላይ የጎላ ክፍተት አለ ብለው እንደማያምኑ የተናገሩት አቶ ትግሉ፤ በየጊዜው እየናረ የመጣው የግንባታ ግብአት በተለይም የሲሚንቶ ዋጋ አዲስ ግንባታ ለማከናወን ቀርቶ ጥገና ለማካሄድ እንኳን ፈታኝ እንደሆነ በተለያየ ጊዜ አጋጥሟቸዋል:: ምንም እንኳን መንግሥት ዋጋ የማረጋጋት እርምጃ ቢወስድም ነጋዴው ግብአቱን በመደበቅ የበለጠ የዋጋ ንረቱ እንዲከሰት ያደርጋል እንጂ እንደማይቀንስ በተግባር ያዩት ጉዳይ እንደሆነ ገልጸዋል::
የአንድ ኩንታል ሲሚንቶ አራት መቶ ብር በነበረበት ወቅት መንግሥት እርምጃ ሲወስድ ምርቱን ደብቀው ዋጋውን አምስት መቶ ብርና ከዚያ በላይ በማድረግ ነበር ያናሩት:: መንግሥት እርምጃውን ተከታታይ በማድረግ፣ ነጋዴውን ሸማቹ ተሳስቦ እንዲገበያይ፣ ብልሹ አሰራሮች እንዲቀሩ፣ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ንረትን ለማስቀረት የሚረዱ በግንዛቤ የባህሪ ለውጥ እንዲመጣ ሥራዎች ጎን ለጎን ካልተሰሩ እላፊ ጥቅም የለመደን አካል በአንዴ ወይንም በእርምጃ ብቻ ማስቆም ከባድ እንደሆነ ሀሳብ ሰጥተዋል::
እንደ አንድ የከተማ ነዋሪ በከተማዋ የግንባታ እንቅስቃሴ ላይ የሚያስተውሉትን ጠይቄያቸው በሰጡት ምላሽ፤ የከተማ ማዘጋጃ ቤቱ በከተማዋ የሚከናወኑ የግንባታና የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች የጋራ እንዲሆኑ በየጊዜው ጠርቶ ያወያያቸዋል:: በኮብልስቶንና በአስፓልት እየተሰራ ያለው መንገድ ለከተማዋ ውበት ብቻ ሳይሆን ለነዋሪውም ምቹ በመሆናቸው ይበል የሚያስብል ተግባር ነው:: አብዛኞቹ መኖሪያ ቤቶች ያረጁ በመሆናቸው በቀጣይ ከመንገዱ ጋር የሚመጥን የመኖሪያ ቤትና የተለያዩ የህንፃ ግንባታዎች መከናወን ይኖርበታል::
በከተማዋ በተለያየ ዘርፍ ስለሚከናወኑ የግንባታ እንቅስቃሴዎች የቡታጅራ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅና የማስፈጸም አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኤርሚያስ ኢሳያስ እንዲህ ያስረዳሉ፤ ቡታጅራ በ1923 ዓ.ም ነው የተቆረቆረችው:: ቡታጅራ በአምስት ቀበሌና በ59 መንደሮች የተዋቀረች ከተማ ስትሆን፣ የከተማነት ይዞታ ወይንም መዋቅር ያገኘችው በ1995ዓ.ም ነው::
በአሁኑ ጊዜም በፍጥነት እያደጉ ከመጡ ከተሞች መካከል አንዷ ለመሆንም ችላለች:: ለዚህ መገለጫው ደግሞ በመሰረተ ልማት ዝርጋታ ተደራሽ ለመሆን የምታደርገው ጥረት ሲሆን፤ በየጊዜውም በየምዕራፉ ደረጃውን የጠበቀ የአስፓልትና በኮብል ስቶን የውስጥ ለውስጥ መንገድ ሥራ በመከናወን ላይ ይገኛል::
የመሠረተ ልማት ዝርጋታውና የተለያዩ የግንባታ ሥራዎች በመከናወን ላይ የሚገኙት ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ሲሆን፣ ከተሞችን ለማልማት በተቀረጸ ፕሮጀክት በአምስት ምዕራፎች ተከፋፍሎ ነው የሚከናወነው:: የዚህ ፕሮጀክት ዋና ዓላማም አቅም መገንባትና ለወደፊት ግንባታ ሥራ የሚያግዝ ሥርዓት ማበጀት ነው::
በተፈጠረው አቅምና ሥርአት ውስጥ መቀጠል ደግሞ ከተማዋን የሚያስተዳድረውና የነዋሪው ኃላፊነት ነው:: ፕሮጀክቱ ሲተገበርም ከተማዋ የምትገኝበት የደቡብ ብሄር፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ጎራጌ ዞን ለፕሮጀክቱ 30 በመቶ ድጋፍ ያደርጋል:: በዚህ ፕሮግራም ተጠቃሚ መሆኗ በርካታ እድሎች እንደተፈጠሩላትም አቶ ኤርሚያስ ያስታውሳሉ::
ካነሷቸው የግንባታ ሥራዎች መካከልም የመንገድ ሥራ፣ በዝቅተኛ ኑሮ ለሚተዳደሩ የህብረተሰቡ ክፍሎች አገልግሎት የሚውል የጋራ መፀዳጃ ቤት፣ በአነስተኛ የኪራይ አገልግሎት የመኖሪያ ቤት ሥራዎች ይጠቀሳሉ:: የከተማ ማዘጋጃ ቤቱም ጅምር ግንባታዎች ተጠናክረው የከተማዋ ነዋሪዎች ኑሮ እንዲሻሻል፣ የከተማዋ ገጽታም እንዲለወጥ በሚችለው አቅም ሁሉ እየሰራ ይገኛል ብለዋል::
እንደ አቶ ኤርሚያስ ማብራሪያ ቡታጅራ ከተማ አራት መግቢያና መውጫ በሮች ስላሏት በመስፋት ላይ ትገኛለች:: በአሁኑ ጊዜ ስብሰባዎችና ስልጠናዎች በስፋት የሚሰጥባት ከተማ በመሆንዋ የኮንፈረንስ ቱሪዝም መዳረሻ ሆና በማገልገል ላይ ትገኛለች::
በኢንቨስተሮችም እንዲሁ ተፈላጊነቷ ጨምሯል:: በመሆኑም ከተማዋን የሚመጥን የመሠረተ ልማትና ለተለያየ አገልግሎት የሚውል ግንባታ በማከናወን የተገልጋዩን ፍላጎት ማሟላትና ተጠቃሚ መሆን እንደሚገባ በማዘጋጃ ቤቱ እምነት ተይዞ በዕቅድ ሥራዎች በመከናወን ላይ
ይገኛሉ:: ለኢንዱስትሪ፣ ለመኖሪያና ለተለያየ አገልግሎት የሚውል ቦታ ማዘጋጀት፣ እየተሰራ ካለው ሥራ መካከል የሚጠቀስ ሲሆን፣ መሬት የማስተላለፍ ሂደቱም በሊዝና በማህበር ተደራጅተው ግንባታ ለሚያከናውኑ አካላት ምቹ ማድረግን ያካትታል:: መኖሪያ ቤት ለመገንባት ፍላጎቱና አቅሙ ላላቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ምቹ ሁኔታ የሚፈጠር ቢሆንም ቅድሚያ የሚሰጣቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ግምት ውስጥ የሚገቡበት የአሰራር ሥርዓት ተዘርግቷል::
እስካሁንም በአማካይ እስከ አስር የሚሆኑ ማህበራትን ተጠቃሚ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል:: የግንባታ ዲዛይኑም ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ግምት ውስጥ ገብቷል:: እስካሁን ባለው ‹‹ጂ ፕላስ ዜሮ እና ጂ ፕላስ ዋን›› ወይም ባለአንድና ከዚያ በታች ፎቅ የሚባለው ደረጃ ነው ተግባራዊ የሆነው::
ለተለያዩ አገልግሎቶች ተገንብተው ሥራ ላይ ከሚገኙት መካከል ደረጃ ያላቸው የሆቴልቤቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል:: ከተማዋ ውስጥ ትልቁ ህንጻ ባለአምስት ፎቅ ያለው እንደሆነም ገልጸዋል:: ከአምስት ፎቅ በላይ ለመገንባት የግንባታ ፈቃድ የጠየቁ በመኖራቸው ወደፊት የተሻለ ግንባታ ይጠበቃል ብለዋል::
በግንባታ ሥራ እንደ ከተማ ስለሚያጋጥሙ ችግሮችና የተቀመጡ መፍትሄዎች ላይም አቶ ኤርሚያስ እንዳብራሩት፤ በማዘጋጃ ቤቱ የህንፃ ግንባታ ቁጥጥር የሥራ ሂደት ተዋቅሯል:: በክፍሉ ውስጥ የሚገኙት ሙያተኞችም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋም በሲቪል ኢንጂነሪንግ የተመረቁ ናቸው::
በባለሙያዎቹ በከተማዋ የሚከናወነውን ግንባታ ጥራት መከናወኑን፣ በተያዘለት ጊዜ መጠናቀቁን ጭምር ክትትልና ቁጥጥር ያደርጋሉ:: ግንባታዎች ሳይጠናቀቁ በጅምር አገልግሎት መስጠት እንደሌለባቸውም አቅጣጫ በመቀመጡ እስከ እዚህ ድረስ የዘለቀ የክትትልና ቁጥጥር ሥራ ነው የሚከናወነው::
አቶ ኤርሚያስ በጅምር ህንጻዎች ላይ አገልግሎት እንዳይሰጥ አቅጣጫ ተቀምጧል ይበሉ እንጂ በተግባር ግን እንዳልሆነ ላቀረብኩላቸው ጥያቄ እርሳቸውም በምላሻቸው እውነታውን አረጋግጠዋል::
እርሳቸው እንዳሉት የተቀመጠውን አሰራር ጥሰው የሚጠቀሙ ቢኖሩም ይጠየቃሉ:: ግን የሚሰጡት ምላሽ አሳማኝ ከሆነ በማስጠንቀቂያ ታልፈው እንዲያስተካክሉ የሚደረግበት ሁኔታ አለ:: ነገር ግን አስተማሪ የሆነ የቅጣት እርምጃም የተወሰደባቸውም ይገኛሉ:: በተቻለ መጠን ግን ማዘጋጃ ቤቱ የተለያየ እገዛ በማድረግ ጭምር አልሚዎቹ በገቡት ውል መሠረት ግንባታውን እንዲያጠናቅቁ ይደረጋል::
በዚህ ወቅት ለግንባታ ዘርፉ የግብአት አቅርቦት ዋጋ መናር ትልቅ ማነቆ እንደሆነም አቶ ኤርሚያስ ያስታውሳሉ:: በተለይም ሲሚንቶና ብረት በዋጋ ንረት በስፋት ከሚነሱት ውስጥ ይጠቀሳል ብለዋል:: ችግሩ ሀገራዊ በመሆኑ በከተማዋ በግንባታ ዘርፍ ላይ የተሰማሩት አቶ ኤርሚያስ ይገነዘባሉ:: መንግሥትም ዘርፉን በማገዝ በኩል ወደኋላ ያለበት ጊዜ ባለመኖሩ ችግሩ ይቃለላል ብለው ያምናሉ::
በማዘጋጃ ቤቱ በኩል ግን የአገልግሎት አሰጣጡን በማቀላጠፍ እንደሚያግዝና የተገልጋዩን ውጣ ውረድ ለማስቀረት የአንድ መስኮት አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል:: በተለያዩ አቅጣጫዎች ባሏት የመግቢያ በሮች እንግዶችዋን የምትቀበለው ቡታጅራ ዕድገት ለማፋጠን የከተማው ማዘጋጃ ቤት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ነው ከአቶ ኤርሚያስ ጋር በነበረን ቆይታ ለመገንዘብ የቻልኩት::
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 12/2013