ግርማ መንግሥቴ
ምርጫ 97ን ያየ የዘንድሮው ምርጫም ሆነ በመሀል ያሉት ምርጫዎች ምርጫ ሁሉ ላይመስሉት ይችላሉ። እስከ ምርጫው ቀን ድረስ ያለውን ባናውቅም እስካሁን ያለው የዘንድሮው ምርጫ ድባብ ብዙም የሚያነቃቃ አይመስልም።
የአሁኖቹ “ተፎካካሪ” ተብለው የሚታወቁት ከ97ቱ ጋር ሲወዳደሩ በቁጥር የትየለሌ ይሁን እንጂ በአቅም፣ ተግባርና አማራጭ ፖሊሲ (እሱ ቀርቶ የፖሊሲ ሀሳብ እንኳ) እስካሁን አላሳዩንም። ለማንኛውም ትንሽም ቢሆን ጊዜ አለና ወደፊት የምናየው ሆኖ አጠቃላይ ሂደቱን ካለው ስጋትና እድሎቹ ጋር እንመልከት።
በአገራችን የምርጫ ታሪክ ምእተ ዓመትን ይሻገራል፤ እድሜውም ለ«የዘውድ ምክር ቤት» «የዘውድ አማካሪዎች» ከተመረጡበት 1911 ይጀምራል። ሕዝብ እንደራሴዎቹን ለመጀመሪያ ጊዜ በቀጥታ ተሳትፎበታል ተብሎ በታሪክ የሚጠቀሰው ግን በ1948 ዓ.ም የተከናወነው ምርጫ ሲሆን ከ1948- 1967 ዓ.ም በየአራት ዓመቱ አምስት ተከታታይ ምርጫዎች ተካሂደዋል፡፡
“ከሦስት ዓመታት ሕዝባዊ አመፅና ተቃውሞ በኋላ በሰፊ ሕዝባዊ ድጋፍ ወደ ሥልጣን የመጣው አዲሱ የኢሕአዴግ አመራርና የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግሥት አስተዳደር፣ ቅድሚያ በመስጠት ‘በትኩረት እየሠራሁባቸው ነው’ ከሚላቸው ሰፋፊ ማሻሻያዎች አንዱ የዴሞክራሲ መጫወቻ ሜዳውን መደላድል በማመቻቸት፣ ሁሉም ተፎካካሪዎች እኩል ለመንግሥትነት ሩጫ ማድረግ የሚችሉበትን ምኅዳር መፍጠር” መሆኑ ወደ ስልጣን ከመጡ ጀምሮ ሲነገር ቆይቷል።
“የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን በቅርፅ፣ በአሠራርና በአመራር እንደ አዲስ” ማደራጀቱን ከራሱ ከመንግስትም ባለፈ ምርጫ ቦርድም ሳያሰልስ ለህዝብ እያሳወቀ ነው። ይሁን እንጂ “መንግስት የለም” የሚል አካል ሳይቀር ተፈጥሮ ወደ “የሕግ የበላይነትን የማስከበር ዘመቻ” ጦርነት እስከ መግባት የተደረሰበት፤ በምርጫው መዳረሻ ደግሞ “በምርጫው አንወዳደርም” የሚል አካል የተፈጠረበት እና ሂደቱን ለሁለት ከፍሎት እያነጋገረ ይገኛል።
(ለጠቅላላ ግንዛቤ፤ የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ መቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1ሺ133/2011 ዓ/ም “ምርጫ”ን እና “የፖለቲካ ድርጅት” ወይም “የፖለቲካ ፓርቲ”ን ምንነት በተመለከተ ብያኔ የሰጠ ሲሆን፤ “ምርጫ” ማለት በሕገ-መንግስታትና በሌሎች አግባብነት ባላቸው ሕጎች መሰረት የጠቅላላ፣ የአካባቢ፣ የሟሟያ ወይም የድጋሚ ምርጫ ማለት ነው። “የፖለቲካ ድርጅት” ወይም “የፖለቲካ ፓርቲ” ማለት የፖለቲካ ፕሮግራም ነድፎ አላማውን በሕጋዊ መንገድ ለማራመድ የሚንቀሳቀስ ቡድን ነው። ሲልም ይገልፃቸዋል።)
“በምርጫው አንወዳደርም” የሚለውን አካል እራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አናግረውትና እንዲሳተፍ ለምነውት እንደነበርና ምላሹም አሻፈረኝ መሆኑን ነግረውናል። ከእነዚህና ሌሎች ዝቅ ብለን ከምናያቸው ጉዳዮች አኳያ “የምርጫው አዝማሚያ ምንድን ይሆን?” የሚለውን ጥያቄ ለራሳችን አንስተን መልስ ለመስጠት እንሞክራለን። በአብዛኛው የተሰነዘሩት ሀሳቦች ክፍት ናቸውና አንባቢ የራሱን እየሞላና ሀሳቡንም እያሟላ ጽሑፉን ሙሉ ሊያደርገው ይችላል ብለንም እናስባለን።
በመብት መጠየቅ ፍልስፍና ውስጥ የመጠየቁ ዐቢይ አላማው ራስንም ጭምር የሚያካትት ነውና ይህ የሁሉም ክፍል የቤት ስራም ጭምር ሊሆን ይገባል ብንል ያስኬደናል። ለምሳሌ አንድ ሰው ተነስቶ ምርጫው ተጭበርብሯል ወይም አጭበርብረውኛል ሲል በመጀመሪያ ደረጃ እሱ እራሱ እንዳላጭበረበረ፤ የማጭበርበሩ አካልም እንዳልሆነ እርግጠኛ መሆን አለበት። “የሴራ ፖለቲካ” አካል ሆኖ “ከፖለቲካ ነፃ ነኝ” አይነት ጨዋታ ማንንም አትመጥንምና ስለማታግባባ።
የባህርዳር ዩኒቨርሲቲው ዶ/ር ዓለማየሁ ቢሻው “የምርምር አጀንዳ መሆን ያለበት በኛ ማህበረሰብ ውስጥ ያሉ እምቅ ተሞክሮዎችን መዝዞ አውጥቶና ሳይንሳዊ በሆነ መልክ አደራጅቶ በጥቅም ላይ ማዋል ነው፡፡” (በዩኒቨርሲቲው በሚዘጋጀውና በኦንላይን ላይ ከሚገኘው “ናይል” ጋዜጣ የተገኘ) እንዳሉት ሁሉ በአገራችን (በ1911 ምርጫን የተዋወቀች) ሊሆን የሚገባው ይሄ እንጂ አየር ላይ ያለ፤ መሬት ያልወረደን ነገር ለማውረድ መሞከር ችግር ፈቺ ሊሆን አይቻልምና ጉዳዩ የዋዛ አይደለም።
አንድን ስርአት “ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ነው” ብሎ ለመመደብ መሟላት ከሚገባቸው ጥብቅ መስፈርቶች ቀዳሚው በዚያች አገር ነፃ፣ ፍትሀዊ፣ ዲሞክራሲያዊና በሁሉም ዘንድ ተአማኒነት ያለው ምርጫ መካሄድ አለመካሄዱ (ከተቻለም “እንከን የለሽ”) ሲሆን፤ ይህም ህዝባዊ መንግስት ማለትም በህዝብ የተመረጠ መንግስት መመስረትና አለመመስረት ጋር፤ አገርን የአምባገነኖች መናኸሪያ ከማድረግና አለማድረግ ጋር የቀጥታ ግንኙነት ስላለው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተግባራዊ ሊደረግና የዜጎች የስልጣን ባለቤትነት ሊረጋገጥ ይገባል፤ ይህ የጤነኛ ሰዎች ሁሉ የጋራ ስምምነት ነው።
ብዙውን ጊዜ ከምርጫ ጋር ተያይዞ ሁከት፣ ብጥብጥ፤ የሰውና የሀብት እልቂትና ውድመት የሚፈጠረው ከ”አላሸንፍም” ወይም “እሸነፋለሁ”፤ ወይም “ባሸንፍም ባላሸንፍም በኃይል ስልጣን እይዛለሁ” ከሚል የተፎካካሪ(ዎች) አጠቃላይና ከፖለቲካም ሆነ ምርጫ ሥነምግባር ያፈነገጠ ድምዳሜ ነው። በመሆኑም ይህ ስጋትና ፍርሀት፣ አደገኛ የስልጣን ፍላጎትና መሻት በሚፈጥረው የተምታታ አስተሳሰብ ምክንያት ወደ ሴራ ፖለቲካ ያመራል። በዚህ የሴራ ፖለቲካ መሳሪያነት ነው እንግዲህ ሁሉም ነገር የሚፈፀመው፤ በተለይ ባላደጉ አገራት።
ይህ ደግሞ ከላይ “ነፃ፣ፍትሀዊ፣ዲሞክራሲያዊና በሁሉም ዘንድ ተአማኒነት ያለው” ያልናቸውም የትክክለኛ ምርጫ አሰራርና መርሆዎች ባፍጢማቸው ይደፉና አገርና ህዝብን ከእሳቱ ወደ ረመጡ እንዲሉ በሁሉ ነገር ወደ ኋላ ነው የሚመልሰው።
ከእስከ ዛሬው የዓለም እንበለው “የአፍሪካ ምርጫ” ልምድ እንደምንገነዘበው አብዛኛው ምርጫ የሚጠናቀቀው በደም ነው። ለዚህ ያመች ዘንድም ምርጫ በተቃረበ ቁጥር ሥልጣን ላይ ያለ መሪ ምርጫ ያጭበረብራል (electoral fraud ያካሂዳል) የሚል ሠፊ ዘመቻ አስቀድሞ በሕዝቡ ውስጥ ይለቀቅና አለመተማመንና ጥርጣሬ የበላይነት እንዲይዝ የሚደረግበት ስልት ሲሆን (“አልወዳደርም”ም የዚሁ አካል እንዳይሆን)፤ ይህንንም የፖለቲካ ተንታኞች በጆርጅያ በሠፊው ተሠርቶበታል ከሚባለው የቀለም አብዮትና አብዮተኞች ጋር በማያያዝ የፖለቲካ ሴራነቱን ያረጋግጣሉ።
በቀዳሚ ማሳያነትም ህዳር 2 ቀን 2003 ዓ/ም ጆርጅያ የተከናወነውን ምርጫና አሳዛኝ ውጤቱን፣ ጥቅምት 2000 ዓ/ም በሰርቢያ የተካሄደውን አብዮት (“bulldozer revolution” ሲሉ የሰየሙት)፣ የ2004 የዩክሬይንን “የምርጫ ተጭበረበረ” ዘመቻ በአፍቃሬ ሩሲያነታቸው የሚታሙት ቪክቶር ያኖከቪች ተወግደው ቪክቶር ዩቸንኮ ለሥልጣን የበቁበትን የቀለም አብዮት፣ የካቲት 27 ቀን 2005 የተካሄደው የኪርጊስታን ምርጫ እና አብዮቱ (የወይን ጠጅ አብዮት (Tulip revolution)) እና የመሳሰሉትን ይጠቅሳሉ።
በተምሳሌትነቷ ስትጠቀስ በኖረችው አሜሪካ (የዘንድሮውን ትራምፕ/ ባይደን ምርጫን ጨምሮ)ም የምርጫ ጉዳይ ሙዝ ላጥ፣ ዋጥ አለመሆኑን የተመለከትን ሲሆን ልዩነት አለ ከተባለም የእነሱ ደም ደም አለመሽተቱና ከቃላት አለማለፉ፤ መጨረሻውም የህግ የበላይነት መሆኑ ነው። ወደ እራሳችን እንመለስ።
ምርጫ በአገራችን ሲካሄድ አዲስ አይደለም ብለናል፤ ምንም እንኳን አንዱ አንዱን ሲተካ ተኪው የተተኪውን “ለይስሙላ” ቢለውም ምርጫዎች ነበሩ (ድህረ 1983ን እንኳን ብንወስድ ይህ 6ኛው ነው)። ዛሬ ምጥ የሆነው ሕገመንግስትን ማሻሻል ሁሉ ነበር። ሽግግሩ ሰላማዊ ሆኖ ቢሆን ኖሮ በየጉዳዩ ላይ በቂ እርሾ ነበረን ማለት ነበር።
ምናልባት በዚህ በመጀመሪያው ምርጫና በየዘንድሮው ምርጫ መካከል አንድነትና ልዩነት አምጡ (አውጡ) ከተባለ ምናልባት “ዲሞክራሲያዊ ምርጫ የሰብአዊ መብቶች አከባበር የሕግ የበላይት ላይ የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የፖለቲካ ሳይንስና የፍልስፍና ምሁራንና ሌሎች የተቋማት ተወካዮች በጋራ እየመከሩ ነው፡፡”
የሚለው ያለፈው መስከረም ወር የሚዲያዎችን ዘገባ አይነት ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ከላይ ያልነውን ማለትም በህዝብ የተመረጠና የህዝብን ይሁንታ ያገኘ (ህዝባዊ) መንግስት ከማምጣት አኳያ ሁለቱም ያውና ተመሳሳይ ከመሆን አይዘሉም፤ አያመልጡምም።
ይህን ስንል ግን የዘንድሮውን የመጨረሻ ማጠቃለያ ውጤት ሳናካትት መሆኑን መጥቀስ እንፈልጋለን። ምክንያቱም የዘንድሮው ምርጫ ከወዲሁ ሲታይና ሲሰማ ዥንጉርጉር የመሰለ፣ አኩራፊው የበዛ፤ ተሳትፎው የቀነሰና ሰላምና ደህንነቱ አደጋ ላይ ያለ ቢመስልም (ኢትዮጵያዊ ጨዋነትና የመራጭ፣ ተመራጭ እና አስመራጭ ሥነምግባር አለ ብለን ስለምናምን) ተስፋ የተጣለበት በመሆኑ መጨረሻው ሊያምር ይችላል በሚል ነው።
አሁን ያለው የምርጫም ሆነ አጠቃላይ የፖለቲካው ድባብ እንደተለመደውና በተለመደው ቋንቋ “ወቅቱ የፖለቲካ ትኩሳቱ ከፍ ያለበት፣ የፖለቲካ ውይይቱ ያየለበትና መራጮችም ከማን ወገን መሰለፍ እንዳለባቸው ማሰብ የጀመሩበት ወቅት ነው፡፡ ” ልንለው እንችል ይሆናል እንጂ ውስጥ ውስጡን ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ “መጪውን ምርጫ ሁከት መቆስቆሻ ለማድረግ የሚፈልጉ ቅጥረኞች አሉ።” በማለት እንደገለፁት፤ ሰሞኑን እዚህ ባሉ ወገኖቻችንና አንዳንድ አገራት ተባባሪነት ኢትዮጵያን የከፋ ቀውስ ማእከል ለማድረግ ታስቦ ከወደ ግብፅ ሲወነጨፍ የነበረውንና በፌስቡክ አስተዳደር ያገደው ስናገናዝብ “ጭስ የለም” ለማለት ቅር ይላል።
“የት ይደርሳል የተባለ ወይፈን …” የት እንደተገኘው ሁሉ በህዝብ ተመርጠው፣ መንግስት ሆነው አገሪቱን በመምራት ወደ ተሻለ ምእራፍ ያሻግሯታል ተብለው እየተጠበቁ ያሉት ሁሉ “በምርጫው አንወዳደርም” በማለት ከጨዋታው ሜዳ ፉር ፉር ሲሉ እየተመለከትን ነው (ይህ ደግሞ በፖለቲካ ቋንቋ ወይ የአቅም ማነስ ወይ የተንኮል ነው)። ይህ ደግሞ መቼም የኋላ ልምዳችንን ከአሁኑ ጋር በማነፃፀርና ማወዳደር አንድ ነገር ላይ የመድረስ ሰዋዊ ባህርይ አለንና በቅርበት ስንመለከተው ከጠብ ያለሽ በዳቦ (“ጭስ ካለ …” እንዲሉ) የሚተናነስ አይደለም። “በምርጫው አንወዳደርም” የሚለው ለሰላም፣ ለዲሞክራሲ ስርአት ግንባታውና ለምርጫው ሂደት ሰላምና ደህንነት ከሆነ እሰየው፤ ሴራ ሆኖ በብሄር ከረጢት ውስጥ ለመወሸቅ ሲባል፤ በዚህም ነውጥን እናስነሳለን ከሚል ብልሹ ስሌት ከሆነ ግን እንደ እንድ ዜጋ ከወዲሁ “እባካችሁ” ከማለት ያለፈ ምን ማለት እንደሚቻል ለጊዜው ግልፅ አይደለም።
እዚህ ላይ የኢትዮጵያ ፖለቲካም ሆነ የምርጫ ሂደቱ ችግሮች ዋና መነሻ ነገሮች ሁሉ መልህቃቸውን የጣሉት ብሄር ላይ መሆኑ (ስርዓቱም የብሄር ፌደራሊዝም ነው ተብሎ መታማቱን ሳንረሳ)ና የሁሉም ነገር መሰረቱ ብሄር እንዲሆን መደረጉ ነው። (ባለፈው 137 ተፎካካሪ ፓርቲዎች መኖራቸው በተገለፀበት ወቅት አገራዊ ፓርቲ ሆነውና አገራዊ አጀንዳን ይዘው የተገኙት 18ቱ ብቻ መሆናቸውን ያስታውሷል።)
ይህ ደግሞ ሄዶ ሄዶ ሳይሆን ሄዶ የሚያርፈው “ማንነት” ላይ ነው። ማንነት ደግሞ አላዋቂ እጅ ከገባ፣ የፖለቲካ ሸቃጭ ከንፈር ላይ “ከተፃፈ” በቀን ሺህ ግዜ ስሙ ሲጠራ፤ በእሱም መሳሪያነት የጦርነት ነጋሪት ሲጎሰም፣ እዛም እዚህም እሳት ሲነድ መዋሉ የማይቀር ብቻ ሳይሆን ተጠባቂ ሁሉ እየሆነ መጥቷል። (በዚህ አይነቱና ተያዥ ምክንያቶች ጦስ አፍሪካ ከ1990 እስከ 2013 ብቻ 3.6 ሚሊዮን ንፁኋን ማጣቷን ልብ ይሏል።)
ከአንድ የቴሌግራም (የራሱ ፔጅ ካለው) ጦማሪ ያገኘሁት “ማንነት ችግር ፈቺ ብቃት ነው። በራሱ ችግር ፈቺ የሆነ ማንነት የተሳሳተ ነው። ማንነት የጥያቄ ምላሽ የእንቆቅልሽ ፍቺ ነው። ጥያቄ የሚሆን ማንነት በራሱ ችግር ነው። የሰው ልጅ ማንነት ለሰው ልጅ ችግሮች መፍትሄ ሆኖ የመኖር ሂደት ነው።
ሰው ሆኖ ሲታመም የሚያክም ሀኪም ችግር ፈቺ ማንነት ነው። የእውቀትን ችግር የሚፈታ መምህር ትክክለኛ ሰው የመሆን ማንነት ነው።” የሚለው መልእክት እንደሚያመለክተው የአሁኑ ዘመን ፖለቲከኞች (የገባቸውም ያልገባቸውም፤ የብሽሽቅ ወይም የቅናት አለያም የሴራና የምቀኝነት ርእዮት የሚያረምዱ) ለ”ማንነት” ከሰጡት እጅጉን የተለየና እጅጉንም የተሻለ ስለመሆኑ ድምፁ ከውስጥ ይሰማል። “ለምን ተለየ? ለምንስ ተሻለ?” ለሚለው ሌላ ፀሀፊ ቢያዘግምበት ያዋጣዋልና ይቀጥልበት።
ይህ የማንነት ጉዳይ በየቦታውና ሰዓቱ አከራካሪ ቢሆንም፤ “አንዳንዴም” ለመግደልና ለመሞት (እጅግ ያሳዝናል) ሰበብ ሲሆን ቢታይም በተለያዩ የእውቀትና ሙያ ዘርፎች ግን አስተያየቶች እንዲሰነዘሩ በሩን ከፍቷል። እነዚህ አስተያየቶች በአይነት፣ በይዘት እና ቅርፅም የተለያዩ ሲሆኑ አሁን አሁን ብቅ እያሉ ያሉት ግን ለየትና ለዘመኑ ፖለቲከኞች (በተለይ ስርነቀላዊያን ለሚባሉቱ) የሚዋጥ አይደለም።
እንደእነዚህ ተመራማሪዎች ግኝትና አስተያየት ከሆነ ከብሄር፣ ዘር ምናምን ጋር በተያያዘ (እነሱ “ሬስ” የሚለውን ነው የተጠቀሙት) ያለው “ማንነት” ቅርስ (“Heritage” በቃ፤ “Racial Heritage” እንዲሉ) እንጂ ሌላ አይደለም። ወደ እዚህ፣ ወደ እኛ ጋ ሲመጣ ግን ይህ አይነቱ ጥናትም ሆነ ግኝቱ “አጥኝው እራሱ ብሄሩ ምንድን ነው?” የሚል ጥያቄን ካላስነሳ በስተቀር የአስተሳሰብ ለውጥን የሚያመጣ ስለመሆኑ የሚረዳም ሆነ የሚያስረዳ ስለመኖሩ መጠራጠር ባይቻልም፤ “አለ ወይ?” እንዳለው ድምፃዊ “የታለ?” ብለን እንድንጠይቅ እንገደዳለን። ስሙን ባለማስታወሴ የሚቆጨኝ የቴሌግራሙ ጦማሪ ይህንኑ ማንነት ቅርስ መሆኑን በሚያሳብቅ መልኩ የሚከተለውንም ጣል አድርጎት እናገኛለን፤
የፖለቲካ መሪ የህዝብን ችግር የሚፈታ ትልቅ ማንነት ነው። የበደል ችግር በጠበቃና ዳኛ ፍትህ አግኝቶ ይፈታል። ስለዚህ ጠበቃና ዳኛ ችግር የሚፈታ ማንነት ነው ማለት ነው። ችግር የማይፈታ ማንነት በራሱ ችግር ነው። ማንነት እሴት የሚጨምር ካልሆነ በኪሳራ መኖር እየኖሩ ሞት ነው። ማንነት የምርት እጥረት የሚፈታ አምራች የመሆን ብቃት ነው። ችግር የማይፈታ ማንነት በጠራራ ፀሀይ እንደተለበሰ ካቦርት ነው። ምንም ካልጠቀመ መጉዳቱ ስለማይቀር አውልቆ መጣል ነው። (እዚህ ጋ ከላይ የጠቀስነውን 18/137 መለስ ብለው ይመለከቷል።)
ከላይ “ማንነት”ን በተመለከተ ያሰፈርናቸው ሀሳቦች ባጠቃላይ የሚሉት ጉዳይ፤ የሚያስተላልፉት ዐቢይ መልእክት ቢኖር “ማንነት” ለበጎ እንጂ ከኋላ የነበረውን ወደፊት አምጥቶ ቋያ እሳት የሚሆንበት፤ (ምርጫ/ቅርጫ እንደተባለው) ለምርጫም ሆነ ቅርጫ ፍጆታ የሚውልበት አንዳችም ዘመናዊ ምክንያትም ሆነ ሥነአመክኗዊ ምክንያት የለውም የሚል ነውና በዚሁ ተስማምተን ወደ ዘንድሮው ምርጫችን ስጋትና ተስፋ እንመለስ።
ምንጊዜም አተካሮ ከምርጫ በኋላ እንጂ በፊት አይመጣም፤ በተለይ የተለመዱት (ተጭበርብሯል፣ ኮሮጆ ተገልብጧል…) ቃላት እና የመሳሰሉት ከእነ አጃቢዎቻቸው እስከ ንፁሀን ደም መፍሰስ ድረስ የሚዘልቁ፤ የአዋጅ ያህል የሚቆጠሩ የጦርነት ቃላት ናቸው። እንዲህ አይነቱ ነገር (ተጭበርብሯል፣ ኮሮጆ ተገልብጧል…) የትም ቢኖርም በተለይ የምርጫ ውጤትን አበጥሮ ለማየት የሚያስችል ሙያ (Psephology) እና ባለሙያው በሌሉባቸው አገራት ጉዳዩ የከፋ ነውና ለሁሉም (መራጭ፣ አስመራጭና ተመራጭ) ወገኖች የምርጫ ሥነ-ምግባር፣ መርህና ሳይንሱን ማክበር እንደሚገባቸው ከወዲሁ ቃል መግባት የግድ ይጠበቅባቸዋል። በቃ ይሄው ነው። አገርና ህዝብ ሲኖሩ ነው ሁሉም የሚኖረው። በመሆኑም አሁን ያለውን የምርጫና ውጤቱን አስፈሪ አዝማሚያ ወደ እማያስፈራና ህዝባዊ (በህዝብ የተመረጠ) መንግስት መመስረት ወደ እሚያስችልበት አዝማሚያ እንገልብጠው።
በመጨረሻም፣ ተመልሶ ለሚመጣ ምርጫ ብለን ተመልሶ ለማይመጣ ህይወት የምንሰጠው ዋጋ ቢያንስ የህሊና ተጠያቂነት እንዳያስከትልብን እንጠንቀቅ!!!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 12/2013