ወርቅነሽ ደምሰው
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ሲሰራባቸው የቆየባቸውን ስትራቴጂና ፖሊሲ ለመከለስ የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ከሁለት ወራት በፊት ከአራት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር መፈራረሙ የሚታወስ ነው፡፡ እነዚህም አራት ዩኒቨርሲቲዎች ሀዋሳ ፣ ጅማ፣ ጅግጅጋና ወሎ ዩኒቨርሲቲ ሲሆኑ ፤ ዩኒቨርሲቲዎች በስምምነቱ መሠረት በጋራ በመሆን ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡
እነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች ጥናትን መሠረት በማድረግ አንድ ወጥ ሀገር አቀፍ ስትራቴጂና ፖሊሲ በማዘጋጀት የኢትዮጵያን ዲያስፖራ ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችሉ ብዙ ሥራዎች እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ዩኒቨርሰቲዎች ወደ ሥራ ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ የሠሯቸውን ሥራዎች አስመልክቶ ከትናንት በስቲያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር አድርገዋል፡፡
የኢትዮጵያ የዲያስፖራ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ ኢድሪስ እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲዎች እየሰሩት ያለው ሥራ በመረጃ ላይ በመመስረት ስትራቴጂና ፖሊሲ በመቅረጽ የዲያስፖራውን ተሳትፎ ማሳደግ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡
በዲያስፖራው ዘንድ ያለውን ፍላጎትና አቅርቦት መሠረት ያደረገ ጥናት ላይ የተመሠረተ ስትራቴጂ መንደፍ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት ከአራት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ለመሥራት የሚያስችል የሥራ ምዕራፍ አሃዱ ተብሎ ተጀምሯል፡፡ ከሀዋሳ፣ ከጅማ፣ ከጅግጅጋና ከወሎ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን ጥናትን መሠረት ያደረገ መረጃ በመስጠት ጠንካራ ሥራ ለመስራት ያለመ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
በፕሮጀክቱ ለመሥራት የታቀዱት አራት ዋና ዋና ሥራዎች ናቸው፡፡ እነዚህም ውስጥ አንደኛው አሁን ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዲያስፖራው ያለው ተሳትፎ ያለበት ደረጃ ያሉ ማነቆችና መልካም እድሎች ምን ይመስላሉ የሚለው የሚያሳይ ነው፡፡ ሁለተኛው የዲያስፖራው ተሳትፎ ቁልፍ ዘርፎች ተብሎ የሚጠቀሱት የእውቀት፣ የክህሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ረገድ በጤና ተቋማትና በህዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ የዲያስፖራው ተሳትፎና ሚና ምን መሆን አለበት? መቆጣጣር ያለበት እንዴት ነው የሚለው ያካተተ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ለወጪ ንግድ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከሚያወጡ ሀገሮች መካከል አንዷ ናት የሚሉት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ይህ ፕሮጀክት ይህንን እንዴት አድርገን በስትራቴጂ ደግፈን ሀገራችንን የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለመምራት እንችላልን የሚለውን ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ያለመ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
ሦስተኛው አሁን ላይ ያለውን የዲያስፖራ ስትራቴጂና እቅድ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉበትን ሀብቶች የማስተዳደር አቅሞችን ታሳቢ ያደረገ ነው ወይ? አብዛኛው በውጭ ሀገራት ያሉ የዲያስፖራዎች በአገር ልማት ላይ የበኩላቸውን ተሳትፎ ለማድረግ ወደ ሀገር ቤት እየመጡ ቢሆንም ከተሞች፣ ከተማ አስተዳደሮችና ክልሎች በመሬት አቅርቦትና አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ረገድ የዲያስፖራውን ፍላጎቶች የሚያሟሉ ናቸው ወይ? የዲያስፖራው ፍላጎቶችስ ምንድናቸው ? የትኛው አካባቢ ምን አይነት ምቹ ሁኔታዎችና እድሎችና አቅም አሉት? ምን አይነት የህጋዊና ተቋማዊ አሠራሮች አሉ የሚሉት ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያስችል በሁሉንም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች መሠረት ያደረገ ፕሮጀክት ለመቅረጽ ያለመ ነው፡፡ አራተኛው ቀደም ሲል የዲያስፖራ ፖሊሲ ያለ ቢሆንም ፤ አሁን ላይ በርካታ ሁኔታዎች ተቀይረዋል፡፡ ይህንን ታሳቢ ያደረገ ለዲያስፖራው ፖሊሲ ግብዓት የሚሆን ጥናት ላይ መሠረት ያደረገ መረጃ ለማቅረብ ታስቦ ፕሮጀክት ተቀርጿል፡፡
እነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች በአራቱ ዋና ዋና ዘርፎች ላይ በተናጥል ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተው አሁን ላይ ዝርዝር የጥናት መነሻ (ፕሮፖዛል) አዘጋጅተዋል፡፡ ይህንን ዩኒቨርሲቲዎች በተናጠል ያዩትን ጥናት በአንድ ላይ በማምጣት አንድ ወጥ የሆነ ሀገር አቀፍ የጥናት ፕሮፖዛል ያቀርባሉ፡፡ ይህም ያስፈለገበት ዋና ምክንያት ስትራቴጂ ሲቀረጽ የባለድርሻ አካላት ያሳተፈ መሆን ስላለበት ነው፡፡ በዚህ ስትራቴጂ ከጥንስሱ ጀምሮ ብዙ ሀሳብ ተንሸራሽሮበት አንጻራዊ በሆነ መልኩ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የስትራቴጂው ላይ ሀሳብ በመስጠት ተካፋይ እንዲሆኑ ታሳቢ ተደርጎ ነው፡፡ በመሆኑም ሁሉም ባለድርሻ አካላት የዲያስፖራ ስትራቴጂና ፖሊሲ በምን መልኩ ሊሻሻል ይገባዋል? ምን ምን ጉዳዮች ማካተት አለበት የሚለውን ሀሳብ አካቶ ከተዘጋጀ በኋላ ተሻሽሎ ወደ ሥራ የሚገባበት ሁኔታ ለማመቻቸት የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በዚህ ውይይት የተሻሉ ሀሳቦች ተንሸራሽረው አሁን ላይ ያለውን ክፍተት መሙላት የሚችሉ ነጥቦች በማካተት ስትራቴጂ በመቅረጽ ለብዙ ዓመታት ማሻገር የሚችል ሥራ መሥራት እንጠብቃለን ብለዋል፡፡
ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጥናት አቅራቢ ከሆኑ መካከል ረዳት ፕሮፌሰር አካለወልድ ፈድሉ በበኩላቸው፣ ዲያስፖራው በሀገሪቱ ውስጥ ያለው የኢንቨስትመንት ተሳትፎ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል? በአብዛኛው በምን አይነት የኢንቨስትመንት ሥራ ላይ ተሰማርተው ነው ያሉት? የሚሉትና የመሳሳሉት ተያያዥ ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያስችል (የጥናት መነሻ) ፕሮፖዛል ተዘጋጅቷል፡፡
በዚህ ዙሪያ በሀገር አቀፍ ደረጃ ጥናት በማከናወን ስትራቴጂ ለመቅረጽ አንዱ ዋንኛው የዲያስፖራውን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ላይ ተመስርቶ ዲያስፖራው የሀገሪቷ ልማት ላይ የበኩሉን ድርሻ እንዲያበረክት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የሚያግዝ ሥራ ለመሥራት አላማ አድርጎ የተነሳ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
እንደ ረዳት ፕሮፌሰር አካለወልድ ገለጻ፤ የዲያስፖራው እንቅስቃሴ ወይም ልማት ፖሊሲና በስትራቴጂ ላይ መስራት አድርጎ ማፋጠንና ለሀገራዊ ልማት ትልቅ አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፡፡ ጥናቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ከጥናቱ በሚገኘው ውጤት መሠረት የዲያስፖራ ኤጀንሲ ዲያስፖራው በሀገሪቱ ውስጥ መጥቶ ኢንቪስት አድርጎ ውጤታማ በመሆን ለሀገሩ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሊያበረክት የሚያስችል ሥራን እንዲሰራ ለማድረግ አስፈላጊ የሆኑት ነገሮች አስቀድሞ በመለየት ሀገራዊ ድጋፎች ለማድረግ መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር እንደሆነ ተናገረዋል፡፡
ከጅማ ዩኒቨርሲቲ የጥናት አቅራቢ ዶክተር መኮንን ቦጋለ በበኩላቸው፤ ዘላቂ ልማት ለማምጣት ከተፈለገ የአፍሪካ ህብረት የትራንስፎርሜሽን አጀንዳ እንደሚለው ዲያስፖራው ትኩረት ያደረገ መሆን አለበት በማለት ለዲያስፖራው በብዙ መንገድ ትልቅ ትኩረት የሰጠ ነው፡፡ አሁን ላይ እንደ ሀገር የምናፈራው ትውልድ በሥነ ምግባር፣ በእውቀትና በቴክኖሎጂ ፈጠራ ላይም የዳበረ መሆን አለበት የሚሉት ዶክተሩ፤ ይህንን ለማድረግ የአሠራር ሥርዓት (ሲስተም) መዘርጋት አለበት፡፡
መሠረቱ የያዘ ሲስተም መዋቅርና የአሠራር ባህል የሚጎለብትበት፤ ስትራቴጂዎችና ማስፈጸሚያ መሳሪያዎች ያሉ መሆኑ አለበት፡፡ እንደዚህ አይነቱ ጥናት ሲስተም በማምጣት በፖሊሲና በስትራቴጂ እንዲመራ ለማድረግ ግብዓት ይሆናሉ፡፡
አሁን ላይ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ስንመለከት በግለሰቦች ደረጃ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች ቢኖርም የተዘረጋ የአሠራር ሥርዓት ስለሌላ በቅንጅት የሚስራ አይደለም፡፡ ስለዚህ በፖሊሲና በስትራቴጂ በመደገፍ ከትውልድ ትውልድ እንዲሻጋገር ማድረግ ይጠበቅበታል ሲሉ ሀሳባቸውን አጠቃለዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 13/2013