ይበል ካሳ
ኢትዮጵያ የታላቁ ፍጥረት የሰው ዘር መገኛ፣ የራሷ ፊደልና የዘመን አቆጣጠር ያላት፣ እንደ ጥምቀት፣ መስቀል፣ ፍቸ ጫምባላላ የመሳሰሉ መንፈሳዊና ባህላዊ ብርቅዬ ቅርሶችን ለዓለም ያበረከተችና ሌሎችም ተዘርዝረው የማያልቁ ታላላቅ ቁሳዊና መንፈሳዊ ቅርሶች ባለቤት የሆነች ታላቅ ሃገር ነች። በውብ ተፈጥሮ ያጌጠች ከመሆኗም ባሻገር ስልጣኔን ቀድመው ለዓለም ያስተማሩ ጥበበኛ ልጆቿ የአዕምሮ ውጤት የሆኑት ዓለምን ያስደነቁት እነ አክሱም፣ ላሊበላ፣ ፋሲልና ጀጎል የመሳሰሉት ታሪካዊ ቅርሶች ባለቤትም ነች።
ይህም ኢትዮጵያና ሕዝቧ በዓለም መድረክ ከፍ ብለው እንዲቀመጡ የሚያደርግ አኩሪ ታሪክ ከመሆኑም ባሻገር በአግባቡ ከተጠቀሙበት የዓለም ሁሉ ዓይን የሚያርፍበትና በከፍተኛ የቱሪስት መስህብነት ታላቅ የሃብትና የብልጽግና ምንጭ መሆንም የሚችል ነው። በዚህ ረገድ ሃገሪቱ ካላት ተዝቆ የማያልቅ የመስህብ ሃብት አኳያ ዘርፉ ገና አልተነካም ማለት ይቻላል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት የቱሪዝም መስህብ ተያያዥ ኢንዱስትሪዎች በተለይም የዘርፉ መንቀሳቀሻ ሞተር የሆነው የሆስፒታሊቲና የሆቴል ኢንዱስትሪው አበረታች ዕድገት እያሳየ መምጣቱን ብዙዎች ይስማማሉ። ይሁን እንጂ በሃገሪቱ የተፈጠረውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ፖለቲካዊና መንግስታዊ ለውጥ ከመጣ በኋላ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ዘርፉ በተለያዩ ጊዜያት በተደጋጋሚ በችግር እየተፈተነ ይገኛል። አንድ ጊዜ ፖለቲካዊ ለውጡን ተከትሎ በእዚህም እዚያም በሚፈጠሩ አለመረጋጋቶችና የፀጥታ መደፍረሶች ሌላ ጊዜ ደግሞ በዓለም ላይ በተፈጠረው የኮሮና ወረርሽኝ ክፉኛ ጉዳት ደርሶበታል።
ባለፈው ዓመት መጋቢት መጀመሪያ ላይ ኮሮና ወደ አገራችን ከገባ በኋላ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሰዎች እንቅስቃሴ ላይ ተደጋጋሚ ገደቦች በመጣላቸው የሆቴል ኢንዱስትሪው ከባድ ጫና ውስጥ ገብቷል።
በቫይረሱ ተፅዕኖ ሳቢያ የእንግዶች ቁጥር መቀነስ ያስከተለው የገበያ መዳከም፣ በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ ሆቴሎች ውስጥ 88 በመቶ ሥራ እንዲያቆሙ አድርጓቸው እንደነበርም የአዲስ አበባ ሆቴል ባለንብረቶች ማህበር የኮሮና ቫይረስ በኢንዱስትሪው ላይ ያስከተለውን ጉዳት ለመረዳትና የመፍትሔ ሐሳብ ለመጠቆም ያካሄደው የዳሰሳ ጥናት ያመላክታል።
በዳሰሳ ጥናት ሪፖርቱ እንደተመለከተው፣ በማህበሩ ሥር ከሚገኙ 130 ሆቴሎች መካከል 56 በመቶው የኮሮና ቫይረስ በፈጠረው ቀውስ ምክንያት ሙሉ በሙሉ ተዘግተዋል። 32 በመቶ የሚሆኑት አገልግሎታቸውን በከፊል ለማቆም እንደተገደዱ፣ የተቀሩት 12 በመቶ ሆቴሎች ከውጭ ለሚገቡ መንገደኞች በለይቶ ማቆያነት እያገለገሉ መሆኑን ማህበሩ በጥናቱ አመላክቷል።
ቫይረሱ በፈጠረው ጫና ምክንያት አስደንጋጭ በሚባል ሁኔታ ዘርፉ ችግር ውስጥ መግባቱን የሚገልጸው የማኅበሩ የጥናት ሪፖርት፣ በአሁኑ ወቅት በከተማዋ የሚገኙ ሆቴሎች የእንግዳ ቅበላ መጠን ወደ ሁለት በመቶ እንዳሽቆለቆለና በወር እስከ 35 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ኪሳራ ያጋጥም እንደነበርም ያስረዳል። የገበያ መዳከም ከዚህም በከፋ ሁኔታ ከቀጠለ ሆቴሎች ከፍተኛ የሆነ የሥራ ማስኬጃ ገንዘብ እጥረት ስለሚገጥማቸው፣ ለሠራተኞቻቸው ደመወዝ መክፈል እንደሚቸግራቸው አሳስቧል።
በሥራ ላይ ለመቆየትም የሆቴል ባለሀብቶች ተጨማሪ ካፒታል ለመመደብ እንደሚገደዱ፣ ይህን ማድረግ ሳይችሉ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ከባድ ጉዳት እንደሚያስከትል ሪፖርቱ ገልጿል። ለዚህም ማህበሩ ሆቴሎቹ የገቡበትን ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ለመፍታ ከመንግሥትና ከሌሎች ፋይናንስ ተቋማት ጋር በመሆን እየሠራ እንደሚገኝ፣ የአዲስ አበባ ሆቴል ባለንብረቶች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ቢንያም ብሥራት ይገልጻሉ።
“ወደ 82 በመቶ የሚሆኑት ሆቴሎች ከፍተኛ የብድር ጫና ስላለባቸው፣ ባንኮች የብድር መክፈያ ጊዜ እንዲያራዝሙላቸው እየጠየቅን እንገኛለን። ይህ መሆን ካልቻለ ግን ሆቴሎቹ ከፍተኛ ጉዳት ሊያጋጥማቸው ይችላል” ይላሉ።
በመዲናዋ ከሚገኙ ትልልቅ ሆቴሎች መካከል አንዱ የሆነው የኢሊሊ ኢተርናሽናል ሆቴል የሽያጭና የገበያ ጥናት ዳይሬክተር ወይዘሮ ኤልሳቤጥ ሳሙኤልም ኮሮና በሆቴሎች ሥራ ላይ እያደረሰ ያለውን ከፍተኛ ጉዳት ይናገራሉ። “በአሁኑ ሰዓት ሆቴል ላይ የምንሰራ ሰዎች በፊት እንደምንሰራው እየሰራን አይደለም። ምክንያቱም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከመጣ ጊዜ ጀምሮ የአየር ጉዞ ላይ ትልቅ ችግር ነው ያለው።
ወረርሽኙ ያስከተለው ችግር በዋነኝነት የመታው ይህን ዘርፍ ነው። እንደ ምሳሌ የእኛን ሆቴል ብንወስድ ባለ አምስት ኮከብ ኢንተርናሽናል ሆቴል ነው፤ ብዙዎቹ ደንበኞቻችን ከውጭ የሚመጡ ናቸው።
በአብዛኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቢሮዎችና መንግስታዊ ያልሆኑ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ናቸው ደንበኞቻችን። በመሆኑ በአየር ትራንስፖርት ላይ ባለው ችግር የተነሳ ደንበኞቻችን ማግኘት አልቻልንም። ይህም ገቢያችንን በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀዛቀዝ አድርጓል” ይላሉ።
በሆቴሎች ሥራ ውስጥ ትልቁን ሚና የሚጫወተው የአየር ትራንስፖርት ዘርፉ መሆኑንና ዋነኛው የኮሮና ቫይረስ ተጎጂም ይኸው ዘርፍ በመሆኑ በሆቴልና መሰል አገልግሎት ዘርፍ ያለው ሥራ እንደ ድሮው ሊሆን አልቻለም። በመሆኑም ወቅቱ በዘርፉ ለተሰማሩ ሰዎች ጥሩ ጊዜ አለመሆኑንም ያመላክታሉ።
“ኮቪድ የጎዳን እኛን ነው ብዬ አስባለሁ፤ በአጠቃላይ አስቸጋሪ ወቅት ነው ለእኛ ” የሚሉት የኢሊሊ ኢተርናሽናል ሆቴል የሽያጭና የገበያ ጥናት ዳይሬክተር ጉዳቱ ለሠራተኛ ደመወዝ መክፈል እስኪያቅት ድረስ የሚፈታተን መሆኑንም ይጠቁማሉ።
የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተም ወይዘሮ ኤልሳቤጥ ተስፋን ሰንቀዋል። ለዚህ ደግሞ ምክንያታቸው የኮቪድ-19 ክትባት መጀመሩ ወረርሽኙ የሚያስከትለውን ቀውስ እንዲቀንስና ቀስ በቀስ ነገሮች ወደነበሩበት እንዲመለሱ ያደርጋል የሚል ነው። “ክትባቱ መምጣቱና መጀመሩ መልካም ነው። ክትባቱ አሁን ላይ ቅድሚያ ሊሰጣቸው በሚገቡ አካላት ላይ ተጀምሯል። ቀስ በቀስ ሁላችንም ጋር ይደርሳል ብዬ አስባለሁ።
ከተከተብን ደግሞ በሽታውን የመቋቋም ሁኔታ ይፈጠራል የሚል እምነት አለኝ። ይህም ዓለም ላይ ያለውን እንቅስቃሴ ወደነበረበት እንዲመለስ ስለሚያደርገው ሁሉም ነገር ሥራችንም ወደነበረበት ይመለሳል የሚል ተስፋ አለኝ። የተሻለ ጊዜ ይመጣል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፤ እርግጠኛ ነኝ መጭው ጊዜ ጥሩ ይሆናል” በማለት በተስፋ ተሞልተው ቀጣዩን ጊዜ ይናፍቃሉ።
በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የሐዋሳ ሴንትራል ሆቴል የኮርፖሬት ዘርፍ ማኔጅንግ ዳይሬክተር አቶ ፀጋዬ ወልደሰንበት በበኩላቸው ከ300 በላይ ለሚሆኑ ሠራተኞች በወር ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ደመወዝና ምግብ በማቅረብ ችግሩን ለማለፍ እየተፍጨረጨረ የሚገኘው ሴንትራል ሆቴል እስከ መጨረሻው ድረስም ሠራተኞቹን ላለመበተን ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ይናገራሉ።
መንግሥት በተገቢው መንገድ ብድር እንዲለቀቅ ካላደረገ ከፍተኛ አደጋ ሊመጣ ይችላል ይላሉ። “ሆቴል አልጋው ብቻ ሳይሆን፣ በርካታ ስብሰባዎችና፣ ሠርግን የመሳሰሉ አገልግሎቶች በማቅረብ የሚሳተፉበት በመሆኑ፣ አንድ ሆቴል ተዘጋ ማለት የሠራተኞች ኑሮ ተዘጋ ማለት ነው። በዙሪያቸው ያሉ ሰዎች ሁሉ ሥራ ፈት ሆኑ ማለት ነው” ይላሉ።
የኢትዮጵያ ሆቴልና መሰል አገልግሎት አሠሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍትህ ወልደሰንበት በበኩላቸው የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል የተወሰዱ ዕርምጃዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፉን ከሥራ ውጪ ማድረጉን ይናገራሉ። በኢትዮጵያም የሚገኙ ሆቴሎች ክፉኛ በመጎዳታቸው ሠራተኞቻቸውን ይዘው ለመቆየት የሚያስችላቸው የአንድ ዓመት 6.6 ቢሊዮን ብር ከወለድ ነፃ ብድር ጠይቀው፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለስድስት ወራት የሚሆን 3.3 ቢሊዮን ብር በአምስት በመቶ ወለድ እንደፈቀደላቸውም ያስታውሳሉ።
ብድሩ በ18 ባንኮች አማካይነት ለሆቴሎች እንዲሰጥ የተደረገ ቢሆንም፣ ባንኮቹ ወለድ የማያገኙ በመሆኑ ብድሮቹን ለመስጠት ዳተኝነት እንዳሳዩ ዶክተር ፍትህ ያስታውሳሉ። ከተፈቀደው ብድር ለሆቴሎች መሰጠት የተቻለው ሰባት መቶ ሚሊዮን ብር ገደማ ብቻ መሆኑን ይጠቁማሉ። ብድሩን ያላገኙ ሆቴሎችም መኖራቸውንም ይናገራሉ።
የኮሮና ወረርሽኝ ለመከላከል የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማብቃቱና ኢትዮጵያ እንደ አገር የተዘጋውን የቱሪዝም ዘርፍ ለመክፈት የሚያስችሉ ሁኔታዎች በመፈጠራቸው ከ2013 ዓ.ም መባቻ አካባቢ ጀምሮ ሆቴሎች ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ ወደ ሥራ ለመመለስ ተሞክሮ በተወሰነ ደረጃ ሲሰሩ የቆዩ ቢሆንም ወረርሽኙ እንደገና እየከፋ በመምጣቱ እንቅስቃሴንና መሰባሰብን የሚያግዱ ፕሮቶኮሎች እየወጡ በመሆናቸው ዘርፉ አሁን ላይ በድጋሚ ችግር እንደገጠመው ያመላክታሉ።
“ሆቴሎች በርካታ የሥራ ዕድል የፈጠሩና የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ በመሆናቸው፣ ለኢኮኖሚው እንቅስቃሴ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ተቋማት ናቸው። ሆኖም ባለፉት አራት ዓመታት በተደጋጋሚ በደረሰባቸው ተግዳሮቶች ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠዋል” ይላሉ።
ሆኖም አሁን ባለው ሁኔታ የሆቴል ባለቤቶች የመንግሥትን አቅጣጫ በመከተል ሠራተኞቻቸውን በሥራ ላይ ለማቆየት ሲጥሩ ቆይተዋል አሁንም ይህንኑ ማስቀጠል ይገባቸዋል። እንዲህ ያለውን አስቸጋሪ ወቅት ተደጋግፈን ማለፍ ይገባናል ይላሉ። ይህ ጊዜ አልፎ ወደ ቀድሞ ሁኔታው ይገባል የሚል ተስፋም አላቸው።
መንግስት በበኩሉ የመስህብ፣ የቱሪዝምና ተያያዥ ዘርፉን ካጋጠመው ጊዜያዊ ተግዳሮት ተላቆ በውጤታማነት እንዲቀጥል ከጀመረው አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ውስጥ በማካተት ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑ ይታወቃል። የቱሪዝም ዘርፍ የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ችግሮችን ለመቅረፍ ትልቅ አቅም እንዳለውም ይታመናል።
ችግሩን ለመፍታት ቱሪዝም ውስጥ ያሉ አካላትን አስተባብሮ የማስፈጸም አቅምን ማጠናከር፣ መሠረተ ልማቱን ማሻሻል የአገልግሎት አሰጣጡን ማዘመንና ተወዳዳሪነትን ማጎልበት ይጠይቃል። ለዚህም በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ አሠሪዎች ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር አንደኛውን አገር አቀፍ የሆቴልና ቱሪዝም ኮንፍረንስ በ2011 ዓ.ም መጨረሻ ማካሄዱ ይታወሳል። በወቅቱ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ እንደ አፍሪካም ሆነ እንደ ዓለም በዘርፉ ያላት ድርሻ ሲፈተሽ ካላት እምቅ አቅም አንፃር ተጠቃሚ አይደለችም።
ለዚህም በርካታ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ። ተወዳዳሪ ሊያደርግ የሚችል ጥራት ያለው አገልግሎት አለመስጠትና የመስህብ ቦታዎች በተገቢው ሁኔታ ለምተውና ተወዳዳሪ ሆነው አለመገኘታቸው ከምክንያቶቹ እንደሚጠቅሱ መግለጻቸው ይታወሳል። ችግሩን ለመለቅረፍ መንግሥት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት፣ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማጎልበት ከባለድርሻ አካላትና ከህብረተሰብ ወኪሎች ጋር እየተመካከረና ተጨባጭ ሥራዎችን ለማከናወን እየተንቀሳቀሰ እንደሆነም ጠቁመዋል።
በአሁኑ ሰዓት ሚኒስቴሩ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ከተሰማሩ አካላት ጋር ምክክሮችን ለማድረግ ሁለተኛው አገር አቀፍ የሆቴልና ቱሪዝም ጉባዔ በባህር ዳር ለማዘጋጀት ዝግጅት እየተደረገ እና በጉባኤው ዘርፉ የገጠመውን ችግር ለመፍታት በርካታ የመፍትሔ አቅጣጫዎች ለማመንጨት መታቀዱን የኢትዮጵያ ሆቴልና መሰል አገልግሎት አሰሪዎች ፌዴሬሽንን ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍትሕ ወልደሰንበት ያመላክታሉ።
በዚህም ኮሮናን ጨምሮ ወቅታዊ ተግዳሮቶችን በምን መንገድ ማለፍ እንደሚቻል የጋራ አቅጣጫ የሚቀመጥ ከመሆኑም ባሻገር መስቦች በተገቢው እንዲጎበኙና የሀብት አመንጪ እንዲሆኑ በየመዳረሻዎቹ ለቱሪስት የሚመጥን የመሠረተ ልማት ሥራዎችን ለመስራት ሚያስችሉ ለኢንዱስትሪው ዘላቂ ዕድገት የሚያገለግሉ ስልቶች የሚነደፉበት መሆኑንም ይጠቁማሉ።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 13/2013