ኃይለማርያም ወንድሙ
መልካምነት ይከፍላል ይላሉ አባቶቻችን። በጎ ማድረግ ለሚደረግለት ሳይሆን ለአድራጊው ለራሱ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ሲገልፁ። ዓለማችን በጥቂት ክፉዎች የምትሸበር ቢሆንም ይሄ ክፋት ግን በብዙ በጎዎች ሁሌም መዳንን እንዳገኘ ነው።
አበው “ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለሃምሳ ሰው ደግሞ ጌጡ ነው” ይላሉ። ይሄ አባባል እውነት ስለመሆኑ ደግሞ እልፍ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል። በተለይ ጉልበት ሲደክም፣ የተፈጥሮ አደጋ ሲደርስ፣ ጦርነት ለሰብአዊ ችግር ሲያጋልጥ ቀድመው የሚደርሱ ተፅእኖ ፈጣሪ ሰዎች ብዙ ናቸው። ከነዚህ ውስጥ ደግሞ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በቀዳሚነት ይነሳሉ። አቅም ባይኖራቸው እንኳን ሙያቸውን ተጠቅመው አንጀት የሚያርስ ድጋፍና አጋርነትን በማሳየት ይታወቃሉ።
ዛሬ በጎነትና ኪነጥበብን አዋህደን ለማቅረብ የወደድነው ያለምክንያት አይደለም። በቅርቡ በኢትዮጵያ ውስጥ በተከሰተው የፖለቲካና ማህበራዊ አለመረጋጋት ምክንያት አጋርነቱን ከባህር ማዶ ያሳየ አንድ ዝናው የናኘ ኢትዮጵያዊ አርቲስት ማንነትን ለማሳየት እንጂ። ይህ ሰው አቤል ተስፋዬ ይባላል።
የአር ኤንድ ቢ ስልት ሙዚቀኛው አቤል ተስፋዬ በመድረክ ስሙ “ዘ-ዊኬንድ” ባለፈው ወር መገባደጃ በትግራይ ክልል እየቀረበ ለሚገኘው ሰብአዊ ድጋፍ የሚውል አንድ ሚሊየን ዶላር በአለም ምግብ ፕሮግራም በኩል መለገሱን በርካታ የመገናኛ ብዙሃን ተቀባብለውታል::
ይህ ኮከብ ድምጻዊ የተወለደው በካናዳ ነው:: በስደት ወደዚያው ከሄዱ ኢትዮጵያዊ ቤተሰቦች የተገኘ ነው:: ታዲያ ችግርን ከሩቅ አይቶ ሳይሆን በቅርበት በቤተሰቦቹ ውስጥ የሚያውቀው ሙዚቀኛው “ ወገኖቼ ኢትዮጵውያን ሰላማዊ ሰዎች ከህፃናት ጀምሮ እስከ አዛውንቶች በስሜት አልባዎች ሲገደሉ እና ሲጎሳቆሉ ሰምቼ ልቤ ተሰበረ “ በማለት እጆቹን ለድጋፍ መዘርጋቱን አስታውቋል::
የዝግጅት ክፍላችን እነዚህን መሰል ጀግኖች በየቦታው እንደ አሸን እንዲበዙ ይመኛል። መመኘት ብቻ ሳይሆን ምስጋናም ያቀርባል። ከዚህ በመነሳት የሙዚቃ ጀግንነቱን በበጎነት የደገመውን ዘዊኬንድ ማንነት በጥቂቱ ከዚህ እንደሚከተለው ልንዳስሰው ወደድን።
አቤል ተስፋዬ (ዘዊኬንድ)
ከዊኪፒዲያ ድረ ገፅ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ አቤል መኮንን ተስፋዬ እኤአ የካቲት 16 ቀን 1990 ነው የተወለደው:: ዘ ዊኬንድ በሚለው የመድረክ ስሙ ይታወቃል:: ካናዳዊው ድምፃዊ፣ የግጥምና ዜማ ደራሲ ሲሆን ፣የሙዚቃ ሸክላ አሳታሚም ነው:: ሁለገብ አርቲስት የሆነው አቤል በድምጹ ስልት በሙዚቃዎቹ እና ወጣ ባለ አቀራረቡ ዝናን አትርፏል:: ሁሌም በሌሎች አርቲስቶች ጭምር የሚጠቀሰው በዘመናችን ተፅዕኖ ፈጣሪ ሙዚቃው ነው::
ዘ ዊኬንድ ዝና ማግኘት የጀመረው እኤአ በ2010 ስሙን ሳይጠቅስ በዩቲዩብ ብዙ ሙዚቃዎቹን ከጫነ በኋላ ነው:: ከዓመት በኋላ mixtapes House of Balloons,(የተቀጣጠሉትና የተደበላለቁት የፊኛ ቤቶች) Thursday,(ሐሙስ) and Echoes of Silence, (የገደል ማሚቱው ዝምታ) በሚል የለቀቃቸውን ሙዚቃዎቹን ተከትሎ በብዙ መደበኛ የህትመት ሚዲያዎች ከፍተኛ ዝናን ያገኘው አር ኤንድቢ በሚባለው ቡድን ሲጫወት እምብዛም ባልደመቀ ስልት ልዩ በሆነ ተስጥኦው በዙሪያው ባሉ ሁሉ ማንነቱ ታወቆ ነው::
ለሪፐብሊክ አሳታሚዎች ፈርሞ ሦስት ተመሳሳይ እሳቤ ያላቸውን አልበሞች ለቋል:: ከዚህ ውስጥ ኪ ላንድ (ቁልፍ መሬት) የሚለው በ2013 የተለቀቀ ነው:: ቀጥሎ ከእብደት በስተጀርባ ያለ ውበት ማለትም Beauty Behind the Madness በሚል በሁለተኛው ዓመት በ2015 አስከተለ፤ይህም በዓመቱ እጅግ በጣም ጥሩ ከተሸጡት አልበሞች መካከል ሆነ::
በቢልቦርድ ሰሌዳ ከአንድ መቶ ቁጥር አንድ ነጠላ ዜማዎች መካከል ‹‹ፊቴን አይሰማኝም ኮረብታዎቹ፣እና ከእብደት በስተጀርባ ያለ ውበት ዘመናዊ ምርጥ የከተማ አልበም በመሆን ከማሸነፋቸውም በላይ የ2016 የግራሚ አዋርድ ተመራጭ ለመሆን በቅተዋል::
የዘ ዊኬንድ ሦስተኛ አልበም ስታርቦይ 2016 ሲሆን በዚህም ተመሳሳይ ስኬትን ተጎናጽፏል፤ በስሙም ላይ ሌላ ዕውቅና ደርቦለታል:: በተመሳሳይ ምርጥ የከተማ የዘመኑ የ2018 ግራሚ አዋርድ አሸናፊ ነበር:: አራተኛው አልበሙ After Hours(2020) ማለትም ከሰዐታት በኋላ የሚለው ነው፤ ከዚህ ውስጥ “Heartless” ማለትም ርህራሄ አልባ እና “Blinding Lights” ብርሃናቱን ማጨለም የሚሉት ጎልተው የወጡ ነጠላ ዜማዎች ናቸው::
ከዓለም ምርጥ ነጠላ የሙዚቃ አርቲስቶች ሽያጭ መካከል 75 ሚሊየን የሙዚቃ ቅጂዎች ተሸጠዋል:: ዘ ዊኬንድ ሦስት የግራሚ አዋርድስ፣ አምስት ጊዜ የአሜሪካ ሙዚቃ ተሸላሚ እንዲሁም ዘጠኝ ጊዜ የቢልቦርድ ሙዚቃ ፣ሁለት የኤም ቲቪ ቪዲዮ ሙዚቃ ፣ዘጠኝ ጊዜ ጁኖ ሙዚቃ ተሸላሚ ነበረ:: ለአካዳሚ አዋርድ ሽልማትም ታጭቶ ነበር::
በርካታ የሰንጠረዥ ሪኮርድ ያለው ሲሆን፣ በቢልቦርድ አር ኤንድ ቢ የሙዚቃ ሰንጠረዥ በአንድ ጊዜ ሦስት ከፍ ያሉ ቦታዎችን መያዙም የመጀመሪያው አርቲስት ያደርገዋል:: በዚህም ፊቴን አይሰማኝም፣ አገኘሁዋት እና ኮረብታዎቹ ተጠቃሽ ነበሩ:: በተጨማሪም የአላን ስላይት እና የካናዳ ወክ ኦፍ ፌም (በከናዳ የዝነኞች ጎዳና ሽልማት) ተሸላሚ ሆኗል::
የልጅነት ሕይወት
አቤል መኮንን በካናዳ ቶሮንቶ ከኢትዮጵያውያን ስደተኛ ወላጆቹ ከላይ እንደጠቀስነው እኤአ በ19 90 ከአባቱ አቶ መኮንን እና ከእናቱ ሳምራ ተስፋዬ ተወለደ:: አባቱና እናቱ ከተለያዩ በኋላ በሴት አያቶቹ እጅ ነው ቶሮንቶ ውስጥ ያደገው:: ከሴት እያቱ ጋር ሲኖር አማርኛ የተማረ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎት ይከታተል ነበር::
ስለአባቱ ሲጠየቅ በስድስት ዓመት በደብዛዛው አይቼዋለሁ ፤በድጋሚ የ11 እና የ12 ዓመት ልጅም ሆኜ አዲስ ቤተሰብ መሥርቶ ከህፃናት ልጆቹ ጋር አይቼዋለሁ:: የት እንደሚኖር ግን አላውቅም:: ባየው ደስተኛ ነኝ፤ ትልቅ ሰው እንደሚሆን እርግጠኛ ነኝ:: በፍፁም ልፈርድበት አልሻም ሲል ያብራራል::
አርቲስቱ የአስር ዓመት ልጅ እያለ የህፃናት ፊልም ማየት ይወድ ነበር:: በቶሮንቶ ስካርቦርግ በሚገኘው በሂል ኮልጊቴ ኢንስቲትዩት እና በቢርችማውንት ፓርክ ኮሊጊቴት ኢንስቲትዩት ሲከታተል የነበረውን ትምህርት ግን አላጠናቀቀም:: በ2007 ትምህርቱን አቋርጦ ቤቱን ትቶ ቶሮንቶ አቅራቢያ ወደ ሚገኘው ፓርክዴል አቀና:: የመድረክ ስሙ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሲነሳ ደረጃውን ከፍ አደረገው::
ወደ ዝና ማማ
አቤል መኮንን አር ኤንድ ቢ ሙዚቃ ፕሮጀክት ሀሳብ ከነበረው ከደራሲ ጀርሚ ሮስ ጋር በ2010 ተገናኘ:: ለመነሻ ለማዜም የሞከረው በሳንቲያጎ የሙዚቀኞች መሰብሰቢያ ነው፤ በወቅቱም ሮስ ለአቤል ተስፋዬ የሙዚቃ መሣሪያዎችን ተጫውቶለታል:: ይህ ሁኔታ ሁለቱም አልበም ለማውጣት እንዲተባበሩ አደረጋቸው::
ሮስ ሦስት ዜማዎችን ለአቤል ሰጠ፤ ዜማዎቹም ዋት ዩኒድ፣ ሎፍት ሚውዚክ እና ዘ ሞርኒንግ የተሰኙት ናቸው:: እነዚህንና ሌሎች ዘፈኖችን ተጫወተ ፤ቀስ በቀስ ተመልካች አገኘ:: ማንነቱ ባይታወቅም እነዚህ ዘፈኖቹ በመድረክ ስሙ በዩ ቲዩብ ላይ ተጫኑ፤ በኦን ላይን ላይም የተወሰነ ትኩረት መሳብ ቻሉ:: በብዙ ሚዲያዎችም እየተለቀቁ ሽፋን ማግኘት ጀመሩ:: በፒች ፈርክና ኒውየርክ ታይምስ ህትመቶችም ጭምር ተዘገበባቸው:: ዌኬንድ የሚለውን የመድረክ ስሙን ከማግኘቱ በፊት በኖይስና ኪነ ካኔ ቡድን ይሠራ ነበር::
አቤል ወደ ቶሮንቶ አቅንቶ በከተማው ሞድ ክለብ አዳራሽ የመጀመሪያውን የቀጥታ ስርጭት ሙዚቃውን ሠራ:: በዚህ መድረክ ላይ ካናዳዊው ራፐር፣ ድምጻዊ ፣ የሙዚቃ ደራሲ ተዋናይ ፣ ስራ ፈጣሪ ድሬክ ተገኝቶ ነበር:: የእሱ በመድረኩ መገኘት የአርቲስቱን ከፍታ ጨመረው:: ከሙዚቃው ታዳሚዎች አንዱ ከነበረው ድሬክ ጋር አብሮ መስራት ጀመረ፤ በብዙ መድረኮች ላይ አብረው ተጫወቱ:: በአሁኑ ወቅት አልበሙ ከተለቀቀ በኋላ ከቃለ መጠይቅ በመራቅ በትዊተር ብቻ መገናኘትን መርጧል::
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 10/2013