ዳግም ከበደ
ሎሬት መላኩ በላይ ይባላል። የዛሬው የዝነኞች የእረፍት ውሎ እንግዳችን ነው። በኪነ ጥበብ ሙያ ዘርፍ በአብዛኞቻችን በሚታወቀው መጠሪያ መሰረት በተወዛዋዥነት እውቅ ባለሙያ ነው። እርሱ ግን በዚህ መጠሪያ ስለማያምንበትና ይልቁኑም እኔን ይገልፀኛል ብሎ በሚያስበው “ጨፋሪ” የሚል ስያሜ እንዲጠራ ይሻል። ምክንያቱን ቆይተን እናጋራቹሃለን። ለአሁኑ ግን የኢትዮጵያውያንን ባህል፣ ማንነት በተወዳጅ ጭፈራው ማስተዋወቅ የቻለው ባለሙያ የዛሬ መሰረት ስለሆኑት ጉዳዮች በቅድሚያ ለማንሳት ወደናል።
ምልሰት
አርቲስት ሎሬት መላኩ በላይ “ ጭፈራን እናቴ ሆድ ውስጥ ነው የተማርኩት” ይላል በፈገግታ ተሞልቶ። ይህን አስተያየት እንዲሰጥ ያስቻለው ከሙያው ጋር ያለው የረጅም ጊዜ ቁርኝትና ፍቅር ስለመሆኑ ከንግግሮቹ መረዳት ይቻላል። በዚህ ሙያ ውስጥ ያሉ አብዛኛዎቹ ሰዎችም ጥበብ መሰጠት አብሮ መወለድን ይጠይቃል በማለት ፍልስፍናዊ ይዘት ያላብሱታል። ከዚህ መነኛ እንደ እነ መላኩ በላይ በኪነ ጥበብ ዘርፉ ላይ ጉልህ ድርሻ ያላቸው ግለሰቦች ይህን ሃሳብ የሚያነሱት።
አርቲስት ሎሬት መላኩ በዓለም አቀፍ ደረጃ በበርካታ ጎብኝዎችና ዜጎች እውቅናን ያተረፈው የ”ፈንድቃ ባህል ማእከል” መስራች ነው። ይህ ተወዳጅ ስፍራ ሲጀምር አዝማሪ ቤት አሊያም ምሽት ክበብ ተብሎ ይታወቅ የነበረ ሲሆን፣ እርሱም በዚያ ወስጥ በጭፈራ ሙያ ተቀጥሮ ነው ስራውን የጀመረው።
ተውዛዋዥና የውዝዋዜ አሰልጣኝ ባለሙያው ሎሬት መላኩ በላይ ለበርካታ አመታት በሙያው ሰርቷል። ፈንድቃና ኢትዮ-ከለር የሚል የሙዚቃ ባንድ በመመስረትም በተለያዩ ሀገራት ተዘዋውሮ የኢትዮጵያን ባህል አስተዋውቋል። በዚህ ስራውም በርካታ ሽልማቶችን አግኝቷል።
በጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር 2020 ዓ.ም መጨረሻ ደግሞ በባህል ዘርፍ ጥሩ ለሰሩ ተቋማትና ግለሰቦች በየአመቱ ሽልማት የሚሰጠው የኔዘርላንዱ« ፕሪንስ ክላውስ ፋውንዴሽን»የባህል ሎሬት ተሸላሚ ሆኗል። ተወዛዋዥ ወይም እሱ እንደሚለው «የጭፈራ ባለሙያ»ው መላኩ በላይ ከ20 ዓመታት በላይ በሙያው የሰራ የጥበብ ሰው ነው።ይህንን የጥበብ ስራ በፍቅር ሲጀምር በነበረው ድንቅ ችሎታ ከሰዎች ከሚያገኘው ምስጋና፣አድናቆትና አነስተኛ ሽልማት ውጭ ምንም ክፍያ አልነበረውም። በዚህ ሁኔታም በመሀል አዲስ አበባ፤ ካዛንችስ አካባቢ በሚገኘው «ፈንድቃ» የባህል ጭፈራ ቤት በነፃ ሰርቷል ። እንዲያውም እርሱ ስለዚህ ጉዳይ ሲያነሳ “ደሞዛችን ሽልማት ነበር” በማለት ቋሚ ደሞዝ እንኳን እንዳልነበረው ይናገራል።
ሎሬት መላኩ ፤ምንም እንኳን ክፍያ ባያገኝበትም በዚሁ የባህል ቤት ባንኮኒ ስር እያደረ የሚወደውን ስራ ለዓመታት ቀጠለ ።ስራውን የተመለከቱ የፈንድቃ ታዳሚዎች የሚሰጡትን አነስተኛ የገንዘብ ሽልማትና በየሰፈሩ እየዞረ በማስተማር የሚያገኘውን ጥቂት ገንዘብ በማጠራቀም ከአስራ ሶስት ዓመታት በፊት የፈንድቃ የባህል ማዕከል ባለቤት ለመሆን በቅቷል። ይህ የባህል ማዕከል ሙያውን ከማሳደግ በተጨማሪ ስራውን በውጭ ሀገራት ለማቅረብም እድል ፈጥሮለታል።
«ዜማ ካለ ጭፈራ አለ» የሚለው መላኩ ፤ለየት ያለ የአጨፋፈር ስልት የሚከተል የቁሳቁስ መጋጨት በሚፈጥሩት ድምፅ ሳይቀር ድንቅ ጭፈራ ማሳየት የሚያስችል ለየት ያለ ተሰጥኦ ያለው ተወዛዋዥ ነው። በዚህም በባህል ማዕከሉና በተጓዘባቸው የውጭ ሀገራት የረባ ጥሪት ባይቋጥርም አድናቆትን አትርፏል።
ያም ሆኖ በሄደበት ሀገር መቅረትን አልመረጠም። በዚህም ለጥበቡና ለሀገሬ ኢትዮጵያ ያለኝን ፍቅርና ታማኝነት ገልጨበታለሁ ይላል።
ኢትዮ-ከለር በሚል ስም በመሰረተው የሙዚቃ ባንድ አማካኝነት የኢትዮጵያን ባህል ለተለያዩ የዓለም ሀገራት ተዘዋውሮ በማስተዋወቅ ላይ የሚገኘው መላኩ፤በፈንድቃ የባህል ማዕከልም ከሙዚቃ ባሻገር የስዕል፣የግጥምና ሌሎች የጥበብ ስራዎችና ዝግጅቶች እንዲቀርቡም በማድረግ ላይ ይገኛል። በዚህ ስራውም በጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር 2020 ዓ/ም መጨረሻ በየአመቱ በባህል ዘርፍ ጥሩ ለሰሩ ተቋማትና ግለሰቦች ሽልማት የሚሰጠው የኔዘርላንዱ« ፕሪንስ ክላውስ ፋውንዴሽን»የባህል ሎሬት ተሸላሚ ሆኗል። በዚህ ውድድር በባህሉ ዘርፍ አወንታዊ ተፅዕኖ መፍጠር የቻሉ ሰባት ሀገሮች የተመረጡ ሲሆን፣ ከአፍሪካ ኢትዮጵያና ጋና ውድድሩን ሲያሸንፉ ቀሪዎቹ አራት ሽልማቶች ለፓኪስታን፣ ለቱርክ፣ ለኮሎምቢያ፣ ለቶንጋና ለአርጀንቲና ተሰጥተዋል።
ጭፈራ የሚለውን ስያሜ ለምን መረጠ?
አርቲስት ሎሬት መላኩ ለውዝዋዜ ሙያ በእርሱ አጠራር “ለጭፈራ” ልዩ ፍቅርና ስሜት አለው። ይህ ሙያ እስካሁንም ከመንግስትና ከሚመለከታቸው አካላት በቂ ትኩረት እንዳላገኘም ያምናል። ለዚህ እንደምሳሌ የሚያነሳው የሙዚቃና ሙያ ፍቃድ እስካሁን ድረስም በንግድ ፍቃድ እንዲወጣ መደረጉን ነው። ለሙያው ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡ መሳሪያዎች ላይ የሚጣለው ቀረጥ ላይም ተመሳሳይ ጫና መኖሩን ያነሳል። ይሁን እንጂ መላኩ ራሱንም ሆነ ሙያውን አክብሮ በዓለም መድረክ ላይ የአገሩን ስም የሚያስጠራ ስራ እየሰራ ይገኛል።
እኔ “ጨፋሪ ነኝ” ይላል። ሙያው ከተወዛዋዥነት ጨፋሪ የሚለው ስያሜ እንደሚቀርበው እየገለፀ። እንዲያውም ተወዛወዘ የሚለው ስያሜ ሙያውን ዝቅ የሚያደርግ መስሎ ይሰማዋል። ጨፋሪ የሚለውም ቢሆን እንደማያረካው አንስቶ ነገር ግን የተሻለ ስያሜ እስኪያገኝ በዚህ ቢቀጥል ይወዳል። ይሄ ግን የግል ምልከታው ነው።
ተጫዋችና ሳቂታው መላኩ
አርቲስት ሎሬት መላኩን ብዙዎች ቀጠን ባለ ሰውነቱ በጎፈሬ ፀጉሩና በመነፅሩ ይለዩታል። ከዚህ ባለፈ ግን በአብዛኛው በሳቂታነቱና ከሰው ጋር ባለው ተግባቦቱ ሰዎች ቀለል ያለ ባህሪ እንዳለው ይመሰክሩለታል።
ይህን ባህሪውን በተፈጥሮ እንዳገኘው ነው የሚናገረው። ሰውን “ነጭ፣ጥቁር፤ ቀጠነ ወፈረ ብዬ ሳይሆን ሰው በመሆኑ ብቻ ነው የምግባባው” የሚለው መላኩ፣ ቀለል ያሉ ጨዋታዎችን ማድረግ ይወዳል። ከዚህ ውጪ ቁምነገረኛ ነው። በሚችለው ሁሉ ሃሳብና ምክር ለሚሻ የቻለውን መጠቆም መተባበርና ማገዝ ይወዳል። ለዚህም ይመስላል ትሁትና አዛኝ ልብ ያለው ስለመሆኑ በብዙዎች የሚነገረው።
በዚህ ብቻ አይደለም የሚታወቀው። በጭፈራ ወቅት ተመልካቹን በብቃቱ ብቻ ሳይሆን ልክ እንደ ጀግኖች አርበኞች ባለው ጎፈሬው ጭምር እንጂ። እርሱ ፀጉሬን ያጎፈርኩት ለፋሽን አይደለም ቢልም ብዙዎች ግን በዚህ ገፅታው ይለዩታል።
የእረፍት ውሎ
በመዝናኛና የኪነ ጥበብ ሙያ ውስጥ የሚገኝን ባለሙያ “ምን ያዝናናሃል” አሊያም “የእረፍት ጊዜህን በምን ታሳልፋለህ” የሚል ጥያቄ ማንሳት ሊከብድ ይችላል። ምክንያቱም ከሳምንት ሳምንት በሚወደውና ሌሎቹንም ሆነ እርሱን በሚያዝናና ሙያ ውስጥ ጊዜውን ስለሚያሳልፍ። ሆኖም መላኩ ትርፍ ጊዜ ካገኘ ለቤተሰቡ ጊዜ ሰጥቶ ከእነርሱ ጋር ማሳለፍን ይመርጣል።
ከዚህ ባለፈ “መክሊቴን ስለምኖረው ስራዬ ራሱ በትርፍ ጊዜዬም የምዝናናበት ነው” በማለት ይናገራል። በአንድ ነገር ግን በተጨማሪ እርግጠኛ እንድንሆን ይሻል “እረፍት የሚባለውን ነገር በአግባቡ አላውቀውም። ምናልባት ስሞት ይሆናል የማርፈው። ምንነቱንም የማውቀው የዛን ጊዜ ነው” በማለት ጠንክሮ በመስራት እንደሚያምን ተናግሮ ሃሳቡን ይደመድማል።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 10/2013