መርድ ክፍሉ
ወጣት ጥሩወርቅ ወርቅነህ ተወልዳ ያደገችው ወሎ ውስጥ ነው። ነገር ግን ውልደትና እድገቷ ወሎ ቢሆንም እናትና አባቷ መምህር በመሆናቸው የተለያዩ ቦታዎች በመዘዋወር ለመኖር ተገዳ ነበር። የተወሰኑ ቦታዎች ማለት ባይቻልም ብዙ ቦታ በመኖርዋ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች ትምህርቷን ተከታትላለች። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማቲማቲክስ ትምህርት መማር ጀምራ የነበረ ሲሆን ባጋጠማት በግል ጉዳይ ወደ መቀሌ ዩኒቨርስቲ በዝውውር ሄደች።
መቀሌ ዩኒቨርሲቲም እንደገባች የሕግ ትምህርት ተማረች። ከዛም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ተግባረ ዕድ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ በኤሌክትሮኒክስ ሙያ ስልጠና ወሰደች። ጎን ለጎንም አጫጭር ትምህርቶችን ትከታተል የነበረ ሲሆን የሞባይልና የኮምፒውተር ጥገና፣ ኦፊስ ማሽን፣ ኤሌክትሮኒክስ ሁሉንም ሥልጠናዎች ወስዳለች። ከዛም የተማረችውን ማስተማርና መስራት ጀመረች። ከዛም የሞባይል ጥገናው ብዙ ገበያ ያለው በመሆኑ ወደ እዛው ተሳበች። የዛሬ እንግዳችን ወደ ሞባይል ጥገና ሥራዋ ከገባች በኋላ የነበሩ ሁኔታዎችንና ስለቀጣይ እቅዷ ከዝግጅት ክፍሉ ጋር ቆይታ አድርጋለች። ተከታተሉት።
አዲስ ዘመን፡- ስራ ፈጣሪና ወጣቱ ተሳስረዋል ማለት ይቻላል?
ወጣት ጥሩወርቅ፡- ወጣቱና ሥራ ፈጠራ ምንም አልተገናኙም ማለት ይቻላል። ምክንያቱም ሥራ የሚፈጥሩ ሰዎች ወይ ቸግሯቸው ወይም መውጫ ቀዳዳ ሲጠፋቸው ነው ሥራ ሊፈጥሩ የሚችሉት። ሥራ ፈጣሪ ማለት ግን ተምሮ ውስጡ ያለውን ፍላጎት ወደ ተሻለ ደረጃ ማድረስ የሚችል ሲሆን ነው። እኔ ከልጅነቴ ጀምሮ የማስበው ሀሳብ ነበር። እሱ አልሆን ሲል ወደዚህ ሙያ ገባሁ። በጣም ከባድ ሁኔታዎችን አልፌ ነው አሁን ያለሁበት ደረጃ የደረስኩት። ነገር ግን ከልጅነት ጀምሮ በሚኖር እገዛ በትምህርት የተደገፈ ቢሆን የተሻለ ይሆን ነበር። በእርግጥ ችግር ያለበት አካባቢ ላይ መፍትሔ መፈለግ ግዴታ ነው። መፍትሔ ደግሞ ሥራ መፍጠር ነው። ሥራ ፈጣሪዎች እስካሉ ድረስ ሥራዎች መፈጠራቸውን አያቆሙም። ነገር ግን ሥራ ፈጣሪው ተቸግሮ ባይሆን ጥሩ ነገሮችን ማከናወን ይችላል።
አዲስ ዘመን፡- ወደ ኤሌክትሮኒክስ ትምህርት እንድትገቢ ያደረገሽ ነገር ምን ነበር?
ወጣት ጥሩወርቅ፡- ወደ ሞባይል ጥገና እንድገባ ያደረገኝ እንደሚታወቀው በእኛ አገር የምትፈልገውን መማርና መሥራት አትችልም። ወደ ሞባይል ጥገና ያመጣኝ ነገር የተለያዩ ተፅዕኖዎች ናቸው። በልጅነቴ እንደዚህ የተለያዩ ነገሮችን እሞካክር ነበር። ነገር ግን እድሜ ሲጨምር መማር የምፈልጋቸው ነገሮች ነበሩ። ሙሉ ለሙሉ ወደ ሞባይል ጥገና እገባለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር።
ኤሌክትሮኒክስ ለመማር እንድወስን ያደረገኝ ቀደም ብዬ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እማር ነበር። ከዛም በተወሰኑ ምክንያቶች ወደ መቀሌ ዩኒቨርስቲ ሕግ ትምህርት ክፍል ገባሁ። ነገር ግን በአጭር ጊዜ እራሴን ለማቆም በማስብበት ወቅት ኤሌክትሮኒክስ መማር እንዳለብኝ ነው የወሰንኩት። በዋናነት በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ሆኜ ስለነበር ነው ወደ ሙያው የገባሁት። ስራውን ሞክሬው የሚያድግ ከሆነ አሳድገዋለሁ የማያድግ ከሆነ ሌሎች አማራጮችን ለመጠቀም ሃሳቦችም ነበሩኝ። ወደ ሥራው ስገባ የተስተካከሉ ነገሮች አልነበሩም። ነገር ግን ቢያንስ እራሴን ማቆም እችላለሁ ብዬ በማሰቤ እንድመርጠው አድርጎኛል።
አዲስ ዘመን፡- ወደ ሙያው ስትገቢ ያጋጠሙሽ ችግሮች ምን ነበሩ?
ወጣት ጥሩወርቅ፡– ወደ ሙያው ስገባ ብዙ ችግሮች አጋጥመውኛል። እንደ ማህበረሰብ ብንመለከት ማህበረሰቡ ብዙ ነገሮችን ለመቀበል አስቸጋሪ ነበር። በተጨማሪም ሴት ሆኖ ወደ ሙያው መግባትና ልጅነትም ስለነበር ፈተናዎች ነበሩት። ከልጅነት ጀምሮ ያለው መንገጫገጭ የመከፋትና ማዘን ሁኔታዎችን ይፈጥር ነበር። በአገሪቱ በግል ለመስራት ሲፈለግ የነበረው አሰራር አስቸጋሪ ነበር። ሥራዎችን ለማከናወን የካፒታል እጥረት በመኖሩ እራስን መስዋዕት አድርጎ ወደ ሥራው ሲገባና ገንዘብ ተይዞ ሲገባ ልዩነቶች አሉት። ገንዘብ ሳይያዝ ወደ ሥራው ሲገባ ከባድ ፈተናዎች ይደቀናሉ። ምክንያቱም ከመጀመሪያው ጀምሮ የሚከፈሉ ነገሮች ይኖራሉ። ለምሳሌ የቤት ኪራይ የመሥሪያ ግብዓት እንዲሁም ሌሎች ነገሮች ስለሚኖሩ እነዚህ ሳይሟሉ ወደ ሥራ ሲገባ ከባድነገር ያጋጥማል።
በሌላ በኩል ሰው የምችል አይመስለውም ነበር። በተለይ በወቅቱ ልጅነቱና ሴት መሆኑ እንዳለ ሆኖ አገልግሎት ለማግኘት የሚመጣው ሰው ችሎታ ያለኝ አይመስላቸውም ነበር። እንደዚህ አይነት ሁኔታዎች በጣም ዋጋ አስከፍለውኛል። ሰርቶ ማሳየት እንደሚገባ ትምህርት ወስጄበታለሁ። በዚህም ኪሳራ ውስጥ ሊገባ ቢችልም ሰርቶ ማሳየት ግን የግድ ይላል። ሴት ሆኖ ይሄን ስራ መስራት በጣም ከባድ ነው። ምክንያቱም ሥራው የወንድ እንደሆነ ስለሚታሰብ ነው። አሁን ያለሁበት ደረጃ ላይ ለመድረስ እራሴን ሰብሬ ነው እራሴን ያስተዋወኩት።
አዲስ ዘመን፡- የገጠሙሽን ችግሮች ለመፍታት ምን አይነት እርምጃዎችን ወስደሽ አሁን ላለሽበት ደረጃ በቃሽ?
ወጣት ጥሩወርቅ፡- ምንም ነገር ለማሳካት ጊዜ መስጠት ያስፈልጋል። ከሥራዬ ውጪ ለምንም የሚሆን ጊዜ የለኝም። በጣም አነባለሁ፣ የተለያዩ በዩ ቲዩብ የሚለቀቁ ኮርሶችን በመከታተል እንዲሁም የተለያዩ ሰዎችን በመጠየቅ ልምድ የመቅሰም ሥራ አከናውን ነበር። ስራ ላይ በአግባቡ ጊዜዬን በመጠቀምና ከትምህርት የበለጠ በሥራ ላይ ያገኘሁት ልምድ በጣም ጠቅሞኛል። ብዙ የሚያዘናጉ ጉዳዮች ቢኖሩም ከሥራዬ ውጪ ምንም ነገር አይታየኝም ነበር። ምክንያቱም ይሄን ጊዜ ማለፍ አለብኝ ብዬ በመወሰኔ ነው። የሚገጥምን ችግር ማለፍ ካልተቻለ ሁልጊዜ ችግር መውጣት አይቻልም።
አንድ ሰው መለወጡንና አንድ ደረጃ መድረሱን ሊያወራ የሚችለው በትኩረት ማየት የሚገባን ነገር ማየት ሲቻል ነው። ሌላው ደግሞ ሰው እንዲህ አለኝ ብሎ ተስፋ መቁረጥ አይገባም። ያሰብኩት ለመድረስ በጣም ትግል አድርጌያለሁ። በአገሪቱ ያለው ለሥራ ፈጣሪዎች ምቹ ያልሆኑ ነገሮች ለምሳሌ የንግድ ፈቃድ ከማውጣት ጀምሮ በጣም ከባድ የሆኑ ነገሮች አሉ። ያሉት ሁኔታዎች በጣም አሰልቺ የሆኑ ናቸው። ነገር ግን ምንም ነገር ቢገጥም መሰልቸት አያስፈልግም። ሲወራ በጣም የተለመደ ነገር ቢመስልም የሚመጡ ፈተናዎችን ማለፍና መሻገር አስፈላጊ ነው። ካሰቡት ለመድረስ እንቅፋት የሚሆኑ ነገሮችን ጠርጎ ማስወገድ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- በቀጣይ ስራ ለመፍጠር የሚፈልጉ ሰዎች እንደ ችግር የሚገጥማቸው ነገር ምንድነው ?
ወጣት ጥሩወርቅ፡- ሥራ ፈጣሪዎች በእኛ አገር በጣም ብዙ ችግር ስላለ በፈለጉት መስክ መሰማራት ይችላሉ። ነገር ግን እንደ ሥራ ፈጣሪ ግን ማህበረሰቡና አካባቢው ከሥራ ፈጣሪ የሚያገኘው ነገር አለ። ሥራ ፈጣሪውም ከማህበረሰቡ የሚያገኘው ነገር አለ። እንደ ማህበረሰብ ለእያንዳንዱ ሥራ ፈጣሪ እውቅና መስጠት አለበት። እንደ ሥራ ፈጣሪ ሲኮን እኔን በግሌ የገጠሙኝ ማህበረሰቡና የመንግሥት አሰራሮች ስላንገጫገጩኝ ሌላው ሰው እንዳያልፍበት በማህበር መደራጀት አስፈላጊ ነው። ሥራ ፈጣሪዎች ተደራጅተው የተለያዩ ሥራዎችን መስራት እንዲችሉ መደረግ አለበት። ለምሳሌ ሥራ ፈጣሪ ሥራ ፈጥሮ እየሰራ ካለ ተጠቃሚ እስከሌለው ድረስ ምንም ለውጥ ማምጣት አይችልም።
እኔ በራሴ መስራት እንደጀመርኩኝ አካባቢ ማንኛውም ሰው እውቅና አይሰጠኝም ነበር። ሰው አይቀበለኝም፣ መስራት አልችልም እንዲሁም አልመረጥም ነበር። በመጀመሪያ ሊመረጡ የሚችሉበትን አቅም ምን ላይ እንደሆነ፣ ምንድነው መስራት ያለብኝ፣ እንዴትስ ተቀባይነት አገኛለሁ፣ እስከምን ድረስ አደርሰዋለሁ እንዲሁም ሌሎች ነገሮችን መለየት መቻል አለባቸው። ምንም ችሎታ ሳይኖር ሌላ ሰው ብቻ ስለሚሰራው ተብሎ መገባት የለበትም። ማንኛውም ሥራ ፈጣሪ የያስኩት ነገር ምን ደረጃ ላይ አደርሰዋለሁ የሚለውን ነገር መለየት መቻል አለበት። ሥራ ፈጣሪው ችሎታውን ከለየ በኋላ ጊዜ መስጠት አለበት እንዲሁም አቅሙን መገንባት ሊኖርበት ይችላል። ከዚህ ውጪ በተገኘው አጋጣሚ አቅምን ሊገነቡ የሚችሉ ነገሮችን፣ እውቀት የሚጨምሩ ነገሮችንና በገንዘብ ደረጃም አቅም ሊፈጥር የሚችል ነገር ሳይለይ መስራት ይገባል።
እኔ ይሄን ስራ መስራት ስጀምር በጣም ብዙ ከባድ ነገሮችን አሳልፌያለሁ። ለምሳሌ ለራሴ መሆን አቅቶኝ ነበር። አሁን ግን ለሌሎች ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችያለሁ። በአሁን ወቅት በልምድ ደረጃ ለሌሎች የማካፍለው ነገር አለኝ። ዛሬ የሚታሰበው ስራ የት ድረስ መድረስ ይችላል የሚለው ነገር በዋነኝነት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። እነዚህን ነገሮች ማሟላት ከተቻለ ሌሎች ሰዎችን ማለትም አብሮ መስራት ብቻ ጥቅም የለውም ዋናው ነገር እውቀት የሚሰጥና ልምድ ማካፈል የሚችል ነገር ላይ ማተኮር ይገባል። ለብቻ ሆኖ መስራት አስቸጋሪ ነው። ነገር ግን ሰው ጋር በትብብር ሲሰራ ልዩነት አለው። ለዚህም ነው የሥራ ፈጣሪዎች ማህበር እንዲመሰረት የተደረገው። አንዱን የገጠመው ችግር ሌላው ላይ እንዳይከሰት ለመመካከር ይረዳል።
ሥራ ፈጣሪዎች ሀሳብ ይዘው ሲመጡ በማህበር ውስጥ ያለው ሰው ጋር በመመካከር ወደ ተግባር ሊገቡ ይችላሉ። ችግሮች ቢከሰቱ አንዱ ያላየውን ሌላው ሊመለከት ስለሚችል መደጋገፍ ይኖራል። በተጨማሪም አካባቢን
በማጥናት የተሻለ ነገር ለመፍጠር በማህበር መስራት ተገቢ ነው። ሁሉም በየግሉ ዝም ብሎ ሲሮጥ ውጤታማ ለመሆን አስቸጋሪ ነው። ስለዚህ በማህበር በጋራ ሲሰራ አንዱ ያየውን ነገር በምን መልኩ እንደተመለከተውና እንዴት እንዳለፈው ማጋራት ይችላል። ለምሳሌ እኔ ያለፍኩበት ህይወት ብዙ ያስተምራል ብዬ አስባለሁ በተለይ ውጣ ውረዶችን አልፌ እዚህ መድረሴን ላጋራ እችላለሁ።
ሥራ ፈጣሪ ሲኮን ከባድ ነገሮች አሉ። ምክንያቱም አሁን ያለኝ አቅምና ስጀምር የነበረን በጣም የተለያየ ነው። ከሰባት ዓመት በፊት ምንም አይነት መሥሪያ እቃዎች አልነበሩኝም። አሁን ግን የሚያስፈልጉኝ ነገሮች በሙሉ አሉኝ። ስለዚህ ምንም ነገር ሲጀመር ከባድ እንደሚሆን የታወቀ ነው። ነገር ግን ከበደኝ ብሎ ከመተው ከሰዎች ጋር በመመካከርና በመወያየት ለውጥ ያመጣል። በእድሜ ከበሰሉ ሰዎች መማርና ልምድ መቅሰም ተገቢ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ቀጣይ እቅዶችሽ ምንድን ናቸው?
ወጣት ጥሩወርቅ፡- በቀጣይ ለመስራት የማስበው ፋብሪካ መክፈት ነው። ፋብሪካ ቢኖረኝ ብቻ ሳይሆን እሱ ላይ መስራት እፈልጋለሁ። በሞባይሉ ዘርፍ የአገር ውስጥ ምርት ይዞ ለመምጣት የመስራት ፍላጎት አለኝ። ምክንያቱም አገሪቱ ላይ ብዙ ያልተሰሩ ነገሮች ስላሉ ነው። በየአቅጣጫው ከሚገኙ በራሳቸው ከሚሰሩ ጓደኞቼ ጋር ያሉንን እውቀቶች አደባልቀን የምንሰራበት ነገር ይፈጠራ ብዬ አስባለሁ። እዚህ ላይ በመተጋገዝ በግሌ ግን ፋብሪካ ይኖረኛል ብዬ አስባለሁ። ይህን ወደ ተግባር ለማስገባት ትልቅ ነገር ይፈልጋል። በሥራዬ ላይ ከበረታሁ መስራት እችላለሁ ብዬ አስባለሁ። እኔ አቅሜንና ልምዴን እጠቀማለሁ ሌሎች ሰዎች ደግሞ እውቀቴ ላይ ኢንቨስት የሚያደርጉ ይኖራሉ ብዬ አስባለሁ። እነዚህን አንድ አድርጌ ወደ ምፈልግበት ደረጃ እደርሳለሁ ብዬ አስባለሁ።
በሞባይል ጥገናው ስልጠና ለመስጠት ከሰዎች ጋር አስበን ነበር። ነገር ግን ወጪው ብዙ በመሆኑ ወደ ተግባር ሳይሻገር ቀርቷል። በእኛ አቅም የሚሆን ነገር አይደለም። በጊዜ ብዛት የሚመጣ ትርፍ ነው ሊኖረው የሚችለው። በግል የማስተምራቸው ሰዎች አሉ። እኔ ጋር ተቀጥረው የሚሰሩ ሰዎች ቅድሚያ ስልጠና እሰጣቸዋለሁ። ሰፋ ያለ ስልጠና ለመስጠት ትልቅ ኢንቨስትመንት ይጠይቃል። ፋብሪካ ሲከፈት ደግሞ ግዴታ የሰለጠነ ሰው ያስፈልጋል። ሞባይል መገጣጠሚያ ፋብሪካ በጣም ትልቅ በመሆኑ የሰለጠነ ሰው ነው የሚገባው።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 8/2013