(ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
እናመሰግናለን ኢትዮጵያ!
“ሐሙስ የቀን ቅዱስ” እንዲሉ፤ በዚህ የሳምንቱ ታሪካዊ የመጋቢት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ጀንበር ኢትዮጵያ ድምጧን ከፍ አድርጋ በኪነ ጥበባቱ ሙያ የተሰማሩ አንጋፋ ልጆቿን ያመሰገነችበት ደማቅ ዕለት ነበር። ተመስጋኝ ልጆቿም እንዲሁ ምስጋናዋን የተቀበሉት በጋለ ስሜትና በሞቀ ጭብጨባ አጅበው ነበር። መንግሥቷን እንዲመሩ ተቀዳሚውን ኃላፊነት በሰጠቻቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ አማካይነት የወርቅ ሜዳሊያ በልጆቿ አንገት ላይ በማጥለቅ አክብሮቷን የገለጸችው ኢትዮጵያ ለምስጋናው ለምን እንደዘገየች ጭምር ምክንያቷን በዝርዝር አስረድታለች።
“የእናት እንጎቻ የሚጋገረው ለዋናው እንጀራ ቅድሚያ ከተሰጠ በኋላ እንጂ የሰማውን ምጣድ የልጆች ጭልሀ እንደማይሻማው ሁሉ” ሽልማቱም ታቅዶ ከነበረው መርሃ ግብር ለአንድ ዓመት ያህል ሊዘገይ ግድ የሆነው ዜጎች ሁሉ በሚረዱት ዘርፈ ብዙ ሀገራዊ ፈተናዎችና ችግሮች ምክንያት እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የምክንያቱን ዝርዝር ይቅርታ አክለውበት በሚገባ አስረድተዋል። “ከመቅረት መዘግየት” እንዲሉ ብዙ አንጋፋ የጥበብ ሰዎችን በእልፈተ ሕይወት በተለየናቸው ማግስት የሽልማቱ መርሃ ግብር መከናወኑና “የብዙዎች የእድሜ ጀንበርም ባሽቆለቆለበት ወቅት” የጥበብ እንቁዎቹ መታሰባቸው በራሱ ትርጉሙ ቀላል ስላልሆነ “ግሩም!” ተብሎ መወደሱ አግባብ ይሆናል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ እናመሰግናለን፤
ነበር ታሪኩን አስከትለን ለማስታወስ እንደም ንሞክረው እንደ ሀገር በተጠናና በተደራጀ መርሃ ግብር በተሰማሩበት የተለያዩ ሙያዎች ፍሬያማ የሆኑ ልጆቿንና ባዕዳን በጎ ተጽእኖ ፈጣሪ የዓለም ዜጎችን በብሔራዊ ደረጃ ኢትዮጵያ ትሸልም የነበረው በግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት እንደነበር ታሪካችን ይነግረናል። ከንጉሡ ዘመን በኋላ በቅን አሳቢ ዜጎችና ቡድኖች አማካይነት እዚያና እዚህ የተከናወኑትና እየተከናወኑ ያሉት “ሽልማት አከል” ሀገራዊ ሙከራዎች እጅግም ተጽዕኖ የመፍጠርና የመሰንበት አቅም ስለማያገኙ ረጂም ርቀት ሊጓዙ አልቻሉም። ከላይ በተጠቀሰው ዕለት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ አማካይነት ለኪነ ጥበባት ባለሙያዎችና ለሀገሪቱ ደራስያን የተበረከተው ሽልማት ምናልባትም ከሃምሳ ዓመታት በኋላ ሁለተኛው መንግሥታዊ የክብር እውቅና ሳይሆን እንደማይቀር ይታመናል።
የዕለቱ ሽልማት የተከናወነው በአራት ዋና ዋና ዘርፎች ተከፍሎ ሲሆን ምድቡም፤ አንጋፋ የቴያትርና የፊልም ባለሙያዎች፣ አንጋፋ ሠዓሊያን፣ አንጋፋ ደራስያንና አንጋፋ የሙዚቃ ባለሙያዎች በሚል ተለይቶ ነው። በዚሁ መሠረትም 34 የቴያትርና የፊልም ባለሙያዎች፣ 29 ሠዓሊያን፣ 31 ደራስያንና 62 የሙዚቃ ባለሙያዎች በጠቅላላው 156 የጥበብ ሰዎች የተሸለሙ ሲሆን ኮሚዲያን ልመንህ በልዩ ተሸላሚነት የአክብሮቱ ተካፋይ ሆኗል። ከተሸላሚዎቹ መካከል በርከት ያለ ቁጥር ያላቸው ባለሙያዎች በህመም ምክንያትና ከሀገር ወጭ በመሆናቸው ሊገኙ አልቻሉም።
ይህን መሰሉ የብሔራዊ ሽልማት መርሃ ግብር “ሀገር ረሳችን፣ አስተዋሽ አጣን!” እያሉ ምሬታቸውን ሲያሰሙ ለኖሩት የጥበብ ባለሙያዎች ትልቅ ደስታ የፈጠረ ብቻም ሳይሆን የጉልምስናና የእርጅና ሽበታቸውን እንዳለመለመላቸውና ተስፋቸውን እንዳደሰላቸው ጭምር ሲናገሩ ተደምጠዋል። “ከሀገር ምሰሶዎች መካከል ቀዳሚው አእምድ ጥበብ መሆኑ” በጠቅላይ ሚኒስትሩ አንደበት መነገሩ በራሱ ትኩረቱ በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ ለመገንዘብ አያዳግትም።
እርግጥ ነው የሽልማቱ መርሃ ግብር የሚመለከታቸውን በሙሉ አካቷል ማለት ባይቻልም ጅምሩ ጥንቃቄ ባልተጓደለበት ሁኔታ ታስቦበትና ተጠንቶ ስለመሠራቱ ግን ብዙዎች ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። በ”ሃሌታ” ጥረቱ ላይ ጉድለት እንደሚኖርበት ስለታመነበትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው “ይቅርታ!” መጠየቃቸው የአስተዋይነታቸውን ልክ ያመልክታል። ይህንኑ ክፍተት ለመሙላትም በተከታታይ መሰል ዝግጅቶች እንደሚከናወኑ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
የሽልማቱን አተገባበር በተመለከተ የብዙዎች ደስታ እንደተጠበቀ ሆኖ በጥቂት ግለሰቦች ዘንድም ቅሬታዎች ተደጋግመው መደመጣቸው አልቀረም። “ህልም ተፈርቶ ሳይተኛ እንደማይታደር” ሁሉ ቅሬታዎች ይኖራሉ ተብሎ መልካም ሥራ ላለመሥራት መሸማቀቅ አግባብነት እንደማይኖረው ሁሉም የሚረዳው ይመስለናል።
በወደፊቱ ቀጣይ ሥራ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረጉ አግባብ ቢሆንም ለተደረገው መልካም ተግባር ግን ኢትዮጵያንና ባለ ራዕዩን መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድን ያለማመስገን ንፉግነት ብቻም ሳይሆን አደራ በልነት ጭምር ነው። ስለዚህም “የሀገርን ህልውና የሚጎነታትሉ” በርካታ ችግሮች የውጥር ይዘውን ባለበት ወቅት “ጠቢባንን በማስቀደም” ይህንን መሰል ታላቅ የሀገራዊ ሽልማት መርሃ ግብር ተግባራዊ በማድረጋቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩንና ከፅንሱ እስከ ትግበራው በትጋት የሠሩትን ሁሉ ጸሐፊው እንደ ግለሰብ ተሸላሚነቱ ብቻም ሳይሆን አብረውት የተሸለሙትን በሙሉ በፈቃዱ ወክሎ ዝቅ በማለት ምሥጋናውን ለኢትዮጵያና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀርባል።
ከዚህ በተረፈ ግን የተሸላሚዎችን የዕድሜ ገደብ መስፈርትና በክብር የተገኙት ታዳሚዎች በሙሉ የተሸለሙ መስሏቸው አንዳንዶች “በቴሌቪዥን ካየነው ከእከሌ እንቶኔ በምን ያንሳል፣ እከሌትስ ለምን ተዘነጋች” የሚሉ አስተያየቶች “በምሬትም ይሁን በቅንነት” የሚሰነዘሩት ምናልባትም መስፈርቶቹ በዝርዝር ተብራርተው ባለመገለጣቸው ይሆን? ለማንኛውም ግን “የሺህ ማይል ርቀት የሚጀመረው በአንድ እርምጃ” መሆኑን ልብ ማለቱ ተገቢነት ይኖረዋል ብሎ መጠቅለሉ ሳይሻል አይቀርም።
ታሪክን የኋሊት፤
የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት ድርጅት ህዳር 1955 ዓ.ም ተጸንሶ ተግባራዊ እንቅስቃሴውን የጀመረው ከስምንት ወራት በኋላ በተጠቀሰው ዓመት በሐምሌ ወር ነበር። መዋቅራዊ አደረጃጀቱና አስተዳደራዊ ጉዳዮች በሚገባ ከተጠኑ በኋላ ምርጫው ተከናውኖ የመጀመሪያው የሽልማት መርሃ ግብር መተግበር የጀመረው ከሁለት ዓመታት በኋላ በ1957 ዓ.ም ነበር። ለተከታታይ አሥር ዓመታት ያህልም ከተከናወነ በኋላ በሀገሪቱ የተቀጣጠለው የፖለቲካ አብዮት እንቅፋት በመሆኑ ድርጅቱ በ1966 ዓ.ም ሊከስም ግድ ሆኗል።
በእነዚያ አሥር ዓመታት ውስጥ በጠቅላላው 59 ግለሰቦችና ተቋማት የተሸለሙ ሲሆን በተለየ ሁኔታ ግን በመጀመሪያው የሽልማት መርሃ ግብር ላይ በግርማዊት እቴጌ መነን ስም ልዩ ተሸላሚ የነበረው የአልፍሬድ ኖቤል የሽልማት ድርጅት ነበር። ሽልማቱን በጊዜው ተገኝተው የተቀበሉትም የድርጅቱ ፕሬዚዳንት የነበሩት ፕሮፌሰር ቲ. ሲሲያስ ነበሩ። ከ55 ዓመታት በኋላ ይሄው የኖቤል ሽልማት ድርጅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድን የሰላም ሎሬት አድርጎ መሸለሙ የታሪካዊ ግጥምጥሞሹን ይበልጥ ያደምቀዋል።
በንጉሠ ነገሥቱ ስም የተሰየመው የሽልማት ድርጅት በቆየባቸው አሥር ዓመታት ውስጥ የብሔራዊ ክብር ያጎናጸፋቸው ግለሰቦችና ተቋማት በሙያ ዘርፎቻቸው ስብጥር እጅግ በርከት ያሉ ነበሩ። ለአብነት ያህልም፤ በባህል፣ በቋንቋ፣ በኪነ ጥበባትና በሥነ ጽሑፍ፣ በህክምና፣ በግብርና፣ በአፍሪካ ጥናት፣ በልዩ ልዩ ማሕበራዊ ተሳትፎዎችና በበጎ ሥራዎች ወዘተ. ላይ ትኩረት በማድረግ ነበር።
በተለይም በሥነ ጽሑፍ፣ በመዛግብተ ቃላት ዝግጅትና በኪነ/ሥነ ጥበባቱ ዘርፍ የተሸለሙት ከበደ ሚካኤል፣ አፈወርቅ ተክሌ፣ ገብረ ክርስቶስ ደስታ፣ ጸጋዬ ገ/መድኅን፣ መንግሥቱ ለማ፣ እስክንድር ቦጎስያን፣ ደስታ ተክለ ወልድ፣ ተሰማ ሀብተ ሚካኤል ግጽው፣ ሐዲስ ዓለማየሁ፣ መርስዔ ሀዘን ወ/ቂርቆስና ማኅተመ ሥላሴ ወ/መስቀልን የመሳሰሉ ጎምቱ አበው የሀገራዊ ክብሩ ተጋሪዎች ነበሩ።
የሽልማት ድርጅቱን በባለ አደራ የቦርድ አባልነት ይመሩ የነበሩትም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር (ጸሐፌ ትዕዛዝ) አክሊሉ ሀብተ ወልድ (በሊቀመንበርነት)፣ ሪር አድሚራል እስክንድር ደስታ፣ አቶ ይልማ ዴሬሳ፣ ዶ/ር ስዩም ሐረጎት፣ አቶ የወንድወሰን መንገሻና አቶ በቀለ በሻህ ነበሩ። በእነዚህ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ሥር የተዋቀረውን የሥራ አስፈጻሚ የመማክርት ጉባዔ ይመሩ የነበሩት ደግሞ ዶ/ር ስዩም ሐረጎት (በሊቀመንበርነት)፣ አቶ መብዓ ሥላሴ ዓለሙ፣ አቶ አበበ ከበደ (የንጉሡ እንደራሴ) እና ሚ/ር ጂ. ፓይል የተባሉ ግለሰቦች ነበሩ።
በመጀመሪያው ዓመት ለተካሄደው ሽልማት እጩ ተሸላሚዎችን እንዲመርጡ በዳኝነት ከተሰየሙት መካከል የወቅቱ የከፍተኛው ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ክቡር አቶ አሰፋ ሊበን፣ ዶ/ር ጌታቸው ኃይሌ (ዛሬ ፕሮፌሰር)፣ አቶ አስፋው ዳምጤና አቶ ተስፋዬ ገሠሠ በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። የሥነ ጽሑፍ ኃያሲው አስፋው ዳምጤ በዳኝነት ብቻም ሳይሆን በሽልማት ድርጅቱ ውስጥ በባለሙያ ተቀጣሪነት ጭምር ለአምስት ወራት ያህል ማገልገላቸውንም ለማወቅ ተችሏል።
በቀደም በተከናወነው የሽልማት መርሃ ግብር ስማቸው ተካቶ የነበረው ኃያሲ አስፋው ዳምጤ በዕለቱ በጤንነታቸው ምክንያት መገኘት ባይችሉም ከደራሲያን ተሸላሚዎች መካከል በመጀመሪያው ረድፍ የሚጠቀሱ ናቸው። አቶ ተስፋዬ ገሠሠም እንዲሁ ከተሸላሚዎች ዝርዝር ውስጥ በአንጋፋ የጥበቡ አባትነት ስማቸው ተመዝግቦ የነበረ ቢሆንም የአጋጣሚ ጉዳይ ሆኖ የሽልማቱ መርሃ ግብር ሀገሪቱን በተፈታተኗት ወቅታዊ ችግሮች ምክንያት ለአንድ ዓመት ያህል በመዘግየቱ እኒህን የተከበሩ የጥበብ ሰው ለማጣት ተገደናል። መርሃ ግብሩ በተካሄደ እለትም አንዱ ተሸላሚ የነበሩትና መገኘታቸውን ያረጋገጡት “የማንዶሊን ጠቢቡ” አየለ ማሞም በአጸደ ሥጋ ተለይተውን የቀብር ሥርዓታቸው የተከናወነው በዚሁ ቀን ነበር። ያሳዝናል።
ቀደም ብሎ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ማንኛውም የሽልማት መርሃ ግብር ሲከናወን “እከሌ ቀርቷል፣ እከሌ ተረስቷል፣ እከሌ አይገባውም ወዘተ.” የሚሉ ቅሬታዎች የተለመዱና የማይቀሩ ሁነቶች ናቸው። በ1957 ዓ.ም በተከናወነው የመጀመሪያው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት ተሸላሚ በነበሩት በደራሲ ከበደ ሚካኤል ላይ ከፍተኛ ክርክር ተነስቶ እንደነበር በሕይወት ያሉ ምስክሮች ያስታውሳሉ። ይህን መሰሉ ጉምጉምታና ተቃርኖ በተሸላሚው በደራሲ ከበደ ሚካኤል ጆሮ በመድረሱም ስሜታቸው ክፉኛ ተጎድቶ በመቀየማቸው በሽልማቱ ላይ እንዳልተገኙ ከታሪካቸው መረዳት ይቻላል።
ታሪክ ራሱን ይድገምም አይድገም “የትናትን” ተሞክሮ ለዛሬና ለወቅታዊው ዐውድ በትምህርትነቱ መመርመር ከፍ ያለ ዋጋ ስላለው ማጣቀሱ አይከፋም። በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ የተጀመረው መልካም ተግባርም ወደፊት ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ እንዲሰነብትና በሕግ የተደገፈ ተቋማዊ ህልውና እንዲፈጠርለት መደረጉ ሳይታሰብበት የቀረ አይመስልም። ኢትዮጵያ ያገለገሉሽን ስላከበርሽ ደግመን ደጋግመን እናመሰግናለን። የጎልማሶቹና የአረጋዊያኑ “የሽበት ምርቃትም” ለሰላምሽ ምክንያት ይሁን። አሜን!
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 9/2013